‹‹ዘንድሮ በዞናችን 600 ሄክታር ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ተችሏል›› – አቶ አክሊሉ ካሣ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ

መንግሥት የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና በምግብ እህል ራስን ለመቻል የተያዘውን ሃገራዊ ግብ ለማሳካት በርካታ መርሐ ግብሮችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል። በዋናነትም የሌማት ትሩፋት የተባለው የልማት መርሐግብር በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ በማድረግ እያንዳንዱ አርሶአደር በማሳው ከአትክልትና ፍራፍሬ ጀምሮ የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ምርት እየሰበሰበ ነው የሚገኘው። አርሶአደሩ ከመቼውም ግዜ ነቅቶና ተግቶ በክላስተር እያለማ ባለው በበጋ መስኖ ልማትም ዘርፉ የሃገር ኢኮኖሚ ዋልታ መሆን እያረጋገጠ ነው።

በዚህ የተቀናጀ ግብርና ልማት ውጤት እያመጡ ካሉ ክልሎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተጠቃሽ ሲሆን በተለይም የክልሉ መንግሥት በቀረፀው የልማት መርሐ ግብር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በከፍተኛ መጠን እየተመረተ ነው ያለው። ከተጀመረ ሦስት ዓመታትን ባስቆጠረው በዚሁ መርሐ ግብር እያንዳንዱ አርሶአደር 100 እና ከዚያ በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ባለቤት ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ ገቢ በማግኘትና ለሌሎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ አብነት ሆነዋል። ከእነዚህ በምርትና ምርታማነት እድገት ውጤት እያመጡ ካሉ የክልሉ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የጉራጌ ዞን አጠቃላይ የግብርና ሥራን በሚመለከት የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ ከአቶ አክሊሉ ካሣ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በዞኑ ከሌማት ትሩፋት ጋር ተያይዞ እየተሠራ ስላለው የግብርና ሥራ ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?

አቶ አክሊሉ፡- በዞናችን በተቀናጀ ግብርናም ሆነ በሌማት ቱፋት መርሐ ግብር ሰፋ ያለ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው። በእንስሳት ዘርፉም ሆነ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራ ይሠራል። በአሁኑ ወቅት በዋናነት እየተሠራ ያለው የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ነው። በበጋ መስኖ ላይ ዞኑ ከ30 ሺ ሄክታር በላይ የተለያዩ ሰብሎች ማልማት ችሏል።

ከዚህም ውስጥ ወደ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ የአትክልት ምርት መሰብሰብ ችሏል። በዞናችን አስር ወረዳና አምስት መዋቅር ያለን ሲሆን የተቀናጀ ግብርና ልማቱም እየተከናወነ ያለው በእነዚህ 15 መዋቅሮች ውስጥ ነው። በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሁሉም የወረዳና ቀበሌ መዋቅሮቻችን ያሉ አርሶአደሮች ከተለምዷዊ አስተራረስ ወጥተው በኢኮኖሚም ሆነ በምግብ እህል ራስን ከመቻል አንፃር ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ይገኛሉ።

የዞናችን አርሶአደር ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ በተወሰኑ የግብርና ምርቶች ላይ ብቻ ነበር የሚያተኩረው፤ አሁን ላይ ግን በእያንዳንዱ አርሶአደር ማሳ ሁሉም አይነት አዝርዕት እየተመረተ ነው፤ ከጓሮውም አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት ያመርታል። በተጓዳኝም ከብትና ዶሮችን ያረባሉ፤ በንብ ማነብም አመርቂ የሚባል ውጤት እየመጣ ነው ያለው። በዚህ ረገድም እኛ እንደዞን ያሉንን መዋቅሮችን መደገፍ ነው ዋናው ሥራችን። በዞን ደረጃ ኤክስፐርቶች አሉ። ከወረዳው በተሻለ ደረጃ በእነዚህ ሥራዎች ላይ ማለትም በሰብል እንስሳቱም ዘርፉም ላይ የተሻለ ክህሎት ያላቸው ኤክስፐርቶች አሉ። እነዚህ ኤክስፖርቶች ወደ ታችኛው መዋቅር በማውረድ የሙያ ድጋፍ ይሰጣሉ። የክህሎትና የሙያ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች እስከ ቀበሌ ደረጃ በመውረድ የአርሶአደር የክህሎትና የሙያ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በነገራችን ላይ ይህ የድጋፍ ሥራ አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚያቋርጥ አይደለም፤ አርሶአደሩ ቤት ድረስ በመሄድ ተከታታይነት ባለው መልኩ ነው የሚሠራው።

ከዚህ ባሻገርም ለመርሐ ግብሩ መሳካት ዞኑ ከምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ጀምሮ የተለያዩ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱና በበቂ መጠን ተደራሽ እንዲሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ይሠራል። በዋናነት እነዚህን ነገሮች ለማምረት ቁልፉ ግብዓት ማዳበሪያ እንደመሆኑ ከማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች በወቅቱ ምላሽ እንዲያገኙና አርሶአደሩ ያለምንም ስጋት ትኩረቱን ልማቱ ላይ እንዲያደርግ ባለሙያዎቻችን ድጋፍ ያደርጋሉ። በተጨማሪም አርሶአደሮቹ የተሻሻሉ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ከትክክለኛ ምንጭ እንዲያገኙ ብሎም የአመራረት ሂደቱን በሚመለከት የባለሙያዎቻችን ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል። እንዲሁም በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ውጭ እውን መሆን የማይችል በመሆኑ አርሶአደሩ ያለምንም መቋረጥ ኬሚካሎችን በዩኒየኖቹ አማካኝነት በቅርበት እንዲያገኝ እየሠራን ነው ያለነው። በአጠቃላይ ግን በእኛ ግምገማ የሰጠነው ያለው ድጋፍ በጣም ጥሩ ነው የሚል ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር የአርሶአደሩ ምርታማነት እንዴት ይገለፃል?

አቶ አክሊሉ፡- በነገራችን ላይ በመገባደድ ላይ ያለው ዓመት እንደዞን የያዝናቸው እቅዶች ጭምር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ማሳካት የቻልንበት ነው። አስቀድሜ የገለፅኩት ከ30 ሺ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በበጋ ወቅት ማልማት ትልቅ ነገር ነው። አብዛኛው የመስኖ ልማት ሥራዎቻችን ወራጅ ወንዞችን በመጠቀም ነው የምናለማው። በተጨማሪም የጉድጓድ ውኃ በማውጣት በፓምፕ በመሳብ፤ ትልልቅ ኩሬዎች በማዘጋጀት፤ አሉ የምንላቸውን የውሃ አማራጮች በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እናደርጋለን። በተለይም በኩሬ ደረጃ ትልቅ ቦታ በማዘጋጀት የክረምት ዝናብና ጎርፍ በማጠራቀም፤ በጋ ላይ ሰብሎቹን እናመርታለን። ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ግን ዓመቱን ሙሉ ማምረት በዞናችን ብቻ ሳይሆን እንደክልልም አይታወቅም ነበር፤ በተለይም ዞኑ በርካታ የውሃ አማራጮች ቢኖሩትም ያንን ተጠቅሞ ማልማቱ እምብዛም አልተለመደም ነበር።

ከዚህ አንፃር ለአብነት ያህል እንድብር ወረዳን ብንጠቅስ፤ በወረዳው በርካታ ወንዞችና ኩሬዎች እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃ በስፋት አለ፤ በእነዚህ የውሃ አማራጮች ግን ከባሕር ዛፍ፤ እንሰትና ጥቂት ሰብሎች ውጪ በቋሚነት የሚመረት ምርት አልነበረም። አሁን ላይ ግን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሠራቱ በርካታ ወጣቶች ተደራጅተው በስፋት እያለሙ ይገኛሉ። ከአምስት ዓመታት በፊት ባዶ፤ ከብት ሲግጠው ይውል የነበረ ሜዳ ዛሬ ለኤክስፖርት ጭምር ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች እየተመረቱበት ይገኛል። በስፋት ወጣቶችም ወደ ልማት እየገቡና ለሌሎችም የሥራ እድል እየፈጠሩ ነው ያሉት። ይህ ውጤት ሊመጣ የቻለውም አርሶአደሩ የሚሰጠውን ምክረ ሃሳብ በመቀበሉና ግብዓቶችም ተጠቅሞ ለማልማት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ በመሆኑ ነው፤ በዚህም ምርታማነቱ በከፍተኛ መጠን አድጓል፤ ከዚህ ቀደም እጅ ጠባቂ የነበሩ ግለሰቦች ሳይቀሩ የሌሎቹን ውጤት በማየት በመርሐ ግብሩ ተካተው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን፡- በበጋ መስኖ ልማት ሥራ በዋናነት በዞኑ እየተመረቱ ያሉ ምርቶች ምንድን ናቸው?

አቶ አክሊሉ፡- የግብርና ሥራ በባሕሪው ዘርፈ ብዙ ነው፤ እንደየወረዳው ሥነ-ምሕዳር አካባቢ ሁኔታ በመመርኮዝ በበጋ መስኖ የተለያዩ ምርቶች እየተመረቱ ነው። የቸሃ ወረዳን ለአብነት ብንጠቅስ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ አርሶአደሩን በክላስተር በማደራጀት ነው እየተመረተ የሚገኘው። ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንፃር 30-40-30 ኢኒሼቲቭ የተባለ መርሐ ግብር አለን። በዋናነት ከእኛ ዞን አንፃር አቦካዶ፣ ሙዝ፣ አፕል የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን። በመርሐ ግብሩ መሠረት በመጀመሪያው ዓመት 30 በቀጣይ ደግሞ 40 እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት 30 በድምሩ 100 የፍራፍሬ ችግኝ እያንዳንዱ አርሶአደር እንዲኖረው እየተሠራ ነው ያለው። ይሄ ሥራ ዘንድሮ የመጨረሻው ዓመት ላይ ነው ያለነው።

ወረዳዎች እንደአግሮ ኢኮሎጂያቸው ታይቶ ነው የፍራፍሬ ችግኝ ልማቱ እየተከናወነ ያለው። ለምሳሌ አፕልን ብንወስድ ደጋ ወረዳዎች ላይ እየለማ ያለው። እነዚህም ጉመር፣ ጎዌታ፣ እንደጋኝና ገደባኖ ጉታ ዘር እና ምሑር ወረዳዎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ወረዳዎች ላይ በዋናነት ትኩረት አድርገን የምንሠራው የአፕል ልማት ላይ ነው። እስካሁን የአፕል ልማቱ በጣም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ያለው። ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ አፕል የደጋ ፍራፍሬ ሆኖ ሳለ ችግኙን የምናገኘው በጣም ሩቅ ተኪዶ ጨንቻ ከሚባል አካባቢ ነበር። አሁን ይሄ ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ በራሳችን አቅም ችግኝ የማፍላት፤ በተለይ ምርጥ ዝርያዎችን በማምጣት በራሳችን የችግኝ ጣቢያዎች አቋቁመን ችግኝ እያባዛንና ከራሳችን የችግኝ ጣቢያ ለአርሶአደሮቻችን እያደረስን ነው። .

በተመሳሳይ ደግሞ እንደአግሮ ኢኮሎጂው ደግሞ ለሙዝ ምርት ወይም መንደርነት የመረጥናቸው ሦስት ወረዳዎች አሉ። እነሱም እኖር፣ የነርና ቸሃ ወረዳዎች ሲሆን ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የሙዝ ክላስተር በማደራጀት በስፋት እያመረቱ፤ እስከማዕከላዊ ገበያ ድረስ ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል። በነገራችን ላይ በጣም የተሻሉ ዝርያ የምንላቸውን የሙዝ ዝርያዎች ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ኢኒሼቲቩ ሲጀመር አርባ ምንጭ ድረስ በመሄድ ነው ያመጣናቸው ። ያንጊዜ ያስገባነው ችግኝ አሁን ላይ ውላጁ ደርሷል። በመሆኑም አሁን ላይ ለችግኝ ሌላ ቦታ መሄድ አይጠበቅብንም፤ ከዚያው ውላጅ ነው ለአርሶ አደሮቻችን በስፋት እያሰራጨን ያለነው። ለዚህ ዓመትም እዚሁ ቀደም ብለን በተከልንበት አርሶአደር ማሳ ላይ በርከት ያለ ውላጅ ስላለ ከዚያ እየገዛን ለሌሎች አርሶአደር የምናደርስበት ሁኔታ ነው ያለው።

ሌላኛው ምርታችን አቦካዶ ነው፤ አቦካዶ በእዣ፤ ቸሃ፣ እኖርና የነር ወረዳ እንደዚሁም ደግሞ ምሑር አክሊል በተጨማሪም በአሽጌ ወረዳ ላይ በሰፊው በመንደር ደረጃ እያለማን ነው። እነዚህ ወረዳዎቻችንን አቦካዶን በሰፊው እያለሙ ነው ያሉት። ከዚህ በፊትም ቢሆን የተሻለ ተሞክሮ ያለበት ዞን ነው። አሁን ብዙ ራቅ ያለ ቦታ አንሄድም፤ ችግኝ ጣቢያዎቻችን በየወረዳው አሉን፤ ለውጭ ኤክስፖርት እየተፈለገ ‘ሃስ፣ ቲንገርና ሩት’ የሚባሉ ዝርያዎች አሉ፤ እነሱን ቀድሞ ከነበረው ዝርያ ጋር እያዳቀልን በሰፊው እያስተከልን ነው ያለነው። በአጠቃላይ በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ላይ እየሠራናቸው ካሉ ሥራዎች በጣም ውጤታማ ናቸው። በዚህ መንገድ ከቀጠልን እንግዲህ ወደፊት አስደሳች ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ።

እንደአጠቃላይ ምንም ካልነበረበት ሁኔታ ተነስተን አሁን ላይ በዞናችን ሙዝና አቦካዶ በየቀኑ በብዛት እየተጫነ በአቅራቢያው ወዳሉ የገበያ መዳረሻዎችና ማዕከላዊ ገበያ በስፋት እየወጣ ነው ያለው። አርሶአደሩ ከዚህ ቀደም ባሕር ዛፍ ብቻ ነበር የሚተክለው። አሁን ይሄ በፍራፍሬ ምርት ተቀይሯል። ከዚያም ባሻገር በዞናችን ቡና በስፋት ይመረታል፤ ስለዚህ በድምሩ በዚህ ዘርፍ የምንሠራቸው ሥራዎች እጅግ በጣም ውጤታማ ናቸው። በኢኒሼቲቩ የያዝናቸውም ሥራዎች በእኛ ደረጃ ገምግመን በጣም ውጤታማ የሆንበት ነው፤ በዚህ ዓመትም ለዚሁ ሥራ የሚያገለግል 1ነጥብ 5 ሚሊዮን የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ አካሂደናል።

አዲስ ዘመን፡- የእርሻ ሥራውን መካናይዜሽን ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ምንአይነት ጥረት እየተደረገ ነው?

አቶ አክሊሉ፡– ልክ ነው የግብርና ሥራችን ወደ ሜካናይዜሽን ካላሳደግነው ውጤታማ አንሆንም፤ ምክንያቱም የሃገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና እንደመሆኑ የአመራረት ሂደታችንን ማዘመን ይጠበቅብናል፤ ሥራችንንም ሰፋ አድርገን መሥራት ያስፈልጋል። ዛሬ ላይ የሰው ጉልበትም ወጪው ከፍተኛ እየሆነ ነው ያለው። ከዚህ አንፃር የሜካናይዜሽን ሥራ በጣም አዋጭ ነው። መስኖንም ሆነ የመኸር ሥራ ያለመካናይዜሽን የሚታሰቡ አይደሉም።

ስለዚህ ከሜካናይዜሽን ሥራ አንፃር አንዱና ቁልፉ ጉዳይ የትራክተር አቅርቦት ነው፤ በዚህም ረገድ እንደዞን ጠንከር ብለን እየሠራን ነው ያለነው። መንግሥትም ያመቻቸው እድል በመኖሩ አሁን ላይ በርካታ ትራክተሮችን ማስገባት ችለናል። ይሄም መንግሥት 60/40 የተባለ ፕሮግራም ሲሆን 40 በመቶውን አርሶአደሩ ቆጥቦ 60 በመቶውን ደግሞ ከባንክ ጋር በማስተሳሰር ከባንክ ብድር አግኝተው አርሶአደሮች ትራክተሮችን እንዲገዙ እየተደረገ ነው። ይህም ቢሆን አርሶአደሩ 40 በመቶውን በሙሉ መቆጠብ አይጠበቅበትም፤ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተሩን ያቀርብና ተያይዞለት 60 በመቶው ተከፍሎለት አርሶአደሩ ጥቅም የሚያገኝበት ሁኔታ እየተሠራ ነው ያለው። በአጠቃላይ የግብርና ሥራችን በሜካናይዜሽን የታገዘ ከማድረግ አኳያ በጣም አመርቂ የሚባል ደረጃ ደርሰናል ባንልም የአቅማችንን ያህል ጥረት በማድረግ ውጤት እያመጣ ነው ማለት እንችላለን።

በተለይም በብድር የእርሻ መሣሪያ አቅርቦት ሥራ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ አርሶአደሮች በዚህ መስመር ውስጥ የገቡ ሲሆን እስከአሁን ከ100 በላይ ትራክተር ማስገባት ችለናል። በዚህ ዓመትም በሂደት ላይ ያሉ ትራክተሮች አሉ፤ ሆኖም ባንክ አካባቢ አንዳንድ ተግዳሮቶች አሉ፤ በሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የምንፈታው ይሆናል።

ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ንግድ ባንክ አካባቢ ክፍተቶች አሉ። ይህንን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደጋጋሚ በመነጋገር እየፈታን ነው ያለነው። በነገራችን ላይ ሜካናይዜሽን ስናስብ ትራክተር ብቻ አይደለም፤ በርካታ መሣሪያዎች አሉ፤ ለምሳሌ መፈልፈያዎች፣ መስመር ማውጫ፣ መዝሪያና መሰል መሣሪያዎች በሂደት ወደ አርሶአደሩ እያስገባን ከሄድን አርሶ አደሩ በቀላሉና ብዙ ጉልበት ሳያባክን ሜካናይዜሽን እርሻ ሙሉ ለሙሉ እንዲገባና እንዲሰፋ የዞኑ ግብርና መምሪያ ጠንክሮ እየሠራ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- በግብርና ልማት ሥራ ለመሠማራት ለሚፈልጉ አዳዲስ ምሩቃንና ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ለብድር የሚቀርበው መነሻ ገንዘብ አነስተኛ መሆንና በቢሮክራሲ የታጠረ መሆኑ እንደችግር ይነሳል፤ ዞኑም ሆነ የክልሉ መንግሥት ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ ምን እየሠራ ነው ያለው?

አቶ አክሊሉ፡- ለወጣቶች መንግሥት ያመቻቸው የተለያዩ የብድር አማራጮች አሉ፤ እንደተባለው ግን አንዳንድ ጊዜ አሁን ካለው የገበያ ዋጋ ከመናሩ ተያይዞ የሚቀርቡ የብድር አገልግሎቶች ወጣቱ የሚፈልገውን ያህል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ከእኛ ክልል አንፃር ኦሞ ባንክ አለ፤ አብዛኛውን ወጣቶቻችንን ከኦሞ ባንክ ጋር በማስተሳሰር የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። ያም የብድር አገልግሎት እነሱ አስበው፤ ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተው ላሰቡት ሥራ የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ ልክ ያለማግኘት ችግር ያጋጥማል።

ነገር ግን በኦሞ ባንክ በኩል ወጣቱ በሰፊው ተደራጅቶ ብድር እየቀረበለት እንደሆነ ይታወቃል። ብዙ እጥረት አለ ተብሎ ባይወሰድም፤ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የቢሮክራሲ ችግር ያጋጥማል፤ በመሆኑም ወጣቱ በሚፈልገው ፍጥነት ያለመሄድ ነገር ካልሆነ በስተቀር ብድር አቅርቦቱ ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። የሚፈቀደውን መስፈርት አሟልቶ ከመውሰድ ጋር ተያይዞ ወጣቱ ጋር ፈጥኖ የሚጠበቅበትን ከማዘጋጀት በስተቀር የጎላ ችግር አለ ብለን አናምንም። እንደተባለው ግን የሚፈቀደው ብድር አሁን ካለው የገበያ ነባራዊ ሁኔታ ጋርና ከገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ አንፃር የሚጣጣም አይደለም። ዛሬ ላይ 50 ሺ ና 70 ሺ ብር ምንም አይሠራም። ሆኖም የዞኑ አስተዳደር ወጣቱ በሚቻለው አቅም ብድር ቶሎ አግኝቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- የዘንድሮ የበጋ ስንዴ ልማት ምን እንደሚመስል ያብራሩልን?

አቶ አክሊሉ፡– የዘንድሮ የበጋ መስኖ ሰንዴ ልማት ሌላ ጊዜ በምንሠራው ልክ በስፋት ተከናውኗል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የዞኑ አካባቢዎች ምርት እየተሰበሰበ ነው ያለው። ከዞናችን አንፃር የእቅዳችንን 60 በመቶ ያህል ማልማት ችለናል። ወደ 1ሺ ሄክታር አካባቢ ለማልማት አቅደን ነበር፤ ሆኖም ዘንድሮ በዞናችን 600 ሄክታር ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ተችሏል። የሰበሰብነውም ምርት በጣም ጥሩ የሚባል ነው። እንዳነሳሁት ለበልግ ሥራ ማሳ መልቀቅ ስላለበት በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ምርት ተሰብስቧል። በበልግ ሥራ ደግሞ የበቆሎ ልማት ሥራ በስፋት ይከናወናል።

አዲስ ዘመን፡- ለበልግ ሥራው ውጤታማነት የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ምን ይመስላል?

አቶ አክሊሉ፡- ከእኛ ዞን አንፃር አሁን ያለንበት ወቅት ቅድመ ዝግጅት አድርገን ወደ ሥራ እየገባን ነው ያለነው። ሰፊ የንቅናቄ መድረኮችንም አካሂደናል፤ አሁን ወደ ሥራው ገብተናል። በሰፊው የማሳ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው ያለው። በዚህም መሠረት በልግ ላይ በስፋት የምናለማው በቆሎና ድንች ነው።

ድንች በደጋ ወረዳዎቻችን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተከላውን ጨርሰናል፤ አሁን ወይና ደጋና ቆላ አዘል አካባቢዎች የበቆሎ ማሳ የማልማት ሥራ እየተከናወነ ነው። በመሆኑም በልግ ላይ 66 ሺ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እናለማለን፤ ዋናው በቆሎና ድንች ሲሆን፤ ማሽላ፤ ሰሊጥ፤ ቦሎቄ ጎመንና እንደ ጎደሬ ያሉ ሰብሎችን በስፋት ለማልማት ጥረት እየተደረገ ነው ያለው። ለዚህም እቅድ መሳካት ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ በተጠናከረ መንገድ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያለው።

አስቀድሜ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የበጋ መስኖ ልማትም ሆነ የመኸር ልማታችን በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ማንኛውም ለሥራው የሚያስፈልግ ግብዓት ሳይሰተጓጎል እንዲቀርብ በማድረግ ረገድ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ትልቅ ትኩረት ነው የሰጡት። በተለይም ከአምና ጀምሮ ከማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት መንግሥት ስርነቀል በሚባል ደረጃ ተንቀሳቅሶ ሠርቷል፤ በዚህም የክልሉም ሆነ የዞኑ አርሶአደር ተጠቃሚ ሆኗል። ዘንድሮም በተለይ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ እስካሁን ድረስ እንደችግር የሚናሳ ነገር የለም፤ ደግሞ ቀሪ ጊዜ ስላለ በእቅዳችን መሠረት ይቀርባል የሚል እምነት አለን። ከምርጥ ዘር አኳያ የማይካደው ነገር በቆሎ ላይ እጥረት አለ። በተለይ በአርሶአደሩ ዘንድ የሚፈለገው ‘ሊሙ’ የሚባል የፓይነር ዝርያ አለ፤ ይሄንን ዝርያ በበቂ ሁኔታ የማግኘት ችግር አለ። በምትኩ የ’ቢ.ኤች’ ዝርያዎችን በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ይህንን የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረትን ለመፍታት በእናንተ በኩል ምንአይነት ጥረት ተደርጓል?

አቶ አክሊሉ፡– የበቆሎንም ሆነ የሌላ ሰብሎችን የተሻሻሉ ዝርያዎች እጥረት ለመፍታት ከግብርና ማዕከላት ጋር ሥራ እንሠራለን። አስቀድሜ የገለፅኩት የበቆሎ ዘር እንደሃገርም ቢሆን እጥረት አለ። ኮርፋይ የሚባል ድርጅት ነው የሚያመርተው። በሀገር አቀፍ ደረጃ እጥረት አለ። ይህንንም ችግር ለመፍታት ከእኛ ዞን አንፃር በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች አሉ፤ እነዚያን ባለሃብቶች በማስተባበር ባለፉት ዓመታት የማባዛት ሥራ ስናከናውን ነበር።

እንዳውም ለሃገር የሚተርፍ ነገር የድርሻችንን ተወጥተናል ማለት ይቻላል። በ2014 ዓ.ም ወደ 350 ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር አባዝተን ወደ 14 ሺ ኩንታል ለግብርና ሚኒስቴር አቅርበናል። ነገር ግን ለእኛም የሚደርሰን ግብርና ሚኒስቴር በሚያቀርበው ድልድል መሠረት ነው። በማምረታችን ግን ሚኒስቴሩ የሚያደርግልን ድጋፍ አለ።

በዚህ ዓመትም በተለይ መሬት ወስደው በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ ባለሃብቶችን አቅርበን እያወያየን ነው። ይህንን የብዜት ሥራ እንዲሠሩ ማለት ነው። እስካሁን ጥሩ ምላሽ የሰጡን ባለሃብቶች አሉ፤ ከእነሱ ጋር በመሆን የምርጥ ዘር ችግርን ሊፈታ በሚችል መንገድ እንሠራለን ብለን እናምናለን። ይህም ደግሞ ከዞናችን ባሻገር ለሃገር የሚተርፍ ሥራ ለመሥራት የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አንዱ ነው፤ ለግብርና ምርትና ምርታማነት የዩኒቨርስቲው ድጋፍ እንዴት ይገለፃል?

አቶ አክሊሉ፡– እንደተባለው በዞናችን ሁለት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሉን። አንደኛው የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ነው፤ ሁለተኛ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ለግብርናው ምርትና ምርታማነት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሽ ነው። በዋናነትም በምርምር በመታገዝ የሚሠሩት ሥራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በቆሎና እንሰት ላይ የሚሠሩት የምርምር ሥራ በስፋት የሚታወቅ ነው። በነገራችን ላይ ከሁለቱም ማዕከላት ጋር ተቀራርበንና ተጋግዘን ነው የምንሠራው። የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከልም ከተቋቋመ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም በጣም ተቀናጅቶ ነው ከእኛ ጋር ሥራ የሚሠራው። በተለይም በብዜት፣ በማላመድና የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራት ከእኛ ጋር ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው። እንደአጠቃላይ የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በቅንጅት በመሥራታችን ነው ውጤት እያገኘን ያለነው የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ አክሊሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You