የግል የበላይነት የቴኳንዶ ውድድር በአዲስ አበባ ይካሄዳል

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በመጪው ግንቦት ወር መጀመሪያ በሚያካሄደው ለሁሉም ክፍት የሆነ የግል የበላይነት የቴኳንዶ ውድድር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።በውድድሩ የሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች በየእድሜ ክልላቸው እና በሚወዳደሩበት የክብደት መጠን ሽልማት እንደተዘጋጀላቸው ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ውድድሩን በገንዘብ ለመደገፍ ከሳኦል ሁነት አዘጋጅ ጋር በመተባበር የውል ስምምነት እንደፈጻመና ድርጅቱ ውድድሩን እንዲሳለጥ እየተሠራ መሆኑ ተናግሯል።የ2016 ዓ.ም ለሁሉም ክፍት የሆነ የግል የበላይነትን የቴኳንዶ ውድድር ከግንቦት 3 እስከ 6 በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል።

በውድድሩ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ የወርልድ ቴኳንዶ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ እድል መመቻቸቱም ተገልጿል።በዚህም 1ሺ እና ከዛ በላይ የሆኑ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።ለዚህም ከክልሎች ጋር በመናበብ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ የውድድሩ ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 19 ድረስ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረትእንደሚሆንም ተጠቅሷል።

በመድረኩ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በዓለም አቀፉ የቴኳንዶ የክብደት ሕግ መሰረት የተሻለ ብቃት የሚታይበት ኪሎ ግራምና ካታጎሪ እንደተመረጠ ተጠቁሟል።ውድድሩ በሦስት አይነት ዘርፎች የሚካሄድ ሲሆን፤ እነዚህም ፋይት፣ ፑምሴ እና ሰበራ የተባሉ ናቸው።በ-46 ኪሎ ግራም ሴቶችና ወንዶች፣ በ-53 ኪሎ ግራም ሴቶች፣ በ- 54 ፣ -58፣ እና -68 ኪሎ ግራም ወንዶች የፋይት ውድድሮች የሚካዱ ይሆናል።በፋይት የሚያሸንፉና የወርቅ ሜዳሊያ የሚያጠልቁ ስፖርተኞች 20ሺ ብር ይሸለማሉ።የብር ሜዳሊያ የሚያመጡ 10 ሺ ብርና የነሐስ ሜዳሊያ የሚያሸንፉ ስፖርተኞች ደግሞ 5 ሺ ብር የሚሸለሙ ይሆናል።

የፑምሴ ውድድር በሴቶችና ወንዶች ነጠላ የሚካሄድ ሲሆን ከ12-14 ዓመት የዕድሜ ክልል እና ወጣት ሴቶች ይሳተፋሉ።በአዋቂዎች ከ18 ዓመት በላይ ሴቶችና ወንዶች፣ ከ12-14 ዓመት ዕድሜ እና ከ15-17 ዓመት ወጣቶች ይካተታሉ።አዋቂዎች ውድድር 10 ሺ ብር ሲሸለሙ ወጣቶች 5 ሺ እና ታዳጊዎች 3 ሺ ብር የሚሸለሙ ይሆናል።

በሰበራ ውድድር እንዲሁ በታዳጊዎች፣ ወጣቶች እና አዋቂዎች በሁለቱም ጾታ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን አንደኛ ለሚወጡት የ3 ሺ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል።በተጨማሪም በሁሉም የውድድር ዓይነቶች የሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሽልማትም ይበረከታል።በውድድሩ የተለያየ ችሎታ ለሚያስመለክቱ ስፖርተኞች ልዩ ሽልማት ለመስጠት ታስቧል።

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላውን ዋሲሁን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተወዳዳሪ የስፖርቱን ስነ-ምግባር፣ ሕግና ደንብ የሚያከብር እና ለስፖርቱ ብቁ ከሆነ መወዳደር እንደሚችል አስረድተዋል።ለተወዳዳሪዎች የውድድር እድልን ከመፍጠር ባሻገር ከተማንና ሀገርን የሚወክል ስፖርተኛ ለይቶ ለማውጣት ጉልህ ሚናን የሚጫወት እንደሚሆን ገልጸዋል።በተጨማሪም ስፖርቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝና አቅም እንዲኖረው እና የራሱን ሀብት እንዲያመነጭ እገዛን ያደርጋል።

ከማርሻል አርት ስፖርቶች አንዱ የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ መነቃቃት ቢያሳይም እንደሌሎች ስፖርቶች ባለማደጉ ይህ ውድድር የንቅናቄ መድረክ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።ከግልና ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በሁሉም ክልል እና ክፍለ ከተማ ስፖርቱ እንዲስፋፋ ለመስራት የሚያስችልም ነው ተብሏል።

ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገና ለተወዳደሪዎች ውድድር ከሚጀመርበትን ቀን ቀደም ብሎ ያስታወቀ መሆኑ ተመላክቷል። የአካል ብቃታቸውንና ስነ ልቦናቸውን ከመጠበቅ አንጻር ዝግጅት እንዲያደርጉና ከትራንስፖርት እና ማደርያም ጭምር የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቁማል።የትራንስፖርት ሁኔታን ለማመቻቸትም ስፖንሰሮችን የማፈላለግ ስራ የሚሰራ ሲሆን ውድድሩ ቀጥታ የቴሌቪዠን ስርጭት እንዲኖረውም ይሰራል።
ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ አዘጋጅ ጋር ለውድድሩ ማስኬጃ 700 ሺ ብር ተፈራርሞ ገቢ ማድረጉን የገለፁት አቶ ጥላውን፣ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን የማዘጋጀት ጫናን ለመቀነስና የውድድር ዕድልን ለማስፋት በክፍለ ከተማ ደረጃ ፌዴሬሽኖችን አቋቁሞ የራሳቸውን ውድድርና ስልጣና እንዲያዘጋጁ እድሎችን እንዳመቻቸ አስረድተዋል።
ውድድሩ ሀገር አቀፍና ሰፊ እንደመሆኑ ከብሔራዊ ፌዴሬሽን ጋር በማነጋገርና በመደጋገፍ ለስኬታማነቱ እየተሰራ ነው።የውድድሩን መክፈቻ ለማድመቅና ውድድሩ ብዙኀኑን ተደራሽ እንዲያደርግ ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ፣ በብሮድካስትና በህትመት መገናኛ ብዙሀን ለማስተዋወቅም ታቅዷል።

ውድድሩ ወደፊት ለሚካሄዱት የክፍለ ከተሞች እና የክለቦች ውድድር እንደግብዓት የሚያገለግል ስለሆነም በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።

ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You