ዓለም አቀፉ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር ፋይዳው እስከምን?

ዜና ትንታኔ
በዓለማችን የሚገኙ ሀገራት በጤና፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ መስኮች ግንኙነት አድርገው ለጋራ ጥቅም እየሰሩ ይገኛል። ተቋማት እርስ በእርስ በሚኖራቸው ግንኙነት ባለሙያ በመለዋወጥና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ችግሮቻቸውን በጋራ ይፈታሉ።

በዚህ የወዳጅነት ልምድ ደግሞ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ግኑኝነታቸውን አጠናክረው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ባለንበት ዘመን ደግሞ ዘመናዊነት እየተስፋፋ የትብብር መስኩም በአካልና በበይነ መረብ አማካኝነት ተጠናክሯል። ያደጉት ሀገራትም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፍሬዎችን ተጠቅመው የትምህርት ዘርፉን እያሳደጉት ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ወዳጀነት ፈጥረዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ ትብብሩን ለማጠናከር እንደ አንድ ዘርፍ ተይዞ እየተሰራበት ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ወዳጅነት ለትምህርት ዘርፍ እድገት ምን አይነት ፋይዳ ይኖረዋል? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ምሁራን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ትምህርተ ኮሌጅ ተመራማሪና መምህር ካሳ ሚካኤል (ዶ/ር) እንደሚልጹት፤ በሀገር ውስጥ አንድ ዩኒቨርሲቲ የ መማር ማስተማር፣ ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎትን የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች አድማሳቸውን በማስፋት ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚችልበት አማራጭ ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አንድ ሀገር በሁሉም የዕውቀት ዘርፍ የተሟላ ልምድ ላይኖራት ይችላል፤ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ መሥራታቸው ወሳኝነት አለው ይላሉ።

ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም አቀፍና በሀገር ደረጃ በጋራ መስራታቸው ጋር ያለውን ባለሙያ ሌላው የሚጠቀምበት አንዱ የሠራውን የምርምር ውጤት በጋራ ለመጠቀም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳሉ።

ዶክተር ካሳ እንደሚገልጹት፤ ግንኙነቱ እየጠነከረ ሲመጣ ሁለት ተቋማትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ፕሮግራም እንዲቀረጽ እና የጋራ ዲግሪ መስጠት እስከሚቻልበት ሂደት በትብብር መሥራት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የባለሙያዎች ውስንነት ስላለባት ከሌሎች ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች የምትማረው ነገር ብዙ ይኖታራል ሲሉ ያመላክታሉ፡፡

ከዓለም ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚደረግ ወዳጅነት እንደ አጠቃላይ በትምሀርት ዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት አስፈላጊ ቢቻ ሳይሆን አስገዳጅም ጭምር ነው ይላሉ፡፡
ተመራማሪው በትብብር መስራቱ ባለሙያዎችን ለመቀያየር፣ ለማሰልጠንና አቅምን ለማጎልበት ያግዛል ሲሉ ያመላክታሉ።
በሀገሪቱ የዩኒቨርሲቲዎች ኅብረት መኖሩን በመጥቀስ፤ በተናጠል ከሚደረገው ግንኙነት ይልቅ በጋራ መወያየትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት ከተቻለ እንደሀገር የሚኖረው ጥቅም ከፍ ይላል ባይ ናቸው።
በቀጣይ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋራ የመሥራት አቅማቸውን ለማሳደግ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በታገዘ መንገድ ከኤምባሲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርሲቲ ትብብሮችን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ተመራማሪው እንደሚሉት፤ የተጀመሩ ትብብሮች እንዳይቋረጡ በጋራ ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን፤ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተመራማሪዎችና ምሁራን የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በዲፕሎማሲ ግንኙነት ደረጃ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል፤ አሁን ሥራው ጅማሮ እንደመሆኑ በቀጣይ እየተጠናከረ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ ይላሉ።

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራርና አስተዳደር መምህር አማኑኤል ኤሮሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በዓለም ደረጃ የዩኒቨርሲቲዎች ተወዳዳሪና መልካም ስነ-ምግባር ያለው ዜጋ የማፍራት ተልዕኮ አላቸው፡፡
ዕውቀት ዓለም አቀፋዊ ነው የሚሉት የትምህርት ምሁሩ፤ በዓለም ያደጉና ያላደጉ ሀገራት እንደመኖራቸው የዩኒቨርሲቲዎች ወዳጅነት በጣም ጠቃሚ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ያደጉ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች በቴክኖሎጂ አቅማቸው፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በፈጠራ ሥራዎችና በእውቀት ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ ደርሰዋል። ያላደጉ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ካደጉ ሀገራት ተቋማት ጋር በመስራታቸው ሰፊ ልምድ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡

በትብብሩ የትምህርት ዕድል የማግኘት፣ የልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እና ስራቸውን በማስተዋወቅ የሚያድግበትን መንገድ የማመቻቸት ዕድል ይፈጠራል ይላሉ።
እንደ ዶክተር አማኑኤል አገላለጽ፤ ዘመኑ የግሎባላይዜሽን እንደመሆኑ አንዱ ያለውን የምርምር ውጤትና ቴክኖሎጂ በጋራ ለመጠቀም በትብብር መስራት ወሳኝ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ወደራስ ገዝነት እየተሸጋገሩ መሆኑን አንስተው፤ ራስ ገዝ ሆነው ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መወዳጀታቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸው ላይ ውሳኔ በመስጠት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳ ይገልጻሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች እራስ ገዝ በሚሆኑበት ወቅትም ከግንኙነቱ ጋር ተያይዞ ምን ምን ማሟላት እንዳለባቸው ግፊት ሊደረግ ይገባል ያሉት ዶክተር አማኑኤል፤ በዚህ ረገድ የትምህርት ሚኒስቴር ወሳኝ ሚና አለው ይላሉ፡፡
ዶክተር አማኑኤል እንደሚናገሩት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በዕውቀትን የመምራት ችግራቸውን ቀርፈውና ሀገር በቀል ዕውቀትን በማሳደግ ትብብራቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል።

መምህራኑ እንደሚገልጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች በሌላው ዓለም ከሚገኙ አቻዎቻቸው ጋር የሚፈጥሩት ትብብር ለተማሪዎቻቸው፣ ለተመራማሪዎችና ለሀገር የሚበጅ ትሩፋትን ይዞ የሚመጣ በመሆኑ አቀማቸውን ለማሳደግ ሊጠቀሙበት ይገባል።

አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You