ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የናይል ወንዝ 85 በመቶ የሚሆነውን የውሃ መጠን ድርሻ በሚገብረው ዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባ ነው። የአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ከሱዳን ጋር ከሚዋሰነው ድንበር በስተደቡብ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ከ1.6 ኪሎ ሜትር በላይ እርዝማኔ እና 145 ሜትር ከፍታ አለው። ሙሉ በሙሉ ግንባታው በ2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የሕዳሴ ግድብ 13 ዓመታትን በግንባታ ላይ ቆይቷል። ከ4ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሀገሪቷ እና የሕዝቧ ሀብት የፈሰሰበት ይህ ግዙፍ ግድብ የኢትዮጵያውያን የመቻል አብነት ነው።
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን እየገነባች ያለችው በጨለማ ውስጥ ያለው 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን እንዲያገኝ ነው። ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም በእጥፍ በማሳደግ ለተቋማት የማያቋርጥ የኃይል አቅርቦት ለማቅረብ እና ልማቱን በማሳደግ ተስፋ ተጥሎበታል። በኃይል ሽያጭም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት ለኢኮኖሚው ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል።
ኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭታቸውን የተወጡበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነበር የተቀመጠው። ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በሦስት ሥራዎች ማለትም በሲቪል ሥራዎች ፤ በኤሌክትሮ መካኒካል እና ሃይድሮ-ስቲል ስትራክቸር ሥራዎች እና ለግድቡ ሥራ አመቺነት የደን ምንጣሮና መኖሪያቸውን የለቀቁትን ሰዎች የማቋቋም ሥራዎች አከናውኖ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ አፈፃፀሙን 95% በማድረስ ለመጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል።
የኢትዮጵውያን የሕዳሴ መሠረት የሆነው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ባለፉት 13 ዓመታት አይረሴ ክንውኖች ተፈፅመውበታል። ከግንባታ ሂደቱ አበይት ክንውኖች መካከል ግንቦት 2005 ዓ.ም የዓባይ ወንዝ አቅጣጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀየረ ፤ መጋቢት 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል የሦስትዮሽ የመርሆች ስምምነት ተፈረመ ፤ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት ሐምሌ 2012 ዓ.ም፣ ሁለተኛውን ነሐሴ 2013 ዓ.ም፣ ሦስተኛውን ነሐሴ 2014 ዓ.ም እና አራተኛው ጳጉሜን 2015 ዓ.ም በስኬት ተከናውኗል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ የተሸፈነ ሲሆን እስከ አሁን ለግድቡ ግንባታ ከ18 ቢሊየን 973 ሚሊዮን 822 ሺህ ብር በላይ በሕዝባዊ መዋጮ ተሰብስቧል። ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያዊያን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው ለመሄድ የሚያስችላቸውን ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሚጥል ነው።
የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት በየዓመቱ በ25 በመቶ አካባቢ እያደገ በመሆኑ ትላልቅ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ካልቻለች ዕድገቷ ቀጣይነት አይኖረውም። ታላቁ የሕዳሴ ግድቡ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከ70 በመቶ በላይ ከማሳደጉም ባሻገር በከፍተኛ የዓሣ ምርትና በቱሪዝም ተደራሽነት ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ግድቡ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውኃ የሚይዝና 1680 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ስለሚኖረው በዚህ ሰፊ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ከፍተኛ የሆነ የዓሣ ሀብት ማፍራት የሚያስችል ይሆናል። ጥናቶች እንዳመላከቱት በዓይነታቸው ለየት ያሉ ከዘጠኝ በላይ የዓሣ ዝርያዎችን ለማርባት በጣም ምቹ እንደሚሆን እና በዓመት ከ10ሺ ቶን በላይ ዓሣ የማምረት አቅም ይኖረዋል።
ከተጀመረ 13ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ፣ በኢትዮጵያውያን የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ ከተገነቡ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የመጀመሪያው ተደርጎ ይጠቀሳል። በተለይም የግድቡ ግንባታ ጅምር እስከ አሁን ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ አልፎ በመገባደድ ላይ መሆኑንም ኢትዮጵያ በፅናት እየተሻገረች ስለመሆኗ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ውሃውን ለብቻችን እንጠቀም የሚሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ያላሳተፉ የቅኝ ግዛት ውሎች ዳግም ለማጽናት የዓረብ ሊግን በመጠቀም ዘመቻዎች ሲያደረጉ ቢቆዩም የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችለዋል።
ኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም ላይ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ግብፅና ሱዳን ተቃውሞና ስጋታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ እስከ ዛሬ ይደመጣሉ። ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ላለፉት አሥር ዓመታት በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ሦስቱንም ሀገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ውድ አንባቢያን ዛሬ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማንሳታችን ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህ ለሀገርና ሕዝብ የሰሩና ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ የባለውለታዎቻችን በሚመሰገኑበት ዓምድ የምናነሳቸው 13 ዓመታትን በጉባ ተራሮች ለኢትዮጵያ ሕዳሴ የደከሙ ኢትዮጵያውያንን ስለሚናመሰግን እንጂ።
የአየር ጠባዩ እጅግ ከባድ በሆነውና ከ45 እስከ 52 ዲግሪ ሙቀት በሚያስመዘግበው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው ጉባ ተራራ የከተሙ ከ13 ሺህ በላይ የግድቡ ሠራተኞች የአየር ሁኔታው ሰይባግራቸው፤ ክረምትና በጋ ሳይሉ በመሥራት ግድቡን እውን አድርገውታል።
ፀሐይ እንጂ እረፍት በሌለበት፤ ምሽት እንጂ እንቅልፍ በማይታሰብበት የጉባ ተራራ ታሪክን ለመሥራት ላባቸውን ያፈሰሱት የግድቡ ሠራተኞች የፕሮጀክቱ መሠራት ከተጣለበት መጋቢት 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁኗ ቀን ድረስ ከዓድዋ በመቀጠል ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያስተሳሰረውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በብዙ ፈተናዎች በማሰለፍ ከፍፃሜው እያደረሱት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያውያን የብርሃን ተስፋ የጋራ ታሪካቸው ማህተም፤ የመተባበርና የአንድነት ውጤት ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ እውን ለማድረግ ዓባይ ለሀገሩ ልማትና ጥቅም እንዲውል ለማድረግ በጉባ ሰማይ ስር ብርቱ እጆች ያለ እረፍት በትጋት ሀገራቸውን እያስቀደሙ ለአካባቢው የአየር ሁኔታ ሳይንበረከኩ ዓባይ ለባዕዳን ብቻ ሳይሆን ለወገኑም ጭምር ሀብት እንዲሆን ለማድረግ ይረባረባሉ።
ለነገ ትውልድ የሚሻገር ሀገርን የሚያስጠራ ይህንን ትውልድ ደግሞ የሚያስመሰግን ግዙፍ ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረጉ የሚገኙት የሕዳሴ ግድብ ሠራተኞች ከአስቸጋሪ የአካባቢው መልከዓ ምድርና የአየር ሁኔታ ግብግብ እየገጠሙ ዓባይን ለሀገሩ እንዲገብር ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ እስከዛሬ ዘልቀዋል።
ከጅማሬው እስከ አሁን ድረስ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሙያው ሀገሩን እያገለገለ የሚገኘው ተስፋዬ ጥሩነህ የተባለ ሠራተኛ ከወራት በፊት ለአንድ የሀገር ውስጥ ሚዲያ በሰጠው አስተያየት እንደሚለው፤ «ሕዳሴ የኢትዮጵያ ካስማ በመሆኑ ከሌሎች መሰል ሥራዎች ይለያል፤ በዚህ ሥራ ዐሻራ ማኖር ደግሞ ለልጅ ልጆች የሚናገር ታሪክ ማስቀረት በመሆኑ ሁሉም የግድቡ ሠራተኛ ከገንዘብ በላይ ታሪክን እያኖረ በመሆኑ የዚህ ታሪክ አካል መሆኑን በማስቀደም ነው በዚህ ሥራ የሚሳተፈው» ይላል።
ሌላኛው ከግድቡ ጅማሮ ላለፉት 13 ዓመታት በሲቪል ምህንድስና ሙያ በዚህ ፕሮጀክት ተሳትፎ ያደረገው ያሬድ እንደሚናገረው፤ ግድቡ አንድ ተብሎ ሥራው ከተጀመረበት እስከ አሁን ድረስ በሁሉም የግድቡ አካላት የግንባታ ሂደት ተሳትፎ አድርጌያለሁ ይላል። ሥራው ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ስጀምር ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርስ አይመስልም ነበር የሚለው ያሬድ፤ በየጊዜው የሚታዩ ለውጦች ግን ተስፋ የሚያሰንቁ በመሆናቸው ዛሬ መድረስ ችለናል ይላል።
ስለ ሕዳሴ ግድብ በቃላት መግለጽ በቀላሉ የሚቻል አይደለም የሚለው ያሬድ፤ «ነገ ለትውልድ የሚናገር ታሪክ እንደመሥራት ደስታ የሚሰጥ ነገር ስለሌለ ሁሉም የዚህ ግንባታ አካል የሆነ ሠራተኛ ከሚያገኘው ገንዘብ በላይ የ120 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አደራ እንዳለበት ሰው ታሪክ ለማኖር ነው የሚሟገተው» ይላል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙዎች መስዋዕት ሆነው እውን ያደረጉት ፕሮጀክት ነው። በሕዳሴ ግድብ ለ12 ዓመታት ሲሰራ የነበረው አቶ ምኒችል ዓለሙ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። በሥራ ላይ በደረሰበት የሥራ ላይ አደጋ ያረፈው ምኒችል ዓለሙ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ መሠረተ ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ለ12 ዓመታት ያክል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ዐሻራውን አስቀምጧል። በሥራ ምክንያት በደረሰበት ደንገተኛ አደጋ ወደ አዲስ አበባ ተልኮ ሕክምናውን ሲከታተል የቆየው ግንቦት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ሌላው በዚህ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ፕሮጀክት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን የሀገር መከላከያ የሠራዊት አባላት ናቸው። የሠራዊቱ አባላት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቀጠና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖረው እና ግንባታው ያለ አንዳች መስተጓጎል መቀጠል እንዲችል ሃያ አራት ሰዓት በተጠንቀቅ ቆመው ለግድቡ ግንባታ ስኬትና ለኃይል ማመንጫው እውን መሆን ጋሻነቱን እያረጋገጠ ዛሬ ደርሷል።
በሕዳሴው ግድብ ቀጠና በምድርም ይሁን በሰማይ ለትንኮሳ የሚያንዣብብና ለጥቃት የሚቃጣ ካለ የማያዳግም ምላሽ በመስጠት የግድቡ ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ ለመላው ሀገሪቱ ሰላም ለማረጋገጥ የሕይወት እና የአካል መስዋዕትነት ከመክፈል በዘለለ፤ በምህንድስና ዘርፉ አማካኝነት ለግድቡ የግንባታና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ግብዓቶችና ቁሳቁሶች የሚቀርቡበትን መንገድ በማመቻቸት ጉልህ ሚና አበርክቷል።
መላው የሀገሪቱ ሕዝብ በብሔር፣ በቋንቋ ወይም በአካባቢው ሳይገደብ በገንዘቡ ተሳትፎ ያደረገበት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው። ከዚህ ባለፈ የግድቡ መሠረት ከተጣለበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን የመሩ መሪዎች ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም በፅናት በመቆምና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሸብረክ ባለማለት ከሀገሪቱ ሕዝብ የተጣለባቸውን አደራና የመሪነት ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተዋል።
በተጨማሪም የግድቡ ተደራዳሪዎች በተለይ ግብፅ የኢትዮጵያን አንድ ደረጃ ከፍ ማለት ባለመፈለግ ብቻ የከፈተችውን ምክንያታዊ ያልሆነ መከራከሪያ ከአፍሪካ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ በመሞገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው። ሌላው የጥበብ ባለሙያዎች ከግድቡ ጥንስስ እስከ አሁን ሕዝቡ በሚችሉት ሁሉ ጥበባዊ አቅማቸውን ለግድቡ በማዋል እና ሕዝቡ ውስጥ የመነቃቃት ስሜት እንዲኖር በማድረግ ረገድ የነበረቸው ሚና የጎላ ነበር።
የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁ ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ እግር በእግር በመከታተል ለህብረተሰቡ መረጃ በማድረስ የነበራቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህ ባለፈ ግብፅ ግድቡን በተመለከተ የምታሰራጫቸውን መሠረት ቢስ ወሬዎች በማጋለጥና እውነታውን ለዓለም ሕዝብ በማሳየት ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ እዚህ መድረስ ታላቅ ዐሻራ አኑረዋል። ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የነበራቸው ተሳትፎ የላቀ ነው። ከዚህ ባለፈ በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ግድቡ መሬት ላይ ያለውን እውነት እንዲረዳ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ከሁሉም በላይ የዚህ ግድብ ዋነኛ አንቀሳቃሽና ልዩ ተሸላሚ ሰፊው ኢትዮጵያ ሕዝብ ነውና ምስጋና ይገባዋል።
የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል ከሆነው ዓድዋ በመቀጠል በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘንድ አንድነትና ትብብር በተግባር የታየበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ፈተናና መሰናክሎችን አልፎ ከመገባደጀው ደርሷል። እኛም በግድቡ የ13 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በተለያየ መልክ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት ለማመስገን እንወዳለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም