ሐረሪዎች ያበረከቱት ቅርስና ዕሴት ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ሆኗል

አዲስ አበባ:- ሐረሪዎች ያበረከቱት ቅርስና ዕሴት ድንበር ተሻጋሪ ሀብት መሆኑን የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርና የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጹ። በሐረሪ ክልል “ሸዋል ዒድ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ ሃሳብ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

በሐረሪዎች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የሸዋል ዒድ ዋዜማ ትናንት በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ሲከበር በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፤ ሐረር የዳበረ ዕሴትና ባሕል ባለቤት ነች፤ በተለይ የሸዋል ዒድ በዓል ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ነው ብለዋል።

ሐረሪዎች ፍቅርና አብሮነትን ከቀደምቶቻቸው ተቀብለው ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፉ በኩል እየተወጡት ያለው ሚና የሚደነቅ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ያበረከቱት ቅርስና ዕሴትም ድንበር ተሻጋሪ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል። ክልሉ ለሚያደረገው እንቅስቃሴ የቱሪዝም ሚኒስቴር ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፤ ሐረር ትውፊታዊና ዕምነታዊ ባህሎች የሚንፀባሩቁባት ከተማ መሆኗን ገልጸው፤ ፍቅርና አብሮነት ባህሉ የሆነው የሐረር ሕዝብ በሸዋል ዒድ ዕለት ደምቆ የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሸዋል ዒድ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ መመዝገቡን አስታውሰው፤ በዓሉ ሁሉም የሚያከብረው መሆኑ ለመመዝገቡ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል።
አሁንም ክልሉ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የቱሪዝም ሚኒስቴር ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ ሐረር ሁለት ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከሀገራችን ከተሞች ቀዳሚ ነች፤ ይህም ለቱሪዝሙ ዘርፍ የጎላ ሚና አለው፤ ይህን ታሳቢ በማድረግም እንደ ክልል እድሎችን የማስፋት ሥራ እየተከወነ ነው ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ሐረር ሁለት ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከሀገራችን ከተሞች ቀዳሚ ነች፤ ይህም ለቱሪዝሙ ዘርፍ የጎላ ሚና አለው፤ ይህን ታሳቢ በማድረግም እንደ ክልል እድሎችን የማስፋት ሥራ እየተከወነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተያያዘ የሸዋል ዒድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል ትናንት በሐረር ከተማ ተከፍቷል።

በባህል ዐውደ ርዕዩና ፌስቲቫሉ አጎራባች ክልሎች እና የአርጎባ የባህል ቡድን እንዲሁም የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ አምራች ማህበራትና ተቋማት ተሳትፈዋል።

ሸዋል ዒድ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እጅ ተረክበዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You