የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ጽዳት ነው። ጽዱ ማህበረሰብ ጤናማ ትውልድን በማፍራት አምራች ዜጋን መፍጠር ይችላል ። ያደጉት ሀገራት ተሞክሮም የሚመላክተው ይህንኑ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት ሰነድ እንደሚያትተው ምንም እንኳ ባለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች (LMICs) ውስጥ የዜጎች የጤና ሁኔታ የተሻሻለ ቢሆንም ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ አዳዲስ እውነታዎችም ተፈጥረዋል።
የተለወጡ የጤና አጠባበቅ ፍላጎቶች፣ እያደጉ ያሉ የማህበረሰብ ጥያቄዎች አብረው መጥተዋል። እነዚህ ደግሞ ከፍ ያሉ የጤና ግቦችን፤ የተሻሻሉ የጤና ሁኔታዎችን እና የላቁ የማህበራዊ እሴቶችን ለመፍጠር አስገድደዋል። እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት ደግሞ አሁን ባለው አካሄድ መቀጠል በቂ አይደለም።
የጤና ሥርዓቱን ጥራት ለማሻሻል ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን (UHC) መነሻ ሊሆን ይችላል። ሽፋኑንና የገንዘብ ድጋፍን ከማስፋፋት በተጨማሪ ጥራትን ማሻሻል ለሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን አውን መሆን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥታትም ለጤናና ተያያዥ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተለይም ለጤና ጉድለት እንደአንድ መንስኤ የሚጠቀሰውን የአካባቢ ጽዳት መጓደልን ለማስተካከል ከፍተኛ በጀት ከመመደብ ጀምሮ ህብረተሰቡን የሚያሳትፉ ሰፋፊ ንቅንቃቄዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በተለይም በአካባቢ ጤና መጓደል ዋነኛ ምክንያት ቀዳሚ ተጠቂ የሚሆኑት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከመሆናቸው አኳያ፤ እነሱን መሠረት ያደረገ የጤናና የአካባቢ ጽዳት እንቅስቃሴ ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ፤ እያንዳንዱ የጤናና የአካባቢ ጽዳት እንቅስቃሴዎች ከመጀመራቸው በፊት ሁሉም ሰዉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ማረጋገጥ እና ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል። ዝቅተኛውን ማህበረሰብ ያላሳተፈ የአካባቢ ጽዳት ንቅናቄ ውጤት አይኖረውም።
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ኑሮ ለጤና ትብብር ንቅናቄ ይህን ሃሳብ የሚደግፍ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን የአካባቢ ንጽህና ጉዳይ ብዙም የዳበረ ባህል አይደለም። በዚህ ምክንያትን በሚከሰቱ ችግሮች /በሽታዎች ምክንያት ተጠቂ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በእጅጉ በርካታ ናቸው ።
ከጤና ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚ ጠቁሙት፤ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጸዳጃ ቤት አይጠቀምም። ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠረው የሀገሬው ነዋሪ ወገቡን የሚፈትሸው በየጥሻውና በየጥጋጥጉ ነው። ይህ እንደ ሀገር በማህበረሰብ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ከግለሰብና ማህበረሰብ አልፎም ጦሱም ለሀገር የሚተርፍ ነው።
የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እነዚህን የማህበረስብ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ ያለመ ነው። ንቅናቄው እንደ ሀገር በርካታ ተቋማት ተቀብለው እያስቀጠሉት ይገኛሉ። ንቅናቄው በጠንካራ ዲሲፕሊን እና በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ ከተመራ የማህበረሰብን ጤና ለማሻሻል ሁነኛ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ነው።
የ “ጽዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ አካል የሆነው የጽዱ ጤና ተቋማት ንቅናቄ ከጀመሩት የፌዴራል ተቋማት መካከል የጤና ሚኒስቴር አንዱ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበረውና “የጽዱ ኢትዮጵያ ጽዱ ጤና ተቋማት ለተሟላ ጤንነት” በሚል መሪ ሃሳብ የያዘውን የአካባቢ ጽዳትና ንፅህናን የማሻሻል እንቅስቃሴ በተለያዩ ሆስፒታሎችም ተጀምሯል። ይህም ንቅናቄ ሆስፒታሎችን ንፁህ በማድረግ ኅብረተሰቡን ጤናማ ለማድረግ የሚያስችልም ይሆናል።
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የጽዱ ጤና ተቋማት ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ጤናማ ለመሆን ንጽህናን ከራስ በመጀመር ወደ አካባቢ ከዛም ወደ ሀገር ማስፋት ይጠበቃል። ይህንንም በያገባኛል ስሜት በጋራ መሥራት እንዲቻል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በስፋት መሥራትን ይሻል።
እንደ ሀገር ለሁሉም ዜጎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን መፍጠር የሚቻለው የነቃና የጤና ችግሮችን መለየት የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ የማህበረሰቡን የጽዳት ባህል ክብርን የጠበቀ ለማድረግ የተወጠነው የጽዱ ኢትዮጰያ ንቅናቄ፤ መጸዳጃ ቤቶችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ መገንባትን ያለመ ነው።
ከተማን ውብ፣ ፅዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ አካል ተደርጎ የተጀመረው የ “ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” የሚል አዲስ ሃሳብ የአፍሪካውያን መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በሰፊው እየተተገበረ ይገኛል። ይህ አዲስ ንቅናቄ ነዋሪዎቹን በሚያሳቅቅና አንገት በሚያስደፋ መልኩ በየመንገዱ፤ በየህንጻው ስር መፀዳዳትን በማስቆም የከተማ ውበት በሚጨምር ሁናቴ ፣ ጤናማ አካባቢንም ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
ይህ ተነሳሽነት “ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ቃል በገንዘብ ወይንም በዓይነት የኅብረተሰብ ደጋፍ ማድረግ እንደሚቻል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በዚህም ንቅናቄ በርካታ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በመተግበር ሁሉም ዜጎች በየደረጃቸው አቅማቸው በፈቀደው ድጋፍ በማድረግ አካባቢን ለጤና ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በዓለም ባንክ ድጋፍ በሀገሪቱ 22 ከተሞች ከማኅበረሰብ የንጽህና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ በመከናወን ላይ የሚገኙ የውሃና የመጸዳጃ ቤት ፕሮጀክቶች በተለያዩ ከተሞች በመገንባት ላይ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ የመጸዳጃ ቤት ሽፋን በፈረንጆቹ 2030 ዓ.ም ወደ መቶ ፐርሰንት ለማድረስ የሚያግዙ ናቸው። እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ሲተገበሩ እንደ ሀገር ንጹህና ጽዱ አካባቢን በመፍጠር ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋን መፍጠር የሚያስችል ይሆናል።
ግርማ ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም