ትምህርት ተኮር የባለሀብቶች ተሳትፎ

ትምህርት ማኅበራዊ ጉዳይ ነው። ፋይዳው ማኅበራዊ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ማኅበራዊ ተሳትፎንም በእጅጉ ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ማኅበራዊ ፋይዳው ፋይዳቢስ ከመሆን አያመልጥም።

በአገራችን ከ“የቆሎ ተማሪ″ ጀምሮ ያለውን የትምህርት ሂደት ታሪክ ስንመለከት ትምህርት ማኅበራዊ ከመሆን ያመለጠበት አንድም ጊዜ የለም። ተማሪ እንዳለ ሁሉ አስተማሪ አለ። ድሮ፣ መምህራን ያለ ደመወዝ ሲያስተምሩ እንደ ነበረው ሁሉ፤ በሂደትም ኅብረተሰቡ እያዋጣ ደመወዝ ይከፍል እንደ ነበር ዛሬ ድረስ ታሪኩ በትኩስነቱ እንደ ቀጠለ፤ ሁሌም እንደ ተነገረ ነውና መልዕክቱ የትምህርትን ማኅበራዊነት ከማፅናት በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልም።

ከአባት የተገኘ፣ ከአበው የተወረሰ፣ ከጥንት የነበረ የማንነት መገለጫ፤ በራስ ቋንቋ፣ በራስ ፊደል፣ በራስ ሥርዓተ-ትምህርት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት የሆነው፣ የ“አበው ትምህርት ቤት″ም የሚያመለክተንና መሠረቱ ትምህርት ያለ ማኅበረሰብ ተሳትፎ ግቡን ሊመታ የማይቻለው መሆኑን ነው።

በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ፣ በልማድ “የቆሎ ትምህርት ቤት” በመባል ይታወቃል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ “የቄስ ትምህርት ቤት” ሲሉት፤ አንዳንዶች ደግሞ “የቤተ ክህነት ትምህርት ቤት″ በማለት ሲጠሩት ይሰማል። ምንም ይሁን ምን፣ ዋና ስሙን፣ “የአብነት ትምህርት ቤት″ የሚለውን በመያዝና ማኅበረሰባዊነቱ ላይ በማስመር በጉዳዩ ላይ መግባባት ይቻላል።

ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን እንደ አንድ የማኅበረሰብ አባል፣ ዜጋና ለትምህርት ተቆርቋሪ የሆኑ ሰዎችን ወስደን በትምህርቱ ዘርፍ ያደረጉትን አስተዋፅዖና የተወጡትን ማኅበራዊና የዜግነት ኃላፊነት እንመልከት። ከሰሞኑ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ድርጅት ክንውንም እንመልከት።

በሪል ስቴት፣ በመንገድ ግንባታዎችና በሆቴል ኢንቨስትመንት መስኮች የተሠማራው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ግሩፕ በሥሩ ከሚያስተዳድራቸው ዘርፎች በተጨማሪ፣ ለትርፍ ሳይሆን ለበጎ አድራጎት ተግባር የተቋቋመው “ሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን″ ይገኛል።

ታሪኩ እንደሚያስረዳው፣ ፋውንዴሽኑ አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦች ለመደገፍና ልጆቻቸውንም ለማስተማር በማሰብ ሥራውን የጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት በነቀምት ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ በነቀምት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የገነባው ትምህርት ቤት፣ 200 ተማሪዎችን ከነሙሉ ወጪያቸው በመሸፈን ማስተማር የጀመረበት ምዕራፍ መሆኑም ይነገርለታል፡፡

በነቀምት ከተማ በተካሄደው የምረቃ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት ያበረከቱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ ፋውንዴሽኑ እያደረገ ያለውን አስተዋፅዖ ማወደሳቸው ያለ ምክንያት አልነበረምና ሌሎችም በአርዓያነት ይከተሉት ዘንድ ሀገራዊና መንግሥታዊ ጥሪ ነው።

በጉዳዩ ላይ አተኩረን የፈተሽናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከነቀምት በተጨማሪ በደቡብ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ አገና ከተማ ሰንሻይን በገነባው ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በርካቶች ናቸው። የዓመቱ የትምህርት ዘመን ማጠናቀቁን መነሻ በማድረግ በፋውንዴሽኑ በኩል በተዘጋጀው ፕሮግራም አማካኝነት ለተማሪዎች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ይሰጣሉ፡፡

ሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን ባለፉት ዓመታት ውስጥ በነቀምት፣ በአክሱምና በጉራጌ አገና በተገነቡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1ሺህ 350 ተማሪዎችን በመቀበል ሙሉ ወጪያቸውን ችሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

ፋውንዴሽኑ ሰሞኑን መጋቢት 26 እና 27 ቀን 2016 ዓ∙ም በሰሜን ሸዋ በርካታ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ያስመረቀ ሲሆን፤ ወደዚህ ጽሑፍም እንድንመጣ ዘንድ ምክንያት የሆነን ይሄው የፋውንዴሽኑ የሰሞኑ፣ መጪውን ትውልድ ሁሉ ያገነዘበ ሰብዓዊና ማኅበራዊ ተግባር ነው።

በሰንሻይን ኮንስትራክሽን ስር የሚገኘው ሰንሻይን ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽን በደብረ ብርሀን ከተማ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ገንብቶ ለኅብረተሰቡ አስረክቧል። በወቅቱም የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ምስጋናና አድናቆቱን ለድርጅቱ፣ ባለቤቱና የሥራ ኃላፊዎች ገልጿል። በወቅቱም ፊላንትሮፒ ፋውንዴሽኑ ይህን አይነቱን ሰብዓዊና ማኅበራዊ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ሌላው በእንደእነዚህ አይነቶቹ ሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተሠማርተው ሀገራዊና ወገናዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ካሉት ፊላንትሮፒስቶች አንዱ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ነው።

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ፊቱን ከአትሌቲክሱ መንደር ወደ ቢዝነሱ ፊቱን ካዞረ ቅርብ ዓመታት ቢሆኑትም በተለያዩ ዘርፎች ሰው ተኮር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ሲሆን፤ ከሰብዓዊ ተግባራቱ አንዱ ትምህርትን አስቦ፣ ትምህርትን ጉዳዬ ብሎ፤ ለአሁንና መጪው ትውልድ ተጨንቆ በትምህርት ተቋማት ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ እያደረገ ያለው ጥረት ነው።

ጀግናው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ (ዶ/ር) መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የዳስ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ ትምህርት ቤቶች ለመቀየር የያዘውን መርሐ-ግብር በመደገፍ በአማራ ብሔራዊ ክልል፣ በዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞን በጻግብጂ ወረዳ የሚገኘውን ገልኩ የዳስ ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አድርጎ ለመገንባት የትምህርት ሚኒስቴርና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፤ እንዲሁም መላው የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት የግንባታ ማስጀመሪያ መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጡን ዜና ከሰማንበት እለት ጀምሮ ባሉት አምስት ወራት ውስጥ አጠናቅቆ አስረክቧል።

በዋግ ኸምራ አስተዳደር በአጠቃላይ 874 የዳስ መማሪያ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ከ1ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች የሚማሩበት መሆኑን የዋግ ኸምራ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ ገልፀው የነበረ ሲሆን፤ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴም ከታላቁ ሩጫ በሚሰበሰብ ገቢ ሁለት ተጨማሪ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ቃል መግባቱ በወቅቱ ተገልፆ እንደ ነበር ይታወሳል።

በምረቃው ሥነሥርዓት ወቅት የአካባቢው ማኅበረሰብ “ጀግናችን በጣም እናመሰግናለን። ትናንት ስትሮጥ ቁሜ አጨብጭቤ ነበር። ዛሬ ደግሞ ከዚያ የበለጠ ደስታ ነው የተሰማኝ። ሌሎች ባለሃብቶችም በተመሳሳይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ላይ ብትሰማሩ ብዙ ለውጥ ይመጣል። ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው ሁላችንም ስንረባረብ ነው። በቀስት ሳይሆን በእስክርቢቶ፣ በጥይት ሳይሆን በብዕር፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር፣ በመለያየት ሳይሆን በአንድነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ተቋማት ያስፈልጋሉ። ብሔራዊ ጀግናችን ኃይሌ እና ተመሳሳይ ሀሳብ ያላችሁ ከልብ እናመሰግናለን።″፤ “ኃይሌ፣ ብሄራዊ ጀግናው፤ እናመሰግናለን።″ ወዘተ በማለት አመስግኖታል።

በተቃራኒው በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ትምህርት ቤቶች የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በቅርቡ በአማራ ክልል፣ ዋግኸምራ ዞን በአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የተገነባው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደመ የሚለው መሰማቱ ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም።

ሌላዋ በትምህርት መሠረተ ልማት ላይ ከዘመቱት፤ በመጀመሪያ ዙር ብቻ በሁሉም ክልሎች 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ያስገነቡት ቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሲሆኑ፤ የመጀመሪያዎቹን ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከጀመሩበት 2011 ዓ∙ም ጀምሮ እስካሁን በየክልል ከተሞች በርካታ ትምህርት ቤቶችን መገንባታቸው፤ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶችም ከስድስት ወር እስከ ስምንት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው እየተጠናቀቀና ለየአካባቢው አስተዳደሮች ርክክብ በመፈፀም ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑ ከጽሕፈት ቤታቸው ከሚለቀቁ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል። ይህ በትምህርት ላይ ያተኮረ ሰብዓዊ ተግባር በየትኛውም መስፈርት ቀዳማዊቷን ያስመሰግናቸዋልና አቅሙ ያላቸው ሁሉ የእሳቸውን አርዓያ በመከተል በአገራችን በትምህርት ላይ የደረሰውን ስብራት ሊጠግኑ ይገባል። በተጨማሪም፣ ጽሕፈት ቤታቸው ለአይነ ስውራን የትምህርት ቤቶች ቁሳቁስ በማቅረብ፣ ለአካል ጉዳተኞች ዊልቸር ድጋፍ በማድረግ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራም አስታውቋል።

እዚህ ላይ እነዚህን ሰብዓዊና ማኅበራዊ ተግባራት ፈፃሚ ሰዎችን ለማሳያ ያህል አነሳናቸው እንጂ፤ በርካታ ባለ ሀብቶች በተመሳሳይና ሌሎች ተግባራት ላይ በመሠማራት የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ያሉ እንዳሉ ይታወቃል።

ባለፈው ሰኔ ወር ይፋ በተደረገ ሪፖርት ላይ እንደ ተገለፀው፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተካሄደ ጦርነት ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ከየአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያሳያል። ከ12ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ደግሞ ከየአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከትምህርት ገበታቸው ውጪ የሆኑ 2.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ደግሞ ብለን የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል ። በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሙሉ በሙሉና በከፊል ከወደሙ 6ሺህ 942 ትምህርት ቤቶች መካከል፣ 6ሺህ 688 ያህሉ ጥገና″ እንዳልተደረገላቸውም የሦስቱ ክልሎች ሪፖርት ያሳያል።

“ውድመት ከደረሰባቸው 4ሺህ 068 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 103 ያህሉ እንደ አዲስ መገንባታቸውን፣ 126 ደግሞ መጠገናቸውን፣ በአጠቃላይ 229 ትምህርት ቤቶች አዲስ ግንባታና ጥገና ቢደረግላቸውም ቀሪዎቹ 3ሺህ 839 ግን ጥገና″ አልተደረገላቸውም ሲሉ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል። 2ሺህ 492 ትምህርት ቤቶች በጦርነት የወደሙ፡፡ ገና የተለቀቀ በጀት ስለሌለ ጥገናም አልተደረገላቸውም ሲሉ ደግሞ የትግራይ ክል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ግዑሽ (ዶ/ር) ተናግረዋል ።

የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱ ሐሰን በሰሜኑ ጦርነት ወቅት 382 ትምህርት ቤቶች እንደ ወደሙና ከእነዚህም መካከል 96 ሙሉ ለሙሉ፣ 286 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል እንደወደሙ ገልጸው፣ በተራድዖ ድርጅቶችና በክልሉ መንግሥት ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ የገቡት 25 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን ከላይ በጠቀስነው ቀን ባቀረቡት ሪፖርታቸው ገልፀዋል። በጦርነቱ ሳቢያ ከወደሙት 382 ትምህርት ቤቶች መካከል 352 ያህሉ እንዳልተጠገኑ፣ በአጠቃላይ ከደረሰው ውድመት ለማገገም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ብር እንደሚያስፈልግ፣ ከ12ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውንም ገልፀዋል።

“የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም ብቻ በትግራይ በጦርነቱ ሳቢያ በመምህራን ላይ የደረሰውን ሞት አደረግኩት ባለው ዳሰሳ ብቻ፣ 2ሺህ 146 መምህራን እንደሞቱ መረጋገጡን የገለጹት የትግራይ ትምህርት በሮ ኃላፊው፣ ከ2013 ዓ.ም. ወዲህ በክልሉ ጦርነት ስለነበር ከዚያም በላይ መምህራን መሞታቸው ዕሙን መሆኑንና በዚህም ምክንያት የመምህራን እጥረት እንደገጠማቸው″ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ በወቅቱ ዘግቦት አልፏል።

ከትምህርት መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ብዙ ሲሆን፣ አንዱም አንዱ ያለማውን አንዱ ያለ ምንም ርህራሄ ማውደሙ ነው።

ዓለም አቀፋዊውን ሁኔታው ሲታይ ደግሞ የትምህርት ቤቶች ደህንነት አዋጅ” የተሰኘውን፤ በመንግሥታቱ ድርጅት የተረቀቀውን ዓለም አቀፍ ሕግ እስካሁን ያፀደቁት 111 ሀገራት ብቻ ናቸው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት በዓለማችን ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2020 ዓመት ድረስ ከ13ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በተሰነዘሩ ወታደራዊ ጥቃቶች ወድመዋል። ጥናቱ “በዓለማችን″ ይበል እንጂ አብዛኞቹ የት እንደ ሆኑ ብዙዎቻችን የምናውቅ ስለመሆናችን መረጃ ማጠናቀር የሚያስፈልግ አይደለም።

እ.ኤ.አ በ2022 “ሰዎች ለሰዎች የተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት በጦርነትና በድርቅ ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አራት ክልሎች በ300 ሚሊዮን ብር 16 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሥምምነት ተፈራርሟል፡፡″ የሚል ዜና ታውጆ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ምንም እንኳን አፈፃፀሙን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ እጃችን ላይ የሚገኝ ባይሆንም፤ ወደ መጠናቀቁ ሊሆን እንደሚችል እናምናለን። ሌሎችም እንደዛው።

ባለፈው ዓመት፣ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ “በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ካሉ 47ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተፈላጊውን ‘ከፍተኛ ደረጃ’ የሚያሟሉት አራቱ ብቻ እንደሆኑ፤ የሚፈለገውን ደረጃ ያሟሉት በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያላቸው ድርሻ 0.001 በመቶ መሆኑን“፤ እንዲሁም “47ሺህ ትምህርት ቤቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ወደ 99 በመቶ የሚሆኑት፤ ለተማሪዎች፣ ለልጆች አመቺ ሁኔታ የላቸውም” በማለት አስረድተው ብዙዎችን አስደንግጠው እንደ ነበር ይታወሳል። ይህም (ጉዳዩ የትምህርት መሠረተ ልማት ነውና) በርካታ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትን ርብርብ ይጠይቃል። በመሆኑም፣ ባለሀብቱም ሆነ ሌላው የሚችለውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ይጠበቅበታል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከላይ በጠቀስነው ቀንና ስፍራ “የትምህርት ቤቶችን ደረጃ እና ጥራት ለማሻሻል፤ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ጥገና አድርጌያለሁ፤ 8ሺህ 700 ገደማ ትምህርት ቤቶችም ጥገና እና እድሳት″ ተደርጎላቸዋል ያለውንም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በመጨረሻም፣ መንግሥት በተቋሙ ትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት “ትምህርት ለትውልድ!” መርሐ ግብርን ቀርፆ፤ “በአምስት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የማዳረስ ዓላማን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ተገልጿል። በዚሁ መርሐ ግብር መሠረትም በርካታና አበረታች ሥራዎችን ከየአካባቢው ማኅበረሰብና ተቆርቋሪ ባለ ሀብቶች ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግሯል። “አጠቃላይ ማኅበረሰቡን” የሚያሳትፍ “ሰፊ ዘመቻ” ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደ ሆነም ይፋ አድርጓል። ከ“አጠቃላይ ማኅበረሰቡ″ ላይ ባለ ሀብቱም የድርሻውን እንደሚወስድ ይታመናል ።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You