ቀምጣላ ጣቶች

ቶሎ ቶሎ የሚርበኝ ነገር አለ። ከክፉ ገመናዎቼ አንዱ በቀን ስድስት ጊዜ መመገቤ ነው። እንደአመጋገቤ ግን አልፀዳዳም… ከሰው የበዛ በልቼ ከሰው ያነሰ ነው የምፀዳዳው። አንዱ የሚገርመውም ይሄ ነው፤ ሰው እንዳበላሉ አይፀዳዳም ነው የሚባለው እኔጋ ይሄ አልሠራም። ብዙ ጊዜ ማዕድ ቤት እንጂ መጸዳጃ ቤት አልታይም። ይሄን ለማንም አላወራውም።

በዚህ የኑሮ ውድነት በቀን አንድ ጊዜ መብላት ባልተቻለባት ሀገር ላይ ስድስት ጊዜ መብላቴ ቢታወቅ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ሊያስተባብልብኝ በቀን ስድስት ጊዜ የሚበላ ወጣት አፈራሁ ብሎ የምስኪን ወገኖቼን ሮሮ ለመከለል ልዩ ጥበቃ የሚያደርግልኝ እየመሰለኝ እፈራለሁ።

አብዛኛው ጊዜዬ የሚያልፈው በማላመጥ እና በመዋጥ ነው። ለዓለም ሕዝብ የመመገቢያ ክፍለጊዜ ሆነው የተቀመጡት ጠዋት ከሰዓትና ማታ እኔ ዘንዳ የሉም። ካሰኘኝ ሌሊት ከእንቅልፌ ተነስቼ እበላለሁ። በዚህ ሁኔታ የሸመተ አይደለም ያረሰ አይችልህም እየተባልኩ በጓደኞቼ እየተተረተብኝ የመጣሁ ነኝ።

የሚያስበላ በሽታ እንዳለብኝም የሚያስቡ ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንዶች በማያገባቸው ገብተው የወር ወጪዬን ለማስላት ይዳፈራሉ። የሚገርመው ነገር ደግሞ ኪሎዬ ነው..በቀን ስድስት ጊዜ የሚበላ ሆድ ኪሎው ስንት ይመስላችኋል? ይግረማችሁ 49 ኪሎ ነኝ..ግን የምበላው የት እየገባ ነው? የዛሬ አስራ አምስት ዓመት በማውቀው ኪሎዬ ነኝ። ግን እንደዚህ መሆን ይቻላል? ሲበሉ ያሰሩት እንጂ በቀን ስድስቴ የምበላ አልመስልም።

በሰውነት እኩዮቼ አልፈውኝ ሄደው ከኋላዬ የሚወለዱ እየደረሱብኝ ነው። ግን ጤነኛ ነኝ..ማንም ታግሎ የማይጥለውም ነኝ። ከእኩዮቼ ተገዳድሮ የሚረታኝ የለም።

አበላሌን የወረስኩት ከአባቴ ነው። ከዛ ጣቶቹ እንጀራ ሲጠቀልሉና ወጥ ሲዝቁ ቲያትር የሚሰሩ ከሚመስሉት የአባቴ እጆች። ብዙ ነገሬን ከእናቴ ወርሼ በአባቴ አጎራረስ ፍቅር መውደቄ ያልገባኝ የሆነ ነገር እንዳለ ይታሰበኛል። እርግጥ አባቴ እንደእኔ በቀን ግማሽ ደርዘን ጊዜ የሚበላ አይደለም። ፍቅር በሚያሲዙ ቄንጠኛ ጉርሻዎች በቀን ሁለት ጊዜ ከበላ በቂው ነው። አበላሉ ግን ሱስ ያሲዛል። የጠገበን ያስርባል። የተነሳን ይመልሳል። በዓለም ላይ እንደአባቴ እንጀራ ሲቆርስ፣ ሲጠቀልል፣ ሲጎርስና ሲያላምጥ የሚያምርበት ሰው ያለ አይመስለኝም። ጣቶቹ እንደምግብ መቁረስና መጠቅለል የሚቀናጡበት የለም። ጠግቤ ውዬ የሚርበኝ እሱ ፊት ነው።

በቃኝ ብዬ ገበታ ስሜ እጄን ታጥቤ ተነስቼ ሲበላ ሳየው ርቦኝ ያውቃል። ሲበላ ቲያትር የሚሰራ ነው የሚመስለው..ሲጎርስ፣ ሲያላምጥ ደግሞ የቲያትሩ ልብ አንጠልጣይ ክፍል። ይሄ ሰው አባቴ ሆኖ በስሙ መጠራቴ ብዙ ነገር ያተረፈልኝ ቢሆንም ከእሱ ጋር በአንድ ማእድ እንደመቅረብና እሱ ሲበላ እንደማየት የተባረኩበት ግን የለም። አቢታይዘሬ ነው።

እናቴ ስትሰራ እንጂ ስትበላ አትታይም። ይሄ የእሷ ብቻ ይሁን የብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶች ታሪክ እርግጠኛ አይደለሁኝም። አፏን ገጥማ የሚጣፍጥ ምግብ ስትሰራ እና አንዳንዴም ማማሰያና ጭልፋ መዳፏ ላይ አሳርፋ የሰራችው ወጥ መጣፈጡን ስታረጋግጥ አያታለው። መች ቁጭ ብላ አብራን እንደበላች፣ አባቴ መቼ በነዛ ቄንጠኛ ጣቶቹ እንዳጎረሳት አላስታውስም። ግን አታሳዝነኝም..ለምን እንደማታሳዝነኝ አላውቅም። በቀን ከስድስት ጊዜ በላይ እንድበላ ያለስስት ደስ የሚላት እናቴ ናት። እኔ ስበላ የእሷ ሆድ የሚጠግብ፣ በእኔ የጥጋብ ግሳት የእሷ ልብ ተመስገን የሚል እናቴ ናት ግን አታሳዝነኝም..ለምን አታሳዝነኝም? ምን አነሰ፣ ምን ልጨምርልህ ስትል ፊቴ የምታሸረግድ፣ ስበላ ብውል የጠገብኩ የማይመስላት፣ ጥሞኝ እንድበላ የጣመ የምትሰራልኝ እናቴ ናት ግን አታሳዝነኝም..ለምን አታሳዝነኝም? አንዳንድ እንዲህ የገዘፉ ጥላዎቻችን የሚሰወሩበት ማምሻ እንዳለ አይገባንም። እንደነበረ በማይቀጥል ሰውነት ውስጥ ያለንን የሚያስረሳ እንቅልፍ መሳይ አለማወቅ አለን፣ በኋላ ሲሆን እንደጤዛ በሚከስም ታሪክ ውስጥ ለዳበሱን እጆች፣ ላስጠለሉን ጥላዎች ላመል ውዳሴ የለንም..እናም አጠገቤ ያለችውን ጥላዬን አልተመጻደኩባትም።

ዛሬ ጠዋት ከእናቴ ጋር ገበታ ካልቀረብኩ አምጻለሁ ብዬ ከራሴ ጋር ተማከርኩ። የአባቴ ቄንጠኛ ጣቶች እናቴን አጉርሰው ወደእሱና ወደእኔ እንዲወናጨፉም አስገድደዋለሁ ስል በረታሁ። ገበታው ቀርቦ አባቴ በቄንጥ ጥቅል ሊጎርስ ሲል እጁን ያዝኩት..‹ከዚህ በኋላ እናታችን ሳትቀድምበት በእኔና በአንተ ፊተኝነት የሚቀጥል ታሪክ የለንም። አጉርሳት› ስል ወደእናቴ እያየሁ አስገደድኩት። ምን ሊመልስልኝ እንደሚችል ግምት አልነበረኝም እሷም እሱም እኩል ሲስቁ የሆነ የሚተዋወቁበት የጋራ እውነት እንዳላቸው ጠረጠርኩ።

የእናቴ ሳቅ ከማዕድ ቤቱ በኩል ይሰማኛል..የሚንተከተክ ሽሮ ወጥ ይዛ ስትመጣው ከነሳቋ ነበር። ከስንት ጊዜ በኋላ እንደሆነ እንጃ በዚህ ጠዋት በእኔ አስገዳጅነት አባቴ እናቴን አጎረሳት። ለእሷም ለእሱም የህይወት ዘመናቸው ምርጥ ጉርሻ ይሆናል እያልኩ ከራሴ ጋር ስብሰለሰል ከዚህ በፊት ሰምቼው የማላውቀውን ታሪክ ከእናቴ አፍ መስማት ጀመርኩ ‹ለመጀመሪያ ጊዜ አባቴ የአስረኛ ክፍል የማትሪክ ፈተናን በጥሩ ውጤት ማለፌን ምክንያት በማድረግ ምሳ ሊጋብዘኝ ወደአንድ ምግብ ቤት ይዞኝ በሄደ አንድ ሰአት ላይ ከሁለት ጠይምና የቀይዳማ ቡራቡሬ ሴቶች ጋር የተቀመጠ አንድ ወጣት ከፊት ለፊቴ ነገር ሲፈልገኝ ተመለከትኩ። አባቴ ካየው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፊቱን በቡጢ እንደሚነርተው ስላወኩ፣ ሆቴሉም ከሳቅና ጨዋታ ወደዋይታ እንደሚቀየር ስለገባኝ እንዲሁም ደስታችን ወደሀዘን ከመቀየሩ በፊት ቦታ መቀየሬ የተሻለ መስሎኝ ምንድነው መቁነጥነጥ? ከምትል የአባቴ ትንሽዬ ግልምጫ ጋር ቦታ በመቀየር ጀርባዬን ሰጠሁት። ምን ተፍረቱን እሱም ቦታ ቀይሮ ከበፊቱ በባሰ ለሽሙጥ እንዲመቸው ፊት ለፊቴ ተጋረጠ። ደግሜ ከቀየርኩ ደግሞ ሊቀይር እንደሚችል እርግጠኝነት በሞላበት ወኔ ቀጥይ በሚመስል ፊት አስተዋለኝ።

ፉክክር የያዘ ስለመሰለኝ የእውነት ተናድጄበት ነበር። እልኸኛ ሴት ብሆን በቀጥታ ለአባቴ ተናግሬ ባስቀጠቅጠው በወደድኩ ነበር። አባቴ ወንድሜም ቢሆን አይቀርለትም ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ቦታ ከቀየርኩ የአባቴ ምን ሆነሻል ጥያቄ መከተሉ ግድ ነበረና በተቻለኝ አቅም ወጣቱን ላለማየት እና በማይመለከተኝ የአባቴ የኢሀፓ፣ የኢዴፓ፣ የመስሪያ ቤት ወሬ ላይ ቀልቤን በመጣል አንዳንዴም ወደሌላ አቅጣጫ እየማተርኩ ችላ ልለው ሞከርኩ። በዚህ የተሳካልኝ ይመስለኛል..ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ መሀል ግን አይኖቼ ሳላዛቸው ወደእሱ ይማትሩ ነበር።

አባቴ እጁን ለመታጠብ ሲሄድና ያዘዙት ምግብ ሲመጣ አንድ ሆነ። እጃቸውን ቀድመው እንደታጠቡ በሚያስታውቅ ሁኔታ ሁለቱ ሴቶችና ወጣቱ ወደምግቡ እጃቸውን ዘረጉ። በምግቡ ተስቦ ችላ ይለኛል፣ ነጻነቴን አገኛለሁ ስል በማሰብ ደስታ ወረረኝ። እንዴት እየሆነ እንደሆነ ላየው ባስገዳጅ ሁኔታ ወዳለበት ተመለከትኩ። በሚያማምሩ ጣቶች፣ በሚያምር አጠቃለል ለረዝም ዘመናት ተዘጋጅቶበት በሚመስል ሁናቴ የመጀመሪያ ጉርሻውን ይዞ ወደእኔ ሲንደረደር ለማመን አመት ፈጅቶብኝ ነበር። ለመግደርደር፣ አይሆንም ለማለት ምንም አቅም አልነበረኝም ብለው እንኳን በአባቴ መመለሻ ሰአት ላይ ስለሆንኩ ያለኝን ከመሆን ውጪ አማራጭ አልነበረኝም። በእጄ ለመከላከል ትንሽ ታግዬ ጎረስኩለት። ምግቡ አፌ ውስጥ ሲላመጥ፣ ወደሆዴ ሲገባ ከሆነ ከአንዳች ለዘላለም እንዳረሳው ከሚያደርግ የሆነ ነገር ጋር እንደሆነ ሲገባኝ አፍታ አልወሰደብኝም። ተገድጄ የጎረስኩት ጉርሻ ወድጄና ፈቅጄ ከጎረስኩት ጉርሻ አንድ ሺ ጊዜ ጣፍጦ ምነው በደገመኝ የሚያስብል ስሜትን ሲፈጥርብኝ ለራሴም ገርሞኝ ነበር።

ማንም ከዛ በፊትም ሆነ ከዛ በኋላ እንደዛ በቄንጥ ያጎረሰኝ የለም። ሳልፈልግ የጎረስኩት ቢሆንም ፈልጌ ከጎረስኳቸው የእናቴና የአባቴ ጉርሻዎች ጋር ተስተካክሎ ሳገኘው ግራ በመጋባት ነበር አጣጥሜ የጎረስኩት። የሌላ ሰው ጉርሻ ሆኖ ልጅነቴ ውስጥ ተቀመጠ። አባቴ ከመምጣቱ በፊት ጉርሻውን አላምጬ ለመዋጥ ያደረኩትን ትግል ዛሬም ድረስ መሳቂያዬ ነው። ሁለተኛ ሊደግመኝ ወደእኔ መምጫውን ሲያማትር እና እኔም ምነው በመጣ ስል አባቴ በመሀከላችን ገብቶ ታሪካችንን አቋረጠው። ይሄ ሰው አጠገብህ የተቀመጠው አባትህ ነው ስትለኝ በእውን የሆነ ሳይሆን ተረት ፈጥራ የምትነግረኝ ነበር የመሰለኝ። ሁለቱንም በየተራ ቃኘኋቸው..በሁለቱም ፊት ላይ እኩልና ተመሳሳይ ፈገግታን አስተዋልኩ።

ከዛን ቀን በኋላ እንዴት ደግመው እንደተገናኙ፣ እንዴት በፍቅሯ እንደወደቀ፣ እነዛ ፉራቡሬ ሴቶች ምን እንደሆኑ እንድትነግረኝ አፍ አፏን ሳስተውል ትታኝ ወደ ማዕድ ቤት ገባች። አጠገቤ ያለውን አባቴን እንዳልጠይቅ እንዴት መጀመር እንዳለብኝ ጠፋኝ።

እኔን በቀን ስድስቴ ለረሀብ ጠኔ የጣሉ ጣቶች እናቴን ምን አድርገዋት ይሆኑ?

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You