በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ

አንዳንዴ እንደዋዛ የምንጀምራቸው ጉዳዮች መጨረሻቸው ላያምር ይችላል፡፡ በተለይ አነሳሳችን ጤናማነት የጎደለው ከሆነ ፍጻሜው እንደ አጀማመሩ በጣፋጭነት መቋጨቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡

‹‹ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› እንዲሉ አንድን የክፋት ድርጊት ሲጀምሩት ለውስጥ የሚያቀብለው ስሜት ለየት ይላል፡፡ ሃሳቡ በሳቅ ደስታ ተዋዝቶ ፣ ውስጥን በሀሴት የሚያረሰርስ እስኪመስልም ለጀመሩት ዓላማ ራስን አሳልፎ እስከመስጠት ያደርሳል ፡፡

ይህ አይነቱ እውነት ከራስ አልፎ የሰዎችን ክብርና ማንነት የሚነካ ከሆነ ደግሞ የክፋቱን ጫፍ ለማግኘት ይቸግራል፡፡ በየቀኑ በራስ ተነሳሺነት ተገፋፍተው የሚሄዱበት ርቀትም መጨረሻ ላይኖረው ይችላል፡ ፡ እንዲህ ያለው መንገድ ከወሰደበት አቅጣጫ በቀላሉ የሚመልስ አይሆንም፡፡ ጠፍተው የቀሩ እስኪመስል ከራስ ጋር ይለያያል፣ ያቆራርጣል፡፡

ተደጋግሞ እንደሚባለው ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ከተጠቀምነው ሁሌም አትራፊዎች ነን፡፡ ከራሳችን አልፈን በርካቶችን ለመድረስ ድልድይ ይሆነናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በክፋት ዓላማ ከተጓዝንበት ግን እንደ አወጣጣችን ልንመለስበት ችግር ነው፡፡

ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ይሉት ጉዳይ እስከአሁን ብዙ አሳይቶናል፡፡ በጎ የሚባለውን በመልካም እንውሰደውና አንዳንዶች በሚዲያው ተጠቅመው እያደረጉት ያለውን ያልተገባ ድርጊት በመጠኑ እንቃኝ፡፡

በቅርቡ ነው፡፡ በዚሁ ሚዲያ የተለያዩ ገፆች ከሀገራችን ታዋቂ ሴት ተዋናዮች መካከል የአንዷ ስም እየተነሳ ይብጠለጠላል፡፡ ጉዳዩ ደግሞ በእሷ ህይወት ብቻ አልቆመም፡፡ ስለ ልጆቿና ባለቤቷ ጭምር የማይወሳ፣ የማይነገር የለም፡፡ በእርግጥ ስለ ታዋቂ ሰዎች ብዙ ቢባል አይገርም ይሆናል፡፡

የሰዎቹ የግል ታሪክ ፣ የቤተሰብ ሁኔታና ሌሎችም በየሰበቡ ሊወሱ ይችላሉ፡፡ የአንድን ሰው የመኖር መብት በመጋፋት ራስን እስከመጥላት የሚያዘልቅ አስነዋሪ ታሪክ መዝራት ግን ከነውርነት አልፎ ወንጀል እንደመስራት ይቆጠራል፡፡

አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያው ሱሰኞች ስለራሳቸው ህይወት የምትተርፍ ሽራፊ ሰከንድ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሌሎችን እንዴት እንደሚጎዱ፣ የከበረ ስማቸውን በምን መልኩ እንደሚያጠለሹ ሲጨነቁ ያድራሉ፡፡ ሌታቸው በነጋ ጊዜ በክፋት ያለሙትን ዓለም ዕውን ለማድረግ የሚቀድማቸው አይገኝም፡፡

እንዲህ አይነቶቹ የስም ጥላሸቶች አጉል ወሬን ይዘው ለመውጣት መረጃ ማስረጃ ስለሚባለው ጉዳይ አንዳች አይጨነቁም፡፡ ለእነሱ የሚዲያውን ገበያ ሊቆጣጠርላቸው የሚችል የአንድ ታዋቂ ሰው ስም ከነአባቱ መሸምደድ ብቻ በቂ ነው፡፡ የዚህን ሰው ክብርና ዝና ለማዋረድ ደግሞ ከየት እንደሚጀምሩ አሳምረው ያውቁታል፡፡

የሰዎች ሞራል እንደ እንጨት ተሰብሮ የሚወድቅበትን ስልት ለማግኘት ያዋጣል በሚሉት አቅጣጫ ሁሉ ይሮጣሉ፡፡ ስም ማጥፋታቸውን ያጠናክርልናል የሚሉትን መሰል ወሬ ካገኙም ዓይናቸውን አያሹም፡፡ በማንኛውም መልኩ የደረሰ ወሬ ለእነሱ ምቹና አስፈላጊ ነው፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ይህ አይነቱ የስም ማጥፋት ሩጫ ከተራ የጽሁፍ ወሬ አልፎ በአካል ወጥቶ እስከመፋጠጥ የደረሰ ሆኗል፡፡ ‹‹የእከሊት ሚስት እከሌ ከሚባል ሰው ጋር ስትወሰልት ተያዘች፣ ባሏ ማንነቷን አውቆ ትዳሩን ፈታ፣ እሷ በአደባባይ ተጋለጠች፡፡›› የሚሉና አንገት የሚያስደፉ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ያለእፍረት ይራገባሉ፡፡

ሰዎቹ ስለሚነዙት ወሬ ታማኝ መሆናቸውን ለማሳየት በፊልምና ፎቶግራፍ የተደገፈ በቂ ማስረጃ በእጃቸው አንዳለ ሲናገሩ በተለየ መተማመንና እርግጠኝነት ነው፡፡ ጉዳዩ ‹‹ከአፍ ከወጣ አፋፍ›› ነውና እነሱን የሰሙ አንዳንዶች ጫፍ ይዘው ለማራገብ ሁሌም ተባባሪዎች ናቸው፡፡

በዚህ መነሻ የሚጀመረው ስም ማጥፋትም ነፍስ ዘርቶ ፣ በአካል ገዝፎ ውስጥን ለመስበር አፍታ አይቆይም፡፡ ብዙዎች ታዲያ የሰሙትን ወሬ እንደዋዛ አያልፉትም፡፡ ሁኔታውን ስለመውደዳቸው በምልክት ገልጸው፣ ያዩትን ለሌሎች አጋርተው፣ ከቻሉም በሌላ ልብ ሰባሪ ቃል ሃሳቡን አራግበው ጫፍ ያደርሱታል፡፡

በዚህ መቀባበል ከብዙኃን ጆሮ የሚዳረሰው አጉል ወሬ አቅም ለማግኘት ጉልበቱ አይዝልም፡፡እውነት ይሁን ሀሰት ባልተረጋገጠበት አፍታ በርካታው ታዳሚ የባለ ታሪኩን የስም ማጥፋት ዘመቻ በእኩል ይጋራዋል፡፡

በጣም አስገራሚው ነገር በጉዳዩ ላይ የአብዛኞች ሃሳብና አስተያየት መመሳሰሉ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ የስም አጥፊዎቹ ኃይልና ተጽዕኖ ሰፊውን ድርሻ ይጫወታል፡ ፡ ‹‹ የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል›› እንዲሉ ነገሩን በወጉ ያልተረዱ ሁሉ ያሻቸውን ሃሳብ ለመሰንዘር ጽሑፍና ቃል የሚለማመዱበት አጋጣሚ ይሆናል፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ ጉዳዩ ለሌሎች መነሳሳት በጎ ምሳሌ አለመሆኑ ነው፡፡ ትናንት ይህን ታሪክ ያዩ፣ የሰሙ አንዳንዶች ተከታዮቻቸውን ለማበራከት በጠማማው መንገድ ማለፋቸው አይቀርም፡፡ እነሱም ስም ለማጥፋት፣ በማያገባቸው ጠልቀው ለመዘላበድ የተጋሩት ተሞክሮ መነሻቸው ይሆናል፡፡ እንደሌሎቹ ሁሉ ያሻቸውን ነውርነት ለመሰንዘር አጋጣሚውን በመነሻነት ይጠቀማሉ፡፡

ለዚህ ሁሉ ክፉ ድርጊት መስፋት ዋንኛ ምክንያት ደግሞ በሀገራችን በዚህ ዘርፍ ላይ የሚስተዋለው የሕግ መላላት ተጠቃሽ ነው፡፡ብዙ ጊዜ ተበዳዮች በማስረጃ ከሳሾቻቸውን መልሰው ያለመክሰሳቸው እውነታና የሕጉ በወግ አለመተግበር ችግሩን አባብሶታል፡፡

የጥላቻ ንግግርና የሕጉ ዕውንነት በአግባቡ ሥራ ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ቢተገበር ግን ማንም ነውርነትን ሕጋዊ ባላደረገ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተበዳዮች ለሚሆንባቸው ክፉ ድርጊት መረጃን በማስረጃ አስደግፈው መብታቸውን ማስከበር ቢሞክሩ የሕጉን የበላይነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ደጋግመን እንዳስተዋልነው ባለቤቱ በራሱ ላይ ማዘዝ እስከማይችል ድረስ በፎቶግራፍ፣ ድምጽና ተንቀሳቃሽ ምስል ማንነቱን እያሰጡ፣መሳለቂያ ማድረግ ከወንጀልም በላይ ወንጀል ነው፡፡ በአንዱ ሃሳብ ላይ ተመርኩዞ ሌላው የሚሰነዝረው አስተያየትም ባብዛኛው ከዋናው ድርጊት የተለየ አይሆንምና በእኩል ሊጤን ይገባል፡፡

እስካሁን እንደተስተዋለው በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው የመጀመሪያ አስተያየት ጠማማ ከሆነ እሱን ተከትለው የሚመጡ ሃሳቦችም ፍጹም የተቃኑ አይሆኑም፡፡ ይህን መረን የወጣ የማህበራዊ ሚዲያ ተሞክሮ እንዳደጉት ዓለማት ፈጥኖ መቆጣጠር ባይቻል እንኳን የራስን ሙከራ ማድረጉ አይከፋም፡፡

ለዚህ አባባሌ መነሻዬ ላይ ልጠቅሰው ወደሞከርኩት ሃሳብ ልመለስ፡፡ ስሟ በማህበራዊ ሚዲያ ሲብጠለጠል ስለከረመው አንዲት ሴት፡፡ ይች ሴት በሀገራችን ጥሩ እውቅና ካላቸው ሴት ተዋናዮች መሀል አንዷ ሆና ትጠቀሳለች፡፡ የማህበራዊ ሚዲያው እሾሀማ ግርፋት ካገኛቸው መካከልም ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ማንነቷን መሠረት ባደረገውና ጊዜያትን ባስቆጠረው የስም ማጥፋት ዘመቻ እሷና ቤተሰቦቿ አንገት ሲደፉ ቆይተዋል፡፡

ባለቤቷንና ልጆቿን ጭምር ሲሸነቁጥ የኖረው ስም ማጥፋት ለጊዜያት ብቻ የቆየ አልነበረም፡፡ በስሟ በተከፈተ ማህበራዊ ገጽ ኑሮና ህይወትን፣ በሚሰረስር ክፋት ብዙ ጉዳዮችን እንዳዛባ ዘልቋል፡፡ በሙያዋና በግል ህይወቷ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ይህ ጉዞ ‹‹ይሁነኝ›› ብለው ዓላማውን ለሚያራምዱ ግለሰቦች ደግሞ በረብጣ የተሞላ ትልቅ ሻንጣ ሆኖ ነበር፡፡

‹‹ትዕግስትም ልክ አለው›› እንዲሉ አሁን ላይ በተበዳይዋ ብርቱ ጥረት ይህን ክፉ ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦች በሕግ የሚጠየቁበት መፍትሔ መገኘቱ ተሰምቷል፡፡ በበቂ ማስረጃና መረጃ በሕግ ተጠያቁ እንደሆኑ የተነገረላቸው የስም ቀበኞች እነሆ! በቃችሁ ሊባሉ ጊዜው ደርሷል፡፡

ማንም ከሕግ አምልጦ የሚኖር የለምና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በርካቶችን አንገት የሚያስደፉ የክፋት ምሳሌዎች ከዚህ አጋጣሚ ይማራሉ ተብሎ ይታሰባል። እዚህ ላይ ‹‹በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ›› ይሉት ብሂል ልኩን ያገኘ ይመስላል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You