የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የመርከቦች እገታ ቁጥር ጨምሯል

የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች አግተን የነበረውን የባንግላዴሽ ባንዲራን የምታውለበልብ መርከብ እና ሠራተኞቿን ለማስለቀቅ 5 ሚሊዮን ዶላር ተቀበልን አሉ። ኤምቪ አብዱላህ የምትባለው ዕቃ ጫኝ መርከብ የድንጋይ ከሰል ጭና ከሞዛምቢክ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እየተጓዘች ሳለች ነበር በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ላይ በባሕር ወንበዴዎች የታገተችው።

መርከቧን አግተው የቆዩት የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ መርከቧን እና 23 የመርከቧን ሠራተኞች ለማስለቀቅ 5 ሚሊዮን ዶላር ተቀብለናል ብለዋል። ይሁን እንጂ የመርከቡ ባለቤቶች በድርድር መርከቧ መለቀቋን ቢያምኑም ገንዘቡን ስለመክፈላቸው ያሉት ነገር የለም።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በሶማሊያ የባሕር ክልል ውስጥ የመርከቦች እገታ ቁጥር ጭማሪ እያሳየ ነው። በተለይ ካለፈው ኅዳር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ መርከቦች ታግተዋል። የደኅንነት ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የባሕር ላይ ውንብድናው የጨመረው በአካባቢው የተለያዩ ሀገራት ጥምረት የባሕር ላይ ቅኝት የሚያደርጉ አካላት ትኩረታቸውን ወደ ቀይ ባሕር ላይ በማድረጋቸው ነው።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ በየመን የሚገኙ የሁቲ አማጺያን ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦችን ዒላማ ባደረጓቸው ጥቃቶች ምክንያት የቀይ ባሕር የንግድ መርከብ እንቅስቃሴን አውከዋል። ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለት የባሕር ላይ ወንበዴዎች ነግረውኛል ብሎ በሠራው ዘገባ ኤምቪ አብዱላህ መርከብ እና ሠራተኞቿን ለማስለቀቅ 5 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ተከፍሏል።

“የተቀበልነው ገንዘብ ትክክለኛ መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ገንዘቡን ተከፋፍለን ለቀናል” በማለት አብዲራሺድ ዩሱፍ የተባለ የባሕር ላይ ወንበዴ ለሮይተርስ ተናግሯል። የመርከቧ ባለቤት የሆነው ኬኤስአርኤም ግሩፕ መርከቧ እና ሠራተኞቿን በድርድር አስለቅቄያለሁ ብሏል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተባለው የዜና ወኪል ደግሞ ሚዛኑል ኢስላም የተባሉ የመርከቧን ባለቤት ድርጅት ባልደረባ ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ነጻ የወጣችው መርከብ በሁለት የጦር መርከቦች ታጅባ ጉዞዋን ወደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አድርጋለች ብሏል። ሚዛኑል ኢስላም “ከባሕር ላይ ወንበዴዎች ጋር ከስምምነት ደርሰናል። ስለተባለው ገንዘብ ምንም ማለት አልችልም። በአሁኑ ወቅት መርከቧም ሆነች የሁሉም ሠራተኞች ደኅንነት የተጠበቀ ነው” ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

እንደ የዓለም ባንክ ግምት ከሆነ እአአ በ2005 እና 2012 መካከል በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ የባሕር ላይ ወንበዴዎች መርከቦችን እና የመርከብ ሠራተኞችን አግተው ከ339 እስከ 413 ሚሊዮን ዶላር የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You