«በጎ ውሳኔ የመልካም በረከቶች ውጤት ነው» – አቶ ወስን ቢራቱ የድሬ ፍሬዎች በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች

የእናቱ ልጅ

እሱ ልክ እንደ እናቱ ነው፡፡ የተራቡን መጋቢ፤ የተጠማውን አጠጪ፣ የታረዙን አልባሽ፡፡ በዚህ መልካምነቱ ብዙዎች ከስሙ ይልቅ ‹‹ሩህሩሁ ሰው›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ከመንገድ ወድቆ ያየውን ሁሉ ማለፍ እንደማይቻለው ስለሚያውቁ ነው፡፡

እሱ ማለት ስጡኝን አያውቅም፤ ያለውን መስጠት፣ ማካፈል እንጂ፡፡ የቤተሰቡንና የጓደኞቹን ገንዘብም ከአልባሌ ቦታ አይጥልም፡፡ ከዚያ ይልቅ የበረከቱ ተቋዳሽ ይሆኑ ዘንድ በጎ ተግባራትን በመስራት የልባቸውን ሀሴት ይሞላል፡፡

ዛሬ ላይ ይህ ደግ ሰው ብዙዎች የሚሰጡትን ገንዘብ ከራሱ ደምሮ ከ 1500 በላይ ተማሪዎችን በቋሚነት እየመገበ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባሩም በትምህርት ቤት ምገባ ‹‹አምባሳደር›› ለመባል በቅቷል፡፡ ከዚህ ሻገር ሲል እጆቹ ሰፊ ናቸው፡፡ በማረሚያ ቤትና በሆስፒታል ቋሚ ሰራተኞች ቀጥሮ ወጎኖቹን ይንከባከባል፡፡ የዛሬው ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አቶ ወስን ቢራቱ፡፡

የእናት ውርስ

ድሬዎች አብዛኞቹን በሚያስብል እውነት መልካምነታቸው የበዛ ነው፡፡ ወስን ደግሞ እንደ ድሬ ልጅነቱ የሚጋራውን ባህሪ አይለቅም፡፡ እሱን ለየት የሚያደርገው ግን መልካምነቱ እጅግ የበዛ መሆኑ ነው። ሁሌም ደግነት መገለጫው ነው፣ ቅንነቱ ይለያል፡፡ ማንንም የሚመርጥ አይደለምና ለሁሉም ደራሽነቱ ይታወቃል፡፡

አቅመ ደካሞች፣ ታራሚዎች፣ ታማሚዎችና ችግረኛ ተማሪዎች የእርሱን እገዛ እስከፈለጉት ‹‹አለሁላችሁ ማለቱን አያቋርጥም፡፡ በእርግጥ ይህንን መልካምነት የወረሰው ከወላጆቹ ነው፡፡ የእነርሱ ቤት ዘወትር ለቸገራቸው ሁሉ መጠጊያ፣ መሰብሰቢያ፤ ማደጊያና ወግ ማዕረግን ማሳያ ነው፡፡

ማንም በእዚህ አጸድ የተገኘ ቢኖር ‹‹አንተ ልጅ አይደለህም፣ ይህ አይገባህም›› ተብሎ አያውቅም፡፡ ቤቱን መጠጊያ፣ መጠለያ ያደረገ ሁሉ በቃ! መብቱ የማይጣስ፣ የማይገፈፍ ልጅ ሆኖ ያድጋል፣ ይኖራል፡፡

በቤቱ እስካለ ደግሞ ‹‹ ወንድሜ፣ እህቴ ተብሎ ሊጠራ ግድ ነው፡፡

እንዲህ አይነቱ ልጅ እናት አባቱ ቢኖሩ እነሱም የቤቱ አባወራና እማወራ ናቸው፡፡ ይህ አይነቱ የቤተሰብ ታሪክ የጀመረው ወስን ገና ሳይወለድ ጀምሮ ነበር። ቤተሰቡ እንደዛሬው የተትረፈረፈ ሀብትና ገንዘብ ሳይኖረው በፊት፡፡ የዛኔ እናት ጉልት ቸርቻሪ፣ አባት ደግሞ ጫማ ሰፊ ነበሩ፡፡

ጥንዶቹ ቤታቸው በሰው ፍቅር የተሞላ ነውና የገቢያቸው ማነስ ታይቷቸው አያውቅም፡፡ መቼም ቢሆን ‹‹አጣን፣ ነጣን ጎደለብን›› አይሉም፡፡ ይህ አይነቱ መልካምነት በድሬዎች አገላለጽ ‹‹ቲከን በሪ›› ወይም ‹‹ በራቸው ለሁሉም ክፍት የሆነ ተብሎ ይተረጎማል። ሁለቱም ከእጃቸው የሚሰስቱት የለም፡፡ ሁሌም ቤታቸው በበረከት ተሞልቶ ከመሶቡ ተርፎ ይነሳል፡፡

ወስን ቤተሰቦቹ ያሳለፉትን ችግር የሚያውቀው ‹‹ነበር›› ተብሎ ሲወራ ነው፡፡ ደግነትን ግን ከልጅነቱ ጀምሮ እያየው አድጓል፡፡ እነሱ ዝናን ያተረፈ ሆቴል ገንብተው ሲያስተዳድሩም መልካምነታቸው አብሮ እንደዘለቀ አረጋግጧል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰራተኞችን ሲቀጥሩ የሚከተሉት መስፈርት እጅጉን ያስደንቀዋል፡፡

ሰዎች አይቀጥሯቸውም የተባሉት ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን በእነርሱ ቤት ቅድሚያ አግኝተው ሲቀጠሩ ተመልክቷል፡፡ ሴት ልጅ ስንትም ልጅ ይኑራት፤ ነፍሰጡርም ትሁን በእነርሱ ቤት የስራ እድል አታጣም፡፡ ልዩ እንክብካቤም ታገኛለች፡፡ በቤቱ የሰራተኛ ምግብ የሚባል ልዩነት ስለሌለ ከልጅነቱ ምግቡንም ፍቅሩንም በእኩል ተሻምቶ እንዲያድግ ዕድል አግኝቷል፡፡

ወስን በልጅነቱ ከቤተሰቡ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ገንዘብ አባካኝና በሱስ የተጠመደ መሆኑን ጭምር አይረሳም፡፡ በቤታቸው እያየ ያደገው መልካምነት ግን እንደገና ሰርቶታል። መልካሙን፣ ሩህሩሁንና ለጋሹን የዛሬውን ወስን ፈጥሯልና፡፡ ያለፈበት አጋጣሚ ማንነቱን ከመልካም ጎዳና እንዲያሳርፍ አስችሎታል፡፡ ዛሬ ለደከሙ፣ ለወደቁ፣ ማረፊያ፣ ለተራቡ፣ ለታረዙ ደራሽ የመሆን ምስጢሩ ይኸው እውነት ነበር፡፡

ለዚህ ማንነት ግን የእናቱ ድርሻ ወደር የለውም፡፡ ‹‹ከእናቴ የወረስኩት ብዙ ነገር አለ፡፡ በተለየ የሕይወት መርህ ሆነውኛል የምላቸው ግን ሁለቱን ነው፡፡ አንደኛው ከሌለኝ ላይ መስጠትን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሥራ መለወጥ እንደሚቻል፡፡ ይህንን ደግሞ እንደ መማሪያ መጽሐፍ ሆኖ ያለፈ ታሪኳን እንድናነበው አድርጋናለች፡፡ በየቀኑ እንደተረት በመንገርም ‹‹ይህም ይቻላል እንዴ! እንድንል አስችላናለች፡፡ እናም ለባህርዬ መለወጥ የእርሷ ጠንካራ እጆች ብርታት ሆነውኛል›› ይላል፡፡

ወስን ገንዘብ ለማይሆን ተግባር ሲውል ምን ችግር እንደሚያስከትል ኖሮት ያውቀዋል፡፡ በዚህም ‹‹ቤተሰብ ነጻ ፈቃድ ሲሰጥ ጎን ለጎንም ቆንጠጥ ማድረግና የት ዋለ ማለት ይገባዋል፡፡ ›› ሲል ይመክራል፡፡ እንደ አብነት የሚጠቅሰው ደግሞ ቤተሰቡን ነው፡፡ የዛኔ እርሱ በሆቴላቸው የፈለገውን እያገኘ ጊዜውን ያሳልፋል፡፡ አመኔታ ባይጣልበትም እንደ ኃላፊ ቁጥጥር ያደርግ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሱስ ውስጥ እየገባ ጭምር ሌሎችን እንዲጋብዝ አድርጎታል፡፡ መለስ ብሎ ሲያስበው ግን ባለሀብት ወላጆች ለልጆቻቸው ገንዘብ ከመስጠት ባሻገር እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ማየት ይኖርባቸዋል ሲል ይመክራል፡፡

የልጆች በረከት

የእነ ወስን ቤተሰብ ሲነሳ ሳይጠቀስ የማይታለፍ አንድ እውነት አለ፡፡ ቤቱ በልጆች ዓለም የተባረከ መሆኑን። የወስን እናት 18 ልጆችን ወልደዋል፡፡ አባቱ ደግሞ ከሌሎች ሁለት ሚስቶች ስምንት ልጆችን ወልደዋል፡፡ በጥቅሉ 26 ልጆች እህትና ወንድም ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሀል ወስን 14ኛው ልጅ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ እንዲህ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁልጊዜ በንግግሩ ‹‹ቤተሰብ የማንነት መሰረት ነው›› ይላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በበዛ ቤተሰብ ውስጥ በልጅነቱ መልካምነትን በጎነትን እንዲያውቅና ከዛሬው መክሊቱ እንዲገናኝ ምክንያት ሆኖታልና፡፡

ወስንና ትምህርቱ …

የወስን እናትና አባት ትምህርት በስነምግባር የተቃኘ መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ በመሆኑም የሚወዱትን ልጃቸውን ወስንን የቀለም ትምህርቱን እንዲቆጥር ክርስቶስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገብተውታል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የቆየበት ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ ድሬደዋ አጠቃላይ ትምህርት ቤት በመዘዋወር እንዲከታተል ሆኗል፡፡ ሁለቱም ትምህርት ቤቶች በስነምግባር የተኮተኮተባቸው ናቸው፡፡ መልካምነቱን ገንብቶ እንዲያድግ አግዘውታል፡፡

በወስን እምነት ሙያዎች ሁሉ በትምህርት መጎልበት አለባቸው፡፡ እሱ ትምህርቱን ከ12ኛ ክፍል ቢያቋርጥም ለተሰማራበት ሙያ የሚሆን ስልጠና ወስዷል፡፡ አሁንም ቢሆን ዘርፉን አሳድግበታለሁ ብሎ ካሰበ መሰልጠን እንደሚፈልግ አጫውተናል፡፡

ወስን ከትምህርት ጋር በተያያዘ የሚለው አለ። ‹‹ዓለማችን በትምህርት፣ በጥበባት፣ ወይም በተወሰኑ ዘርፎች ብቻ የተገደበች አይደለችም፡፡ ከትምህርት ባሻገር ብዙ ዘርፎች ደግፈው ያቆሟት እንጂ›› ሲል ይናገራል፡፡ ይህ አቋሙ ትምህርቱን ከ12ኛ ክፍል አቋርጦ የንግዱን ዓለም እንዲቀላቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ መሆኑ ‹‹የእኔ ድርሻ በንግዱ ዘርፍ ተሰማርቼ ሀገርንና ትውልድን መታደግ ነው›› እንዲል አስችሎታል፡፡

የሥራ ሕይወት

ወስን ከቤተሰቦቹ ቤት የወጣው ጋብቻን ባሰበ ጊዜ ነው፡፡ ‹‹አሁን የራስህ ጌታ መሆን አለብህ፤ ትዳር መስርት ›› ሲባል ቤተሰቡን ትቶ አባወራነቱን ለማስመስከር ደፋ ቀና ወደማለቱ ገባ፡፡ መጀመሪያ የወሰደው ርምጃ ባለቤቱ የራሷ ሥራ እንዲኖራት ማድረግ ነበር፡፡

በወቅቱ ከአባቷ በተማረችው ሙያ የውበት ሳሎን ከፍታ እንድትሰራ ተገቢውን ዕቃ ገዛላት። ቀጥሎ ደግሞ ለራሱ የሚሰራበትን አመቻቸ፡፡ በስድስት መቶ ብር ደሞዝ ተቀጥሮ ውሎውን ‹‹ሚቶ መናፈሻና በርገር ›› ላይ አደረገ፡፡

መናፈሻው ግዙፍ የሚባል ሲሆን፤ በርካታ ሰራተኞችን በውስጡ አቅፏል፡፡ በቀን 13 ትላልቅ ሙክት አርዶ ደንበኞቹን ያስተናግዳል፡፡ በዚህ ቤት የእርሱ ድርሻ የማስተዳደሩ ተግባር ነበር። እንደ ስራአስኪያጅ ሳይሆን እንደ ባለቤት ሆኖ ይሰራል፡፡. ስራዎችን በሁሉም ቦታ እየገባ የሚያከናውነው እሱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያት ነበረው፡፡

የመናፈሻው ባለቤት ወይዘሮ ቀለሟ አበበና አቶ ግርማ ወልዴ የነጻነቱ ምንጭ ናቸው፤ ልክ እንደ እናትና አባቱ ድረው ኩለውታል፡፡ ለእነሱ ከተባለ ደከመኝን አያውቅም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከቀናት በአንዱ እምቢኝ ሲል ከማያሳልፈው የሥራ ዕድል ጋር ተገናኘ፡፡

በወቅቱ ‹‹ቢጂአይ ወይም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ›› ‹‹የሚሊኒየም ፓርክ በአሁኑ አጠራር አሊቢራ ፓርክ››ን ለድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በከፍተኛ ወጪ ሰርቶ ያስረከበበት ግዜ ነበር፡፡ የቦታው ኃላፊ ሆኖ እንዲሰራ አማራጭ ያገኘው ወስን እድሉ ያልጠበቀው በመሆኑ ለውሳኔ እንዲቸገር ሆኖ ነበር፡፡

በተለይ የልብ ወዳጆቹን የቀድሞ አሰሪዎች ትቶ መውጣቱ እጅጉን ሲያጨንቀው ከርሟል፡፡ ምን ብሎ እንደሚናገርም ግራ ሲጋባ ቆይቷል፡፡

የመናፈሻው የመመረቂያው ጊዜና ሥራ የሚጀምርበት ሰዓት በመድረሱ መናገሩ ግድ ነበር። በዚህም ሲፈራ ሲቸር ሁኔታውን ለባለቤቶቹ አሳወቀ። በወቅቱ ሰዎቹ ነገሩን ቀድመው ስለሰሙት ምንም ሊሉት አልወደዱም፡፡ ይልቁንም መልካም እድል ተመኝተው በቸር ሸኙት፡፡ እሱም ስለዚህ ውለታቸው ዘወትር ያመሰግናቸዋል፡፡

ወስን በአዲሱ መናፈሻም የገጠመው መልካም ነገር ብቻ ነበር፡፡ በዚህም እንደለመደው ጠንክሮ ይሰራል። ጊዜው ባይፈትነው ኖሮ ስኬታማ እንደሚሆንበት ያምናል፡፡ ይሁንና ድሬ ችግር ስለገጠማት ገበያውም በዚያው ልክ ወደ መቀዛቀዙ ገባ፡፡ ወስን ሥራውን ሊቀጥል ቢከበደው ጥቂት ለማረፍ ወሰነ፡፡

የወስን እረፍት እስከመጨረሻው አልዘለቀም። በግዜው የአክስታቸው ልጅ ሆቴል ስለሚያስመርቅ ወደ ቡታጀራ ጠራው፡፡ በሆቴሉ ምርቃት ወቅትም እንደለመደው ሁሉም ቦታ ደምቆ ታየበት፡፡ እስከ ቆየበት ጊዜ ለሆቴሉ ባለቤት ጥሩ ገቢ አስገኘ። አካሂዱ ቤተሰቡን ትቶ ስለነበር ከ15 ቀን በላይ አልቆየም፡፡

ወስን ወደ ቤተሰቡ ከተመለሰ በኋላ የተመረቀው ሆቴል እርሱ እንደነበረበት ጊዜ አልሆንልህ አላቸው፡፡ ይህ ሲታወቅ በልመና እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ለስድስት ወር ያህል የአስተዳደሩን ቦታ ሸፍኖ በጥሩ ሥራ ሆቴሉን ወደ ቀደሞ ክብሩ መለሰው፡፡ ወስን ረጅሙን ጊዜ ከቤተሰቡ ተለይቶ በማሳለፉ ከዚህ በላይ በዚያ መቆየት አልተቻለውም፡፡ ቤተሰቡን፤ የልጅነት ጥሪውን ትቶ ቡታጀራን የሙጥኝ ማለት አልሆነለትም፡፡ ዳግም ወደ ትውልድ ቀዬው ድሬደዋ ተመለሰ፡፡

ድሬደዋ እንደገባ ጊዜ ሳይፈጅ የምግብ ዝግጅት ሥራውን ጀመረ፡፡ ለምግብ መስሪያ የሚሆኑ እቃዎችን በማሟላት ተለያዩ ተቋማትና ዝግጅቶች ብፌ አዘጋጅቶ ማቅረብን ለመደ፡፡ ሰርግ፣ ክርስትና፤ ልደትና ቁርባን ልዩ ልዩ በዓላትና ፕሮግራሞች በእርሱ መድመቅ ጀመሩ፡፡ የምግብ መገልገያ እቃዎቹን ለኪራይ አገልግሎት ጭምር በማዋል ጥቅም አገኘ፡፡

ወስን ገቢውን ለማሳደግ የሚያከናውናቸው ተግባራት አሉት፡፡ አንዱ ፋሚሊ ወተትን ከቤተሰቡ በመረከብ በድሬደዋና ሐረር ዙሪያ ማከፋፍል ነው፡፡ ሰርግን በመምራት ዝግጅቱን ማድመቅንም ተክኖታል ውሃን ጨምሮ የለስላሳ መጠጦችን የማከፋፈል ተግባር ይከውናል፡፡ የእንቁላልና ዳቦ ማከፋፈል ሥራም ሌላው የገቢ ምንጩ ነው፡፡ በተለይ የዳቦ ጉዳይ ሲነሳ የእሱ መሰረት የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እንደሆነ ያነሳል፡፡

የወቅቱ ምክትል ከንቲባ የአሁኑ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ‹‹የድሬ ፍሬዎች በጎ አድራጎት ድርጅት›› ከተመሰረተ በኋላ ሥራውን ስላዩ 200 ሺህ ብር እንዲሰጠው ታስቦ ነበር፤ ሆኖም ገንዘቡ ጠፊ ነውና 100 ሺህ ብር ተሰጥቶት፡ በቀሪው የዳቦ ማሽን ይገዛለት

ተብሎ ተወሰነ፡፡

እርሱ ግን በጊዜው ተናዶ እንደነበር ። አሁን ላይ ሆኖ ሲያስበው ግን ውለታ እንደዋሉለት ያምናል፡፡ ምክንያቱም እንዲያ በመሆኑ ዛሬ ብዙዎችን መመገብ ችሏል፤ የራሱን የገቢ ምንጭም አሳድጓል፡፡

ወስን ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የሚያራምደው የተለየ አቋም አለ፡፡ ይህም ‹‹ገንዘብ ባንክ መቀመጥ የለበትም፤ ማህበረሰቡን እያገለገለ መዟዟር አለበት ›› የሚል ነው። እርሱም የሚያደርገው ይህንኑ ነው፡፡ እንዲያውም ከዚህ አቋሙ አንጻር በቅርቡ የሰርግ ዲኮር ላይ በስፋት ለመሳተፍ አስቧል፡፡ ለዚህ ደግሞ እህቱ በባለቤትነት የምትመራው ‹‹ላሊዛ ዲኮር›› እንደሚያግዘው ነግሮናል፡፡

የድሬ ፍሬዎች

‹‹መልካም ነገር ሁሉ ከፈጣሪ፣ መጥፎ ነገር ሁሉ ደግሞ ከሰይጣን እንዳልሆነ አስተውል፡፡ ምክንያቱም ፈጣሪ መጥፎን ወደ መልካም የመቀየር ብቃት አለው። ሰይጣንም ያጠፋህ ዘንድ መልካም የሚመስል ነገር ሊያዘጋጅልህ ይችላል። እናም ሁልጊዜ መልካም ማሰብና መልካም መሆን መልካም ነገር እንዲገጥምህ ማመቻቸት ነው፣ መጥፎዎችን ማራቅም ነው፡፡ መጥፎ ደግሞ ለአንተም ሆነ ለሰዎች ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም›› የወስን የሁልጊዜ መመሪያ ነው፡፡

ይህ መመሪያውም ትናንት ላይ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በጎ ተግባርን ሲከውን እንዲቆይ አስችሎት ዛሬ ላይ ይዞት የቀጠለውን ‹‹የድሬ ፍሬዎች በጎ አድራጎት ድርጅት››ን እንዲመሰርት አግዞታል፡፡ ይህ የሆነውም ከ2012 ዓ.ም በኋላ ነበር፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በዓላት ከትናንቱ ይልቅ ትልቅ ትርጉም የሚሰጣቸው ሆነዋል፡፡ የጎዳና ልጆችን በእናትና አባቱ ቤት ሰብስቦ የሚመግብበት፤ በዓልን ማክበር የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ደስተኛ የሚያደርግበት፤ ሆስፒታሎች አካባቢ እየሄደ የቻለውን የሚያደርግበት ልዩ እለታት ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘወትር ጓደኞቹ ከጎኑ ናቸው፡፡ በተለይም የ06 ወጣት አመራሮች ለእርሱ በጎ ተግባር ትልቅ አስተዋዕጾ ነበራቸው፡፡ በስራው የተደሰቱ አንዳንድ ድርጅቶችም ቢሆኑ ከስሩ አልተለዩም።

ቤተሰቦቹም ቢሆኑ ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው፡፡ እንደዛሬው ችግረኞችን ማብላት፤ ማጠጣት፣ ለተማሪዎች ዩኒፎርም ማሰፋት፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገንና መሰል ተግባራትን መከወን ባልተለመደበት ወቅት ወስን ለብዙዎች መድረስ እንዲችል አግዘውታል፡፡ ሆኖም በዓላትን ብቻ ተጠቅሞ ለሰዎች መድረስ ለእርሱ እርካታን አልሰጠውም፡፡ በተለይም ሰፈራቸው ትምህርት ቤት ተከፍቶ የማይመገበውን ተማሪ ቁጥር ሲመለከት ‹‹የምሰራው ተግባር በቂ አይደለም›› እንዲል አስችሎታል። ነገር ግን ስራውን ዘላቂ ለማድረግ ቋሚ ገቢ የግድ ነው። እናም የእያንዳንዱን ሰው ቤት ማንኳኳት ጀመረ፡፡ የዛኔ ብዙዎች ተስፋ አስቆራጭ መልስ ይሰጡት ነበር። እሱ ግን ድርጅቱን እስኪመሰርት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን ቀጠለ፡፡

የድጋፉ መጀመሪያ 2007 ዓ.ም ሆነ፡፡ ሰፈራቸው በተከፈተው ሕዳሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሚማሩና ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ላሉ ውስን ተማሪዎች በመድረስ፡፡ በቻለው ልክ በሰበሰበው ገንዘብ ዩኒፎርም በማሰፋትና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን በመግዛት እስከ 2008 ዓ.ም ዘልቋል፡፡ ቀጥሎም በጣም ችግረኛ የሆኑ ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ተማሪዎች እንዳሉ ሰማና እነርሱን ለማገዝ ፈጠነ፡፡ በ2010 ዓ.ም ደግሞ ሕልሙን እውን የምታደርግለት የባለቤቱ የአክስት ልጅ ወይዘሮ ወጋየሁ ኃይሉ ተገኘች፡፡

ውጭ ሀገር የምትኖር ሲሆን፤ በየአራት ወሩ አንድ ሺህ ዶላር ቃል ገብታ ትልክለታለች፡፡ በዚህም ከተማ አስተዳደሩ የመለመላቸውን 120 ተማሪዎች ሙሉ ምገባ እንዲያገኙ አደረገ፡፡ ቀጠለናም ሀጅ አሕመድ ኦክሰዴ በሚባሉ ባለሀብት ስም የተመሰረተ በጣም ችግረኛ ተማሪዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበረና ወደዚያ በማቅናት በአብዱልአዚዝ ከሪም አጋዥነት የ100 ተማሪዎችን ምግብ እንዲቻል ሆነ፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ ዋች ኤንድ ፕሪር ኢን ሚኒስትሪስ ድርጅትንና ቤተሰቦቹን ከጎኑ በማድረግ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ባሉ ቀበሌዎች 15 ትምህርት ቤቶችን ይዞ በአማካኝ 100 ተማሪዎችን በድምሩ ከ1500 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ደረሰ፡፡

በዋናነትን የገቢ ምንጩ ቤተሰቡ ቢሆንም ከእነርሱ ባሻገርም የእናቱ እህት ወይዘሮ አበራሽ ወንድሙና በአሜሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙት የአቶ አሰፋ ወልደ ጻዲቅ ልጆች እንዲሁም በአዲስ አበባ የምትገኘው አክስቱ ወይዘሮ እመቤት ወንድሙና ባለቤቷ አቶ ማስረሻ ስዩም ሳይጠቀሱ የማያልፉ አጋዦቹ ናቸው፡፡ ለዚህም ሁሉንም አጋዦቹን በተማሪዎቹ ስም ከልብ ያመሰግናል፡፡

ወስን በትምህርት ቤት ምገባ ብቻ ሳይወሰን በትምህርት ቤት እድሳትም ላይ ተሳታፊ ነው፡፡ የሕዳሴ ትምህርት ቤትን የተወሰኑ ክፍሎች ከቤተሰቡ በሰበሰበው ገንዘብ ሙሉ እድሳት አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ የመማሪያ ክፍሎችን ሰርቷል፡፡ በሌላ በኩል በሆስፒታሎች ውስጥም በቋሚነት በየዓመቱ ዕለተ ስቅለት ላይ ሕሙማንን ይመግባል፡፡ በትልቁ ድሬደዋ ሪፈራል ሆስፒታልም በቋሚነት ሁለት ሰራተኞችን ቀጥሮ ሕሙማን ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ተንከባካቢ ለሌላቸው ሕሙማን አጃ፣ ወተት፣ ዳይፐርም ያቀርባል፡፡

ወስን ለድሬደዋ ማረሚያ ቤትም ለሴቶችና ሕጻናት ማቆያ ሙሉ ግብዓት አሟልቶ በቋሚነት ሞግዚት ቀጥሮ እንክብካቤ ያደርጋል፡፡ አሁንም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለታራሚ ልጆች ያቀርባል፡፡ የወስን ተግባር ይህ ብቻም አይደለም፡፡ በወር አንዴ ከየክልሉ የመጡ ግን መኖሪያቸውን ጎዳና ያደረጉ ወገኖችን ቁርስ የመመገብ ፕሮግራም ያከናውናል፡፡ ከታመሙ መድሀኒት እንዲገዛላቸውም ያደርጋል፤ ወደ ሀገራቸው መመለስ ከፈለጉም እንዲሁ ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ ይሸኛል፡፡

ፈተናዎች…

ወስን በበጎ ሥራው ላይ ፈተና አላጣውም፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ተፈትኗል፡፡ በማብሰያ ቦታ ጥበት፤ በማጓጓዢያ መኪና፣ በነዳጅ፣ በመብራት መጥፋትና በሌሎችም ችግሮች መሀል ተመላልሷል፡፡ ለዚህ ደግሞ አጋዥ አካላት እንደሚያስፈልጉት ያምናል፡፡ አብሮ በመስራት በረከቱ እንዳለ ሆኖ ሀገርን ከፍ ማድረጉ ላይ አስተዋጽኦው ላቅ ያለ በመሆኑ፡፡

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በአንዳንድ ጉዳዮች እንደሚያግዛቸው ቃል ገብቶለታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ለሌሎች ለመድረስ ብዙ ጎዶሎዎችን የሚሞላ አካል ያሻቸዋል፡፡ ‹‹ወገኖቻችን የእኛ ግዴታዎች ናቸውና ኑ አብረን እንስራ፣ እንደግፋቸው›› ሲልም ጥሪ ያቀርባል፡፡

ቀጣዩ እቅድ

የወስን የቀጣይ እቅድ በጎነቱን መጨመር ብቻ ነው። ወደፊት ኑሮ ቢወደድም በበጎነት የሚተርፈው ብዙ ነውና ሰባት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በአማካኝ 100 ተማሪዎችን በማከል 2200 ተማሪዎችን መድረስ ይፈልጋል፡፡ ይህ እውነት ደግሞ የነፍሱ ጥሪ ነው፡፡

በአካባቢው ሆስፒታል የሚገቡ እናቶች ቁጥር በየጊዜው ይጨምራል፡፡ በዚህ ምክንያትም እናቶች ከወለዱ በኋላ በሆስፒታል የሚቆዩት ቢበዛ ለሦስት ቀናት ብቻ ነው፡፡ ይህ ችግር የገባው ወስን እነዚህ ሴቶች ሜዳ እንዳይወድቁ የሚያስችል ተግባር ለማከናወን አስቧል፡፡ይህን ሀሳብ የሚከውነው ደግሞ ግቢ ተከራይቶ አስር ክፍሎችን በማዘጋጀት ይሆናል፡፡

ወስን በዚህ ቤት ባህሉን በጠበቀ መልኩ እናቶች በወጉ እንዲታረሱ ይፈልጋል፡፡ የእርሱ ሀሳብ ቢያንስ ሦስት ወር የሚታረሱበትን እድል መስጠትና ከዚሁ ጎን የሙያ ስልጠና እንደዲያገኙ ማገዝ ነው፡፡ ከስፍራው ከወጡ በኋላም ሥራ እስኪያገኙ ለሦስት ወራት ቤት ተከራይቶ ሊንከባከባቸው ዕቅድ ይዟል፡፡

ቤተሰብ

ረጅም ዓመታትን በእጮኝነት አሳልፈዋል ከዛሬዋ ባለቤቱ ወይዘሮ አይናለም ማሞ ጋር፡፡ እርሷ ጥሩ የውበት ባለሙያ ነች፡፡ እርሱ ደግሞ በልምድም ቢሆን ጎበዝ ሼፍና ነጋዴ፡፡ የእርሷ የሙያ መሰረት አባቷ ናቸው፤ ታዋቂ የውበት ሳሎን አላቸው፡፡ የሁለቱ መጣመር ይፋ ሊሆን ሲቃረብ ወስን ከቤተሰብ ቤት መውጣት ግድ አለውና የራሱ ጌታ ሊሆን በብዙ ደከመ፡፡ ድካሙ ግን በከንቱ አልቀረም፡፡ ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማኖር ቻለ፡፡

አሁን አባወራነቱ ለልጁ ብቻ ሳይሆን ለ1500 ተማሪዎች ጭምር ተርፏል፡፡

ዛሬ ለ20 ሕጻናትና በሆስፒታል ለተኙ አቅመ ደካሞች አባት ነው፡፡ ይህንን ያረጋገጠው ደግሞ ገና ሲሞሸር ጀምሮ ነበር፡፡ የእርሱ ሰርግ ድምቀቱ ችግረኞቹ ነበሩ። የጎጆው መሰረቶችም ሆነዋል፡፡ ድግሱን አድምቀው ጋብቻውን ቀድሰውለታል፡፡ በሰርጉ ታድመው በረከትን ሸልመውታል፡፡ በእነርሱ ስም ኬክ አሰርተው ቆርሰዋል። ‹‹ትዳርህ ይባረክ ሲሉም መርቀውታል፡፡ ምርቃታቸው ደርሶም አንድ ሆና በአስተሳሰቧ ሺህ የሆነች፤ የተባረከች ልጅን እንዲያገኝ ሆኗል፡፡

መልዕክት

በጎነት ውሳኔን ይፈልጋል፡፡ ከተረፈ ላይ ሳይሆን ካለ ላይ መስጠትንም ይጠይቃል፡፡ በጎ ማድረግን ሁሉም ሊመኘው ይችላል፡፡ እንዲያም ሆኖ ቁርጥ ውሳኔ የግድ ይላል፡፡ አንዳንዴ ላለመስጠት፣ ከእጅ ላለማውጣት ምክንያት ይደረደርበታል፡፡ ሀብታም ስሆን፤ ሲኖረኝ፤ እግዚያብሔር ሲሰጠኝ. ወዘተ የሚሉ የስስት ሀሳቦች በአዕምሮ ውል ይላሉ፡፡ እናም የእኛ ሰው መስጠት የኖረበት ባህሉ ቢሆንም ይህ አይነቱ ሰበብ ወደኋላ ይጎትተዋልና ማካፈልን ከጎደለን፤ ከሌለን ነገራችን ላይ እናድርገው፤ በውሳኔም እንደግፈው፡፡ የዚህ ጊዜ ፈጣሪ በረከቱን ያድለናል›› ሲል ወስን ይመክራል፡፡

‹‹በጎ ውሳኔ መቼም ቢሆን አያስቆጭም፡፡ ይልቁንም መልካም በረከቶችን ይዞ ይመጣል›› የሚለው በጎ አድራጊ፤ በጎ ውሳኔ የመልካም በረከቶች ውጤት ስለመሆኑ ይናገራል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የሚጠቁመው ማኅበረሰቡን ነው፡፡ ወስን እንደሚለው ‹‹ማኅበረሰቡ በመስጠት ልምዱ ችግር እንኳን ሲያጋጥም ተቋቁሞ ማለፍን ያውቅበታል፡፡ ከእርሱ እጅ ያለው ጥሪት ለራሱ ብቻ የሚበቃው ሆኖ ሳለ ለሌሎች መትረፍን ልምዱ አድርጎታል፡፡ አሰጣጡ ዘላቂነት እንዲኖረው ግን ይህን ልምድ የሚያዳብርበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ ችግረኞችን በቋሚነት እንዲያግዝም በወጉ በመቀናጀት የተወሰኑ ሰዎችን መያዝ ይቻላልና፡፡ ይህ ዕቅድ ደግሞ በተግባር ሊሰራበት ይገባል፡››፡ ሲል አቶ ወስን መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You