በኢትዮጵያ ለጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ መስፋፋት የማህበራዊ ሚዲያዎች ሚና ጉልህ ነው

በቪዲዮ ከተሰራጩት የጥላቻ ይዘቶች ቲክቶክ ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል

አዲስ አበባ፡- በተዘጋጀው ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ለጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ መስፋፋት የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሚና ጉልህ እንደሆነ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ በቪዲዮ ከተሰራጩት የጥላቻ ይዘቶች ቲክቶክ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙ ተመላክቷል።
ባለስልጣኑ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የተመለከተ ሀገራዊ ሪፖርት ትናንት ይፋ አድርጓል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ በአዋጅ የተሰጠውን መብት በመጠቀም ባለፉት ስድስት ወራት የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን የተመለከተ ሪፖርት አዘጋጅቷል።

በሪፖርቱ ግኝት መሠረት ለጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ለችግሩ መስፋፋት ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ተመላክቷል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ድርጅቶቹ የተጠቃሚ ማህበረሰቡን ደንብና መመሪያ ቢያዘጋጁም ባስቀመጡት ደንብ መሠረት ችግሩን ለመቀነስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ሲሉ ጠቁመዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች የሚሰራጩ መልዕክቶች የኢትዮጵያዊያንን ማህበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎችን ቋንቋና ባህል ባገናዘበ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም አገልግሎታቸውን በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ማቅረብ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ከአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ለመሥራትና ጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል ሪፖርትን መነሻ ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡
ሪፖርቱ የማህበራዊ ሚዲያዎች ምን ያህል በኃላፊነት ሲሰሩ ነበር የሚለውን ለሕዝብ ከማቅረብ ባሻገር የሚነሱ ምክረ ሃሳቦች ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት ሆነው እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል፡፡

በባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ኤደን አማረ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳመለከቱት፣ በጥላቻ ንግግርና በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ዙሪያ እያንዳንዳቸው የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ባወጡት አሠራር መሠረት የማህበረሰብ ደንብና መመሪያ አክብረው ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በፍረጃ፣ ሰብዓዊነትን በማዋረድ፣ በጭካኔ አገላለጽ፣ ጽንፍ በያዘ አገላለጽና የጋራ እሳቤዎችን በሚንድ መልኩ የጥላቻ ንግግሮች መተላለፋቸውን ኃላፊዋ አመላክተዋል።
እንደ ዴስክ ኃላፊዋ ገለጻ፤ በስድስት ወራት የጥላቻ ንግግር ይዘቶች የተላለፉበት ቅርጽ በዋናነት በጽሑፍ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች በኤክስ (ትዊተር) ማህበራዊ ድረ-ገጽ 66 በመቶ፣ በፌስቡክ 63 በመቶ እና በቴሌግራም 59 በመቶ በስፋት ተጠቅመዋል። በቪዲዮ የተሰራጩ የጥላቻ ይዘቶች በቲክቶክ 74 በመቶ እና በዩቲዩብ 70 በመቶ ሆነው ታይተዋል።
የተሰራጩት የጥላቻ መልዕክቶች ለአመጽና ለጥቃት የማነሳሳት፣ የግለሰብን ሰብእና የመጉዳት፣ የማህበረሰብን ባህልና ወግ በመናድ የሕዝብን አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸርን የሚያስከትሉ ሆነው መታያታቸውን ተናግረዋል።
አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች የኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎችን ቋንቋ፣ ባህልና እሴት ተረድተው የሚሰራጩ መልዕክቶችን ተከታትሎ የሚያርም ባለሙያ ማካተት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። የማህበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቀምን አስመልክቶ መሠረታዊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል።
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ እያስከተለ ካለው አደጋ ሰፊና ውስብስብ እየሆነ ከመምጣቱ አንጻር በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ሚና ያላቸውን ማህበራዊ ትስስር አውታሮች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ አዋጁን ለማስፈጸም ሚና የተሰጣቸው መንግሥታዊ አካላት፣ የሲቪል ማህበራትና ኅብረተሰቡ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You