ኢትዮጵያ በገፀ ምድርና በከርሰ ምድር ውሃ የተሞላች ለምለም ሀገር ነች። ገበሬዎቻችን ግን የክረምትና የበልግን ዝናብ ጠብቆ ሰብል ከማምረት የዘለቀ በመስኖ የማምረት ልምድ እምብዛም የላቸውም።
ባለፈው ዓመት በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመስኖ የተመረቱ ሰብሎች መታየታቸው ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው። ዘንድሮም በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ መመረቱን በዚህም 20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ኢትዮጵያ በገፀ ምድር 122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሲኖራት፤በከርሰ ምድርም ከፍተኛ የውሃ ክምችት አላት። ጌታቸው ወልዩ ‹‹የዓባይ መዘዝ›› በሚል መጽሐፋቸው፣ ግብፅ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር እንዲሁም ሱዳን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬታቸውን የዓባይን ወንዝ ተጠቅመው በመስኖ እንደሚያመርቱ ጠቅሰዋል። የተመድ ምግብና እርሻ ድርጅት በ2015 ባወጣው መረጃ ግብፅ አራት ነጥብ 42 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ እያለማች መሆኑን ያስረዳል።
በመስኖ ሰብል ማምረት ልምድ በዓለም ቀዳሚዎቹ ግብፅና ሜሶፖታሚያ መሆናቸውን በመስኖ ዙሪያ የተጻፉ ሰነዶች ያሳያሉ። ሜሶፖታሚያ ጤግሮስና ኤፍራጥስ ወንዞችን ግብፅ ደግሞ ዓባይን በመጠቀም ያለሙ ነበር። ይህም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከስምንት ሺህ ዓመታት በፊት ነበር።
ግብፅ የዓባይን ተፋሰስ በመጥለፍ ወደ ማሳዎች በማድረስ በመስኖ ሰብል ታለማ እንደነበር ”Easy Irrigation” በድረ ገፁ ያወጣው መረጃ ያሳያል። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3100 ዓመት ደግሞ ግድቦች ገድበው፤ ሰፊ የመስኖ ፕሮጀክት ሠርተው እስከ 20 ኪሎ ሜትር ውሃ እያቆሩ ያለሙ እንደነበርም የታሪክ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት መስኖ የሚለውን ቃል ፣ሰነወ፣ ቦይ ፣የውሃ መሄጃ፣ውሃ የጠጣ ዝሪት ፣ሰብል፣መስክ ብሎ ይተረጉመዋል። ቃሉ ሲበዛ ‹‹መስኖዎች›› ይሆናል። መስኖጌ በወግዳ ክፍል ያለቀበሌ መስኖ ያለባት ምድር ማለት ነው። መሰነ ሲል መስኖ አወጣ፤አቦየ ማለት ነው በሚል ይፈታዋል።
ስለ ሀገራችን በመስኖ የማልማት ልምድ አስመልክቶ ወርልድ ዳታ አትላስ ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ በ2021 በመስኖ 858 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መጠቀሟንና በ2002 ከነበረችበት 328ሺህ ሄክታር በብዙ መሻሻሉን ያስረዳል። ይህም የመስኖ ልማት አጠቃቀሟ በአማካይ በየዓመቱ በ5ነጥብ 26 በመቶ እያደገ መሆኑን ነው። ይህም ሆኖ ግን እውነታው ከግብፅ ጋር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በያዝነው ዓመት በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች የደረሰ የበጋ መስኖ ስንዴን ለመሰብሰብ እየተሠራ ባለው ሥራ በባህላዊ መንገድ 620 ሺህ 563፣ በኮምባይነር 162 ሺህ ስድስት ሄክታር መሬት እስከ መጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት በመስኖ ለምቷል። በመስኖ ተመርቶ ከተሰበሰበው ውስጥ 20 ሚሊዮን 213 ሺህ 611 ኩንታል ምርት መገኘቱን ግብርና ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሰጠው መረጃ ያሳያል። ይህም በቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች 782 ሺህ 569 ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን ያስረዳል።
በድህነት እየተጎሳቆለች ላለችው ኢትዮጵያ ዜጎቻችን የመስኖ አጠቃቀም ልምዳቸውን እያሳደጉ መሄድ አለባቸው። ይህም መንግሥት ከውጭ የሚያስገባቸውን የግብርና ምርቶች በማስቆም የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያድን ነው። በተጨማሪም በሰብል ምርት ላይ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትም የሚኖረው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው።
”www.statista.com” በድረ ገፁ ባወጣው መረጃ ግብፅ ከ2011 እስከ 2020 ለግብርናው ዘርፍ መስኖ ልማት የተጠቀመችውን የውሃ መጠን አስቀምጧል። ለአብነት ያህል በ2016 43ሺህ 658ነጥብ 77 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ተጠቅማለች።
ይህን ያህል የመስኖ ውሃ መጠቀም የቻለችው የኢትዮጵያ ስጦታ በሆነው ዓባይ መሆኑን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ይሆንብኛል። ከዚህ በበጎ ቅናት ተነሳስተን ዓባይን ጨምሮ ባሉን ወንዞቻችን በመስኖ ሰብልና አትክልት ምርቶችን በመትጋት፣ የማምረትን ነገር ባህል በማድረግ፣ ድህነትን መዋጋት እንዳለብን ይሰማኛል።
ግንባታው ከተጀመረ 13ኛ ዓመቱ የሆነው የዓባይ ግድብ ግንባታ በያዝነው ዓመት በክረምቱ ወራት ሲጠናቀቅና ሥራውን ሲጀምር ደግሞ ኢትዮጵያ ለዜጎችዋ ኤሌክትሪክ ከማዳረስ አልፋ ለጎረቤት ሀገሮች በውጭ ምንዛሪ ኤሌክትሪክ በመሸጥ የተሻለ ገቢ የም ታገኝበትም ነው።
ግድቡ በሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ዓሳ በማምረት ይጠቀማሉ። ቱሪስቶቹም ሐይቁን እና ግድቡን ለመጎብኘት ስለሚሔዱ ለሀገሪቱ እና ለአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተጨማሪ ገቢ ያመነጫሉ። ከሐይቁም በመስኖ ተጠቅመው ሰብልና አትክልት ሊያመርቱ እንደሚችሉም ይጠበቃል። ይህም የሀገሪቱን በመስኖ የማምረት ባህል ያሳድጋዋል፤ድህነትና ሥራ አጥነትን የምትዋጋበት ተጨማሪ አቅም ይሆናታል ተብሎ ይታመናል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ባወጣው መረጃ እ.ኤአ. ከ2020 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ምርት ያመረቱ የአፍሪካ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ በሁለተኝነት ደረጃ ትገኛለች። ዘርፉ ከሴራሊዮን የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (GDP) 60 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እና ኒጀር በግብርና፣ ደን ልማትና በዓሳ ምርት በቅደም ተከተል 38 በመቶ እና 36 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርታቸውን ይሸፍናል።
በሰብል እህል አምራችነት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በፊታውራሪነት ስትጠቀስ ናጄሪያ ፣ግብፅና ደቡብ አፍሪካ እንደሚከተሉዋት የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ያወጣው መረጃ ያስረዳል።
በቆላማ ቦታዎች በመስኖ እንደሚመረቱ ምርቶች ሁሉ በከተሞችም ይህንኑ የከተማ ግብርና ሥራ አጠናክረን ድህነትን እና የዋጋ ንረትን የምንዋጋባቸው ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ ነው። ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያላት አቅም ከፍተኛ የመሆኑ እውነት ከሕዝብ ቁጥሩ መጨመር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲደመር የመስኖ ልማቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላካች ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም