የሻማው ብርሃን …

የገበሬ ልጅ ነች። ወሎ መርሳ አባ ጌትዬ ፣ ከአንድ የገጠር መንደር ተወልዳ አድጋለች። ልጅነቷ እንደ እኩዮቿ ነው። በሜዳ በመስኩ ከብትና ፍየል ትጠብቅ ነበር። ከጓሮው እሸት ከማጀቱ ትኩስ ወተት አላጣችም። ወላጆቿ ፍቅር አልነፈጓትም። እንደ አቅማቸው የልቧን መሻት ሞልተዋል።

አጋጣሚ ሆኖ ትምህርት ይሉትን አታውቅም። ፊደል ለመቁጠር፣ ቀለም ለመለየት ዕድል የሰጣት የለም። ትንሽዬዋ ቆንጆ በያን አብዱ ዕድሜዋ ከፍ ሲል ዓይን የሚጥሉባት በዙ።

አስራ ሶስት ዓመት እንደሞላት ወላጆቿ ‹‹ልጅህን ለልጄ›› በሚል ለጋብቻ ተስማሙ። በያን እንደ ወጉ አምራ ፣ ተኩላ ተዳረች። ‹‹ሙሽሪት ልመጂ›› ተብላ ከወላጆቿ ቤት ተሸኘች። ልጅቷ ገና ልጅ ናት። ዕድሜዋ ለጋብቻ አልደረሰም። እንደ ባህሉ ከአማቾቿ ዘንድ በእግድ መቆየት አለባት።

ባለቤቷ መልካም ሰው ነው። ሚስቱን የሚወድ ጎጆውን የሚያከብር አባወራ። አማቾቿም እንደ ልጅ ይወዷታል። አስራ አምስት ዓመት ሲሞላት በያን ከአማች ጉያ ወጥታ ወደ ባሏ ልትሄድ ግድ ሆነ። ጥንዶቹ የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው ትዳር ጀመሩ።

እንዲህ ከሆነ ጥቂት ጊዜ በኋላ በያን አረገዘች። የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ስትታቀፍ አካሏ ያልበረታ፣ ጉልበቷ ያልጸና ለጋ ነበረች። ጨቅላው እንግዳ የቤቱ ድምቀት ሆኖ ጎጆውን አጸና። ገበሬው አባወራ በዚህ ውስጡ ሀሴት አደረገ። በልጅ ስጦታው ልቡ ቢረካ አርቆ አሰበ። ሌሎች ልጆች ቢወለዱ ፣ ቤቱን በጸጋ ቢሞሉት ወደደ።

ይህ ምኞቱ በሚስቱ ዘንድ አልተደገፈም። በያን ገና በልጅነቷ የልጅ እናት መሆኗ አድክሟታል ። ሕፃኑ በወጉ ሳያድግ ሌላ መጨመርን አትሻም። ይህን የሰሙ የእሱ ዘመዶች የአባወራውን ሃሳብ ደገፉ። በያን ሁለተኛ ልጅ ደግማ እንድትውልድ ፈረዱባት።

ውሎ አድሮ ባልና ሚስት መጋጨት ጀመሩ። አባወራው ‹‹አሁን አልወልድም›› ማለቷን በበጎ አላየውም። ስለምን ሲል ጠዋት ማታ ሞገታት። ይህ እውነት በቀላሉ አልፈታም። ነገር ጭሮ ጠብ ፈጠረ። ከቀናት በአንዱ ባል እጁን አነሳባት። የበያን ቅያሜ ጠነከረ።

በያን በድንገት ጓዟን ይዛ ከወላጆቿ ሄደች። አባት የሚወዷት፣ የሚሳሱላት ልጃቸው በባሏ መመታቷን ባወቁ ጊዜ ‹‹ምን ሲደረግ›› ብለው ‹‹አትመለስም›› አሉ። ውሎ አድሮ ጉዳዩን እንፍታ ያሉ ሽማግሌዎች ከቤት ደረሱ። እንደታሰበው አልተሳካም። በፍቅር የጸናው ትዳር እንደዋዛ ፈረሰ። በያን ይህ በመሆኑ አልከፋትም ። በልጅነቷ ከገባችበት ጎጆ መውጣቷ አስደሰታት።

በያን ትዳሯን ከፈታች በኋላ ወደልጅነቷ ዓለም ተመለሰች። መዝለል፣ መጫወት ልምዷ ሆነ። እናት ነፍስ ያላወቀውን ጨቅላ ጡታቸውን እያጠቡ እንዳሻት እንድትሆን ፈቀዱላት። ልጇን ከእናቷ እጅ የጣለችው ለጋ በትዳር የባከነባትን የልጅነት ጨዋታ እንደልቧ አጣጣመች።

አሁን በያን አስራ ሰባት ዓመቷን ደፍናለች። ይህ ዕድሜ አርቃ እንድታስብ ስለነገ እንድታልም አስችሏታል። እንዲህ ዓይነቱ ህልም ባለበት አልቀረም። በሌሎች የምትሰማውን የዓረብ ሀገር ሕይወት ልትሞክረው ወሰነች። ልጇን ትታ ወደ ጅዳ ተጓዘች።

ኑሮ በዓረብ አገር

የጅዳ ሕይወት ለወጣቷ በያን ቢከብድም አልፈተናትም። ተቀጥራ ለምትሠራበት የጽዳት ሙያ ኃላፊነቷን ታውቃለች። አንዳንዴ ከሥራ መልስ ሀሳቧ ወደ ሀገር ቤት ያከንፋታል። ትንሹ ልጇ፣ ወላጆቿ፣ ያደገችበት ሰፈር ቀዬ ውል እያላት ትቸገራለች። ይሄኔ ሁሉን ትታ ለመመለስ ትወስናለች። እሷን የሚቀርቡ ስለሕይወቷ የሚመክሯትን አትዘነጋም። ባለችበት ዕድሜ ትዳር ይዛ ልጅ መውለድን ትሻለች።

በያን አስር ዓመት ከቆየችበት የዓረብ ሀገር ኑሮ ወደ ሀገር ቤት ተመለሰች። ያለፈችው ጊዜ ክፉን ከደግ ያየችበት ነው። አሁን ያለችበት ዕድሜ ሁሉን መለስ ብላ የምታይበት ነው። በልጅነቷ የፈታችውን ትዳር ዛሬ በበሰለ አዕምሮ ልታየው ወስናለች። በያን ያለፈውን ታሪኳን የሚሽር መልካም የትዳር አጋር ብታገኝ ትወዳለች።

ትውውቅ

በያን ሀገር ቤት ተመልሳ ከልጇ ከወላጆቿ ተያይታለች። የዓረብ ሀገር ቆይታዋ ዓላማውን አልሳተም። የላብ የድካሟን ይዛለች። የሠራችበትን ጥሪት ቋጥራለች። ሀገሯ ገብታ ወራት እንዳስቆጠረች እንደ ቤተሰብ ከምትቀርበው አንድ ሰው ጋር ማውጋት ያዘች። እሱ እንደሷው በስደት የቆየ ነው። የሰው ሀገርን ስቃይ መከራ አሳምሮ ያውቃል።

ከዚህ ሰው ጋር ልብ ለልብ ተናበበች። እሱ ያለፈበት መንገድ ከእሷ ሕይወት ይመስላል። ሁለቱም ሃሳብ ዓላማቸው አንድ ነው። በትዳር ተሳስበው ጎጆ መቀለስ፣ ልጆች ወልዶ መሳም ይሻሉ። የልባቸው እውነት ውሎ አድሮ ካሰቡት አደረሳቸው። በራሳቸው ፈቃድ በቤተሰብ ይሁንታ ተመርቀው ወደ ትዳር ገቡ።

የበያን ባለቤት ልጅ ለማግኘት ጓጉቷል። ከዚህ ቀድሞ ባለመውለዱ ከትዳሩ ፍሬ እየጠበቀ ነው። እሷ ቶሎ አላረገዘችም። ጥቂት ወራት የዘለቀው ቆይታ የአባወራውን ትዕግስት ነጥቆ የቤቱን ሰላም እየነሳ ነው። በድንገት የሚሰነዝረው ክፉ ቃልም የበያንን ልብ የሚሰብር ሆኗል።

በያን ውስጧ ቢያዝንም መታገስን መረጠች። ባህሪውን ችላ ክፉ ቀናትን በዝምታ አለፈች። ውሎ አድሮ ግን ጥያቄዎች መልስ አገኙ። አባወራው ሚስቱ ማርገዟን አወቀ። ይሄኔ የትናንቱን ረስቶ በደስታ ተዋጠ። የልጅ አባት እንደሚሆን ሲያውቅ ባህሪውን አክሞ መልካም ባል ሆነላት። ይህ ቆይታ ብዙ አልዘለቀም። አባወራው በየሰበቡ የቤቱን ሰላም ይነሳ ያዘ።

በያን ጊዜው ሲደርስ ወንድ ልጅ ወልዳ ታቀፈች። አባወራው የሚሻው ቀን ቢመጣለት የልቡ ምኞት ሞላ። ለአራስነቷ ገጠር እናቷ ቤት የከረመችው ወይዘሮ ወራትን ቆይታ ጎጆዋ ተመለሰች። በቤቱ የልጅ ለቅሶ ቢሰማም እንደቀድሞው ፍቅር አልታየም። በጥንዶቹ መሀል ሳቅ ፈገግታ የጎደለው ኑሮ ቀጠለ። በያን የአባወራዋ ባህርይ መለዋወጥ አልገባትም። እንደ ዓመሉ ለማደር የምታደርገው ጥረት እየተሳካ አይደለም። ደስታ የራቀው ባሏ በየሰበቡ እያበሳጨ ያሳዝናታል።

የስልኩ መዘዝ …

ዕለቱን መብራት ጠፍቶ ውሏል። እንዲህ ሲሆን በቤት፣ በአካባቢው ብዙ ይጎድላል። በያንም ከዚህ ችግር ተጋርታለች። የሞባይል ስልኳ ባትሪ ጨርሷል። ለዚህ መፍትሔ ባለቤቷ ከተማ ሲወጣ ኃይል ሊያስሞላላት ተሰማምተዋል። እንደተባለው ሆኖ የታሰበው ተደርጓል። ምሽት ላይ ባትሪ የሞላው ስልኳን አየት አደረገች። በአንድ ቁጥር ተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጓል። ቀረብ ብላ አየችው። ከዚህ በፊት የማታውቀው ስልክ ነው።

ሞባይሏ ቀኑን ሙሉ ከእሱ ነበርና ቁጥሩን ያውቀው እንደሁ ጠየቀች። አይቶት እንደማያውቅ መለሰላት። ጥያቄዋ ሲደጋገም ደውላ እንድታረጋግጥ ነገራት። ምሽት አራት ሰዓት በማለፉ መደወሉ ከበዳት። ባል ግን ምናልባት የቤተሰብ ስልክ እንደሚሆን ግምቱን ገለጸ። እንዲያም ሆኖ ልትደውል አልደፈረችም። ደጋግሞ ማንነቱን እንድትጠይቅ ወተወታት። በያን ምርጫ አልነበራትም። ቢመሽም ወደ ቁጥሩ ደውላ ሀሎ! ስትል ጠበቀች።

ከጥሪው መነሳት በኋላ የተሰማው ምላሽ ለሁለቱም አስደንጋጭ ነበር። ‹‹ሀሎ የኔ ፍቅር ! ረሳሸው እንዴ አውርተን፣ተነጋግረን የለም እንዴ ›› ሰውየው አላቋረጠም። ሁለቱም ዓይን ለዓይን ተፋጠጡ። በተለይ አባወራው ፊቱ በንዴት ጋየ። በያን የሰውየው ቃል በእጅጉ ቢያስጨንቃት ዝምታን መረጠች። ንግግሩ ቀጠለ ‹‹የኔ ፍቅር ምነው ዝም አልሽ አጠገብሽ ሰው አለ እንዴ›› በያን የንዴት ሳግ ይዟት ጠየቀች። ምንድነው የምትዘባርቀው ለመሆኑ አንተ ማነህ ቀኑን ሙሉ ለምን ደወልክ ምን ፈልገህ ነው››

ሰውዬው አሁንም ምላሽ ሰጠ። ‹‹እኔ አልዘባረኩም የኔ ፍቅር አዋሪኝ እንጂ ›› በያን እጇ እየተነቀጠቀጠ ስልኩን ጠረቀመችው። ባል በጥርጣሬ አተኩሮ እያየ ጥያቄ አቀረበ። ‹‹ይህ ሰው ማን ነው? መልሽልኝ›› አምባረቀባት። አራሷ በያን መልስ አልነበራትም። የእጅ ስልኳ የዋለው በእሱ እጅ ነው። በግራ መጋባት ጥያቄውን መልሳ ወደራሱ አዞረችው። ከዚህ በኋላ ድንገቴው የነገር እሳት ተጫረ። ባልና ሚስት መግባባት ተሳናቸው። ወይዘሮዋ ዳግመኛ ወደ ስልኩ ደወለች። ባለትዳር መሆኗን ገልጻ ምናልባት ተሳስቶ እንዳይሆን ጠየቀች። የሰውየው ሃሳብ አልተለወጠም። እየደጋገመ በፍቅር አንደበት ማዋራቱን ቀጠለ።

አባወራው በእጇ ላይ ያለውን ውድ ሞባይል በድንገት ነጥቆ ከሰከሰው። በዚህ አልበቃውም። በግራ መጋባት ከፊቱ የቆመችውን አራስ ሚስቱን እንዳይሆን አድርጎ ደበደባት። ባልታወቀው ደዋይ የተጫረው እሳት ወደ ሕፃኑ አልፏል። ክፉኛ የሚያለቅሰው ጨቅላ ባልተለመደ ባህርይ ሰውነቱ እየተንቀጠቀ ፣ እየተገላበጠ ነው። እናት ክንፍ እንዳለው ሁሉ ልጇ የሚበር መስሎ ታያት። አንስታው ልትወጣ ታገለች። አልቻለችም። በር መስኮቱ ጥርቅም ብሎ ተዘግቷል።

ሚስት በለቅሶ እየተማጸነች ልጃቸውን በሰላም እንዲያሳድጉ ለመነች፣ አባወራው አሁንም እሳት ጎርሷል። ጨቅላው ልጅ አምርሮ ማልቀሱን ቀጥሏል። ጥቂት ቆይቶ እንደሚገድላት እየዛተ ተጠጋት። ወደ ልጁ አልፎ ሲራመድ አምልጣው ወጣች። የልጇ ድምጽ ከኋላ እየተከተላት ነው። ጎረቤት ገብታ ‹‹አድኑኝ›› ስትል ባዶ ርቃኗን ነበረች።

ሌሊቱ ተጋምሷል። ሕፃኑ ያለማቋረጥ ማልቀሱን ቀጥሏል። አባወራው ልጁን ለእናቱ እንዲሰጥ እየተለመነ ነው ‹‹ይሙት በቃ›› ፈርዶበት ‹‹እምቢኝ›› ብሏል። በውድቅት ፖሊስ ጣቢያ የደረሰችው እናት ጥቂት ፖሊሶችን አስከትላ ተመለሰች። ከቤት ሲገቡ በአባቱ እጅ ያለው ሕፃን ማልቀሱን አላቆመም። ካልታወቀው ሰው የደረሰው የስልክ ጥሪ ከቀናት በኋላ ለፈረሰው ትዳር ምክንያት ሆነ። በያን የሆነውን ሁሉ ዛሬ ላይ ቆማ ስታውስ ዓይኖቿ ውሃ ይሞላሉ። በልጇ ላይ የደረሰው ፈተና ግን ከሁሉም ይለያል።

የመጨረሻው መጀመሪያ

ከተከሰተው ችግር ሶስት ቀናት በኋላ ሕፃኑ ክፉኛ ታመመ። ዓይኑ መንሸዋረሩን፣ እጁ ፣ አፉና አንገቱ በድንገት መጣመሙን ያየችው እናት ክፉኛ ደነገጠች። ቤተሰቦቿ በጭንቀት አንገታቸውን ደፉ። በፍጥነት ወልድያ ሆስፒታል የደረሰው ሕፃን አስቸኳይ ህክምና አገኘ። ችግሩ ማጅራት ገትር መሆኑ ታወቀ። ለጊዜው መፍትሔ ቢያገኝም ወደ ጤናው አልተመለሰም።

አንዳንዶች ሕፃኑን እያዩ ስጋታቸውን ተናገሩ። አብዛኞቹ ቅጭት መሆኑን ገምተዋል። በያን ልጇን ከአንዲት ታዋቂ ወጌሻ ዘንድ ወሰደችው። ሴትየዋ ሰውነቱን አገላብጣ ፈተሸችና ቅጭት ያለመሆኑን ነገረቻት። አስከትላ የሰነዘረችው ቃል ግን እናትን ክፉኛ አሰደነገጠ። ‹‹ልጁ በክፉ መንፈስ ድንገት ተመቷል›› አለቻት።

በያን ስለ ልጇ ጤና አልተቀመጠችም። በሀገር ባህል የተሰጣትን መድኃኒት ሞከረችና እጅ እግሩ ተፈታላት። ‹‹ተመስገን›› ብትልም የዓይኑ ተንሸዋሮ መቅረት አስጨነቃት። ጥቂት ቆይታ በዓይኑ ላይ አንዳች ነገር አስተዋለች። ነጭ መሳይ ምልክት ጥሎበታል። ለእሷ ብቻ በግልጽ የሚታያት ምልክት በሌሎች ዘንድ በበጎ ተተረጎመ።

እናት በያን የሚሏትን አላመነችም። ወደ ደሴ ሆስፒታል ወሰደችው። ሐኪሞ ምርመራውን ሲጨርስ በአስቸኳይ ወደ አዲሰ አበባ መሄድ እንዳለበት ወሰነ። የበያን ኑሮ ወላጆቿ ቤት ሆኗል። ባለቤቷ የልጁን ህመም በእሷ ማሳበብ ይዟል። አንዳች ሳንቲም አያግዛትም። በቂ ገንዘብ ባይኖራትም ለመሄድ ወስናለች።

አዲስ አበባ

ከወዳጅ ዘመድ ገንዘብ የታገዘችው በያን የጎደለው እስኪሞላ ሁለት ወር ፈጀባት። በማታውቀው ሀገር አዲስ አበባ እግሯ ሲረግጥ ሕፃኑ ስምንት ወር ሞልቶት ነበር። በዚህ ቦታ ተቀባይ ዘመድ የላትም። መሄዷን የሰማው ባሏ ያለእሷ ፈቃድ ተከትሏታል። ለሕይወቷ ብትሰጋም ምርጫ አልነበራትም። በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተደረገው ሕክምና ብዙ ወጪ ይጠይቃል። የልጇ አባት ይህን ቢያውቅም አንዳች አልረዳትም። በቤት ኪራይ፣ በምግብ፣ በትራንስፖርት የእጇ ገንዘብ ማለቅ ያዘ።

ከቀናት በአንዱ በያን ከሐኪሞች የሰማችው እውነት ከአቅሟ በላይ ሆነ። የልጇ ሕመም ‹‹ካንሰር›› በመሆኑ አንድ ዓይኑ ሊወጣ ግድ ነው ተባለች። ከማልቀስ በላይ አነባች፣ ከማዘን በላይ ተሰበረች። የልጇን ዓይን ለማዳን ሀገር ቆርጣ የመጣች እናት ዓይኑ ካልወጣ አይድንም ስትባል ዙሪያው ጨለመባት። ሐኪሞቹን የአቅሟን ለመነች፣ ሞገተች። ይህ ካልሆነ ልጇ በሕይወት እንደማይቀጥል ቁርጡ ተነገራት።

ለመፈረም ውሳኔ ላይ ሳለች አባትየው ‹‹አይሆንም›› ሲል ‹‹እምቢኝ›› አለ። ሐኪሞች ግን ይህ ይሁንታ ከእናቱ እንጂ ከእሱ እንደማይጠበቅ ነግረው አሰናበቱት። በያን የሆነውን ለቤተሰብ ነግራ የጎደላትን ለመጠየቅ ስል አነሳች። ወቅቱ ጦርነቱ የከፋበት ጊዜ በመሆኑ የሁሉም ድምጽ ጠፋባት። ችግሯን የተረዱት ዶክተር ሳዲቅ የተባሉ ሐኪም የሚያስፈልጋትን ሁሉ እንደሚሸፍኑ ቃል ገብተው አጽናኗት።

ሕክምናው ከሁለት ወር በኋላ ይጀመራል። በያን መኖሪያና ምግብ የላትም። ደጉ ሐኪም በሆስፒታሉ ሁሉን አመቻቹ። በአጭር ጊዜ ቀዶ ሕክምናው ተካሄደ። እናት የልጇን ዓይን ናሙና ለማሰራት በተቀበለች ጊዜ ከባዱን ጊዜ ተጋፈጠች። ለልጇ ከእሷ በላይ የሚሯሯጥ ማንም የለም። ማደንዘዣው በወጉ ሳይለቀው የሚሆነውን ሁሉ ብቻዋን ጥርሷን ነክሳ ፈጸመች።

ከሄደችበት ስትመለስ ልጇ እንደትናቱ በሁለት ዓይኑ አላያትም። ከላዩ ተደፍታ አምርራ አነባች። ቆይታ ግን ዕንባዋን ጠርጋ ስለነገው አሰበች። ያሰራችው የናሙና ውጤት መልካም ሆኗል። ዶክተር ሳዲቅ አሁንም ከጎኗ ናቸው። ከኪሳቸው ሶስት ሺህ ብር ቆጥረው ሰጧት። ለኬሞቴራፒ ወደ ጥቁር አንበሳ ስትሄድ ፈጣሪዋን እያመሰገነች ነበር። ቀጣዩ ሕክምና እንደ አዲስ ተጀመረ።

ይህ ጊዜ በያን ካርቶን አንጥፋ የተኛችበት፣ በዕለት ክፍያ አልጋ ይዛ ከሰፈር ያደረችበት ፈታኝ ወቅት ነው። ስለ ልጇ ተባይ በልቷታል ፣ ርቦ ጠምቷታል፣ ስታገኝ ሻይ በዳቦ ስታጣ ጾም ማደር ልምዷ ነበር። ልጇን አዝላ በእግሯ የኳተነችበቸውን ጊዜያት አትረሳም። ትንሹ ሰልማን በጀርባ አጥንቱ የናሙና ምርመራ አልነቃ ባለጊዜ የሆነችውን ታስታውሳለች፣ ለናሙና ምርመራ ስትወጣ አደራ እያለች የምትሄድበት ትዝ ይላታል። አንድ ኩባያ አጥሚት የገዛችበት ጊዜ የብቸኝነት ታሪኳ ነው። በያን ፊደል አለመቁጠሯ ደግሞ ከሰው እገዛ አላወጣትም። ስለማታነብ ችግሯ ብዙ ነበር። የዓረብ ሀገር ጓደኞቿ በገንዘብ የደገፏትን አትረሳም። የኬሞ ቆይታው ለእሷም ለልጇም ከባድ ነበር። በልጇ አባት ብዙ ተፈትናለች። ለሕጻኑ የከፈለችው ዋጋ በእሱ ዘንድ ትርጉም አልባ ነበር።

ዛሬ ላይ ሰልማን ሶስት ዓመቱን ደፍኗል። ከእናቱ ጋር በማቴዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ውስጥ ይገኛል። ይህ ተቋም። እሷንና ልጇን ከጎዳና እንዳነሳቸው ታስባለች። መድኃኒት፣ ማረፊያና ምግብ ቸግሯት አያውቅም። ቀድሞ በሁለቱም ዓይኖቿ ላይ ባጋጠማት ሕመም የቀዶ ሕክምና አድርጋለች። ለዚህ ድጋፍ ያደረጉላትን የግቢውን አባላትና አቶ ዑመርን ከልብ ታመሰግናለች።

ሳቂታው፣ ደስተኛው ሰልማን አሁን በጥሩ የጤና አቋም ላይ ነው። እነሆ! ያልፍ አይመስለው ታሪክ በጠንካራዋ እናት ትከሻ እንዲህ ታልፏል። በያን ዛሬም ብርቱ ሴት ናት። እንደ ዓይኗ ብሌን ለምታየው ልጇ ተነግሮ በማያልቅ ታሪክ መሀል ተራምዳለች። ዛሬም ግን ስለእርሱ መኖር የሻማው ብርሃን ናት።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You