“የዳታ ማዕከሉ እውቅና ማግኘት የሀገሪቱን ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም ያሳድጋል”ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ

አዲስ አበባ፡- የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ የሀገሪቱን ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም እንደሚያሳድግ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል፤ከአፕ ታይም ዓለም አቀፍ ካምፓኒ የጥራት እውቅና ማግኘቱን አስመልክቶ በትናንትናው እለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ የዳታ ማዕከሉ እውቅና ማግኘት የሀገሪቱን ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም ከፍ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ የዲጂታል ለውጥ ጉዞ እንደመጀመሯ የዳታ ማዕከል ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የማዕከሉ መረጃ ደህንነቱ ከ99 ነጥብ 9 በመቶ በላይ የተጠበቀ ነው በሚሉ መስፈርቶች ዕውቅና መሰጠቱ እንደሀገርም ጠቀሜታው ብዙ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዕውቅናው የዳታ ማዕከሉን መጠቀም የሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ ያግዛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሥራ እድል ለመፍጠርና ተጨማሪ የቴክኖሎጂ አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝ አመላክተዋል።

በተጨማሪም የእውቀት ሽግግር እንዲኖር፣ ከሀገር ውጭ ዳታ ማስቀመጥ እንዲቀር እና የቀጣናዊ ትስስር እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል፡፡ መንግሥት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂው በአፍሪካ ከሦስት ባልበለጡ ሀገራት መኖሩን የተናገሩት ዶክተር ይሽሩን፤ በምሥራቅ አፍሪካ በኢትዮጵያ በዊንጉ አፍሪካ አማካኝነት የተገነባው ማዕከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማግኘቱ በዘርፉ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

የዳታ ማዕከሎችን ለመገንባት መንግሥት ኢንቨስት የሚያደርግ ቢሆንም ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ጊዜ ማሟላት ስለማይችል እንደ ዊንጎ አይነት ድርጅቶች መጥተው እንዲያለሙ ይጋብዛል፤ ይህም የዲጅታል ትራንስፖርሜሽን ጉዞን ያፋጥናል ሲሉ አስረድተዋል።

ሚኒስትር ዴታው እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል ገንብቶ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት እየሰጠ ነው፤ የተገኘው ማረጋገጫም ተጨማሪ ሥራዎችን በዘርፉ ለማከናወን ይረዳል።

አፕታይም ካምፓኒ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዳታ ሴንተሮች ግምገማ የሚያካሄድና የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ የዳታ ማዕከሎች ልክ እንደ አይ. ኤስ. ኦ እውቅና ይሰጣል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ መውጣቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች እና ሥራ ፈጣሪዎችን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡

የዊንጉ አፍሪካ የመንግሥትና ሕግ ጉዳዮች ከፍተኛ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወርቁ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከዳታ ማዕከሉ ጋር የተለያዩ ባንኮች በጋራ እየሠሩ ይገኛል፡፡
አቶ ተሾመ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ለኢንቨስትመንት እድል ሲሰጥ የሥራ እድል ፈጠራ አንዱ መስፈርት ነው፤ ዳታ ሴንተሩ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡

በተሠሩ ጥናቶች መንግሥት ዲጂታል 2025 ጉዞን መጀመሩ እና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ከፍተኛ መሆኗ ሥራውን ለመጀመር ተመራጭ አድርጎታል ብለዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You