የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ በዓለም አቀፍ መስፈርቶች ላይ በመመስረት ለእንግዶች እንዲሁም ጎብኚዎች መረጃ የሚሰጥበት ዘይቤ ነው። ማንኛውም ሀገር ላይ የሚገኝ አንድ ሆቴል ባህሪ፣ ለእንግዶች የሚሰጠውን ምቾት፣ ከደህንነት ጋር ያለውን ጥብቅ መርህ እና የንፅህና ደረጃዎች ከሚይዘው የኮከብ ደረጃ ጋር በቀጥታ ይገናኛል። አገልግሎት ፈላጊዎችም ከዚያ ሆቴል ምን ማግኘት እንደሚችሉ አስቀድመው ለማወቅ ይረዳቸዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በአንድ ሀገር ውስጥ ብዛት ያላቸው ጥራታቸውን የጠበቁና መመዘኛ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሆቴሎች መኖራቸው የቱሪዝም አቅምን ለማሳደግ፣ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመርና በብዙሃን ተመራጭ ለመሆን ያግዛል።
በቅርቡ የቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ያስቀመጣቸውን አስገዳጅ መስፈርቶች ላሟሉ 31 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ውጤታቸውን ይፋ አድርጓል። በ2014 እና 2015 ዓ.ም ምዘና ከተደረገላቸው 64 ሆቴሎች መካከል ሰባቱ ባለ አራት ኮከብነት ደረጃ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ዘጠኝ ሆቴሎች ደግሞ የሦስት ኮከብ ደረጃን ማግኘታቸውን አሳውቋል። አምስት ሆቴሎች ደግሞ የሁለት ኮከብ እና ስምንት ሆቴሎች ባለ አንድ ኮከብነት ደረጃ የተሰጣቸው መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጾ ሁለት ሆቴሎች ደግሞ ከደረጃ በታች መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የኮከብ ደረጃው ይፋ በሆነበት ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት፤ ምደባው ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ በቅርበት ካሉ ተፎካካሪ ሀገራት ሆቴሎች ጋር ያላቸውን አቅም በማሳየት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ተናግረው ነበር።
የዝግጅት ክፍላችን የኮከብ ደረጃ ምደባን (star rating) አስመልክቶ ያነጋገራቸው በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት የሠሩት ባለሙያና አሁን ደግሞ በደረጃ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የተመረጡት የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ እንዳሉት፤ በዓለማችን ላይ በአገልግሎት ዘርፍ ሰዎች የሚዝናኑባቸው ካፌዎች፣ ሆቴሎች፣ ላውንጆች፣ ሪዞርቶች የየራሳቸው ደረጃ አላቸው።
በተለያዩ ሀገራት ለሆቴል ደረጃዎች እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ይህም የተለመደ አሠራር መሆኑን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህን መሰል የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ የቅርብ ጊዜ ታሪክ መሆኑን አመልክተው፣ ከዚህ ቀደመ ለሁለት ጊዜያት ብቻ የምደባ ሥራው መከናወኑን ተናግረዋል። እነዚህም የተካሄዱት በ2007 እና በ2011 ዓ.ም መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹የመጀመሪያዎቹ የኮከብ ደረጃ ምደባዎች ከተካሄዱ በኋላ በድጋሚ ለመስጠት ረጅም ጊዜያትን ወስዷል›› የሚሉት የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንቱ፤ ይህንን ያህል ጊዜ ለመቆየቱ ምክንያቶቹ የኮቪድ ወረርሽኝና በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭት መሆናቸውን ይገልጻሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በተናጠል አንዳንድ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ውጤታቸው ይወጣ እንደነበርም ነው ያመለከቱት። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ለአገልግሎት ዘርፉ የኮከብ ደረጃ ምደባ በመስፈርቶች ምዘና መስጠት መጀመሯ ተገቢና የወቅቱ አስፈላጊ ርምጃ መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ አሸናፊ እንዳብራሩት፤ ለሆቴሎች የኮከብም ምደባ (star rating) ሲካሄድ ወደ አስር መስፈርቶች ገምት ውስጥ ይገባሉ። የመኝታ ክፍላቸው የተሟላ መሆን፣ አጠቃላይ ፅዳት፣ የደህንነት፣ የሠራተኞች እና የልዩ ልዩ የሆቴል አገልግሎቶች አቅም ደረጃ ከግምት ውስጥ ከሚገቡ ነጥቦች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
እነዚህ መስፈርቶች በዋናነት የጎብኚዎችን፣ የደንበኞችንና በሆቴሉ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ሁሉ ያላቸውን ምቾትና በቀዳሚነት ከግምት ውስጥ ያስገባሉ። በእነዚህ መስፈርቶች መሠረት ሆቴሎች ከኮከብ አንድ ጀምሮ በተከታታይ ያሉ ደረጃዎች ይሰጧቸዋል። በኢትዮጵያም የቱሪዝም ሚኒስቴር በዚህ መንገድ የሆቴሎችን መደባ አድርጓል።
‹‹አንድ ሆቴል ደረጃ ቢኖረውም ባይኖረውም ደንበኞቹን በጥራትና በጥሩ መስተንግዶ ማገልገል ይኖርበታል›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ ብዙ ሆቴሎች ገና ከጅምሩ የኮከብ ምደባ ይኖራቸዋል ወይም አይኖራቸውም የሚለው ተረጋግጦ ወደ ሂደት እንደሚገባ ይናገራሉ። ባለኮከብ ሆቴሎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አውጥተውና የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት ይዘው እንደሚገቡም ነው ያብራሩት። ሆኖም ማንኛውም ሆቴል አገልግሎቱን በጥራት የሚሰጥ አቋም ኖሮት ሊሰራ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፈው ሳምንት በርከት ያሉ ሆቴሎችን በመገምገም የሆቴሎች የኮኮብ ምደባ ተደርጓል። ሂደቱ ሙያን የተከተለና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። የቱሪዝም ሚኒስቴር በየጊዜው የግምገማ ነጥቦችን በማውጣት በአገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚገኙትን ሆቴሎች ይገመግማል። ከደረጃ ምደባው በፊት ሆቴሎቹ ያሉባቸውን ክፍተቶች በማሳየት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ጥቆማም ይሰጣል። ይህ ሂደት ከታለፈ በኋላ ነው ወደ ደረጃ ምደባ የሚገባው።
‹‹የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ሙሉ ለሙሉ ዓለም አቀፍ ደረጃን ይከተላል ማለት አይቻልም›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ በአንዳንድ ሀገራት ያሉ ትላልቅና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የሌላቸውን የኮከብ ምደባ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚያ ያነሰ የጥራት ደረጃ ላይ ለሚገኙት ሲሰጥ ይታያል ይላሉ። አሰጣጡ ልምዱ እየዳበረ ሲሄድ እንደሚሻሻል ገልጸው፣ ይህንን ለማሻሻል የቱሪዝም ሚኒስቴር በግምገማና በተከታታይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ለሆቴል ባለንብረቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እየሠራ መሆኑን ያብራራሉ።
ዓለም አቀፍ የኮከብ ደረጃ ምደባን ለማግኘት ሆቴሎች መስፈርቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ማሟላት ይኖርባቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ሆቴሎች ውስኖቹ በእነዚህ መስፈርቶች ላይ ይሠራሉ። በምሳሌነት ባሳለፍነው ሳምንት 60 ከሚደርሱ ሆቴሎች ለመጀመሪያ ደረጃ ምደባው ግምገማ የደረሱት 31 የሚሆኑት ናቸው። ከ31 ሆቴሎቹ ደግሞ ሁለቱ ከደረጃ በታች መሆናቸው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይፋ ሆኖ ከምደባው ዝርዝር መውጣታቸውን አቶ አሸናፊ ይገልፃሉ።
ከፍተኛ የሆነ የኮከብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆቴሎች በያዙት ምደባ የማይቀጥሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ የሚሰጡት አገልግሎት በየተወሰኑ ዓመታት ዳግም እየተገመገመ ምደባው ሊስተካከል የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ይናገራሉ። በውጤቱም ጥራታቸው የሚወርድ ምደባው ሆቴሎች ዝቅ የሚሉበት ደረጃቸውን ያሻሽሉት ደግሞ ከፍ የሚሉበት እድል እንደሚፈጥር ይገልፃሉ። ሆቴሎችም የውድድር አቅም እንዲፈጥሩ፣ አገልግሎታቸውን በየጊዜው እንዲያሻሽሉ እድል እንደሚፈጥር ያስረዳሉ። የቱሪዝም ሚኒስቴርም በየሶስት ዓመት ልዩነቱ ግምገማ ለማድረግ ማቀዱ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ሆቴሎች ዓለም አቀፍ የኮከብ ደረጃ ኖራቸው ማለት በብዙ ነገር ተጠቃሚ ያደርገናል›› የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንግዶች አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልጉ ሆቴሎች ያላቸውን የኮከብ ደረጃ እንደሚያጣሩ ይናገራል። በመሆኑም እዚህ ደረጃ ውስጥ ያሉ ሆቴሎች መኖራቸው ደንበኞች ለደህንነታቸው ስጋት ሳይገባቸው ግልጋሎት ስለሚያገኙ በብዛት ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ይገልፃሉ። እንደ ሀገርም የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያድግ የሆስፒታሊቲ ዘርፉ የጥራት ደረጃም የተሻሻለ እንዲሆን ትልቅ እድል እንደሆነ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትንም ቱሪስቶችን ለመሳብ ትወዳደራለች የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ በአምስት፣ አራት፣ ሦስት እና ሁለት ኮከብ ደረጃ በብዛት በአንድ ሀገር ውስጥ ሆቴሎች መኖራቸው ጎብኚዎችንም ለመሳብ የሆስፒታሊቲ ዘርፉን ለማላቅ ያግዛል ሲሉ ያብራራሉ።
አቶ አሸናፊ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ከ360 ወይም 370 የማይበልጡ ሆቴሎች በኮከብ ደረጃ ውስጥ ይገኛሉ። ይህንን ቁጥር በየጊዜው ማሳደግ ሲቻል የቱሪስት ፍሰቱን መጨመርና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራል። በተለይ በማይስ ቱሪዝም ትላልቅ ኤግዚቢሽኖች፣ ስብሰባዎች እንዲሁም መሰል ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ሲኖሩ በቀላሉ ጨረታውን ለማሸነፍና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተፅእኖ ማሳደር የሚችል አቅም ለመፍጠር ያግዛል።
በዘንድሮው የቱሪዝም ሚነስቴር የኮከብ ደረጃ ምደባ ላይ ቅሬታዎች መቅረባቸውን የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፤ ከተለያዩ የዘርፉ ሙያዎች የተውጣጡ አባላት ያሉት ገለልተኛ ኮሚቴ መቋቋሙን ይናገራሉ። እርሳቸውም በዚህ ኮሚቴ ውስጥ አባል እንደሆኑ ተናግረው፣ ቅሬታዎቹን ለመመልከት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ በበባህሪው አጨቃጫቂ መሆኑን በመግለፅም ቅሬታዎችን ከመስፈርቶች አኳያ ለመፍታት እንደሚሞክር ተናግረዋል። ብዙ የሆቴል ባለንብረቶች በባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ቢመደብላቸው ፍላጎታቸው ነው በማለት የሚያነሱት አቶ አሸናፊ፣ የቅሬታውን ተገቢነት ከመስፈርቱ አንፃር ማጣራት ግን ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹የቀረቡ ቅሬታዎች አሊያም ትችቶች ሁሉ እውነትነት ላይኖራቸው ይችላል›› ሲሉም ጠቅሰው፣ በምደባ ወቅት ስህተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉም ይገልፃሉ። የገለልተኛ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ቀዳሚ ኃላፊነት ከመስፈርቶቹ አንፃር ለሆቴሎቹ የተሰጡት የኮከብ ደረጃዎች ተገቢነትን በሚቀርበው ቅሬታ ላይ ተመስርቶ ማጣራት እና መፍትሔ መስጠት መሆኑን ያስረዳሉ።
የሆቴሎች የኮከብ ምደባ የተካሄደው ከሳምንት በፊት ነው የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ በምደባው ያልተስማሙ ባለንብረቶች ቅሬታቸውን ለኮሚቴው እያስገቡ መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህ እልባት ለመስጠት ኮሚቴው ሆቴሎቹ የሚገኙባቸው ቦታዎች በመሄድ የአካል ምልከታና ግምገማ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ። በወጤቶቹ መሠረትም ምደባውን ካደረገው የቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመቀመጥ ችግሮች ያሉባቸውን ውሳኔዎች ለመመልከትና ውሳኔ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ አሸናፊ የቀድሞው አሠራር ደረጃ መዳቢዎቹ ቀድመው ሆቴሎቹን እንዲያውቁ እድል የሚፈጥር እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ አሠራር ለድርድርና ተገቢ ላልሆነ አሠራር ክፍተት የሚፈጥር እንደነበር ያስረዳሉ። አሁን ግን ይህ አካሄድ መቀየሩ ጠቅሰው፣ የቴክኒክ ቡድኑ እስከ ግምገማ ቀኑ ድረስ የት ቦታ እንደሚመደብ እንደማያውቅ ይገልፃሉ። ውሳኔውም ከመስፈርት ውጭ ሊደረግ የሚችል የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ሂደትን እንደሚያስቀር አስረድተዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም