ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዝመራ ስብሰባው የበለጠ ውጤታማነት!

በሀገራችን በተለመደው የግብርና ሥራ አሁን ያለንበት ወቅት ለመጪዎቹ የበልግና የመኸር ግብርና ወቅቶች የማሳ ዝግጅት የሚጀመርበት ነው። ለበልጉ ወቅት ከዚህም ያለፈ የሚሠራበትም ነው። በተለይ እንዲህ እንዳሁኑ ዝናብ በሚኖርበት ጊዜ አርሶ አደሩ ለማሳ ዝግጅት ሥራው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ማሳው ከታረሰ የዝናቡን ውሃ በሚገባ በመያዝ መሬቱ እርጥበት እንዲኖረው ማድረግ ያስችላል።

ይህ ወቅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዝመራ ስብሰባ የሚካሄድበት ወሳኝ ወቅት ሆኗል። በአሁኑ ወቅትም የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ ስብሰባ በስፋት እየተካሄደ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል።

መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በ2016 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሦስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በስንዴ ዘር መሸፈን ተችሏል። ከዚህ ልማት 120 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዶ ሲሠራም ቆይቷል። የበጋ ስንዴ መስኖ ልማቱ ዘንድሮ በሁሉም ክልሎች ላይ እየተካሄደ ይገኛል።

ከግብርና ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዝመራ ስብሰባ አዝመራው አስቀድሞ ከደረሰበት የቆላማው አካባቢ በመነሳት በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። በደጋና በወይናደጋ አካባቢዎች የሚካሄደው የአዝመራ ስብሰባ ሥራም አሁን በአካባቢዎቹ እየጣለ ካለው ዝናብ አኳያ ሊዘገይ ቢችልም በተቀናጀ መልኩ በርብርብ የሚፈጸም ይሆናል።

በዚህ የአዝመራ ስብሰባ በ2016 ዓ/ም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከተሸፈነው ሦስት ሚሊየን ሄክታር ማሳ እስከ መጋቢት 23 ቀን 2016 ድረስ በአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የስንዴ አዝመራ ተሰብስቧል፤ ከዚህም ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ወደ ጎተራ ገብቷል።

የአዝመራ ስብሰባውም አርሶ አደሩን በማስተባበር በደቦና በመሳሰሉት እንዲሁም በኮምባይነር እየተፈጸመ ነው። በቀጣይም እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ አርሶ አደሩን፣ ሌሎች የግብርናው ዘርፍ ተዋንያንና የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ አካላት በማስተባበር የአዝመራ ስብሰባውን ለማጠናከር እየተሠራ ነው።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በቆላ፣ በደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎች ሁሉ በስፋት እንደመካሄዱ፣ በልማቱም ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር እንደመሸፈኑ የአዝመራ ስብሰባውም ከፍተኛ ርብርብ ማድረግን ይጠይቃል፤ በአዝመራ አሰባሰቡ እየታየ ያለው ርብርብና ውጤት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በአጠቃላይ እየተከናወነ ያለው ተግባር በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑን ያመለክታል።

ይህን የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ አሰባሰብ አቅም ገና ባልተሰበሰበው አዝመራ ላይም በማዋል በዕቅዱ የተያዘው የስንዴ ምርት ያለምንም ብክነት እንዲሰበሰብ አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል። በእቅድ ከተያዘው ከ120 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የተሰበሰበው ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ነው። እስከ አሁን አዝመራውን ለመሰብሰብ ጥቅም ላይ ውለው የአዝመራ አሰባሰቡን ውጤታማ ያደረጉትን አርሶ አደሩን የማስተባበርና ሜካናይዜሽንን በስፋት የመጠቀም ተሞክሮዎችን በቀሪው አዝመራ አሰባሰብ ላይ በሚገባ መተግበር ይገባል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከመምጣቱ በፊት ባለው ተሞክሮ መሠረት ለአዝመራ ስብሰባ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ የቆየው ለመኸር አዝመራ ብቻ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመኸር ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው በዘር የተሸፈነ ማሳ ያለበትና ከፍተኛ ምርት የሚጠበቅበት በመሆኑ ነው። ወቅቱ ደግሞ ዝናብ የሚጥልበት ከሆነ ርብርቡን ከፍተኛ እንዲሆን ሲያደርገው ኖሯል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በዘር የተሸፈነው ማሳ ብዛትና አሁን እየጣለ ያለው ዝናብም በቀጣይ መካሄድ ያለበትን የመስኖ ስንዴ አዝመራ የመሰብሰብ ርብርቡን ከእስከ አሁኑም በላይ ማድረግ አስፈላጊትነትን የግድ ያደርጉታል። ዝናቡ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎበት በለማ የበጋ መስኖ ስንዴ አዝመራ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳያስከትል መላውን ሕዝብ አስተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል።

በባሕላዊ መንገድ የሚካሄደውን የአዝመራ ስብሰባ በስፋትና በተቀናጀ አግባብ ማካሄዱ እንዳለ ሆኖ፣ በተለያየ አካባቢ የሚገኙ እንደ ኮምባይነር ያሉ የአዝመራ መሰብሰቢያና መውቂያ ማሸኖችን አስተባብሮና አቅናጅቶ መሥራትም ሌላው ሥራውን የበለጠ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም የሚያስችል ተግባር ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ በበጋ መስኖ ልማቱ ብቻ ሳይሆን፣ በመኸር አዝመራ ስብሰባ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ኮምባይነሮችን አሰባስቦ በማቀናጀት ውጤታማ ተግባር የተከናወነበትን ተሞክሮ መለስ ብሎ መመልከትና መተግበር ይገባል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሜካናይዜሽን በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል። አርሶ አደሮች በግልም በጋራም የእነዚህ ማሽነሪዎች ባለቤት የሆኑበት ሁኔታ ሰፊ ነው። የግሉ ዘርፍም ማሽነሪዎችን በኪራይ እያቀረበ ያለበት ሁኔታም እንዲሁ ተስፋፍቷል። እነዚህን አቅሞች አቀናጅቶ ሌት ተቀን በመሥራት ለእዚህ አዝመራ ስብሰባ ሥራ መጠቀም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል!

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You