ትላንት በጉርምስናና ጉልምስና እድሜያቸው ላይ ሀገራቸውን በብዙ ያገለገሉ ጀግኖች ዛሬ ላይ ቀን ዘምበል ሲልባቸው፤ ጎንበስ ቀና ይሉላቸው የነበሩ ሁሉ የት እንዳሉ እንኳን አስታውሰዋቸው አያውቁም። ጊዜ እራሱ አድሎ የሚፈጽም እስከሚመሰል ድረስ ለሀገር ለወገን ብዙ የዋሉ ሰዎች ሳይከበሩ እሱ እንኳን ቀርቶ አስፈላጊ ነገር ሳይሟላላቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እድሜያቸውን ሲጨርሱ ማየት አሳዛኝ ነው። በተለይ እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች ሀገርና ሕዝብ ዘንድ ዋጋ ቢስ ሆነው ተስፋ ሲቆርጡ ከመመልከት የከፋ ነገር የለም።
የዛሬ የሕይወት ገጽታ ዓምዳችን ባለታሪክ በእውቀት የገፉ፤ ለትልልቅ ሀገራዊ ኃላፊነቶች ታጭተው በብቃት የተወጡ ናቸው። ሮጠው መሥራት በሥራቸው ያሉትንም በሚገባ መምራት በሚችሉበት ቁመናና የጤና ሁኔታ ላይ ሆነውም ሀገራቸውን በብዙ ያገለገሉ ጀግና ነበሩ። ባገለገሉባቸው ዘመናትም ለብዙዎች ብርሃን መሆን ችለው ነበር። በተለይም እንደ ሀገር ገዝፈን እንታይበት በነበረው ባህር ኃይል ውስጥ የወጣትነት እድሜያቸውን አሳልፈዋል፤ ማሳለፍም ብቻ ሳይሆን ለሀገር አለኝታ የሆኑ ተግባራትንም ፈጽመዋል።
በባህር ኃይል ውስጥ በተሰማሩበት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብዙ የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ካልመጡ ሊሰሩ አይችሉም የተባሉ ቴክኒካል ችግሮችን በአስተማማኙ የሙያ ብቃታቸው ሰርተውና ችግሮቹን ፈተው ለተገቢው አላማ እንዲውሉም ማድረግ የቻሉ ናቸው። በዚህም በቅርብም በሩቅም አለቆቻቸው የታመነባቸውና ምስጋናን ያተረፉ ባለሙያ ነበሩ።
ዛሬ ላይ እድሜያቸው ገፍቶ ከሁሉም በላይ ደግሞ ማጣትና የጤና መጓደል ተደራርበውባቸው የሰው እጅ ያዩ ዘንድ ተገደዋል። ይህም ቢሆን ገን ለሀገራቸው የዋሉት ውለታ ምንጊዜ የሚነገር እና ከመቃብራቸው በላይም በጉልህ የሚጻፍ የአንጸባራቂ ታሪክ ባለቤት ናቸው። እኛም ዛሬ በእንግድነት ስናቀርባቸው ተዝቆ ከማያልቀው የሥራና የሕይወት ልምዳቸው ላይ ጥቂቷን ጨልፈ ን ነው።
ማስተር ቺፍ ዓለም ገብረሥላሴ የተወለዱት ሰባት ቤት ጉራጌ ውስጥ በ1933 ዓ.ም ነው። በወቅቱም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ከብት በማገድ በእድሜያቸው ሊሰሯቸው የሚችሉ ሥራዎችን ሁሉ በማከናወን እስከ ስምንት ዓመታቸው ድረስ በትውልድ መንደራቸው የመኖርን እድል አግኝተዋል። ከስምንት ዓመታቸው በኋላ ግን አዲስ አበባ ከተማ በነበረው ወንድማቸው አማካይነት ዘመናዊ ትምህርትን ተምረው ሀገር ወገናቸውን ይጠቅሙ ዘንድ ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ አደረጉ።
“…….በገጠር ከእናትና አባቴ ጋር ስኖር የማደርገው ነገር ቢኖር ከብቶች ማገድና በምችለው አቅም ቤተሰቤን ማገልገል ብቻ ነው። ኋላ ላይ ግን ታላቅ ወንድሜ አስተምርሃለሁ በማለቱ ምክንያት የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ አዲስ አበባ ከተማ መጣሁና ትምህርት ቤት ገባሁ” ይላሉ።
በቄስ ትምህርት ቤት የፊደልን ገበታ የተዋወቁት ማስተር ቺፍ ዓለም በሚገባ ፊደሎቹን እየቆጠሩ ማንበብና መጻፍን እየተለማመዱ ሂሳብ ስሌትንም እየሞከሩ ቆዩ። ከዛም የቄስ ትምህርቱ ሲያልቅ አልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ በሚባል ትምህርት ቤት በመግባት ለሶስት ወራት ያህል ተምረዋል፤ ነገር ግን እንግሊዘኛ ቢማር ነው የሚጠቅመው በመባሉ ምክንያት ወደ ደጃች ገብረማርያም ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ።
“…….መጀመሪያ ቄስ ትምህርት ቤት ነው የገባሁት እዛም አማርኛ ነበር የተማርኩት። በጣም ደስ ብሎኝ ያሳለፍኩት የትምህርት ጊዜዬም እሱ ነው፤ ከዛም ወደተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ለመከታተል በቃሁ” ይላሉ።
ማስተር ቺፍ በወቅቱ ትምህርት ቤት ይቀያይሩ እንጂ ያን ያህል ትምህርት ይጠቅመኛል ብለው የሚያስቡና የሚማሩ እንዳልነበሩ ይናገራሉ፤ ያም ቢሆን ግን ትምህርት ቤት ከመሄድ አልቀሩም። ነገር ግን ትምህርት ቤት መቆየታቸው ያን ያህል የተፈለገውን ለውጥ የሚያመጣ ያልመሰላቸው ወንድማቸው ጎበዝ ተማሪ ይሆኑላቸው ዘንድ በመሻት በቅሎ ቤት አጠገብ ወደሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አደረጓቸው።
እውነትም የማስተር ቺፍ ዓለም የትምህርት አቀባበል በአንድ ጊዜ ተቀየረ። ትምህርት ወዳድና በቀላሉ ትምህርትን የሚቀበሉ ከጓደኞቻቸው ጋር በእውቀት የሚፎካከሩ በጠቅላላው ጥሩ የሚባሉ ዓይነት ተማሪ ለመሆን ቻሉ። ትምህርት ቤት ውስጥ ከአንዲት አሜሪካዊት መምህርት ጋር በመገናኘታቸው ትምህርትን በጣም እየወደዱ እንደመጡም ራሳቸው ይናገራሉ።
“…….በወቅቱ አሜሪካዊቷ መምህርት በጣም ጎበዝ ከመሆኗና ስታስረዳም ደስ ትል ስለነበር ወደትምህርት ሳበችኝ። ከዛ ሁሉ በላይ ደግሞ በተማሪዎች መካከል ጤናማ የሆነ የእውቀትና የውጤት ፉክክር እንዲኖር በየሳምንቱ ምርጥ ተማሪን ታወጣና ታበረታታ ስለነበር እኔም ከማን አንሼ በሚል መንፈስ በጣም አጠና በክፍል ውስጥም የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ እከታተል ነበር። በጠቅላላው ትጉህ ተማሪ ለመሆን ስለበቃሁ ቢያንስ ከቀዳሚዎቹ እንኳን ባልሆንም መካከለኛ ተማሪ ለመሆን ግን ችያለሁ” ይላሉ።
በዚህ ሁኔታ የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ ያመሩት ባህር ኃይልን መቀላቀል ነበር። “…ትምህርቴን አቋርጬ ባህር ኃይል የሄድኩበት ዋናም ምክንያት አንደኛ የደሃ ልጅ መሆኔ ነው፤ ቀጥሎም እያደኩ ነው፤ ግን ከሁሉም በላይ ብዙ ልጆች ባሉበት ቤት ውስጥ በድህነት መኖርን ለማምለጥ የተጠቀምኩበት ዘዴ ነው ብሎ መውሰድ ይሻላል” ይላሉ።
እሳቸው ባህር ኃይል የገቡት በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤታቸው ነበር። አስፈላጊውን ወታደራዊና ባህር ኃይል ለመሆን የሚያበቃውንም ስልጠና በሚገባ አጠናቀው ሥራቸውን እየሠሩ ኑሮን በድል አድራጊነት አሸንፈው ያሰቡበት መድረስ ባይችሉም የወር ደመወዝ ያላቸው ሳይቸገሩ በልተው ጠጥተው የሚያድሩ ለመሆን ግን አስችሏቸዋል።
እሳቸውና ጓደኞቻቸው ባህር ኃይልን ከተቀላቀሉ በኋላ ባህር ኃይል ለመሆን የሚያስቡ ወጣቶች የግድ አስረኛ ክፍልና ከዛ በላይ ያለ የትምህርት ማስረጃን ማቅረብ ነበረባቸው ፤ ያንን የያዙ በርካታ ወጣቶች ባህር ኃይሉንም ተቀላቀሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለማስተር ቺፍ ዓለም ምቾት አልሰጣቸውም። ምክንያቱም እሳቸው እዛው ላይ ትምህርታቸውን ሳያሻሽሉ ከቆዩ ከኋላቸው የመጡ ሰዎች አዛዦቻቸው ሊሆኑ ነው፤ ይህንን ለማስቀረት መማር እንዳለባቸው ይወስናሉ፤ በወቅቱ ግን ወታደር ቤት ባስፈለገ ጊዜ ልማር፤ ይሄንን ላድርግ፤ ያንን እፈልጋለሁ የሚባልበት ስላይደለ ማስተር ቺፍ ተማር የሚለውን ፍቃድ ከአለቆቻቸው እስከሚሰጣቸው ድረስ ብዙ እልህ አስጨራሽ ትግሎች ማድረግ ውጤቱንም ከፍ ባለ ትዕግስት መጠበቅ ነበረባቸው።
የመማር ርሃብ የያዘቻው ማስተር ቺፍ ከብዙ እልህ አስጨራሽ ትዕግሥት እንዲሁም ከአስመራ አዲስ አበባ ድረስ በደረሰ የጽሑፍና የቃል ንግግር ውይይት በኋላ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን እዛው አስመራ ሆነው እንዲከታተሉ በበላይ ሹማምንቱ ተፈቀደላቸው። ይህንን የሰሙ ቀን ደስታቸውን ዛሬ ላይ ቆመው ሲያስቡት እንባ በዓይናቸው ሙልት ይላል። ደስታቸውን ይዘው ብረትም እንደጋለ የሚለውን ተረትና ምሳሌ እየተናገሩ በፍጥነት ትምህርታቸውን ለመጀመር ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ተመዘገቡ።
“……በእውነት የእዛን ቀን የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ራሱ በጣም ይከብደኛል። ዛሬም ድረስ ሳስበው ሰውነቴ ይረበሻል። ከተፈቀደልኝ በኋላ ለአራት ዓመታት ያህል ደመወዝ እየተከፈለኝ በቤቴ እያደርኩ ብቻ ምን አለፋሽ ዘና ብዬ ትምህርቴን በከፍተኛ ፍላጎት ተምሬ በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ቻልኩ”ይላሉ።
በወቅቱ የአራት ዓመት ትምህርታቸውን ከቀለም ትምህርት ባሻገር ሙያዊ ወይም ቴክኒካል እውቀትንም የመማር እድል አግኝተው ስለነበር ልክ 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ በዲፕሎማ የመመረቅ እድልን አግኝተው ነበር። ይህ ዲፕሎማ ደግሞ በቴክኒሻንነት የሥራ ዘርፍ ላይ እንዲመደቡ አስቻላቸው። ማስተር ቺፍ ዓለምም አሁን የልባቸው ደረሰ። ከውትድርናው ዘርፍ ወጥተው ወደ ቴክኒካል ባለሙያነት ተሸጋገሩ።
“…….በወቅቱ 12ኛ ክፍል ትምህርቴን በቀለምም በቴክኒክም አጠናቅቄ ዲፕሎማ ይዤ ነው የተመለስኩት። ይህ ደግሞ የሥራ መስኬን እንድቀይር በአየር ኃይል ውስጥም ተፈላጊ ባለሙያ እንድሆን አስችሎኝ ነበር። በወቅቱ የነበረው የእኔ የሥራ ድርሻም ጀነሬተሮች እንዲሁም በአሰብና ምጽዋ ላይ የነበሩንን የሞተር ጀልባዎችና መርከቦች ሲበላሹ መጠገን ነበር” በማለት ይናጋራሉ።
በወቅቱም ከምጽዋ አሰብ እንዲሁም ወደ ጦርነቱ ቦታ ምግብ ቁስለኛ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች
የሚጓጓዙት በመርከብ ነበር። በአንድ ወቅት አንዲት መርከብ በሥራ ላይ እንዳለች ሞተሯ ተቃጠለ፤ በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ መደናገጥ ተፈጠረ። የመደናገጡ ዋናው ምክንያት ደግሞ ሞተሩን ሊሰራ የሚችል ባለሙያ በሥፍራው አለመኖሩ ነበር።
“……ይህች ቀኝ እጅ የሆነች መርከብ ባልታሰበ ሁኔታ ሞተሯ ተቃጠለ። በዚህ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያው ተረበሸ ፤ አዛዦቹ ሁሉ ተደናገጡ፤ ምጽዋ ያሉትም አስመራ ቴክኒሻን ስላላ የጠየቀውን ገንዘብ ከፍላችሁ በአስቸኳይ አሰሩ የሚል ትዕዛዝ ተላለፈ። ነገር ግን በወቅቱ አስመራ ላይ የነበሩት ጣሊያኖች ሀገራቸው ገብተዋል ፤ በጠቅላላው የመርከቧን ሞተር ጠግኖ ወደ ስር የሚያስገባ አልተገኘም “ ይላሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ማስተር ቺፍ ዓለም ምጽዋ ባህር ኃይል ውስጥ ብዙም እውቅና ሳይሰጣቸው ተቋሙ ላይ ያሉ ሥራዎችን ብቻ እየሠሩ ቁጭ ብለዋል፤ በወቅቱ ግን የሚሰሩበት የኤሌክትሪክ ክፍል ውስጥ በርካታ ባለሙያዎች ያሉ ቢሆንም ያን ያህል አመርቂ ሥራን የሚሰሩ አልነበሩም። እሳቸውም ከዛ በፊት የሰሯቸው አመርቂ ሥራዎች በመኖሩ እስኪ እሱ ይሥራው ብለው አዲስ አበባና አስመራ ያሉት አለቆቻቸው ተነጋግረው ወሰኑ።
እሳቸውም ትዕዛዙን በመቀበል መጀመሪያ የሞተር ክፍሉ በስዕል ቁጭ ካደረጉት በኋላ ከለአለቃቸው በማሳየት ልሠራው እችላለሁ የሚል ማረጋገጫ ይሰጣሉ፤ ከዚህ በኋላም አለቃቸው ተስማምተው “በቃ ሥራው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጧቸዋል ፤ በዚህን ጊዜ ማስተር ቺፍ ዓለም በመነቃቃትና ረዳት በመያዝ ሥራውን በከፍተኛ ጥንቃቄ መሥራት ስለመጀመራቸው ያብራራሉ።
“……..ሞተሩ በጣም ትልቅ ነው፤ ሥራውም እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ እንዲሁም አድካሚ ነበር፤ ነገር ግን በብቃት በመሥራት በመበየድና አስፈላጊው ቦታ ላይ በመግጠም እንዲንቀሳቀስ አደረግኩኝ። ከፍተኛ የሆነ ደስታ ተሰማኝ። አለቆቼም ከሚገባው በላይ ኮሩብኝ። እንደ ሀገርም ችግር ውስጥ ከመግባት ዳንን” ይላሉ።
በመቀጠልም ሌሎች በጣም አስፈላጊ ሥራዎችን ከመስረታቸውም የተነሳ አለቃቸው በሚገባ ስለተማመኑባቸው ሌላ በጣም አስፈላጊ እጅግ ውድና በመጠኑም ግዙፍ ጀኔሬተር እንዲሠሩ ትዕዛዝ ተሰጣቸው። የአለቃቸውን ትዕዛዝም በመቀበል ሥራውን በብቃትና በአንደኝነት አጠናቀቁት።
ማስተር ቺፍ ለባህር ኃይሉም ሆነ ለሀገር ብዙ ውለታን ውለዋል በሙያቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በበረሃ ተቃጥለው ብዙ ቁምነገሮችን ሰርተዋል። በዚህ ውለታቸውም በተቋማቸው እስከ ማስተር ቺፍነት የደረሰን ማዕረግ እድገት አግኝተዋል። ማስተር ቺፍ የሰሯቸው ሥራዎች ከማዕረግ በተጨማሪም አዲስ አበባ ከተማ ላይ ዝውውር እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።
ከምጽዋ አዲስ አበባ ከተዘዋወሩ በኋላም በባህር ኃይል ውስጥ በሙያቸው ከፍ ያለ አገልግሎትን መስጠት ጀመሩ። በዚህም ብዙ አገልግሎትን ካደረጉ በኋላ በገዛ ፍቃዳቸው ጡረታ ጠይቀው ከተቋሙ በክብር እንደተሰናበቱ ይናገራሉ።
ወዲያውም ሀገሪቱ በመንግሥት ለውጥ ውስጥ ገባች። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ አብዛኞቹ የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባላት ሁሉ ለማስተር ቺፍም የተመቸ አልሆነም። ብዙ የኑሮ ውጣውረድና ችግሮች ደረሱባቸው። አይበገሬው ወታደር ግን ሂልተን ሆቴልን ጨምሮ ሸራተን አዲስ ሆቴልና ሌሎች ቦታዎች ጋር እየተዘዋወሩ በሙያቸው ማገልገለን ተያያዙት።
የቤተሰብ ሁኔታ
ማስተር ቺፍ ትዳር የመሠረቱት በቤተሰብ ነው። የወንድሞቻቸው ልጆች ጓደኛ ሆነው ቤት ሲመጡም ነው ከባለቤታቸው ጋር የተዋወቁት ፤ በዚህ ሁኔታ የሚጀምረው ግንኙነታቸው ፤ ወደጓደኝነት አድጎም ትንሽ ከቆዩ በኋላ በ1956 ዓ.ም ወደ ትዳሩ ዓለም ገቡ። በዚህ ሁሉ የትዳር ዓመታትም ልጆች ወልደው ለመሳም በቅተዋል።
የብዙዎች የመኖር ተስፋ
የ“እኛና እነርሱ” ድንበር የሌለው፣ በዘርና በጎሳ የማይገደብ ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚለካበት ነው ሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ሥራ። የስያሜው መሠረትም ይሄው ነው፤ ሰብዓዊነት-ሰው ለሰው የሚከውነው ክቡር ሥራ ነው። ሰው በመሆኑ ብቻ! በቃ ሌላ ምንም ምክንያት አይሻም። እኛም እንደ ማስተር ቺፍ ዓለም ያሉ በጉርምስናና በጉልምስና እድሜያቸው ወቅት ለሀገር ብዙ ውለታን ያበረከቱ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ቀን ዘንበል ብሎባቸው የተቸገሩ ከችግርም አልፈው ይገቡበት ይጠለሉበት ያጡትን እየሰበሰበ ስለሚያኖረው ባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት ለማንሳት ነው።
ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ በርካታ አቅመ ደካሞችን ሰብስቦ በማኖር እንዲሁም ሌሎችን ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ መግቦ ወደመኖሪያቸው በመሸኘት በበጎ ሥራው ከፍ ያለ አስተዋጽኦን እያበረከተ ነው።
ማስተር ቺፍ ዓለምም ምንም እንኳን ዘመናቸውን ሙሉ ለሀገራቸው የቁርጥ ቀን ልጅ ሆነው በዱር በገደሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ልጆች እያሳደጉ የኖሩ ቢሆንም ዛሬ ላይ በእርጅና ዘመናቸው ግን አለሁ የሚላቸው አላገኙም። ይህ ሁኔታ ደግሞ እሳቸውም ለበጎ አድራጊዎች እጅ ይሰጡ ዘንድ አስገድዷቸዋል።
ማስተር ቺፍ ስለቤተሰባቸው ስጠይቃቸው ብዙ ደስተኛ አልነበሩም። እሳቸው በማያውቁት ምክንያት ልጆቻቸው እንደ አባት ሊጠይቋቸው ባላቸው ነገርም ስብስብ አድርገው ሊጦሯቸው ፍቃደኛ አልሆኑም። ነገር ግን ብዙ የዋሉላት ሀገር ብዙ ደጋጎችን የማፍራት አቅምም ያላት ናትና ልጆቻቸው የጨከኑባቸውን አባት ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ስብስብ አድርጓቸዋል። ሆዳቸው እንዳይርበናቸው፤ ሰውነታቸውን እንዳይበርዳቸው ፤ ማረፍ ሲፈልጉም ያርፉበት ዘንድ መጠለያ አመቻችቶ እየጦራቸው ነው።
“…….እዚህ የመጣሁት በግል ችግሬ ምክንያት ነው፤ አንዳንዶቹ መግለጽ ስለማልፈልግ ልለፋቸው። ነገር ግን ልጆቼ ሁለቱ ተድረዋል። እንደውም አራተኛዋ በትዳሯም በሀብትም ጥሩ ላይ ያለች ናት። ወንዱም አዲስ አበባም አሜሪካን ሀገርም ተምሮ ኑሮውንም አሜሪካን ሀገር አድርጎ በጥሩ ሁኔታ እየኖረ ነው። ይህ ቦታ ለእኔ በጣም ጥሩ ነው። ምንም ብስጭት የለብኝም። የማየውም የምሰማውም ክፉ ነገር የለም ፤ እበላለሁ እጠጣለሁ አርፋለሁ፤ አሁን ላይ ዓይኔ አንደኛዋና እግሬ በጣም ያመኛል እነሱን መታከም ብችል በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም