የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ የ66 ኪሎ ግራም የቦክስ ተወዳዳሪዋ ቤተል ወልዴ ውጤታማ ለመሆን ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረባት። ባገኘችው ጠባብ ዕድል ተጠቅማ በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች በሴቶች ቦክስ ታሪክ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያን ለሀገሯ ማስመዝገብ ችላለች። በፍጻሜውም ጨዋታ የሞዛምቢክ አቻዋን ገጥማ 5 ለምንም በሆነ ውጤት ድል አድርጋ ታሪክ ሰርታለች። ከሳምንት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በተካሄደው የፕሮፌሽናልና ሰሚ ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድርም ተጋጣሚዋን ድል በማድረግ 100 ሺ ብር አሸንፋለች።
የቦክስ ስፖርትን ከመጀመሯ በፊት በሌሎች ስፖርቶች ውጤታማ በመሆን አስመስክራለች። ሀ ብላ መሥራት የጀመረችው የሰርከስ ስፖርት ሲሆን በመቀጠል የውሹ ስፖርትን ተቀላቅላ እየሠራች ወደ ቦክስ ስፖርት ቀልቧ ተስቧል። በውሹ ስፖርት ውጤት እያስመዘገበች የተመለከታት አሰልጣኟ ብቃቷን አስተውሎ እሷ ፍላጎቱ ባይኖራትም የቦክስ ስፖርትን እንድትጀምር ምክር ይለግሳት ነበር።
ቤተል የአሰልጣኛን ምክር ተቀብላ የቦክስ ስፖርት ብትጀምርም፣ እሷ በምትሳተፍበት 66 ኪሎ ግራም (ከባድ ሚዛን) ተወዳዳሪ በማጣት ለብዙ ዓመታት የውድድር እድልን ሳታገኝ ቆይታለች። ፈተናዎች ቢደራረቡባትም ከድል ሊያገዷት አልቻሉም።
በአሰልጣኟ ግፊትና ማባበል በደቡብ ክልል የዞኖች ማጣሪያ ውድድር ተሳትፎ በማድረግ የቦክስ ስፖርት ሕይወትን በወርቅ ሜዳልያ አንድ ብላ ጀምራለች። በቦክስ ውጤታማ እንድትሆን በውሹ ስፖርት የነበራት ልምድ ነገሮችን ሊያቀልላት ችሏል።
የቦክስ ስፖርት ውስጥ ከፕሮጀክት ጀምሮ 11 ዓመታትን አሳልፋለች። ወላይታ ዞንን ወክላ በዞን ውድድሮች፣ በኋላም ደቡብ ክልልን ወክላ በኢትዮጵያ ቻምፒዮና ተጫውታለች። በወቅቱ በነበረ ምልመላ ወርቅ በማስመዝገብ አካዳሚ መግባት ችላለች። የአካዳሚ ቆይታዋን ከጨረሰች በኋላም ኒያላ ቦክስ ክለብን ተቀላቅላ ለሶስት ዓመታት ቆይታ ከዛም የአዲስ አበባ ቦክስ ክለብ ተፋላሚ ሆናለች።
አሁን ውጤታማ የሆነችበትን ቦክስ ጨምሮ በቴኳንዶ፣ ውሹ፣ ኪክ ቦክስና ሞይንታይ ስፖርቶች ቀበቶና 68 የወርቆ ሜዳልያዎችን ማጥለቅ ችላለች። ሁሉም ስፖርቶች ላይ ስኬታማ እንደነበረችና በአንድ አጋጣሚ በቦክስ ኪሎ ቀንሳ ተጫውታ ከመሸነፍ ውጭ የወርቅ ሜዳልያና የቀበቶ ባለቤት እንደሆነች ትናገራለች።
ቤተል በሌሎቹ ስፖርቶች ውጤታማ መሆኗ ለቦክስ ስፖርት ውጤታማነት ትልቅ አቅም እንደሆናት ታምናለች። ወላጅ አባቷን በልጅነቷ ያጣችው ብርቱዋ ቦክስኛ የእናቷ ድጋፍ ልዩ እንደሆነና ለውጤት እንድትበቃም ረድቷታል።
ከሀገር ወጥታ የመወዳደር ብቃት ቢኖራትም ብዙ እድሎች አምልጧታል። ይህም የሆነው እሷ የከባድ ሚዛን ተወዳዳሪ በመሆኗና ሌላ የከባድ ሚዛን ተወዳዳሪ ቦክስኛ ባለመኖሩ ለመምረጥ አስቸጋሪ በመሆኑ ነበር። ቦክሰኞች የሚከፈላቸው ክፍያ አናሳ በመሆኑና ከስፖርቱ የሚገኝ የድካም ዋጋ እምብዛም በመሆኑ ተስፋ በመቁረጥ ከስፖርቱ ስለሚወጡ በሚፈለገው ሚዛን ቦክሰኞችን ማግኘት አይቻልም።
ቦክሰኛዋ አድካሚውን የቦክስ ልምምድ አድርጋ ከጨረሰች በኋላ በከባድ ሚዛን ተጨዋች ማጣቱ ብዙ ፈትኗታል። ይህ ደግሞ ካላት ብቃት አኳያ በብሔራዊ ቡድን እድል አግኝታ እንዳትወዳደርና ህልሟን እንዳትኖር እንዳደረጋት በቁጭት ትናገራለች።
ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ በሪንግ ውስጥ የእሷን ብቃት መለካት ግዴታ በመሆኑና ውድድር በማጣት መጥፎ ስሜት ውስጥ የገባችበትም ወቅት ቢኖርም አንድ ቀን እንደሚሳካ ተስፋ ነበራት። የውድድር ማጣትንና ሌሎች ጫናዎችን ተቋቁማ ለውጤት ልትበቃ ችላለች። ልምምዷን ሳታቋርጥ ለኦሊምፒክ ማጣሪያ እድሏን ለመሞከር ደብዳቤ ጽፋ ወደ ፌዴሬሽን ያመራችው ቤተል፣ በስፖርቱ የቆየችበትን ረጅም ጊዜና ድካም ተመልክተው በብሔራዊ ቡድን የመሳተፍ እድልን በልዩ ሁኔታ ብሔራዊ ቡድኑን ታቅፋ ለውጤት እንድትበቃ አድርጓታል።
የልፋቷን ዋጋ ባገኘችው ውጤት እንደተካሰችና ተጫዋች ለማግኘት ኪሎ በማውረድ ትጨወት እንደነበር የምታስታውሰው ቤተል፣ ለዚህ የማሸነፍ ስነ ልቦናን መላበስ ዋንኛ ማሳሪያዋ መሆኑን ታስረዳለች። ለውድድሩ የነበረው የመዘጋጃ ጊዜ አጭር ቢሆንም የተሰጠው የተመጠነ ስልጠናና የልዑካን ቡድኑ ጥሩ መንፈስ ለድሉ አስተዋጽኦ አድርጓል ትላለች።
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ስታደርግ የአፍሪካ ጨዋታዎች የመጀመሪያ እንደመሆኑ እንግዳ ቢሆንባትም እሷ ትኩረትና ሃሳባን ፍልሚያዋ ላይ ብቻ እንዳደረገች ታስታውሳለች። በዚህም ረጅም ዓመት በቦክስ ውስጥ የቆየችበትን ልምድ ተጠቅማ በራሷ መንገድ ለመጫወት ወስና ወደ መፋለሚያ ሪንጉ ገብታለች። የነበራትን የማሸነፍ አቅምንና የተሰጣትን ጠባብ እድል ተጠቅማ ለነገ እድል መክፈት እንዳለባት አስባ በትልቅ ሞራል ድልን ተቀዳጅታለች።
የቦክስ ስፖርት በሕይወቷም ላይ ጠንካራ እንድትሆን በማድረጉ ሰዎች ከሚሏት ነገር በላይ በመሆኑ ፈተናዎችን ተቋቁማ ለውጤት ልትበቃ ችላለች። ‹‹ሴት ልጅ የትኛውንም ተጽዕኖ ተቋቁማ ማንኛውንም ነገር ማሳካት እንደምትችል እኔ ምስክር ነኝ›› ስትልም ተናግራለች።
የጥንካሬ ተምሳሌቷ እንስት ቦክሰኛ፣ የታላቁ ቦክሰኛ ማሃመድ አሊ ሴት ልጅ የሆነችው ላኢላ አሊም አድናቂ ናት። ፍቅረማርያም ያደሳና ሌሎች የሀገር ውስጥ ቦክሰኞችን አርአያ በማድረግ ለውጤት መብቃትን የምትናገረው ቤተል፣ ከልጅነት ጀምሮ ህልሟ በሆነው የኦሊምፒክ መድረክ ተሳትፋ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክራ እየሠራች እንደምትገኝም ጠቁማለች።
ዓለማሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም