ዩኒቨርሲቲው ከ350 በላይ ለመድኃኒትነት በሚውሉ እጽዋት ላይ ምርምር እያካሄደ ነው

ቦንጋ፡- ከባህላዊ ሐኪሞች ጋር በመተባበር ከ350 በላይ በሚሆኑ ለመድኃኒትነት በሚያገለግሉ እጽዋት ላይ ምርምር እያካሄደ መሆኑን የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ የእንሰት እርሻን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማስፋፋት እየሠራ ነው፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህብረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ከለላው አዲሱ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከ350 በላይ እጽዋት ተለይተው በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲበዙና እንዲቀመጡ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቡድን አዋቅሮ በየወረዳው ከሚገኙ የባህላዊ ሐኪሞች ጋር እጽዋትን ለይተው እንዲያሰባስቡና በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲበዙና እንዲቀመጡ ማድረጉን አስረድተዋል።

እያንዳንዱ እጽዋት ለየትኛው በሽታ መድኃኒትነት እንደሚያገለግሉ በመለየት ለእጽዋት መድኃኒቶቹ ሳይንሳዊ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ያሉት ዶክተር ከለላው፤ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ በላብራቶሪ የታገዘ “የኬሚካል ካራክተራይዜሽን” የመለየት ሥራ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉ የእንሰት ችግኞችን በግቢው ውስጥ እና ከግቢው ውጪ ባሉ ቦታዎች ላይ በስፋት የማፍላት ሥራ በማከናወን ለማህበረሰቡ እያስተላለፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የእንሰት እርሻን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማስፋፋ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀው፤ የተለያዩ አፍሪካዊያንን እንሰት በቀላሉ ለምግብነት መዋል እንደሚችል በጥናት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

እንሰት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ቢመረት እንደሀገር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ይህን ታሳቢ አድርጎ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የምግብ ዋስትና ጉዳይ በጣም ትኩረት የሚሻው በመሆኑ እንሰት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ለማህበረሰቡ ማስተማርና እንሰትን እንዲያመርት ማድረግ ያስፈልጋል  ሲሉ ዶክተር ከለላው አመላክተዋል፡፡

ከውጭ ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ጌሻ በተባለ ወረዳ ላይ ወደ 20 ሄክታር መሬት በእንሰት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አካታች የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ሥራ በማከናወን ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ በአትክልትና ፍራፍሬ በእንስሳት እርባታ የምርምር ግኝቶችን ወደ ውጤት በመለወጥ ለማህበረሰቡ እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ፤ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፣ አሳ፣ እንቁላልና ሌሎች ምርቶችን ያመርታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሺህ በላይ ዶሮዎች በግቢው ውስጥ በማራባት በቀን እስከ አንድ ሺ 900 እንቁላል ለማህበረሰቡ ያሰራጫል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከምርምር ሥራው ጎን ለጎን ለ54 አቅመ ደካሞች በየወሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀው፤ በተጨማሪም በዘላቂነት 110 አረጋዊያን መኖር የሚችሉበት የመኖሪያ ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከለላው አዲሱ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነው ሙሉ ቃለ ምልልስ በዛሬው የተጠየቅ አምዳችን ላይ ያገኙታል፡፡

በሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You