መሐመድ ሳኒ ሀቢብ
ሀገራቸውንና እምነታቸውን በመወከል ስለ ሰላምና ጦር መሳሪያ ቅነሳ በሶቭየት ሕብረት በሳውዲ አረቢያ፣ በኩየት፣ በሊቢያ፣ በአልጄሪያና በሌሎችም ሀገሮች በተደረጉ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ ተካፍለዋል:: ለልማትና ማህበራዊ ሥራዎችም ትኩረት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል:: በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል ትምህርት ቤቶችና መስኪዶች እንዲቋቋሙ በማድረግ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን አጥተው ያላሳደጊ የቀሩ ሕፃናት የሚያድጉበት የሕፃናት ማሳደጊያ እንዲቋቋም ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል:: እኝ ሰው ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ይባላሉ:: እኝህ ትልቅ ሥራ የሰሩትን የኃይማኖት አባት የሥራና የሕይወት ተሞክሮ ልናስነብባችሁ ወደናል:: መልካም የንባብ ጊዜ እንዲሆንላችሁም እንመኛለን::
ስለ ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ የተለያዩ መረጃዎችን አሰባስበን እንዳገኘነው፤ ለሥራቸው ልባዊ ፍቅር ያላቸው ትጉህና ታታሪ ናቸው:: ለሥራ ቅድሚያ ስሚሰጡ ያላቸው የእረፍት ጊዜ እጅግ ውስን ነው:: በተለያዩ መድረኮች በመገኘት መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጣሉ:: ከትምህርቱ በኋላ በሚኖራቸው ጊዜ ደግሞ ጽሁፎችን ያዘጋጃሉ:: ለህትመት የበቁ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ በርካታ ፅሑፎችን አበርክተዋል:: በሥራቸው፣ በተባባሪነታቸውና ለሌሎችም ባላቸው አክብሮት፣ ተወዳጅነትን ያተረፉ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ አባት ስለመሆናቸውም ይነገርላቸዋል:: ሁሉንም በእኩልነት የሚመለከቱ፣ ለችግረኞችም አዛኝ እንደነበሩ እንዲሁ ከታሪካቸው መረዳት ችለናል።
በኃይማኖቱ ውስጥ ካላቸው ተሳትፎ በተጨማሪ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይም ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ይታወቃሉ:: ለአብነትም በሀገር አቀፍ ደረጃ በብሔራዊ መሰረተ ትምህርት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር የደረሰባቸውን ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸውን ለመርዳት በተቋቋመው ብሔራዊ እርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ እንዲሁም በሌሎች ሀገር አቀፍ ኮሚቴዎች ውስጥ በመመረጥ ለሀገርና ለወገን ሰላምና እድገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ይጠቀሳል::
ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ በእምነትም እውቀት ያላቸው ሰው ናቸው:: በቁራን፣የሸሪዓ ሕግ፣ ፊቄ፣ የአረብኛ ቋንቋና ሰዋሰው፣ የቁራን ትርጉም ተፍሲር፣ የሸሪዓ ሕግ ፍልስፍና ኡሱል የነብዩ መሐመድ ቃልና ተግባር ሀዲስ፣ የአረብኛ ቋንቋ ስነፅሁፍ ሌሎችም መሰል ትምህርቶችን ከታላላቅ የእምነቱ ሊቃውንትና ኡለማዎች በየ ደረጃው ተከታትለዋል።
ሰፊና ጥልቅ እውቀት የነበራቸው ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ይህ ሥራቸውም በብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ምሁራን ምስክርነት አግኝተዋል። በተለይ በአረብኛ ቋንቋ ሰፊና ትልቅ እውቀት አላቸው ከሚባሉት ጥቂት ኢትዮጵያውያን የእስልምና ሊቃውንት አንዱ ነበሩ። አንቱ የተባሉበትን የሀይማኖት እውቀት ለመገብየት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ በተፈለጉበት ሥፍራ ሁሉ እየሄዱ በማስተማር እርሳቸውም በመማር አሳልፈዋል።
በሕይወት ዘመናቸው ምን ጊዜም ለመማርም ሆነ ለማስተማር የመሰልቸትና የድካም ስሜት አይታይባቸውም የሚባሉ፤ በአጠቃላይ በአርያነት የሚጠቀስ ከፍተኛ የሆነ ስነምግባርና መልካም ባህሪይ ባለቤት የሆኑት ሀጂ መሐመድ ሳኒ ለሀገርና ለሕዝብ ሕያው የሆነ ሥራ ሳይታክቱ ሠርተዋል።
የኃይማኖት ትምህርታቸውን የተማሩት በባህላዊ መንገድ በሀገራቸው ውስጥ ሲሆን፤ ዘመናዊ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው ሰው ናቸው:: ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ፤ ከእሳቸው በፊትና በእሳቸው ዘመን በነበሩት በብዙሀኑ የእስልምና ምሁራን ዘንድ ልጆችን ዘመናዊ ትምህርት ማስተማር ከሃይማኖታቸው ያርቃል የሚል ጎታች የሆነ አስተሳሰብ እንዳልነበራቸው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።
ከዘመኑ ጋር መራመድ ያስፈልጋል የሚለውን እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት ሲሉም እድሜያቸው ከገፋ በኋላ አንድ ብለው ጀምረው ዘመናዊ ትምህርት እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ የተማሩ የተግባር ሰው ነበሩ። ይህንን በተመለከተ ከእሳቸው ስር የእስልምና ትምህርት የተማሩት ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ ይመሰክሩላቸዋል:: ‹‹እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ዓለማዊ ትምህርትን በክፉ አይን ነበር የምንመለከተው:: ከሀይማኖት ከባህል ይነጥላል የሚል አመለካከት ስለነበር ትምህርት እንዲስፋፋ ፍላጎት አልነበረንም:: ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ግን ከዚህ በተለየ ለዘመናዊ ትምህርት በጎ አመለካከት ነበራቸው:: ብዙዎችም ጥቅሙን እንዲረዱት ሰርተዋል’’ ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ሀይማኖቱን በመማር ማስተማር ሂደት የተለየ ራዕይ ያላቸው ሰው ነበሩ በማለትም ገልጸዋል። የእስልምና ሀይማኖትን አማኙ በሚገባ እንዲረዳው ካስፈለገም በሚረዳው ቋንቋ በአማርኛ በቀላል መንገድ ማስተማር ይገባል የሚል እምነት እንደነበራቸውም መስክረውላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህንን የትምህርት አሰጣጥ ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ መስጠት እንዲችሉ አጋጣሚ እስከተፈጠረላቸው እስከ 1956 ዓ.ም ድረስ የእውቀታቸውን ያህል በሙስሊሙ ሕብረተሰብ ዘንድ ሳይታወቁ በደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ግብረገብ እያስተማሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
አፄ ኃይለሥላሴ ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኝ ያስተረጎሙት ቅዱስ ቁራን ትርጉም አልሰጥም ቢላቸው ቤተመንግሥት ባስቀመጡት በአስራ አንደኛ ዓመቱ ድንገት ቅዱስ ቁራንን በምንጩ ቋንቋ ከአረብኛ ወደ አማርኛ የሚተረጉም ሰው እንዲፈልጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድን ያዛሉ:: ጠቅላይ ሚኒስትሩም የወቅቱን የአልዓለም ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩና 35 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩ ሰሊም ቡሸከር የተባሉ ሊባኖሳዊ ንጉሱ ፊት ያቀርባሉ:: የጋዜጣው ዋና አዘጋጅም “ለአረብኛው እኔ አለሁ ሆኖም ግን ጥሩ አማርኛ የሚያውቅ የሀይማኖት ሊቅ እፈልጋለሁ’’ አሉ:: በዚህ ጊዜ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ይሰሩ የነበሩት የአላዘር ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆኑት ሀጂ በሽር ዳውድ ይጠራሉ:: እርሳቸውም ቁራኑን አንብበው ትርጉሙ እጅግ ብዙ ስህተት እንዳለው ገልፀው አረብኛውን በሚያውቁ ኢትዮጵያዊ የሀይማኖት ምሁራን በቡድን ቢተረጎም የተሻለ ነው የሚል ምክረ ሀሳብ በማምጣታቸው ይህንኑ ሥራ እንዲሰሩ ከተመረጡ የእምነቱ አባቶች አንዱ ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ነበሩ።
ሀይማኖቱን በተመለከተ በቂ እውቀት ያላቸው ለዘመናዊነት ቅርብ መሆናቸውና አርቆ አሳቢ በመሆናቸው ለትርጉም ሥራው የተመረጡት ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ፤ ሥራውን በጥራት በመስራት ለንጉሡ አስረከቡ:: ንጉሡም ትርጉሙ ቅሬታ እንዳይነሳበት ሌሎች የእምነቱ አባቶች እንዲገመግሙት ትእዛዝ ሰጡ:: ለአንድ ዓመት በተደረገ ግምገማ ትርጉሙ ስህተት የሌለው በመሆኑ የቅዱስ ቁራን አማርኛ ትርጉም ለህትመት መብቃት ቻለ።
ለትርጉም ሥራ የመጡት ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ኑሯቸውን አዲስ አበባ ማድረግ መርጠው ደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትን የግብረገብ ትምህርት በደጃች ኡመር ሰመተር ትምህርት ቤት ለማስተማር ተቀጠሩ። በዚህ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ እያሉ ለአኗር መስጂድ ኢማም የታጩበት አጋጣሚ ተፈጠረ:: ስለዚህ አጋጣሚ የያኔው የአኗር መስጂድ አስተባባሪ ሀጂ አብዱረህማን ሸርፍ ሲናገሩ “ ከዕለታት አንድ ቀን እኚህ የተማሩ ሊቃውንት በአኗር መስጂድ ለስግደት በተሰየሙበት ወቅት ኢማሙን አስፈቅደው አንድ የቁራን ጥቅስ አንብበው በአማርኛ ይተረጉማሉ በዚህ ጊዜ መላውን የመስጅዱን ሕዝብ በአቀራረብና በአነጋገራቸው አስደመሙ:: ሕዝቡም ለምን እኚህ ሰው በዚህ መስጂድ ኢማም አይሆኑም የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፤ የመስጂዱ አመራሮችም የሕዝቡን ስሜት በመደገፋቸው ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ በምክትል ኢማምነት እንዲሰሩ ተመደቡ።
ይህ ኃላፊነታቸው እውቀታቸውን ለመግለጥና የእምነቱን ተከታይ በስፋት አግኝቶ ለማስተማር ዕድሉን ሰጣቸው:: የትምህርት አሰጣጣቸውም በአጭር ጊዜ ተቀባይነት አስገኘላቸው:: በመስጂዱና በመኖሪያ ቤታቸው ከሚሰጡት ትምህርት በተጨማሪ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የእምነቱን አመጣጥና ምንነት ይበልጥ እንዲያውቅ ለማድረግ በርካታ መፅሐፎች በአማርኛ በመፃፍ ለማበርከት አስቻላቸው።
በ1963 ዓ.ም የታላቁ አኗር መስጂድ ዋና ኢማም ሆነው የተሾሙት ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ከ1966ቱ አቢዮት መፈንዳት በኋላ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መሪ ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባኤ ወይም መጅሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቋቋም ከመሪዎች አንዱ ነበሩ።
ሀጂ መሐመድ ሳኒ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ተወካይና መሪ በሆኑበት በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ መጂሊስ እንዲመሰረት ያደረጉት ተጋድሎ ከፍተኛ ነበር። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መብትና ጥቅም በጋራ የሚያስከብር ተቋም ስላልነበር ሙስሊሞችን ወክሎ የሚናገር፣ የሀጂና ኡምራ ጉዞዎችን የሚያቀላጥፍ፣ መስጂዶችን የሚገነባና የሚያስተዳድር ተቋም ያስፈልግ ስለነበር ሀጂ መሐመድ ሳኒ ከሌሎች ኡለማዎች ጋር በመሆን ሙስሊሞች የራሳቸው ተቋም እንዲኖራቸው ለረዥም ጊዜ ይሟገቱ ነበር።
ከፍተኛ ብሔራዊ ስሜት የነበራቸው ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ፤ ሙስሊሙ ሕብረተሰብ የመብት ጥያቄ የማንሳቱን ያህል ብሔራዊ ግዴታውን የመወጣት ኃላፊነት እንዳለበት በማስገንዘብ በሀገሪቱ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ በያገባኛል ባይነት እንዲሳተፍና ብሔራዊ ስሜቱን እንዲያሳድግ በማስተማር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አብሯቸው ይሰሩ የነበሩና የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ሙስሊሙ ሕብረተሰብ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፍ በማስተማር ብቻ ሳይሆን፣ እርሳቸው በተለያዩ ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች በንቃት ተሳትፈዋል። በመሰረተ ትምህርት ማዕከላዊ ኮሚቴ ፣ በ1977 በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ደርግ በሰየመው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴና በብሔራዊ ሸንጎ በአባልነት ማገልገላቸው በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ሁለት ልጆቻቸው በደርግ ቀይ ሽብር ምክንያት የተገደሉባቸው ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ፤ የግል ፍላጐት ሳያሳዩ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ መብትና ጥቅም እንዲከበር ከወታደራዊ መንግሥት ደርግ ጋር በጋራ በመስራት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋም እንዲመሰረት መብታቸውም እንዲጠበቅ ከፍተኛ ትግል አድርገዋል።
ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሁለት ልጆቻቸውን ከገደለባቸው መንግሥት ጋር አብረው መስራታቸው የሚገርማቸውና እንዴት የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች አልጠፉም፤ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ግን ከደርግ ጋር መስራታቸው ታጋሽና አርቆ አሳቢ መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት ወዳጃቸው ሀጂ መሐመድ በሽር የደረሰባቸው በደልና እንግልት በቅርብ ያውቃሉና ጥያቄ ለሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ አቀረቡላቸው “ሀጂ ለምን በተጠሩበት ቦታ ይሄዳሉ የደርግ መንግሥት ሁለት ልጆችዎን ገድሎቦታል፤ እርሶ ላይም ቢሆን ያደረሰቦት በደል አይረሳዎትም:: እርሶ እኮ እዛ መገኘትዎን የሙስሊሙ መብት ተከብሯል የሚል የፖለቲካ መስበኪያ አድርጎ እየተጠቀመ ነው:: ስለዚህ ለምን ይሄዳሉ በማለት ሀጂ መሐመድ በሽር ይገስጿቸዋል። የሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ መልስ ግን አርቆ አሳቢነታቸውን በጉልህ ያሳየ ነበር። “ የእኔ ኃላፊነት ሀገራዊ ኃላፊነት ነው። ሙስሊሙን ወክዬ የተቀመጥኩ ሰው ነኝ፤ እኔ የማነሳው የቤተሰብ ጥያቄ መሆን የለበትም:: ምክንያቱም ስንት ያልተነሳና ያልተመለሰ ጥያቄ አለ፤ ይህ ጊዜ ያመጣው ችግር ነው። እኔ ልጆቼንም ቢገድሉ እኔም ብዋረድም፤ የእኔ ዓላማ የነገ የኢትዮጵያ ሙስሊም ዕድል በር መክፈት በመሆኑ ሁሉንም ነገር በትዕግሥት መቀበል አለብኝ’’ ነበር ያሉት።
የሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ ሌላኛው ትልቅ ሥራ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ገብተው ሰው አስተምረዋል። በሀይማኖት ትምህርታቸውም ተተኪ አፍርተዋል። በተለይ ከዘጠኝ በላይ የእስልምና ምሁራንን አስተምረው ያበቁ ሰው ናቸው:: በዘመናዊ ትምህርትም የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ፣ የዘመናዊ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ እንዲስፋፉ ያደረጉ፣ እስልምና እንዲስፋፋም የራሳቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ታላቅ ሥራ የሰሩ ሰው ናቸው።
በደቡብ ወሎ አስተዳደር በቃሎ አውራጃ አንቸሮ ከረቢቴ በተባለ ቀበሌ ከአባታቸው ከሀጂ ሀቢብ በሽርና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፋጡማ መሊክ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1906 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። ባለትዳርና የስምንት ልጆች አባት የነበሩት ሀጂ መሐመድ ሳኒ ሀቢብ በ75 ዓመታቸው በ1981 ዓ.ም ላይ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው። ሀጂ መሐመድ ሳኒ በሕይወት ዘመናቸው፤ ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ እውቀታቸውን አስተላልፈዋል:: በእምነቱ ተከታይ ዘንድ ከበሬታና ውዴታ አግኝተዋል::
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም