የሥነ -ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ

ንግግሩ የቅብጠት ይመስላል። ወላጆቹም ቆንጥጠው ያሳደጉት አይመስልም። አዋቂዎች ‹‹ድምበር አያውቅም፤ ልክ የለውም እንዴ?›› ይሉታል። ወጣቶች ደግሞ እንዲህ የሚያደርገው ለጨዋታ እንጂ ለሌላ አይደለም ብለውታል። ልጁ እንዲህ የተባለው ግን በርግጥም ቀብጦ አልነበረም። ወላጆቹም በሚገባ ሳያሳድጉት ቀርቶ አይደለም። ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ልጅ በመሆኑ እንጂ።

ናታን ይባላል። ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ልጅ ነው። አቶ ዘርይሁን ተከስተ ደግሞ አባቱ ናቸው። በእርሱ ህመም ምክንያት ብዙ ተብለዋል፤ ብዙ ፍዳም አይተዋል። ከኦቲዝም ጋር የሚኖር በመሆኑ የናታን ንግግርና ድርጊት ለየት ይላል። ስለርሱ እንዲህም ነው እንዲያም ነው ሲሉ የቆዩት ሰዎችም ባህሪውን ለማወቅ ብዙ ዓመት ፈጅቶባቸዋል።

ከዓመታት በፊት ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች የትምህርት ዕድል አልነበራቸውም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። የልዩ ፍላጎት ባለሙያዎች ማግኘትም አይታሰብም ነበር። ከሃያ ሁለት ዓመት በፊት በዘሚ የኑስ የተመሠረተውን ‹‹ጆይ የኦቲዝም ማዕከል›› በኦቲዝም ላይ መሥራት መጀመሩ ግን ከአመለካከት ጀምሮ በኦቲዝም ላይ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል።

የአቶ ዘሪሁን የበኩር ልጅ ናታንም ማዕከሉን የተቀላቀለው ገና ከአምስት ዓመት እድሜው ጀምሮ ነበር። ናታን በዚህ ማእከል የትምህርት ዕድል በማግኘቱ ብዙ ለውጦች በማሳየት በኦቲዝም ላይ የሚደረጉ ድጋፎች ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ማሳያ ሆኗል።

አቶ ዘሪሁን ከዚህ ቀደም ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲወስዱ የነበረው ፈተና ከባድ ነበር። ዛሬ ግን በኦቲዝም ዙሪያ የሰዎች ግንዛቤ እያደገ መጥቷል። ልጃቸው ናታንም የአስራ ስድስት ዓመት ታዳጊ ሆኗል። ዛሬ ላይ አባት በልጃቸው እድገት ደስተኛ ናቸው። በትናንትናና በዛሬ መካከል ያለውን ለውጥም ‹‹የንጋት ብርሃን ነው›› ሲሉ ይገልጹታል።

በአብዛኛው ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን የሚያሳድጉት እናቶች ናቸው። ያውም ለብቻቸው ሆነው። አቶ ዘሪሁን ግን ከባለቤታቸው ጋር በመተጋገዝ ለልጃቸው ዕድገት የቻሉትን ሁሉን አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው። አሁን ወደ ጉርምስና ዕድሜ እየተጠጋ ያለውን ናታንን ከሥነ ተዋልዶ ጋር ያሉትን ነገሮች ለማስተማር አባት የድርሻቸውንን እየተወጡ ይገኛሉ። ሌሎች አባቶች ማህበራዊ መገለል ይደርስብናል የሚል ፍራቻቸውን ወደ ጎን ትተው ለጆቻቸውን ተንከባክበው ማሳደግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

ዛሬ ላይ ከኦቲዝም ጋር ተያይዞ ልጆቹ ከቤት አይውጡ የሚለው ሃሳብ ተቀይሯል። ብዙዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል። ከተደበቁበት የወጡት ልጆቹ አድገዋል። ወጣት ሆነዋል። ለአቅመ ሄዋንና አዳም ደርሰዋል። እናም ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ እንዲያገኙ ምን ይሠራ? ምን ይደረግ? ወደሚል ሃሳብ ተደርሷል።

አቶ ዘሪሁን ልጃቸው የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃ እንዲያገኝ የአቅማቸውን እየሞኮሩ ነው። በቀጣይም ልጃቸውና ሌሎች ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች የበለጠ ለውጥ እንዲያመጡና በሥነ ተዋልዶ ጤና በኩል በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ህይወታቸውን እንዲኖሩ ይመኛሉ። ምንም እንኳን የኦቲዝም ማዕከላትን ከፍተው በበጎ ሥራ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ቁጥራቸው እየጨመረ ቢገኝም እንደ ሀገር የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ መንግሥት መደገፍ እንዳለበት ይናገራሉ።

ከዚህ ሃሳብ ጋር ተያይዞ የኦቲዝምና ተዛማጅ የአእምሮ እድገት እክል ያሉባቸው ዜጎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲደገፉ ለማስቻል እራሱን የቻለ መዋቅር በማደራጀት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ችግራቸውን ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስፔሻሊቲና ሪሀብልቴሽን ዴስክ ተወካይ ዶክተር ጎበና ጎዳና ይገልፃሉ፡፡

ዶክተር ጎበና የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ‹‹ድምፅ አልባ የኦቲዝም ልጆችን ማብቃት›› በሚል መሪ ሃሳብ የተከበረው ኦቲዝም ያለባቸውን ዜጎች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በሌሎች መስኮች ተሳትፏቸውን ከፍ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን ይጠቁማሉ። የዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ2007 እንዲከበር ተወስኗል። ከውሳኔው በመነሳት ግንዛቤ በመፍጠር የኦቲዝምና ተዛማጅ ችግሮች ያለባቸው ዜጎች መሠረታዊ መብታቸው እንዲጠበቅና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑንም ያብራራሉ።

የኒያ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ እሌኒ ዳምጠው እንደሚናገሩት፤ ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረ ሃያ ሁለት ዓመት ሆኖታል። ከዛሬ ሃያ ሁለት ዓመት በፊት ታዝለው፣ታስረው እና በር ተቆልፎባቸው የነበሩ ልጆች ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል። ይህም ምግብ ራሳቸውን ችለው እንዲመገቡ፣ ልብሳቸውን በትክክል እንዲለብሱ፣ ራሳቸውን ችለው መጸዳጃ ቤት እንዲጠቀሙና ሌሎች መሰል ሥራዎችን ያካትታል። ልጆቹ ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ብዙ ወላጆች በተለይም እናቶች ያቋረጡትን ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ፤ ሥራ ውለው እንዲገቡ ማድረግም ተችሏል፡፡

ኒያ ፋውንዴሽን የተለያየ ችሎታ ያላቸውን ልጆች በማዕከሉ ይዟል። ልጆችን አስተምሮ ካስመረቀ በኋላ አስራ ሁለቱ በፋውንዴሽኑ ተቀጥረው እንዲሰሩ አድርጓል። ከወላጆቻቸው ጋር ሥራ የሚሠሩ ልጆችም አሉ። በርካቶችም ወደ ትምህርት ቤት ገብተዋል። ዛሬም ወደ ማዕከሉ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ያሉ ልጆች ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነም ነው ሥራ አስኪያጇ የሚናገሩት።

ግንባታው ከአስራ ስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረውን የኒያ ፋውንዴሽን በማስገንባት ላይ የሚገኘው የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በከፊል ለምርቃት ይበቃል። የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ 500 ለሚሆኑ ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችለው ወይዘሮ እሌኒ ይናገራሉ። የሚያዚያ ወር የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር መሆኑን ምክንያት በማድረግ በክልሎች በጅማ፣ በመቀሌ እና በድሬዳዋ የኦቲዝም ማዕከላትን በመቋቋም የሚሠሩ ተቋማትን ለማስተማር እና ለመደገፍ እንደሚሠራም ያስረዳሉ።

ዶክተር አሊ ሳዲ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። በተጨማሪም በላይት ፎር ዘወርልድ ኢንተርናሽናል የአካቶ ትምህርት አማካሪ ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት አብዛኛው አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት አይመጡም። ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ደግሞ ምን ያህሎቹ ወደ ትምህርት ቤት እንደመጡ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። ከኦቲዝም ጋር ተያይዞ ጥሩ ሥራ እየሠሩ ያሉት በማዕከል ወይም ከግለሰብ ተነሳሽነት የሚከፈቱ ድርጅቶች ናቸው።

ከኦቲዝም ጋር ሚኖሩ ልጆች የተግባቦት ወይም የኮሙዩኒኬሽን ብሎም ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለመቀላቀል ችግር ይታይባቸው እንጂ እንደ ማንኛውም ልጅ ግን አካላዊና ስሜታዊ እድገት አላቸው። ይህንን ያወቁ አንዳንድ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር ዝንባሌ ሊታይባቸው ይችላል። እነዚህን እና መሰል ችግሮችን በመረዳት ወላጆች ከሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በግልጽ ማስተማር ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ሰፊ ውይይቶች ማድረግ ይገባል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You