እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ ምላሽ ብትወስድ አሜሪካ ተሳታፊ እንደማትሆን አስታወቀች

ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን በማምከን ድጋፍ ስታደርግ የነበረችው አሜሪካ እስራኤል የበቀል እርምጃ ብትወስድ ተሳታፊ እንደማትሆን አስታወቀች።አንድ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ እስራኤል ልትወስድ በምትችለው የአጸፋ እርምጃ ውስጥ አሜሪካ ተሳትፎ አይኖራትም ብለዋል።

ኢራን ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ እስራኤል ከተተኮሱት ሚሳኤሎች እና ድሮኖች በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በአጋር ሀገራት ዒላማቸውን ሳይመቱ ተመትተው ወድቀዋል። ከዚህ ከኢራን ጥቃት በኋላ የእስራኤል ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል በስፋት ይጠበቃል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግን እስራኤል ቀጣይ እርምጃዋን በአስተውሎት እንድትወስድ አሳስበዋል። የአሜሪካ ባለስልጣናት ከ300 በላይ የሚሆኑት ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ከኢራን፣ ኢራቅ እና ከየመን ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን ገልጸው፤ 99 በመቶ የሚሆኑት ጉዳት ሳያደርሱ በእስራኤል እና በወዳጆቿ አማካይነት እንዲከሽፉ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በቀጣናው የነበሩት የአሜሪካ የጦር ጀቶች እና የጦር መርከቦች በርካታ የኢራን ሚሳኤሎችን መትተው ጥለዋል። የሀገሪቱ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከ80 በላይ ድሮኖች እና ስድስት ባሊስቲክ ሚሳኤሎች በኢራቅ እና የመን የአየር ክልል ውስጥ በአሜሪካ አማካይነት ተመትተው ወድቀዋል።

ኢራን በዚህ ጥቃቷ 100 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን በተመሳሳይ ጊዜ ወደ እስራኤል አስወንጭፋ ነበር ተብሏል። ከኢራን ጥቃት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና ፕሬዚዳንት ባይደን ባደረጉት የስልክ ንግግር “ነገሮችን እንዴት ማቀዛቀዝ እንደሚቻል” ተወያይተዋል ተብሏል።

አሜሪካ እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ብትሰጥ ተሳታፊ አልሆንም ትበል እንጂ እስራኤል በኢራን ላይ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ አለባት የሚል ማስጠንቀቂያ ስለመስጠቷ የተባለ ነገር የለም። የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ አሜሪካ በግልጽ በቀጣናው የተስፋፋ ጦርነት እንዲኖር እንደማትሻ ለእስራኤል አሳውቃለች ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኢራን በጥቃቷ የምትቀጥል ከሆነ አሜሪካ እስራኤልን በመከላከል ትቀጥላለች ብለዋል የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባዩ። ይህ የኢራን ጥቃት ድንገት የተከሰተ አይደለም። ኢራን ከ12 ቀናት በፊት በሶሪያ ዋና ከተማዋ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቆይታለች።

ከአሜሪካ በተጨማሪ ይህን የኢራን ጥቃትን በመከላከል ለእስራኤል ድጋፋቸውን ከሰጡ ሀገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም እና ጆርዳን ይገኙበታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You