በቡና ምርትና ኤክስፖርት የተጀመረው የድርጅቱ የስኬት ጉዞ

ቡናን በጥራት አልምቶ እንዲሁም ገዢ ሀገራት በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ አዘጋጅቶ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ቀዳሚ ነው። በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ያወጣውን ሕግም ተግባራዊ በማድረግ የዕውቅና ሰርተፍኬት አግኝቷል።

ሕጉ እኤአ ከ2024 ጀምሮ ለዓለም አቀፍ ገበያው የሚቀርበው ቡና ሙሉ ለሙሉ ዱካውን የተከተለና ከደን ጭፍጨፋ ነፃ በሆነ መንገድ የለማ መሆን እንዳለበት ያስገድዳል። ከዚህ በተጨማሪም ለቡናው ከተከፈለው የዓለም ገበያ ድርሻ አርሶ አደሩ በአግባቡ ተጠቃሚ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ሌላው የአውሮፓ ህብረት ያስቀመጠው ሕግ ነው። እነዚህን ሕጎች ተግባራዊ በማድረግም ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኘ የመጀመሪያው ድርጅት ቀርጫንሼ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ነው።

የድርጅቱ መሥራችና ባለቤት አቶ እስራኤል ደገፋ እንደሚናገሩት፤ ቡና አልምቶ ኤክስፖርት ከማድረግ ባለፈ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በመቀላቀል ቡና እስኪሪብቶ፣ ቡና ሳህን፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን፣ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ሥራ ላይ ተሰማርቷል። በተያዘው በጀት ዓመት የጀመረው የሥጋ ኤክስፖርትም እንዲሁ አበረታች ውጤት እያሳየ ስለመምጣቱ ገልጸዋል።

አቶ እስራኤል ቡና ከማልማት ጀምሮ ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ከኖረ አርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙት ሶስተኛ ትውልድ ናቸው። ትውልድና እድገታቸው በጉጂ ዞን የመጀመሪያዋ ቡና አብቃይ ወረዳ በሆነችው ቀርጫንሼ አካባቢ ነው። የድርጅቱ መጠሪያም ‹‹ቀርጫንሼ›› መባሉ በዚሁ ምክንያት እንደሆነ አጫውተውናል። ከቡና ልማትና ንግድ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው አቶ እስራኤል፤ ቡናን በማልማትና ለውጭ ገበያ በማቅረቡ ሥራ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

በሀገሪቱ ቡና አምራች በሆኑ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ 56 ሺ ከሚደርሱ አርሶ አደሮች ጋር ተቀናጅተው በመሥራት አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገቡ ያሉ ታታሪ ናቸው። ድርጅታቸውም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና በዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ ከሆኑ የዘርፍ ተዋናዮች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን፤ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማስጠበቅ ረገድም አበክረው ይሰራሉ።

‹ቀርጫንሼ›› ከቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር በቅንጅት ይሰራል፤ በዚህ ሥራ ከሚያገኘው ቡና በተጨማሪ በራሱ የእርሻ ቦታዎች ላይም ቡና በዘመናዊ እርሻ ያለማል። ቡናውን ወደ ውጭ ገበያ በመላክም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተዋጽኦ እያበረከት ሲሆን፤ እያስገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ መጠንም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን የጠቀሱት አቶ እስራኤል፤ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 125 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማስገኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።

መንግሥት በአሁኑ ወቅት ለቡናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ እስራኤል፤ የቡናና ሻይ ባለሥልጣንም አጋዥ በመሆን በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ይገለጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ቡና አምራች የሆኑ አካባቢዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወዘተ ቡናንን በቀጥታ መላክ የሚችሉበት/ የቀጥታ ግብይት አማራጭ/ አሠራር የተዘረጋ በመሆኑ ድርጅቱ ያመረተውን ቡና ካመረተበት አካባቢ በቀጥታ ወደ ወደብ እየላከ ይገኛል።

ለአብነትም ድርጅቱ በደቡብ አካባቢ የሚያለማውን ቡና ቡሌሆራ በሚገኘው የኤክስፖርት ጣቢያው አዘጋጅቶ በቀጥታ ወደ ጅቡቲ ይልካል። በደቡብ ምዕራብ አካባቢ በሚገኘው የቡና እርሻው የሚያለማውን ቡናም እንዲሁ ጅማ ላይ ባለው የኤክስፖርት ፋብሪካ አዘጋጅቶ ይልካል። ይህ አሰራርም ቡናውን ወደ አዲስ አበባ በማጓጓዝ ይወጣ የነበረውን የነዳጅ ወጪ፣ ድካምና አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን የቀነሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቡና ሳይባክንና ጣዕሙን ጠብቆ ወደ ውጭ እንዲወጣም ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎቹ የሥራ ዕድል በመፍጠር አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።

‹‹ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል የቡና እርሻን ዘመናዊ ማድረግ በዋነኝነት ይጠቀሳል›› ያሉት አቶ እስራኤል፤ ይህንንም በሶስት የቡና እርሻ ቦታዎቹ ማለትም በይርጋጨፌ፣ በጉጂና በጅማ ዞን በሚገኙ የእርሻ ቦታዎቹ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደቻሉ ይናገራሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሀገር አለኝታ የሆነውን ቡና ኋላቀር ከሆነ አመራረት በማውጣት በዘመናዊ መንገድ ለማምረት ድርጅቱ ባደረገው ከፍተኛ ጥረትም በሄክታር አንድ ኩንታል ቡና ይገኝ የነበረውን በአሁኑ ወቅት በሄክታር ወደ 56 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል።

ለዚህም ሀገሪቷ በተፈጥሮ የተቸራት ጸጋ በብዙ አግዞናል ያሉት አቶ እስራኤል፤ ለቡና ምርታማነት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከእስራኤል እንዲሁም አግሮኖሚስቶችን ከብራዚል በማምጣት ሰፋፊ ሥራዎችን ሰርተዋል። የቡና እርሻ ውሃ በበቂ መጠን እንዲያገኝ በማድረግ እንዲሁም ቡና በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኝ ያለ ጥላ ማልማት አንዱና ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል። ዘመናዊ ቡና መልቀሚያ ማሽን ከብራዚል በማስመጣት ቡና ሳይባክን በዘመናዊ ማሽን ይለቀማል። ይህም ለምርትና ምርታማነት እድገት ትልቅ አበርክቶ አለው።

በቀጣይ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ አሁን ከምታመርተው የቡና ምርት መጠን ከ50 እስከ 60 ሺ ሜትሪክ ቶን የሚደርሰው የቡና መጠን በቀርጫንሼ ቡና ላኪ ድርጅት ብቻ የሚሸፈን ይሆናል ያሉት አቶ እስራኤል፤ ቡና ከመግዛትና ከመሸጥ ባለፈ አቅም ያላቸው ድርጅቶች ወደ ቡና ልማት ሥራው መግባት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ቡና የኢትዮጵያ ትልቅ በረከት እንደመሆኑ በዘመናዊ መንገድ ማምረት የቻለና በርትቶ የሠራ ማንኛውም ሰውና ድርጅት በብዙ ሊያተርፍና የሀገርን ኢኮኖሚም በብዙ እጥፍ ሊያሳድግ እንደሚችልም ነው ያስታወቁት።

አቶ እስራኤል ከቡና ልማትና ግብይት ባለፈ በአሁኑ ወቅት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በመቀላቀል የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። ለአብነትም ቡና እስክሪብቶ፣ ቡና ሳህን፣ ቡና ኩባያ፣ ቡና ስኒ የተባሉ 126 ዓይነት የቤት ውስጥ ቁሳቁስን በተለያየ መጠንና ቅርጽ እንዲሁም ቀለማት አምርተው ገበያ ውስጥ በመግባት ተወዳዳሪ መሆን ችለዋል። የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ ገበያውን የተቀላቀለው ቡና እስኪሪብቶ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፤ እሱን ተከትሎ የመጣው ቡና ሳህንም እንዲሁ በከፍተኛ ጥራት የሚመረት በመሆኑ ከውጭ የሚገቡ ሳህኖችን በከፊል መተካት ችሏል።

‹‹ሀገራችን የሸቀጥ ማራገፊያ እንድትሆን አልመኝም›› የሚሉት አቶ እስራኤል፤ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የገቡበት ዋና ዓላማም በተቻለ አቅም ጥራት ያለውን ምርት በሀገር ውስጥ በማምረት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ምርቶቹን ለሌሎች ሀገራት ለመሸጥ እንደሆነ አመላክተዋል። ከሳህንና እስክሪብቶ በተጨማሪ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችንም በሀገር ውስጥ እያመረቱ ይገኛሉ። ማሽነሪዎቹን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ከመሸጥ ይልቅ የተወሰኑ ግብዓቶችን ከውጭ በማምጣት በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያምናሉ። በሀገሪቱ የዓባይ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለእዚህ ደግሞ አስተማማኝ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅታቸው በአቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው ቀርጫንሼ ማሽነሪ ፋብሪካ የማዕድን ማውጫ ማሽነሪዎችን ጨምሮ ኤክስካቫተር፣ ሎደር፣ ዶዘር፣ ግሬደርና ሌሎችም ማሽነሪዎችን ይገጣጥማል። ማሽነሪዎቹ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚከናወኑ ግንባታዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፤ አገልግሎታቸውም ለአንዲት ሰከንድ እንዳይቋረጥ የድርጅቱ ቴክኒክ ቡድን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል።

በቡና ንግድና ልማት ዓመታትን ያስቆጠረው ቀርጫንሼ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ቡናን በዘመናዊ የአመራረት ዘዴ በማምረት እያስመዘገበ ካለው አበረታች ውጤት ባለፈ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ይበል የሚያሰኝ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ከቡና እስኪሪብቶና ሳህን በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ማሽነሪዎቹም እንዲሁ ገበያውን በስፋት በመቀላቀል ግስጋሴውን ቀጥሏል።

‹‹ምርቶቻችን ተወዳዳሪ ሆነው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ጥራት ላይ ትልቅ ትኩረት እናደርጋለን›› የሚሉት አቶ እስራኤል፤ ተወዳዳሪ መሆን የቻሉትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። የትኛውም ምርት ከውጭ ከሚገባው ያልተናነሰ እንዲሁም የበለጠ ጥራት እንዳለው ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ቡና እስኪሪብቶን ጨምሮ ቡና ሳህንና አጠቃላይ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ የሀገር ውስጥ ገበያ ለመሸፈን እየሰሩ እንደሆነና ወደ አፍሪካ ሀገራት መላክ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።

ቡና ሳህኖችን ለማምረት ድርጅቱ የማርብል ፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተረፈ ምርቶችን እንደሚጠቀሙ የገለጹት አቶ እስራኤል፤ 50 በመቶ ያህል ጥሬ ዕቃዎችን ከሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎች እንደሚጠቀም ተናግረዋል፤ ቡና እስኪሪብቶውም እንዲሁ 30 በመቶ በሀገር ውስጥ 70 በመቶ ከውጭ በሚገባ ጥሬ ዕቃ እንደሚመረት አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ቀርጫንሼ ማኑፋክቸሪንግ በዓመት 250 ሚሊዮን እስክሪብቶዎችን የማምረት አቅም አለው፤ 126 ዓይነት የሚደርሱት ቡና ሳህኖቹንም እንዲሁ በዓመት እስከ 35 ሺ ሜትሪክ ቶን ይመረታሉ።

ድርጅቱ በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ አቅዷል፤ በተለያዩ ዘርፎች በመሳተፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራን አጠናክሮ እንደሚሰራ አቶ እስራኤል አስታወቀው፣ ለዚህም አበረታች የመንግሥት እገዛና ድጋፍ እንዳለም ተናግረዋል።

አቶ እስራኤል እንደ ሀገር የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪው ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ እያደረገ ነው፤ በተለያየ ጊዜ በሚያዘጋጀው መርሃ ግብር ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርስ ተገናኝተው የገበያ ትስስር መፍጠር የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል። በንቅናቄው መንግሥትን ጨምሮ ተጠቃሚውም በሀገር ውስጥ ምን እየተመረተ እንደሆነ የማወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ዕድል አግኝቷል። በመሆኑም አዳዲስ ምርቶች በስፋት ወደ ገበያው እየገቡ ሲሆን፤ ይህም ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለማሳየትና ለማስተዋወቅ በር ከፍቷል። ይህ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሊበረታታ ይገባል።

‹‹የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ የዓለም ሸቀጥ ማራገፊያ ከመሆን ይልቅ አምራች እንድትሆን ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል›› ሲሉ አቶ እስራኤል አስታውቀዋል። ይህንን ሃሳብ ያመነጩ መሪዎች ሊበረታቱና ሊመሰገኑ እንደሚገባም ገልጸው፤ ልክ እንደ ቡና ሁሉ ሌሎች የኢትዮጵያ ምርቶችም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ታዋቂ ሆነው ገዢ ሀገራት የኢትዮጵያ ምርት ብለው እንዲገዙ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ለዚህም በመንግሥት ተነሳሽነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምሳሌ ነው ብለዋል።

በቡና ምርትና ኤክስፖርት የተጀመረው የቀርጫንሼ ትሬዲንግ ረጅሙ ጉዞ በከፍተኛ የሥራ ትጋትና ጥረት እንዲሁም ጥልቅ በሆነ ሀገራዊ ስሜት ብዙ መሰናክሎችን እያለፈ ዛሬ ላይ ደርሷል። ቀርጫንሼ ትሬዲንግ በቡና እስኪሪብቶና በ126 የሳህን ዓይነቶች ማምረት እንዲሁም በኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች መገጣጠም የጀመረው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ግስጋሴ ዘመናዊ በሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ድርጅቱ ዮቶንግ ከተባለ የውጭ ድርጅት ጋር የቤት መኪኖችን እና አውቶብሶችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ ሊያቀርብ ዝግጅቱን አጠናቅቋል ሲሉም ጠቁመው፣ በቅርቡም ለሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚውሉ 100 የቤት መኪኖችን 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በማስከፈል ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

ቀርጫንሼ ትሬዲንግ በቡና ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ በማዳንም እንዲሁ አበርክቶው የጎላ ነው። ድርጅቱ ከግብርና እስከ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባቋቋመው ድርጅቶች ውስጥ ለሚሰሩ 28 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

ማህበራዊ ኃላፊነትንም እንዲሁ በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ እስራኤል ደገፋ፤ በቀጣይም በርካታ ሥራዎች ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል። በበጀት ዓመቱ 55 ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 200 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፤ በሥጋ ምርትም እንዲሁ 65 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማምጣት አቅደው እየሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You