“ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ውጪ አማራጭ የላትም”

ወጣት ኤልያስ ይርዳው ይባላል። ውልደትና እድገቱ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማው አምቦ ተከታትሏል። በመቀጠልም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣት የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በኮምፒውተር ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በመቀጠልም የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት ትምህርቱን ተከታትሏል።

በልጅነቱ ማለትም ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባለው የትምህርት ቆይታው በትምህርት አቀባበሉ ጥሩ ከሚባሉ የደረጃ ተማሪዎች መካከል እንደነበር የሚናገረው ኤልያስ፤ ከክፍል የመማር ማስተማር ሂደት ውጭ በተግባር የተደገፉ የፈጠራ ሥራዎች ቀልቡን ይዞት እንደነበርና በክፍል የተማራቸውን የፊዚክስ ወይም ኬሚስትሪ ሕጎች በተግባር ምን ይመስላሉ የሚለውን ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ እንደነበር ይገልፃል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ሆነ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ከክፍል ትምህርት ይልቅ ላብራቶሪ ውስጥ ረዥሙን ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር የሚናገረው ኤልያስ፤ በወቅቱ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የነበረው አመለካከት ትክክል ስላልነበር የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመስራት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ብዙ ፈተናዎች እንዳጋጠሙት ነገር ግን ትልቁን ራዕይ ለማሳከት በተቻለው አቅም ሁሉ ተግዳሮቶችን ለመሻገር ጥረት እንዳደረገ ይናገራል።

በአሁኑ ወቅት ፋሪስ የተሰኘ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መስራችና ባለቤት የሆነው ወጣት ኤልያስ፤ ስለ ድርጅቱ አመሰራረት ሲናገር፤ “ ኢትዮጵያ ውስጥ በተናጠል የሚሰሩ የፈጠራ ሥራዎች ቢኖሩም ከአንድ ወቅት መነጋገሪያነት ያልፋሉ አይደሉም፤ ይህ ደግሞ ግለሰቡንም ሀገርንም የማይጠቅም በመሆኑ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ሥራዎች እንዲሰሩ በማሰብ ይህንን ድርጅት ወደ መመስረት ገባሁ” ይላል።

ለድርጅቱ ፋሪስ የሚለውን ስያሜ ለምን እንደሰጠ ወጣት ኤልያስ ስናገር፤ ቃሉ በክርስትና ጥሶ የሚወጣ የሚል ትርጉም አለው በአረብኛ ደግሞ ፈረስ ላይ ሆኖ የሚዋጋ የሚል ፍቺ ይሰጣል ስለዚህ ጥሶ የሚወጣ ሀሳብ የሚያመነጭ ግዙፍ ኢትዮጵያዊ ተቋም ለመገንባት ካለው ራዕይ መነሻ የተሰጠ እንደሆነ ይናገራል።

ድርጅቱ ሲመሰረት በመጀመሪያ ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ልጆች አቅም ለማብቃት ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንደገባ የሚናገረው ኤልያስ፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተውጣጡ ከ 12ሺ በላይ ለሚሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች ስልጠና በመስጠት ተሰጥኦ ያለቸውን መጠየቅ፣ መመራመር፣ መፍታት፣ ማበላሸት የሚወዱ ልጆችን ለማብቃት እንደሰራ የዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ በተለያየ ቦታ ሀገር የሚለውጥ ሀሳብ ያላቸው ልጆች እንዳሉ እምነት ስላላቸው እንደሆነ ይናገራል።

“ኩባ ዶክተሮችን ለዓለም ታቃርባለች፣ ፊሊፒንስ ደግሞ መርከበኛን ታፈራለች፤ ኢትዮጵያም ሳይንቲስቶችን ለዓለም ኤክስፐርቶች ማድረግ ትችላለች ብለን እናምናለን” የሚለው ወጣት ኤልያስ፤ የኢትዮጵያ ኢንጅነሮች ዛሬ በዓለም ላይ ተበታትነው ነው ያሉት በአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም ናሳ ውስጥ አሉ፣ ፌስቡክ ኩባንያ፣ በጎግል ኩባንያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አሉ፤ ይህ የሚያሳየው ሀገሪቱ ውስጥ አቅም ያለው ትውልድ እንዳለ ነው ይላል።

ኤልያስ እንደሚገለፀው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ልጆች አሉ። ይህንን ይበልጥ ለማሳደግና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች በማሰልጠን ቁጥሩን ማሳደግ የግድ አስፈለጊ በመሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ ሶስት ማዕከላት በመክፈት በክልሎች እንዲሁ ስድስት የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከላት በማደራጀት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ከ17 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አጋርነት በመፍጠር በቴክኖሎጂ የላቁ ኢትዮጵያውያንን ለማፍራት ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይናገራል።

“ልጆችን አሰልጥነን ብቻ አንተውም ወደ ገበያ በማስገባት አቅም ያላቸውን (Business processing outsourcing) በተሰኘው የድርጅቱ ክፍል ጋር በመተባበር የፋሪስ ኩባንያ ከተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ተቋማት ፕሮጀክቶችን በመውሰድ ስለምንሰራ ይህንን ሥራ እንዲሰሩ በማድረግ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን ብሏል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ሕብረተሰቡ ለዘወትር አገልግሎቱ የሚጠቀማቸው መገልገያዎች በአብዛኛው ከውጭ የሚመጡ ናቸው የሚለው ኤልያስ፤ ይህ ግን ከሆነ ጊዜ በኋላ ይቆማል ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ፈጥረው ሰርተው የሚሸጡበትና ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡበት ጊዜ ይመጣል፤ ለዚህ ደግሞ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል። ድርጅቱም ትኩረቱን የጥናትና ልማት ሥራ ላይ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው ውጤታማም እየሆነ ነው ይላል።

ድርጅቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኤሮ ኢስፔስ መሳል ዘርፎች በራስ አቅም ብሎም በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ አጋር አካለት ጋር በመቀናጀት ጥናቶችን እየሰራ እንደሚገኝ የሚናገረው ኤልያስ፤ ለአብነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተቃኙ የሕዝብን ችግር በከፍተኛ ደረጃ መፍታት የሚችሉ፤ በገንዘብ ተቀይረው ደግሞ ድርጅቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንዲሁም ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገቡ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልፆል።

ኤልያስ እንደሚናገረው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽን ወይም ኮምፒዩተር የሰው ልጆችን ተክቶ ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድ እና ፈጠራዎችን ማከናወን እንዲችል የሚያደርግ ነው። በዚህ ሁኔታ ማሽኖቹ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ፣ የተገነዘቡትን እንዲተነትኑ፤ ችግሮችን እንዲፈቱ እና አንድ የተወሰነ ግብ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ያስችላቸዋል። ይህም በተለይ የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ ለምርት መጨመር፣ የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ እና ውስብስብ ስራዎችን ያለ ከፍተኛ ወጪ ለመፈፀም ያስችላል። ከጊዜ አንፃርም ያለማቋረጥ እና ያለ ምንም እረፍት ይሰራል ይህም የሕብረተሰብን ኑሮ የሀገርን ዕድገት እንደሚያቀላጥፍ ያስረዳል።

የፋሪስ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሌላው ሥራ በአይሲቲ ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ የሚገልፀው ወጣት ኤልያስ፤ ለአብነት መንግሥት የጀመረውን ተቋማትን ዲጂታል የማድረግ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ በማገዝ አብሮ እየሰራ እንደሆነ ይናገራል። የመንግስትና የግል ተቋማት አገልግሎት ዲጂታል እንዲሆንና ተገልጋይ የሚፈልገውን አገልግሎት ቤቱ ሆኖ እንዲያገኝ ለማስቻል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ያስረዳል።

ወጣት ሆኖ ቴክኖሎጂን መውደድ የውዴታ ግዴታ ነው የሚለው ኤልያስ፤ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና ላይ ቴክኖሎጂን መጠቀም ካልተቻለ ሕይወትን ማሻሻል የማይቻልበት ምክንያት የለም። ቴክኖሎጂን መጠቀምና ማወቅ ብሎም ወደዚህ ዘርፍ መጠጋት ለነገ የማይባል በመሆኑ የወጣቶች ትኩረት አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃል።

ኤልያስ እንደሚናገረው፤ አንድ ሰው ሰላሳ ዓመታት ነግዶ ያላገኘውን ገቢ በቴክኖሎጂ ዓለም በሶስትና በአራት ዓመት ውስጥ ማምጣት ይቻላል። በዓለማችን ላይ ከሚገኙና በሀብት ማማ ላይ ከተቀመጡ ቢልየነሮች በደረጃ ከአንድ እስከ አስር ያሉት መነሻቸው ቴክኖሎጂ ነው። ያለ ቴክኖሎጂ ትልቅ ድርጅትና ጎበዝ ወጣት የሚባል የለም፣ ያለ ቴክኖሎጂ ሀያል የሆነችው ሀገር የለችም፤ የዚህ ሁሉ ምክንያት የሰዎች ጭንቅላት ነው። ስለዚህ እንደ ሀገር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለመለወጥ ርብርብ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል መነቃቃት ተፈጥሯል የሚለው ኤልያስ፤ ለአብነት 81 ሚልዮን የሚሆን ሕዝብ የሞባይል ስልክ ተጠቀሚ ነው። ከዚህ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኘው ከ 30 ሚልዮን በላይ ደርሷል። ይህ የሚያሳየው ሕብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመቀበል ግንዛቤው እያደገ ስለመምጣቱ ነው። ይህ ደግሞ ለዘርፉ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን አሁንም ሰዎች ቴክኖሎጂን ይበልጥ እንዲጠቀሙ መገፋፋት እንደሚገባ ይገልፃል።

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በቋሚነት ሰማንያ ሰባት ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የሚናገረው ወጣት ኤልያስ፤ የፕሮጀክት ሥራ ሲኖር ግን በጊዜያዊነት ሥራ የሚያገኙ ዜጎች ቁጥር ወደ ሁለት መቶ እንደሚደርስ ገልፆ፤ ይህንን ቁጥር በቀጣይ አራት ዓመታት ወደ አምስት ሺህ ለማድረስና ቤተሰቡን መርዳት የሚችል፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አበርክቶ ሊኖረው የሚችልና በቴክኖሎጂ ዘርፍ አዳዲስ ፈጠራ ስራዎችን እያመጣ ወደ ገበያ የሚያቀርብ ትልቅ ሀብት የሚያንቀሳቅስ ወጣት ለማፍራት እቅድ እንዳለው አስረድቷል።

ጨረታ አሸንፎ ለትርፍ ከመስራት ባለፈ በነፃ ለመንግሥታዊ ተቋም የተለያዩ ሥራዎችን በድርጅቱ አማካኝነት እየሰራ እንደሆነ የሚናገረው ኤልያስ፤ ለአብነት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለፌዴራል የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ቢሮዎች <<ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው>> በሚል መርህ ቢሮው የሚሰራቸው ሥራዎች ዲጂታል በሆነ መልኩ የተመዘገቡ ስላልሆኑ ይህንን የሚያስተካከልና ድጋፍ ለሚሰጡ ሰዎች ደግሞ ሰርተፍኬት በራሱ የሚሰጥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ ስይስተም ለ 106 ወረዳዎች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ይገልጻል።

በተጨማሪም ፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትልቅ ፕሮጀክት አብሮ ለመስራት ውል መፈራረሙን የሚናገረው ኤልያስ፤ ይህ አጋርነት Business Process Outsourcing (ቢፒኦ)፣ ምርምር፣ ፈጠራ፣ ንግድ ስራ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ላይ አብሮ ለመስራት ያለመ ነው። የፈጠራ ጉዞ ለመቅረጽ የአካዳሚክ እና የኢንደስትሪ እውቀትን በመጠቀም የኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ እድገት ከፍ ለማድረግ ያለመ ሥራ እንደሆነ ይገልፃል።

ኢትዮጵያ ሁለቱን ሳተላይት ወደ ህዋ ስትልክ የድርጅቱ ባለሙያዎች እንደተሳተፉ የሚናገረው ወጣት ኤልያስ፤ በክልልና በፌዴራል የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተቋማትን ዲጂታል በማድረግ ሰፊ ሥራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ በማፋጠን የራሳቸውን ሚና እየተወጡ እንደሆነ ይገልፃል።

ትልቁ ሥራና ኢንቨስትመንት የሰውን ጭንቅላት መገንባት ነው የሚለው ኤልያስ፤ በዚህ ረገድ የሀገሩን ልጆች አቅም ለመገንባት ለፈጠራና ምርምር የተነሳሱ ወጣቶችን ለማፍራት ድርጅቱ ገንዘብ ለማግኘት ከሚሰራቸው ሥራዎች በበለጠ በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት የማብቃት ሥራ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራ ይናገራል።

በአሁኑ ወቅት በተሳሳተ ግንዛቤ ቴክኖሎጂ መሰል የፈጠራ ሥራዎች ላይ የሚቀልዱ ሰዎች አሉ ወይም እንደ ቅንጦት የሚመለከቱ ነገር ግን በምድር ላይ ዘላለም የምንኖር አይደለንም በሚኖረን ጥቂት ጊዜ ተጠቅመን መቼ ነው ዓለም የሚጠቀማቸውንና የታጠቀቸውን ቴክኖሎጂዎች ኢትዮጵያም ባለቤት የምትሆነው ብለን ጠይቀን እራሳችን የመፍትሔ አካል ለመሆን ነው መስራት ያለብን ይላል።

የእስፔስና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ከልታጠቅን በስተቀር በድህነት መዳከራችን አይቀሬ ነው የሚለው ወጣት ኤልያስ፤ ዓለም ላይ ያለውን ሀብት ወደራሳችን ኪስ ለማምጣት ግዴታ የዓለም ትኩረት የሆነውን ቴክኖሎጂ ማወቅ አስፈለጊ ነው። ስለዚህ እንደሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን መረባረብ የግድ እንደሆነ ያስረዳል።

በዚህ ዘርፍ እውቀት ያለው ወጣት ተፈላጊነቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገረው ኤልያስ፤ ወጣቶች ዓለም ለሚፈልገው ገበያ እራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ይላል። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ላይ ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ያለው ድጋፍና ክትትል የሚበረታታ በመሆኑ ዕድሉን ተጠቅሞ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ ደግሞ የወጣቶች ኃላፊነት መሆን አለበት ይላል።

ስለ ወደፊት እቅዱ ወጣት ኤልያስ ሲናገር፤ ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይት ቢኖራት በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች፤ ስለዚህ ድርጅቱ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ ሕዋ የሮኬት ማምጠቅ የሚችል እንዲሆን የማድረግና ሥራ እየሰራ እንደሆነ ተነግሮ፤ ስለ እስፔስና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስነሳ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት ሆነ መቅረብ እንድትችል ለማድረግ ውጥን እንዳለው አስረድቷል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You