ኢትዮጵያን በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ለማድረግ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በስፋት መጠቀም ይገባል

ኢንስቲትዩቱ “አስተውሎት” የተሰኘ ሳይንሳዊ ፊልም አስመርቋል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን በተለያዩ መስኮች ውጤታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ “አስተውሎት” የተሰኘ ሳይንሳዊ ፊልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት አስመርቋል፡፡

በምርቃቱ ወቅት የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር) እንደገለጹት፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በርካታ ሀገራት ችግራቸውን የሚፈቱበት ዋነኛውና ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በርካታ ሀገራት በዘርፉ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡበትና የመወዳደሪያ አውድ እያደረጉት ነው ያሉት ኢንጂነር ወርቁ፤ ኢትዮጵያም  በዘርፉ ቀዳሚ እንድትሆን በሁሉም ዘርፍ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጅን የማሰብ፣ የማቀድ፣ የመማር፣ ምክንያታዊ የመሆን፣ የማመዛዘን፣ ቋንቋን የመረዳትና የአቅም ግንባታ ቀመርን ለማሽኖች በማስተማር በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን የሚያስችል በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ወርቁ ገለጻ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰው ሠራሽ አስተውሎት ማዕከል ግንባታ ያስተላለፉትን መልዕክት ከተቋማችን አልፎ በሀገሪቱ ለሚገኙት ተቋማት ታላቅ ብርታት ሆኗል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሀገሪቱን በዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ወጣቶችን ለማብቃት በክረምት መርሀ ግብር እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ድረስ በማሰልጠን እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪከ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጆችና በኢትዮጵያ የተሠሩ ሮቦቶች በትብብር “አስተውሎት” የተሰኘ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ ፊልም ሠርተው ለእይታ መብቃቱን ተናግረዋል።

ለምረቃ የበቃው “ፊልም በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት የተዘጋጀ ሲሆን፤ ዝግጅቱ አንድ ዓመት ተኩል የፈጀና ሙሉ በሙሉ በእውነተኛ ታሪክ የተመሰረተ ሳይንሳዊ ፊልም ነው ብለዋል።

በፊልሙ አንጋፋ ተዋንያን፣ ታላላቅ ሰዎችና ወጣት ተዋንያን መሳተፋቸውን ገልጸው፤ “አስተውሎት” ፊልም ለእይታ እስከሚቀርብ እገዛ ላደረጉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለሌሎች ተባባሪ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በፊልሙ ምርቃት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር)፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You