100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎች የሚጋሯቸው ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያት

100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎች የሚጋ ሯቸው ሥነልቦናዊ ባሕሪያት አላቸው። አብዛኞቹ አሁንም ጤናማ ናቸው፤ ጥንካሬያቸው ያስቀናል፤ ከሰው ጋር ለማውራት ጉጉ ናቸው።

በእንግሊዝኛው ሴንቴናሪያንስ ይባላሉ። 100 ዓመት ያለፋቸው የዕድሜ ባለፀጋዎች ናቸው።

አብዛኞቹ ጭንቅላታቸው ሁሌም በእንቅስቃሴ እንዲጠመድ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ስፖርት መሥራት አሊያም ጨዋታ መጫወት።

የተባበሩት መንግሥታት የሕዝብ ጥናት ክፍል እንደሚለው አሁን አሁን በርካታ ሰዎች የመቶ ዓመት ዕድሜያቸውን ለማክበር 100 ሻማ ሲለኩሱ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1990 ይህን ፀጋ መጎናፀፍ የቻሉት 92 ሺህ ሰዎች ብቻ ነበሩ። በ2021 ይህ ቁጥር ወደ 621 ሺህ ተመንድጓል።

እርግጥ ይህ ቁጥር ለምን በዛ የሚለውን ለማወቅ ዘረ-መል እና የኑሮ ዘይቤን መመልከት ግድ ይለናል። ነገር ግን ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያትን መዘንጋት የለብንም።

ማሪያ ዶሎረስ ሜሪኖ በማድሪድ ኮምፕሉተንስ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ናት። 100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎችን ለዓመታት አጥንታለች።

ዘ ጆርናል ኦፍ ሀፒነስ ስተዲስ የተሰኘው መጽሔት ላይ በቅርቡ ባወጣችው አንድ ጥናት እነዚህ ሰዎች 19 ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያትን ይጋራሉ ትላለች።

ማሪያ እነዚህን ባህሪያት በስምንት ከፋፍላ እንዲህ ታቀርባቸዋለች።

እነኚህ የዕድሜ ባለፀጋዎች ከሚጋሯቸው ባህሪያት አንዱ ጥንካሬ ነው። ለመኖር ያላቸው ጉጉት፣ ንቃታቸው እና ጉልበታቸው ከሌሎች ለየት ያደርጋቸዋል።

“በጣም የሚገርም ነው። ያናገርናቸው ሴንቴናሪያኖች የመኖር ፍላጎታቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው” ስትል ማሪያ ዶሎረስ ሜሪኖ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ስታናግሪያቸው 100 ዓመት የደፈኑ አይመስሉም። በጠቅላላው በቃ በጣም ወጣት የሆነ ሰው የምትናጋሪ ነው የሚመስለው” ትላለች።

ማሪያ ለጥናቷ ካናገረቻቸው ሰዎች መካከል 98 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ሥራ ይሠሩ የነበሩ ወንዶች እና ሴቶች ይገኙበታል።

የዕድሜ ባለፀጋዎቹ ጭንቅላታቸውንም ሆነ አካላቸውን የሚያንቀሳቅስ ሥራ ከመሥራት አይቦዝኑም። በየቀኑ ደረጃ ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ፣ ካርታ ይጫወታሉ፣ ሶዱኩ የተሰኘው የቃላት ጨዋታንም ያዘወትራሉ።

ስቴሲ አንደርሰን የኒው ኢንግላንድ ሴንቴናሪያን ስተዲ ጥምር ዳይሬክተር ናት። ይህ መቀመጫውን በአሜሪካዋ ቦስተን ከተማ ያደረገ ማዕከል 100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎችን ያጠናል።

ስቴሲ እነዚህን ሰዎች አንድ ከሚያደርጋቸው መለያ መካከል አንዱ ጥንካሬ መሆኑን ትስማማበታለች።

“አብዛኞቹ ሕይወትን በደንብ እንደሚያጣጥሙ ይናገራሉ። ይህ ለእኔ በጣም የሚደንቅ ነገር ነው” ብላለች ስቴሲ ለቢቢሲ።

በማሪያ ዶሎረስ ሜሪኖ ጥናት መሠረት ዕድሜያቸው ከ100 የተሻገረ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ጤናማ ነው።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሌላኛው 100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎች የሚጋሩት ነገር ቁርጠኝነት ነው።

“በጠቅላላው ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። ተፎካካሪ እና ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው። ያሰቡትን ነገር ከማሳካት ወደኋላ አይሉም” የምትለው ማሪያ ናት።

በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ክፍለ ዘመን የደፈኑ ሰዎች ከሚጋሯቸው ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያት መካከል አንዱ ፅናት ነው።

ፅኑ መሆን ማለት ፈተናን መቻል ማለት ነው። እንዲያውም ይህን ልምድ ተጠቅሞ የበለጠ ጠንካራ መሆን ረዥም ዓመት ለመኖር መሠረታዊ ነው።

አጥኚዎች እንደሚሉት ከአንድ ክፍለ ዘመን ለላቀ ጊዜ እዚህች ምድር ላይ የኖሩ ሰዎች ውሳኔ ለመወሰን አይሳሱም፤ ሕይወታቸውን ተቆጣጥረው መኖር ይችላሉ።

በተጨማሪ አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት አላቸው። ትምህርት መገብየት ይወዳሉ። ራሳቸውን ያስተምራሉ።

“100 ዓመት ሞልቷቸው «እስካሁን ባልቆይ ደስ ይለኝ ነበር» የሚሉ ሰዎች ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን አንድ የ40 ዓመት ሰው እስከ 100 መኖር ትፈልጋለህ? ቢባል «አልፈልግም» እንደሚል እሙን ነው።”

እንደ አጥኚዎች ከሆነ እነዚህ ሰዎች ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ ምክንያታዊነት፣ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ማበጀት እና በፍጥነት መማር ይችላሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You