ልማት… ሀብት ሳይባክን …

 

በመዲናችን አዲስ አበባ መንግሥት ‹‹የኮሪደር ልማት ብሎ›› በሰየመው ፕሮጀክት በከተማዋ የሚገኙ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎችንና የእግረኛ መንገዶችን የማስፋት ሥራ በስፋት እያከናወነ ይገኛል። በዚህ ልማት ከፒያሳ መገናኛ፣ ከፍላሚንጎ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ መገናኛ፣ ከሜክሲኮ ሳር ቤት፣ ከመገናኛ ሃያት አደባባይና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች ፈርሰው እንዲሰፉ እየተደረገ ነው።

በዚህ የተሽከርካሪዎችና የእግረኛ መንገዶችን የማስፋት ሂደት በመንገድ ዳርቻ ያሉ ያረጁ ቤቶች፣ ሕንፃዎች፣ ዛፎች፣ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ እንጨቶችና ሌሎችም እንዲነሱ ተደርገዋል፤ አሁንም እየተነሱ ነው። መንገዶችን ለግንባታ ሥራ በማፅዳት እንቅስቃሴ የሥልክና የመብራት፣ የውሃና ፍሳሽና የመንገድ ገንቢ ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ሆኖ ታይቷል።

በመንገድ ዳርቻ የነበሩ ነዋሪዎች፣ የሕንፃ ባለቤቶች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት፣የእምነት ተቋማትና ሌሎችም ለልማቱ ያሳዩት ትብብርም እጅግ የሚደነቅ ነው። መንገዱን የማስፋት ሥራ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለተሽከርካሪና ለእግረኞች ክፍት ለማድረግ በመንግሥት በኩል ሌት ተቀን እየተደረገ ያለው ጥረትም ይበል ያሰኛል። ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በርከት ያሉ ባለሙያዎች በፈረቃዎች ሌትም፤ ቀንም የግንባታ ሥራውን እያከናወኑ ይገኛሉ። ይህም በኢትዮጵያ የሥራ ባህል እየዳበረና እያደገ መምጣቱን ጠቋሚ ነው።

የኮሪደር ልማቱ ትችትም ወቀሳም ቀርቦበታል። ልማቱ ትችትም ወቀሳም ይቅረብበት ቁጥሩ እያደገ ለመጣው ሕዝብና ተሽከርካሪ ግን እጅግ አስፈላጊ የሆነና ለነገ የሚተውት ተግባር አይደለም። ዛሬ ላይ ጨክኖ ልማቱን ማስጀመር ካልተቻለ ነገ ከነገ ወዲያ እየጨመረ ከሚመጣው የግንባታ ዋጋ ጋር መጋፈጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ለልማቱ የሰፋ ጊዜ በተሰጠ ቁጥር የነዋሪው ችግር የዛኑ ያህል እያየለ ይሄዳል እንጂ ፈጽሞ አይቀንስም። ስለዚህ ዛሬን ጨክኖ ሰርቶና ትንሽ ተሰቃይቶ ነገን እፎይ ማለት ይሻላል።

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር አንፃርም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የማይታበል ሀቅ ነው። የከተማዋ ገፅታ ተቀየረ ማለት ደግሞ ለቱሪስት መዳረሽ ምቹ ስለሚያደርጋት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አንፃር ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በመንገዶች ዳርቻ የተለያዩ መናፈሻዎችና ፓርኮች መገንባታቸው አይቀሬ ነው። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችም እንደሚሰሩ ጥርጥር የለውም። በዚህ የግንባታ ሂደትም ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዚዊ የሥራ እድል መፈጠሩ አይቀርም። ይህም የኮሪደር ልማቱን ሌላኛው ትሩፋት ያደርገዋል።

በዚህ ኮሪደር ልማት የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች ስለሚሰፉ ለተሽከርካሪዎች የተሳለጠ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል። በተመሳሳይ ለእግረኞችም ሳይገፋፉ በነፃነት መንገዶችን ለመጠቀም ያግዛቸዋል። መንገዱ በሰፋ ቁጥር የትራፊክ ምልልሱም የዛኑ ያህል ስለሚፋጠን የሰዎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴን ያፋጥናል። ንግዱንም፤ ግብይቱንም ያሳልጣል። በዚህ ደረጃ መንገዶቹን ማስፋቱ በቀጣዮቹ ሃያና ሰላሳ ዓመታት እየጨመረ የሚመጣውን የሕዝብና የተሽከርካሪዎች ቁጥር ተሸክሞ ለማስተናገድ ጭምር ያግዛል።

የኮሪደር ልማቱ በበጎ የሚታይና የሚደገፍ ቢሆንም ታዲያ ልማቱን በማካሄድ ሂደት የሚታዩ ስህተቶችን መጠቆም ደግሞ እንደ አንድ ዜጋ የግድ ይላል። በዚህ ልማት በስፋት እየታየ ያለው ችግር የሀብት ብክነት ነው። የግንባታ ግብአቶች ምን ያህል እየተወደዱ እንደመጡ ሁሉም የሚመሰክረው ሀቅ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የመንገድ ጠርዞች እንደ አዲስ ተሰርተው የሚፈርሱበት ሁኔታ ይታያል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ እንደሚካሄድ እየታወቀ በመንግሥት በጀት እየተሰሩ ያሉ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተግባራት የሚውሉ አዲስ የተገነቡ ቤቶች እንደገና ሲፈርሱ ታይተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የእግረኛ መንገዶች ተሰርተው፤ ቴራዞ ሁሉ ተነጥፎላቸው ካበቃ በኋላ ዳግም የሚፈርሱበት ሁኔታ ተስተውሏል። የእግረኛ መንገዶቹ ከፈረሱም በኋላ የተነጠፈው ጠጠርና ቴራዞ ዳግሞ ጥቅም በማይሰጥ መልኩ ከተቆፈረ አፈር ጋር የመደባለቅና በአግባቡ ያለማንሳት ችግሮች ይታያሉ። ለአስፓልት ሥራ የሚያገለግል ጠጠር ከፈሰሰና ከተደለደለ በኋላ እንደገና ጠርጎ የማንሳት ችግርም ተስተውሏል።

ወቅቱ የዝናብ ጊዜ ከመሆኑ ጋር ለግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች በዝናብ ተጠርገው እንዳይወሰዱ በአግባቡ ጠብቆ የመያዝ ችግሮችም እየታዩ ነው። በተመሳሳይ የአስፓልት ጠርዞችን በግንባታ ማሽኖች የመሸራረፍም አጋጣሚዎች ይታያሉ። ይህ ደግሞ የተሸራረፉ የመንገድ ጠርዞችን ዳግም ለመስራት ቀላል የማይባል ወጪ የሚጠይቅ ነው።

ስለዚህ ይህ የሕዝብ ሀብት በመሆኑና ሲሚንቶ፣ አሸዋና ጠጠርን የመሰሉ የግንባታ ግብአቶች ዋጋ ጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የሚመጣ በመሆኑ እነዚህ ግብአቶች ሳይባክኑ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ግንባታውን የሚያካሂደው አካልም በየቀኑ የግንባታውን ሂደት መከታተልና ሀብት እንዳይባክን የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ይህ ሲሆን ነው ትክክለኛውን ጊዜ ተጠቅሞ በድፍረት የተገባበትን የኮሪደር ልማት ከውጤት ማድረስ የሚቻለው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You