የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚተጋው ‹‹ኢንዳን››

የቀድሞ መጠሪያው ‹‹ሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር›› እና በዓለም የሠራተኞች ድርጅት (ILO) አማካኝነት ‹‹ዲስኤቢሊቲ ፎረም›› በሚል ስያሜ ነበር የተቋቋመው፡፡ የአሁኑ ስያሜው ‹‹ኢትዮጵያን ናሽናል ዲስኤቢሊቲ አክሽን ኔትዎርክ››(ኢንዳን) ይባላል፡፡ አቶ ዓለሙ ኃይሌ ደግሞ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን አብሮ የመብላት ችግር የለብንም። በጋራ የመሥራቱ ነገራችን ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው።›› የሚሉት አቶ ዓለሙ፤ ከዚህ ሃሳብ በመነሳትና በጋራ መሥራት እንደሚቻል በማመን በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች በተናጠል ከሚሠሩ ይልቅ እነርሱን አቅፎና ደግፎ ችግራቸውን በጋራ የሚያሰሙበት ድርጅት የዛሬ 20 ዓመት እንደተመሰረተ ያስታውሳሉ፡፡

በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠሩ 34 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የ‹‹ኢንዳን›› አባል እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ ዓለሙ፣ ከአባላቱ መካከል ሁለቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለፃ፣ የአንድ ሰው ድምጽ እና የ34 ሰዎች ድምጽ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም ድርጅቱ በዋናነት የሚሠራው በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ላይ የሚሠሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድምጻቸውን በጋራ እንዲያሰሙ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሆን የሚወጡት ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች፣ የሕግ ማዕቀፎች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ትኩረት እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በምን መልኩ ታይቷል በማለትም ከመንግሥት ጋር በጋራ ይሠራል፡፡ ከዚህ ባለፈ ለአባላቶቹ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት እና ከሚያገኘው ድጋፍ አባላቶቹን መልሶ መገደፍ አንዱ ተግባሩ ነው፡፡

‹‹ኢንዳን›› የተለያዩ አባላቶች ያሉት ሲሆን አባላቶቹ ከተቋቋሙለት ዓላማ በመነሳት እና የሚሠሩትን በጎ ሥራ መሠረት አድርጎ የተለያዩ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጥረት ያደርጋል፡፡ ለአብነት የዳንቴል ውጤቶች፣ ስጋጃ፣ እና  መሰል ምርቶችን በመሥራት ጥረት ለሚያደርጉ ድርጅቶች ምርቶቻቸው ገዢ እንዲያገኝ ያበረታታል፡፡ በተለያዩ ባዛሮች ላይ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ያመቻችላቸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮም ከፋይናንስ ተቋማት እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመወያየት አካል ጉዳተኞች ማምረት እና መሥራት እንደሚችሉ እነርሱም ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ግንዛቤ የመስጠት ሥራዎችን እንደሚሠራ አቶ ዓለሙ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ዓለሙ እንደሚገልጹት፣ ኢንዳን የተለያዩ አባላቶች አሉት፡፡ በአትዮጵያ ጥቂት ከሚባሉ ኦቲዝም ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል ጆይ የኦቲዝም ማዕከል፣ ነህምያ የኦቲዝም ማዕከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአእምሮ እድገት ውስነንት ላይ ከሚሠሩት መካከል መካነ ኢየሱስ፣ ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማህበር ፣ቁጥራቸው በዛ ያሉ ዓይነ ሥውራን ላይ የሚሠሩ ማሕበራት፣ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማሕበር፣ የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማሕበር፣ የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማሕበር እና ሌሎቹም ካሉት 34 አባላት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ቆየት ካሉ ጥናቶች በመነሳት በአገራችን 20 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች መኖራቸው ይገለጻል፡፡ በአሁን ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥሩ ከፍ ቢል እንጂ ሊቀንስ እንደማይችል መገመት አያዳግትም፡፡ አቶ ዓለሙም የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ በፋይናንስ ተቋማት በኩል ብድርም ይሁን ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል ይላሉ፡፡ አካል ጉዳተኞች የሚስተናገዱበት ልዩ መስኮቶች ቢዘጋጁም ተቋማቱ የበለጠ ተመራጭ እና ብዙ ተገልጋይ እንዲኖራቸው ያግዛል ይላሉ፡፡

በሁሉም ክፍለ ከተማ ደረጃ ባዛሮች ይዘጋጃሉ፣ ነገር ግን የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ የለም ማለት ይቻላል ያሉት አቶ ዓለሙ፣ መንግሥት በሚያዘጋጃቸውም ሆነ ፍቃድ በሚሰጥባቸው ባዛሮች ላይ ተሳትፏቸው እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ቢደረግ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡

‹‹የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ›› ጸድቆ ወደ ተግባር ቢገባ አካል ጉዳተኞች ስለሚገጥማቸው ችግር ግንዛቤ ከመስጠት ባሻገር ሕጉ አስገዳጅ እንደመሆኑ ብዙ ችግሮችን ሊፈታ እንደሚችልም ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም አካል ጉዳተኝነት እና ሞት መምጫቸው አይታወቅና ሁሉ ሰው ለራሱ ሲል የድርሻውን በጎ ነገር ማበርከት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

ድርጅቱ በ20 ዓመታት ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል፡፡ በተለያዩ አገራት ላይ ባሉ ጦርነቶች፣ የኑሮ ውድነት እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በለጋሽ አገራትም ሆነ ድርጅቶች በኩል እጅም ፍላጎትም እያጠራቸው እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ዓለሙ፣ ድርጅቱ በፊት ከሚያገኘው ድጋፍ አንፃር ከፍተኛ የድጋፍ መቀዛቀዝ ታይቷል ይላሉ፡፡ ሌላው ችግር የኢንዳን አባል የሆኑ ድርጅቶች የድጋፍ እጥረት ስላለባቸው ሊዘጉ የደረሱ ድርጅቶች ቢኖሩም ለእነርሱ ለመድረስ አለመቻላቸውን ከገጠማቸው ተግዳሮት አንዱ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ በተጨማሪም በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ባለው የጸጥታ ችግር እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አለመቻልም ሌላኛው ፈተና ነው፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን ቀጣይነት ያለው ፈንድ አለመገኘቱ ድርጅቱን እየፈተነው ያለ ነገር መሆኑን በማንሳት የሚመለከተው አካል ድጋፉን እንዲያደርግ ይጠይቃሉ፡፡

ኢንዳን ከተቋቋመለት ዓላማ በመነሳት በቀጣይ አባል ድርጅቶቹ ያለምንም ችግር በጎ ሥራቸውን ከውነው ለብዙዎች ሲደርሱ ማየት ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪም በሁሉም ዘርፍ አካል ጉዳተኞች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You