ጀርመን ለስምንት ማስተማሪያ ሆስፒታሎች የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፡- የጀርመን መንግሥት በልማት ባንኳ አማካኝነት ለስምንት ከፍተኛ ትምህርት ማስተማሪያ ሆስፒታሎች ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገች።

የኒራስ ጀርመን ባዮ ሜድካል ፕሮጀክት ቡድን መሪ ጌሪት ክሉግ ትናንት ድጋፉ በተደረገበት ወቅት እንደገለጹት፤ ለስምንቱ ማስተማሪያ ሆስፒታሎች የሚከፋፈሉት አይሲዩ አልጋዎች፣ ቬንቲለተሮች፣ ኦክሲጅን ኮንሰንትሬተርስና ሌሎችም የሕክምና መሳሪያዎች ናቸው፡፡

ከሕክምና ድጋፉ በተጨማሪ ለጤና አጠባበቅ ስፔሻሊስት እና ቴክኒሻኖች በሥልጠና መስክ የአቅም ማጎልበት ድጋፍም ይሰጣል ብለዋል።
የተደረገው እገዛ የሆስፒታሎቹን አቅም ለማጎልበትና ለተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት ለማቅረብ ያግዛል ያሉት ጌሪት ክሉግ፤ ድጋፉ ከዚህ ቀደም በጀርመንና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ለሕክምናው ዘርፍ ድጋፍ ለማድረግ የተደረገ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ የሕክምና መሳሪያዎቹ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለሕክምና ተማሪዎቻቸው የተግባር ተኮር የክህሎት ስልጠና እንዲሰጡ የሚረዱና የጤና ባለሙያዎች ለህይወት አድን ሥራቸው የሚጠቀሙባቸው ናቸው።
ጀርመን ለኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍ እያደረገች መሆኑን የገለጹት ጌሪት ክሉግ፤ በቀጣይም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አመላክተዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ በጤናው ዘርፍ ላይ ተግዳሮት እየሆነ ያለው የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ነው፤ ይህንን ለማሟላት እንደሀገር ለሚደረገው ጥረት ድጋፉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

ድጋፉ ወደ ሕክምና ተቋማት ሲገባ አሁን ላይ እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከርና ጥራቱን ለመጨመር ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት አቶ አሰግድ፤ ከሕክምና መሳሪያው በተጨማሪ ብልሽት ቢያጋጥም ጥገና ለማድረግ የሚያስችሉ መሳሪያዎች አብረው መኖራቸው ድጋፉን ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ድጋፉ በየሆስፒታሉ የሚገኙ የባዮ ሜዲካል ወርክሾፖችን ለማጠናከርም አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የሕክምና መሳሪያዎቹ ጊዜውን የሚዋጁ በመሆናቸው በሀገሪቱ አሁን ላይ እየተሰጠ ያለውን የሕክምና አገልግሎት ይበልጥ ለማዘመን እንደሚረዱ ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማትና ግብዓት ዴስክ ኃላፊ ዘውዱ ካሳ እንደተናገሩት፤ ድጋፉ በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል፣ የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ሚና ይኖረዋል፡፡

ከሚሰጠው የሕክምና መሳሪያ በተጓዳኝ ከፍተኛ ወጪ ተመድቦ ለባለሙያዎችም ስልጠናዎች እንደሚሰጡ የገለጹት የዴስክ ኃላፊው፤ የተደረገው ድጋፍ በማስተማሪያ ሆስፒታሎች ለጽኑ ሕሙማን ሕክምና ለመስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ፤ የጀርመን መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ መሻሻል ለረጅም ጊዜ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ያሁኑ ድጋፍ ትኩረቱን የሚያደርገው በጤና ተቋማት የሚገኙ የላቦራቶሪ፣ የወርክሾፕ መሳሪያዎችን መጠገን የሚችሉ ሠራተኞችን ማብቃት ላይ ነው፡፡

ድጋፉ የተደረገላቸው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል፣ አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል፣ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ማዕከል፣ አይደር ሪፈራል ሆስፒታልና አርባ ምንጭ ሪፈራል ሆስፒታሎች መሆናቸው በመርሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You