
ታዋቂው የ63 ዓመቱ ባህላዊ ቄስ የ12 ዓመት ታዳጊ ማግባታቸው በጋና ትልቅ ቁጣ ቀስቅሷል። ኑሞ ቦርኬቴ ላዌህ ትሱሩ 33ኛ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደ የሠርግ ሥነ-ሥርዓት ነው ታዳጊዋን ያገቡት። ምንም እንኳ በርካታ ትችት እየዘነበ ቢሆንም የማህበረሰብ መሪዎች፤ ሰዎች ባህል እና ወጋችን አይገባቸውም የሚል ምላሽ እየሰጡ ነው።
በጋና ከ18 ዓመት በታች ጋብቻ መፈፀም ሕጋዊ አይደለም። ምንም እንኳ በሀገሪቱ ያለዕድሜ ጋብቻ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም በአንዳንድ ሥፍራዎች ይህ ሲከናወን ይታያል።‘ገርልስ ኖት ብራይድስ’ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት እንደሚለው በጋና 19 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች 18 ሳይሞላቸው ነው ትዳር የሚመሠርቱት።
5 በመቶ ደግሞ ገና 15 ዓመት ሳይሆናቸው ይዳራሉ። ቅዳሜ ዕለት የነበረውን ፕሮግራም የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች እንደሚጠቁሙት በርካታ የማህበረሰብ መሪዎች ታድመዋል። ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ ጋናዊያን ቁጣቸውን እያሰሙ ነው።
በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት አንዲት ጋ በተሰኘው ቋንቋ ንግግር ያሰሙ ሴት፤ ታዳጊዋ ባሏን በሚማርክ መልኩ እንድትለብስ ሲመክሩ ይደመጣሉ። አክለው የሚስት ተግባራትን ለመከወን እንድትዘጋጅ እና በስጦታ የተሰጣትን ሽቶ ተቀብታ ለባሏ ወሲብ ቀስቃሽ ሆና እንድትገኝ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ይህ ንግግር በጋናዊያን ዘንድ ያለውን ቁጣ እጅግ ያጋለው ሲሆን፤ ጋብቻው እንዲሁ ለወግ ብቻ የተዘጋጀ አይደለም ማለት ነው የሚል ሃሳብ ጭሯል። ብዙዎች መንግሥት ጋብቻውን እንዲያፈርስ እና ትሱሩን የተባሉትን ቄስ እንዲመረምር ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
ታዳጊዋ እና ቄሱ አባል የሆኑበት ኑንጋ የተባለው ጥንታዊ ብሔረሰብ መሪዎች ከተቀረው የጋና ክፍል የቀረበባቸውን ትችት አስተባብለው ትችቱ “ካለማወቅ የመነጨ ነው” ብለዋል። ኒ ቦርቴ ኮፊ ፍራንክዋ 2ተኛ የተባሉ አንድ የማህበረሰብ መሪ እሑድ ዕለት ታዳጊዋ የቄሱ ሚስት ሆና የምትጫወተው ሚና “ባሕላዊ እና ወጋዊ ብቻ ነው” ብለዋል።
ታዳጊዋ የቄሱ ሚስት ለመሆን የታጨችው ከ6 ዓመት በፊት መሆኑን ተናግረው፤ ነገር ግን ይህ ከትምህርቷ እንዳላገዳት ይናገራሉ። ታዳጊዋ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄድ ሥነ-ሥርዓት የቄሱ ሚስት ለመሆን የሚያስችላት ንፅህና እንዳላት ይረጋገጣል። ይህ ሥነ-ሥርዓት ልጅ ወልዶ ማሳደግን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን የምትለማመድበት ነው ሲሉ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ትሱሩ በጥንታዊው የኑንጋ ብሔረሰብ “ግቦርቡ ውሎሞ” የተሰኘ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ቄስ ሲሆኑ፤ ነዋሪነታቸው በዋና ከተማዋ አክራ ነው። ብሔረሰቡን ወክለው መስዋዕት ይፈፅማሉ፤ ይፀልያሉ፤ ባህላዊ ልማዶች እንዲፈፀሙ ያደርጋሉ። የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለአከራካሪው ጋብቻ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ምንም እንኳ የጋና ሕግ ባህላዊ ጋብቻዎችን ቢፈቅድም በባህል ስም የሚደረጉ ከዕድሜ በታች የሚፈፀሙ ጋብቻዎችን አይፈቅድም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም