ነውር ነው!

ነውር የምንላቸው የአደባባይ ህጸጾቻችን እንደ ሰልፈኛና ታንከኛ ወታደር ጦር አንግበው ተጠግጥገዋልና፤ ዘንድሮ እህ! ከተባለ የማይሰማ፤ ዞር ዞር ብለው ካዩ ከአይን አልፎ የማያዞር ነገር የለም። “ነውር ነው!” ብንልም ጉዶች እየበዙ መጣያ ጉድጓዶቹም ሞሉ። በጨለማ እያደፈጠ በአፍ ጢም የሚደፋው አንደኛው ጉድጓድም፤ የትዳር ዳቦ የተቆረሰበት ትሪ፤ ላይወርድ ከሚሰቀልበት የፍቺ ቤት ውስጥ ነው።

ነገርየው ሲጀማምር አካባቢ የምንናገረው፤ በዓሉ አሉ…በወሬ ወሬ ቢሆንም አሁን ግን ሁላችንም ለዚህ አዲስ የምንሆን አይመስለኝም። ድሮ ድሮ ድል ያለ ድግስ ሲባል ለሠርግ ነበር። ድል የምትለዋን ቃል ስንሰማም ወዲያው በአዕምሯችን የሚከሰትልን ምናባዊ ስዕል፤ ሠርግና ሠርግ ቤት ነበር። ወዳጄ፤ አሁንም እንዲህ ብቻ ከታየህ፤ የምናብህ ሰዓሊ ተሳስቶ እያሳሳተህ ነው። ለምን በለኝና ልንገርህ… ምክንያቱም ዘንድሮ ላይ ድል ካለው የሠርግ ድግስ የላቀ ድል ያለ የፍቺ ድግስ እየተደገሰ ስለሆነ ነው። ካላመንከኝ ከአንዱ ቅንጡ ሆቴል ጎራ በልና ዘልቆ የመግባቱን ዕድል ካገኘህ አንደኛውን አስተናጋጅ በጨዋታ አደንዝዘህ፤ ወገቡ እስኪንቀጠቀጥ ጎንበስ ቀና እያለ ያስተናገደባቸው የፍቺ ዝግጅቶች ስንት እንደሆኑ ጠይቀው ይነግርሃል።

እንዲያውም ቀለል ያለውን ልጠቁምህ፤ ከአንደኛው የፎቶግራፍ ስቱዲዮ ግባና፤ እስካዛሬ በስንት የፍቺ ዝግጅቶች ላይ ተገኝቶ፤ ካሜራውን አንቀጫቅጮ እንደወጣ ብትጠይቀው እሱ ይነግርሃል። ይህ ሁሉ የሚያደክምህ ከሆነ ግን ስልክህን ከፍተህ እነ ቲክቶክና ዩቲዩብ መንደር ዝለቅ፤ እንዲያውም እሷን መርጬልሃለሁ። ቀድሞ በሠርግ ላይ እንደለመድነው ሁሉ “ከነባለቤትዎ..” የሚል የጥሪ ካርድ ቢደርስህስ ግን ምን ይሆን የሚሰማህ? ይልቅ እንዳይሆን ብቻ ጸልይ፡፡

ወትሮ ፍቺ ስነልቦናዊ ጫናን ያስከትላል የሚሉት የስነ አዕምሮ ጠበብት አሁን አሁን ግን ብሂላቸውን ለመቀየር ሳይገደዱ አልቀረም። ነገሩ በተቃራኒው አኩሪ ጀብዱ እየሆነ ስለመምጣቱ ከማንም በላይ የማህበራዊ ሚዲያዎቻችን ይነግሩናል። “የዛሬ ዓመት፤ የማሙሽ አባት/እናት፤…ለክርስትናው እንመጣለን ገና..” ሲሉ አባሯውን ያስጨሱ ሚዜና አጃቢዎች “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ፤ የዛሬ ዓመት የፍቺው ድግስ ላይ የሚገናኙ ቀላል አይደሉም። በሠርጉ ዕለት ቢራ እየከፈቱ ተራጭተው፤ አበባው ከላይ ከታች ተበትኖ በዓመቱ የሰማንያውን ወረቀት እየቀደዱ በሂሊኮፕተር የተበተነ ያህል፤ ፍርድ ቤቱን አልፎ ከየአዳራሹ … ምን አይነቱ የአዕምሮ ልህቀት ይሆን? ጽድቅ ካለ ኩነኔ፤ ህይወት ካለ ሞት፤ ትዳር ካለም ፍቺ ሁሌም የሰው ልጆች ባሉበት ሁሉ የሚኖር ነገር ነው።

ይህ አፈንጋጭነት ነውና መሆን የለበትም ስንልም ፍቺውን ብቻ ሳይሆን ከፍቺው በስተጃርባ ያሉትን የህጸጽ አጀቦችንም ነው። ዘንድሮ ላይ ከሚያገባው ይልቅ የሚፋታው፤ ከሠርጉም ፍቺው በልጧል፤ የሚልን መረጃ በውሸት ለመንቀፍ የሚያዳግት ሆኗል። ካለን የጠነከረ ባህልና ሃይማኖት እንዲሁም የማህበረሰባችን የአኗኗር ዘዬ የተነሳ፤ ፍቺም ሆነ ስለፍቺ ጎልቶ የማይታይባት የኛ ሀገር ነበረች። “ከኋላ የመጣ አይን አወጣ” አይነት ሆኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብቻ የሚታዩ ነገሮች የአፍሪካ ቀንድ ላይ ብቻም ሳይሆን የፍቺው ቀንድ ላይም ሊያስቀምጣት ነው። የፍርድ ቤቶቹ የፍቺ መዝገብም አልበረክት ብሏል። ለዛሬው ይህን እንተወውና ከፍቺዎቻችን በስተጀርባ ያለውን ተንጠራርተን ለማየት እንሞክር።

ለምን እና በምን ምክንያት ነው የምንፋታው ከማለት ይልቅ እንዴትና በምን መልኩ ነው የምንፋታው፤ የሚለው አይሎ ከያኔው ሠርግ በላይ አስጨናቂ ሆኗል። ሰው እንዴት ድል ያለ የፍቺ ድግስ ፈችሮ፤ ምርጥ ፈቺና ተፋቺ ለመሆን ይጥራል? ነውር አይደለም? በዚህ ፍቺ ውስጥ፤ ሰብአዊ ስብዕናችንን፤ ባህልና ሥርዓታችንን፤ ሃይማኖትና እምነታችን…አስቀድመን ወደ ገደል የምናስገባቸው ነገሮች ናቸው።

ዛሬ እንደ መብት ያየነው ነገር ውጤቱ ከባህል ማፈንገጥ ብቻ ሆኖ አይቀርም፤ የኋላ ኋላ እንደ እባብ በደረታቸው እየተሳቡ የሚመዘዙ ጉዶች አሉት። ምን ችግር አለው ያልናቸውም፤ መልሰው ከማንወጣው ችግር ደፍቀውናል። እዚህ ጋር የማንዘለውን ሃሳብ ላስፍር። ፍቺ ከነጻነት ጋር የተያያዘበት መንገድ ግለሰባዊና የእይታ ጉዳይ ብቻ እንዳይመስለን። ከፍቺ በስተጀርባ ከግለሰብና ከሀገር የላቀ ግዙፍ እጅ ያለበት ነው። ይህ እንደነውር የተገለጠው ጉዳይ ጀርባው ከነውርነትም ያለፈ ሌላ ጉድ አለው። እኛ እንደ ግለሰብ፤ ለመፋታታችንም ሆነ ለመደገሳችን አንዳንዶች የራሳችን የውስጣዊ ምክንያት ሊኖረን ይችላል፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያየለ የመጣው የፍቺ ሁኔታና ድል ያለው ድግስ፤ግብሩ በዘፈቀደ ቢመስልም፤ አጀማመሩ ግን በምክንያትና በዓላማ ነው፡፡

የፍቺው ድግስ ከትዳር ባርነት አምልጦ፤ ወደ ነጻነት ደሴት የመግቢያ ማብሰሪያው ነው። በፍቺ ጀልባ ተሳፍረን ወደ ደሴቱ እንድንገባ እየሰሩ ያሉ ስውር ደላሎች እንዳሉ ስንቶቻችን እናውቃለን? የሚሰዱን ግን በበረሃ ሳይሆን ከደሴቱ በስተጀርባ ወዳለው በረሃ ነው።

አሁንም በድጋሚ ካላመንክ፤ ልበልና መከረኛውን የማህበራዊ ሚዲያ ተመልከትን ልድገም፤ ብዙ የፀረ ትዳርና የፍቺ አብዮት አቀንቃኝ ሰባኪዎችን ታገኛለህ። ከእነርሱ በስተጀርባ ያለውንም ዓለም ከተመለከትክ፤ መንገዱ በቀጥታ ወደ ምስጢራዊው ዓለም ማህበረሰብ ይወስድሃል። በአንድ ደሴት ሁለት ንጉሥ አይኖርምና፤በተመሳሳይ ጾታ የሚሰራውን ዓለም ለመገንባት፤ በተቃራኒ ጾታ የተጋቡትን ማፍረስ ግድ ይላቸዋል። አሁን የምንለውን ጉዳይ በዓለም ዙሪያ እንዲስፋፋ በማድረግ ወደዚህ የነጻነት ወደሚሉት ዓለም ማጋዝ ጀምረዋል። ፍቺው መበርከቱ በዋዛና በአጋጣሚ አይደለም። በእንቅስቃሴያቸው ውስጥ ያላገቡትን እንዳያገቡ፤ ያገቡትንም እንዲወጡ ማድረግ ቁልፍ ነገር ነው። በእነርሱ እሳቤ ጎጆ ማፍረስ፤ ከትዳር መፋታት ሳይሆን ከእስር መፈታት ነው። እኛ ምንም እንበለው ምን፤ በድግሱ ጅምር ዓላማ ውስጥ ግን፤ የዚህ ትግል ድልና የድል ማብሰሪያ መስዋዕት እንዳለበት ግን እንወቅ። ይህን በዚሁ እንቋጨውና ሌላ አንድ ነገር ልመርቅላችሁ፡፡

ከወራት በፊት የወዳጄ ወዳጅ፤ የገጠመውን ነገር ወዳጄ አጫወተኝ። እናም፤ የወዳጄ ወዳጅ የሩቅ ዘመዱ ሞቱና ወደለቅሶው እንደሚሄድ ለወዳጄ ነገረው። በማግስቱም አግኝቶ፤ ታዲያስ ለቅሶውን ደርሰህ መጣህ፤ ብሎ ቢጠይቀው፤ “አዎን ነገር ግን የደረስኩት ሠርጉ ላይ ነው” አለው። ለቅሶ ሄዶ ከለቅሶ ቤት ደግሞ የምን ሠርግ ነው፤ በማለት ቀልዱን ነው ብሎ ቢያስብም ከፊቱ ላይ ግን ምንም የቀልድ ለዛ አይታይበትም። ይልቅስ ቃላቱም የንዴት ስላቅና አሽሙር ናቸው። ግራ መጋባቱን ግራ በተጋቡ ቃላት እንዴት ሲል ጠየቀው። ልጁም እንዲህ አለው፤ ሰውየው ስለመሞቱና ለቅሶ ቤት ስለመሆኑ ያመንኩት ከተንጣለለው ግቢና ከተንፈላሰሰው ህንጻ ወገብ ላይ የተንጠለጠለውን የሟችን ፎቶ የያዘ የሸራ ላይ ጽሁፍና “ጋሼ እንወድሃለን” የሚለውን መፈክር አይቼ ነው። የምመለከታቸውና የሚሆኑ ነገሮች በሙሉ ከሞት የተነሳ እንጂ ወደ ሞት ሄዶ የተለያቸው አይመስልም። የሰውየው ልጅ ያገባች ጊዜ ሠርጉን በልተን ሀገር ምድሩ ጉድ! ብሎ ነበር። ነገር ግን ይህኛው የባሰ ነው። ሲል የታዘባቸውን ጉዳዮች እንደነገረው አጫወተኝ። በጊዜው በገጠመኙ ብንሳሳቅም፤ በባህልና በሰብአዊነት ማንነት ካየነው ግን በጥርስ አያድርስ የሚያስብል ነው። ጉዱን ባየ ሟች…እዚህ ጋር ግን ምንም ለማለት አልወድምና የነብስ ይማር ሥርዓታችንን እራሱኑ ነብስ ይማር ብለን ሳንቀብረው በፊት፤ እናንተው አይታችሁ ባህልን ፍረዷት፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You