“ከግል ኢንቨስተሮች ባሻገር የክልሉ መንግሥት በኢንቨስትመንት እየተሳተፈ ነው” – አቶ ማስረሻ በላቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተመሠረተ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል። ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ ያነሳቸው የነበሩ የመልማት ጥያቄዎች በተለይም ግብርናውን ከማዘመን፤ አካባቢው ያለውን የመልማት አቅም በተገቢው መንገድ ከመጠቀም አንጻር የግብርና ቢሮ ምን ሰርቷል?

ክልሉ በሚታወቅባቸው እንደ ቡና፤ ማር፤ ኮረሪማ፤ ግብርና፤ ካለው የተፈጥሮ ጸጋ አኳያ በወተትና ዶሮ እርባታ፤ በሥጋ ምን እየሰራ ነው? በግብርናው ዘርፍ ላይ ያሉ ችግሮችን ከመፍታትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደርና ሥነ ምግባር ዝግጅት ክፍል ከክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ጋር ቆይታ አድርጓል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በአዲስ መልክ እንደመደራጀቱ ቢሮው ምን እድሎች እና ፈተናዎች ገጠሙት?

አቶ ማስረሻ፡- አዲሱ ክልል በስድስት ዞኖችና 41 ወረዳዎች የተመሠረተ ነው። ክልሉ ከተመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱ የሞላው በቅርቡ ነው። በርግጥ ዞኖችና ወረዳዎች አዲስ ቢሆኑም የክልሉ መዋቅር አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች አሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ነባር ዞኖች የተደራጁት ባላቸው ሀብትና አቅም ላይ በመመሥረት ነው።

ለክልል አደረጃጀት አዲስ እንደመሆናችን መጠን ያለንን አቅም በመለየት ባለው ውስን የሰው ኃይል እና የፋይናንስ አቅም ላይ ተመስርተን ፤ የሚፈልገውን የአመራር እና የባለሙያ ቁጥር በመቀነስ ወደ ሥራ ገብተናል። ይህ አሠራር ላይ ችግር ፈጥሯል። አሁን ላይ እያጋጠሙን ካሉ ፈተናዎችም አንዱ ነው። ችግሩን ለመሻገር ካለን አቅም አኳያ ወሳኝ ለሆኑ የሥራ መደቦች ቅድሚያ በመስጠት ባለሙያዎች ሥራዎችን ደርበው እንዲሰሩ እያደረግን ነው።

የሕዝባችን ክልል የመሆን ጥያቄ ትክክለኛ ስለነበር እና ጥያቄው ስለተመለሰለት አመራሩ እና ሠራተኛው ሥራዎችን በቁርጠኝነት ማከናወን እንዲችሉ ተነሳሽነት ፈጥሯል። ይህም በመሆኑ በክልሉ የአቅምና የሀብት ችግር ቢኖርብንም፤ በሀገሪቱ ካሉ ነባር ክልሎች ባልተናነሰ መልኩ ሁሉንም የልማት አጀንዳዎች ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ችግሮችን በመቋቋም በውስን የሰው ኃይል ከነባር ክልሎች ባልተናነሰ መልኩ እየተንቀሳቀሳችሁ ስለመሆኑ ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?

አቶ ማስረሻ፡- ራሳችን በክልል ካደራጀንበት ጊዜ ጀምሮ ችግሮቻችን ተቋቁመን በተለያዩ ሀገራዊ የልማት አጀንዳና ሌሎች ሥራዎች እያከናወን እንገኛለን። በተለይ በግብርና ዘርፉ እንደ ሀገርም የተያዙ የልማት አጀንዳዎችን ከሌሎች ክልሎች እኩል በሆነ መንገድ እየሠራን ነው።

ክልሉ በሀገሪቱ በርካታ ዕምቅ አቅም አላቸው ከሚባሉ ክልሎች ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው። ከዚህ በመነሳት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ሥራዎችን ጀምረናል። በክልሉ ውስጥ በተለይ ከእርሻ እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ በመኸርና በበልግ ከ650 ሺ ሄክታር በላይ መሬት እየታረሰ ነው። በዚህም በዋና ዋና የሚባሉ ሰብሎችን ለማምርት በሚያስችል አቅም ላይ እንገኛለን።

ክልሉ እንደ ሀገር ከኦሮሚያ ቀጥሎ ከፍተኛ የሆነ የቡና አብቃይ ብቻ ሳይሆን የቡና መገኛ ከልል ነው። በክልሉ ከ560 ሺ ሄክታር በላይ የሚሆን የቡና ማሳ አለ። ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ ገና ሊለማ የሚችል ከ480 ሺ ሄክታር በላይ የሚሆን የቡና ማሳ አለ። ከዚህ አንጻር በክልል አጠቃላይ ያለው የቡና ማሳ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ሊጠጋ የሚችል ነው።

በአትክልትና ፍራፍሬ ሲታይ ከ69 ሺ ሄክታር ማሳ በፍራፍሬ ተሸፍኗል። በመኸር በተለይም በአንደኛ፣ ሁለተኛ ዙር መስኖ የለማ ከ67 ሺ ሄክታር በላይ በሚሆን አትክልትና ስራ ስር አምርተናል። ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ከ80 ሺ ሄክታር በላይ የሚሆን የቅመማ ቅመም ማሳ አለ። በቅመማ ቅመም በሻይ ቅጠል ምርት ከ2ሺ 300 ሄክታር በላይ የሚሆን የሻይ ቅጠል ምርት በክልሉ ይገኛል። እንደ ሀገር ሶስት የሻይ ቅጠል እርሻዎች አሉ፡ ከሶስቱ ሁለቱ እርሻ ያለው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እነዚህን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል ።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ጸጋ አንጻር በበጋና በበልግ ምን ያህል ምርት እየሰበሰበ ነው?

አቶ ማስረሻ፡- ከዚህ ቀደም ከዋና ዋና ሰብሎች በመኸርና በበልግ ወቅት ብቻ በአማካይ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኝ ነበር። በዚህ ዓመት የበልግ ወቅት 321ሺ ሄክታር መሬት በማረስ 11 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። በጥቅሉ ከዋና ዋና ሰብሎች በበልግና በመኸር ከ18 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።

በአትክልትና ፍራፍሬ በመኸርና በመስኖ ከምናለማው ቅድም ከተጠቀሰው ወደ 67 ሺ ሄክታር መሬት 16 ነጥብ 4 ሚሊዮን አትክልትና ስራ ስር ምርት ይገኛል። ወደ 69 ሺ ሄክታር በሚጠጋው የፍራፍሬ ማሳ 9 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል፡፡

ቡናም ከተጠቀሰው ሄክታር ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ሺ ቶን የሚሆን ቡና የሚመረት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ45 እስከ 67 ሺ ቶን ቡና በየዓመቱ ለውጭ ገበያ ይቀርባል። በዚህ ዓመት ወደ 69 ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ይህ የሆነው አመራሩ ወደ ሕዝቡ ቀርቦ በመሥራቱ ነው ።

ሌላው ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር የተያያዘው ነው። ክልሉ እንደሚታወቀው ከሞላ ጎደል አረንጓዴ ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የደን አቅሞች ያሉበት አካባቢ ነው። ነገር ግን አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የተራቆቱ በመሆናቸው መልሶ ማልማት ያስፈልጋል። እነዚህን ቦታዎች መልሶ በደን ለመሸፈን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ እንደመነሻ በመያዝ ባለፉት ሁለት ዓመታት አንድ መቶ 80 ሚሊዮን የሚሆን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የተሠራ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ መቶ 75 ሚሊዮን የሚሆን ችግኝ ተተክሏል።

በዚህም የእቅዳችንን 98 በመቶ የሚሆነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነናል። የጽድቀት መጠናቸው 86 በመቶ ነው። ይህም 600 ሺ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተሠራ ነው። በክልሉ በሁለት ቢሮዎች አማካኝነት የአካባቢና አፈር ጥበቃ ሥራዎች ተከናውኗል። አንደኛው በግብርና ቢሮው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ በጀት ዓመት ምን ያህል ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፤ እስካሁንስ ምን ያህል ችግኞች ተዘጋጅተዋል?

አቶ ማስረሻ፡– በዚህ ዓመት ወደ 889 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል እየተሠራ ነው። በዚህም ከ41 ሺ 700 በላይ የሚሆን ሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ዘርፈ ዛፎች ናቸው። ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ያካተተ የዘር ዝግጅት ተደርጓል። ችግኞቹ የሚተከሉት በሁለት ዙር ሲሆን አንደኛው ሚያዝያ ላይ የሚከናወን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሐምሌ ወር የሚከናወን ይሆናል።

በክልሉ ሶስት ሺ 886 የችግኝ ጣቢያዎች አሉ። በእነዚህ ጣቢያዎች የተለያዩ ችግኞች እየለሙ ነው። 71 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ለሚያዝያና ሐምሌ ተከላ ዝግጁ ተደርገዋል። የተለያዩ የደን ዝርያ ያላቸው ወደ ሁለት መቶ 60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ችግኞች በግብርናው ዘርፍ ይተከላሉ። በተጨማሪም በደንና አካባቢ ጥበቃ የሚተከሉ አሉ። ይህም እንደ ክልል በአረንጓዴ ዐሻራ በኩል ያሉንን የጎላ ተሳትፎ የሚያመላክት ነው።

ሌላው እንደ ክልል ከተደራጀን በኋላ አዲስ የሆነው የበጋ መስኖ ስንዴ ነው። በዚህም በመጀመሪያ ዓመት 450 ሄክታር መሬት ለምቷል። በአካባቢው ያለው አንዱ መሠረታዊ ችግር የመስኖ መሠረተ ልማት አለመኖር ነው። በክልሉ ሰፊ መሬት ማልማት የሚችሉ ትልልቅ ወንዞች የሚፈሱበት ሆኖ አንድም የመስኖ መሠረተ ልማት የለም። ይሁን እንጂ ወንዞችን በባህላዊ መልኩ በመጥለፍ ባለፈው ዓመት ወደ ሶስት ሺ 46 ሄክታር፤ በዚህ ዓመት ደግሞ አምስት ሺ ሶስት ሄክታር መሬት በመስኖ እንዲለማ ተደርጓል። ከዚህም መካከል አራት ሺ 500 ሄክታር የሚሆነው መሬት በጂፒኤስ ካርታ ላይ ተሰርቶ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል ከተጀመሩ ሥራዎች መካከል አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው። ክልሉ በዚህ ተግባር ምን ያህል እየሠራበት ነው?

አቶ ማስረሻ፡- የሌማት ትሩፋት ሥራው ከክልል ምስረታው ጋር አብረን ወደ ሥራ ያስገባነው ነው። በክልሉ እንደ ሀገር በተያዘው የሌማት ትሩፋት በወተት፤ በዶሮ ሥጋ፤ በማርና በዓሣ ከፍተኛ ሥራዎችን እያከናወነ ነው። ክልሉ ካለው አቅም አንጻር በተለይም በቀይ ሥጋ ምርት ላይ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠራ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በወተት 504 የሚሆኑ መንደሮችን በመለየት በአራት ዓመት የሚከናወን ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህ ዓመት ከዚህ ውስጥ አንድ መቶ 22 የወተት መንደሮች በመለየት እየተሠራ ነው። በእነዚህ መንደሮች ወደ 14 ሺ 400 የሚሆኑ የወተት የላም አርቢዎችን በማደራጀት ሥራ እየሠራን ነው።

በወተት መንደሮች የሚከናወኑ ሥራዎች ሁለት ናቸው። አንደኛው ዝርያን ማሻሻል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመኖ ልማትን በስፋት በመሥራት ከአራት ዓመት በኋላ በወተት መንደር ውስጥ የሚኖረውን የወተት ምርት ከፍ ማድረግ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ 18 ሺ 209 የሚሆኑ የውጭ ደም ያላቸው ላሞችን በማዳቀል ወደ ስድስት ሺ 256 የሚሆኑ ጥጃዎች ተገኝተዋል። 86 ሺ የሚሆኑ ጊደሮችን ወደ መንደሮች እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡

ሌላው የወተቱ ምርት ሊቀየር የሚችለው በመኖ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። ከዚህ አንጻር 55 ሺ ኩንታል በላይ የሚሆን መኖ ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ ተደርጓል። አሁን ባለው ሁኔታ በወተት ምርት ወደ 222 ነጥብ15 ሚሊዮን ሊትር ወተት አምርተናል።

ዶሮ ጋር በተያያዘ ለአራት ዓመት የሚቆይ እቅድ ተይዟል። በዚህም 703 ላይ መንደሮች ለእርባታ ተመርጠዋል። በዚህ ዓመት 218 መንደሮች ውስጥ ለመሥራት ጥረት ተደርጓል። 21 ሺ የሚሆኑ አርቢዎችን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

በዚህም አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሰራጨት ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ 131 ሚሊዮን እንቁላል ለማግኘት ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት 113 ነጥብ 49 ሚሊዮን እንቁላል መሰብሰብ ተችሏል። ይህም የእቅዱን 86 መቶ ገደማ ነው። የዶሮ ሥጋ ወደ 2 ሺ 24 ነጥብ 5 ቶን የእቅዱን 89 በመቶ መሰብሰብ ተችሏል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በማር ምርት የታወቀ ነውና በማር ምርት ላይ ያለው ሥራስ እንዴት ይገልጹታል? ክልሉ ያለው የዓሣ ምርት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

አቶ ማስረሻ፡– በክልሉ አንዱ አቅም ንብ ነው። በክልሉ ውስጥ የንብ ‹‹ኮሎኒ›› በከፍተኛ ሁኔታ ይገኛል። 970 የሚሆኑ የተለዩ የማር መንደሮች አሉ። ለእነዚህ መንደሮች በዚህ ዓመት 50 ሺ 523 የሚሆኑ ዘመናዊ፣ የሽግግርና የጨፈቃ ቀፎዎችን ማሰራጨት ተችሏል። ከጫካ ወደ ጋጣ የማምጣት ሥራ ተከናውኗል። በዚህም 4ሺ 700 በላይ የሚሆኑ የንብ ጋጣዎችን በመንደሮቹ በማዘጋጀት 26ሺ በላይ የሚሆኑ የንብ መንጋዎችን የማዘዋወር ሥራ ተከውኗል።

በስድስት ወር ውስጥ ወደ 26 ሺ 615 ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ 28 ሺ 946 ቶን የማር ምርት ማምረት ተችሏል። በዓመቱ ወደ 69 ሺ ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ቀሪው 40 ሺ ቶን በሚያዝያ ወር የሚሰበሰብ ነው።

በአካባቢው የዓሣ ምርት ብዙ የሚታወቅ አልነበረም። ይሁን እንጂ ከተለያዩ አካባቢዎች የዓሣ ጫጩቶችን በማምጣት የማለመማድ ሥራ ተሠርቷል። አሁን ላይ “ዓሣን ከጓሮ” የሚል ሃሳብ ተይዞ እየተሠራ ነው። በክልሉ የዓሣ ልማት ለማከናወን 91 መንደሮች ለመገንባት የታቀደ አሁን ላይ በ15 መንደሮች የዓሣ ልማት ሥራዎች ተጀምረዋል። በዘርፉም 979 አርቢዎች ተሰማርተዋል።

በዚህ ዓመት 180 ኩሬዎች ለዓሣ ልማት ተዘጋጅተዋል። ለዚህም ፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር የዓሣ ጫጩት ማመላለሻ ተሽከርካሪ ድጋፍ አድርጓል። ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ብር  ወጪ በማድረግ ቦንጋ ዶሮ እርባታ ማዕከል ውስጥ የዓሣ ጫጩት ማምረቻ ማዕከል ግንባታ ይካሄዳል ።

ከዚህ ባሻገር ክልሉ በቀይ ሥጋ (የበግ፤ የፍየል፤ የበሬ) ከፍተኛ ሥራዎችን እያከናወነ ነው። በጣሙ በከፍተኛ ሁኔታ የተደነቀ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ‹‹ብራንድ›› ያገኘ የቦንጋ በግ አለ። ይህ የበግ ዝርያ በአንድ ጊዜ በአማካኝ እስከ ሶስት ግልገሎችን በመውለድ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ለምግብነት የሚያደርስ ነው። ይህን መነሻ በማድረግ 406 የሚሆኑ የቀይ ሥጋ መንደሮችን በመለየት በበጀት ዓመቱ 88 መንደሮች ላይ፤ ሁለት ሺ 640 አርሶ አደሮችን በመለየት ሥራው ተጀምሯል።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እንደ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲና መሰል ተቋማት ጋር ያለው የቅንጅት ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ማስረሻ፡- ከተቋማት ጋር በቅንጅት ከመሥራት አኳያ በተለይ ከቦንጋ፤ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተለያዩ መስኮች ተባብሮ መሥራት የሚስችሉ ተግባራትን እናከናውናለን። ዩኒቨርሲቲዎቹ በክልላችን ለሚገኙ ባለሙያዎችን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እና የሙያ ማጎልበት ሥራ ከመሥራት ባሻገር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በጋራ እየሠሩ ነው።

ለምሳሌ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሀገርም ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ በምርምር የተደገፉ በተለይም በግብርናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ ነው። በግቢው ውስጥ ከ160 በላይ የወተት ላሞች አሉ። በከተማው ውስጥ የህብረተሰቡን ወተት ፍላጎት እየሸፈነ ነው።

በቡና በአትክልትና ፍራፍሬ፤ በእንሰት፤ ‹‹አፍሪካን እንመግብ›› በሚል መሪ ሃሳብ ፕሮጀክት ጅምሮ በእንሰት ከሀገር አልፎ አፍሪካን መመገብ የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው። በተለያዩ ዞኖችም የተለያዩ ምርምሮችን እያደረገ ነው። ይህም ቢሮአችን በአካባቢያችን ከሚገኙ ዩኒቨርሲዎች ጋር ተባባሮ እየሠራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ እንደ ቡና፤ ኮረሪማ፤ ማርና ቅመማ ቅመሞች መሰል ምርቶች ይታወቃልና ምርቶቹ በተገቢው ሁኔታ በመሰብሰብ የክልሉን ብሎም የሀገርን ገቢ ከማሳደግ አኳያ ያሉ ማነቆዎችን ከመፍታት አንጻር ምን ተሰርቷል?

አቶ ማስረሻ፡- ዋናው የክልሉ ሕዝብ የገቢ ምንጭ ብለን በተራ ቁጥር አንድ ካስቀመጥናቸው መካከል የቡና፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶች ሲሆኑ አትክልትና ፍራፍሬዎች ተከታዩን ሥፍራ ይይዛሉ። በእነዚህ ምርቶች አርሶ አደሮቻችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚዎች ናቸው። በተለይ ቡና ስትራቴጂክ ምርት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የግለሰብ ብቻ ሀብት አይደለም። የመንግሥትም የጋራ ሀብት ነው።

ቡና ሀብቴ ነው ብሎ በዘፈቀደ እንደፈለግን የምንሸጠው እና የምንለውጠው አይደለም። ቡና በግብይት ሥርዓት የሚመራ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግበታል። በግብይት ሥርዓቱ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ ከአመራረቱ ጀምሮ ቁጥጥር የሚያደርግ ግብር ኃይል አቋቁመናል።

የቡና ዋጋው የሚታወቀው ከአበቃቀሉ፣ ከተኛበት፣ ከተሰጠበት፣ ከተያዘበት ኬሻ ጀምሮ ነው። ስለሆነም የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው ለማድረግ እያንዳንዱ ሥራ ጥንቃቄ ይከናወናል። እነዚሀን ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ግብር ኃይሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡

ይህም ሆኖ ግን የዓለም የቡና ዋጋ ከመዋዠቅ ጋር ተያይዞ በሁለት ዓይነት መልኩ ቡናን በሕገወጥ መልኩ ለመሸጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አሉ። አንደኛው ነጋዴዎች ከገበሬው የገዙትን ቡና በሀገር ውስጥ ገበያ በኮንትሮባንድ ለመሸጥ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ናቸው። ሌላው ደግሞ የገበያ አማራጭ ሲያጡ በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩ ነው።

እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ከዓለም አቀፍ ዋጋ መዋዠቅ ጋር የተፈጠሩ ቢሆንም ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰድን ነው። ከዓለም አቀፍ ዋጋ መዋዠቅ በተጨማሪ በቡና ግብይት ሥርዓቱ ቁልፉ ማነቆ እየሆነው ያለው በተለይ በአምራች ባለሀብቱ እና በአቅራቢው በኩል እንደ ሀገርም ሁልጊዜ እየተነሳ ያለው ችግር ከቡና እና ሻይ ባለስልጣን ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ችግር ነው።

በቀጥታ ትስስር በሚደረገው ግብይት ቡና መንገድ ይሸኛል ወይም ይሸጣል። ሽኝት የሚከናወነው “በኢሲኤክስ” እና በቀጥታ ትስስር ነው። ሽያጭ የሚከናወነው ደግሞ “በቨርቲካል ኢንትግሬሽን” በቡና እና ሻይ ባለስልጣን በኩል ነው። ላኪዎች ከሰብሳቢዎች እና ከአምራቾች የወሰዱትን የቡና ምርት በቡና እና ሻይ ባለስልጣን በኩል ከሸጡ ብዙ ጊዜ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን የወሰደውን ቡና ገንዘብ በአግባቡ ቶሎ አይከፍልም። በዚህም ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተፈጠረ ነው።

ይህን ጉዳይ በክልላችን የሚገኙ የቡና ላኪዎችን፣ አምራቾች እና ሰብሳቢዎችን አግኝታችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ። ይህ በቡና እና ሻይ ባለስልጣን በኩል የሚስተዋለው ችግር በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር እየፈጠረብን ነው። ቡና እና ሻይ የሚፈጥረው ችግር ነጋዴው በወቅቱ ምርት መሰብሰብ እንዳይችል ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው።

ነጋዴው በፈለገው ጊዜ እና በአግባቡ ገንዘቡን ባለማግኘቱ ደግሞ አርሶ አደሩ በተገቢው እና በትክክለኛው ሰዓት ቡና እንደይሸጥ እክል ይፈጥራል። ይህ ችግር ዞሮ ዘሮ የሚጎዳው የሀገርን ኢኮኖሚ ነው፡፡

ሌላው የቡና ግብይትን እየጎዳው ያለው ደግሞ ባንኮች ለነጋዴዎች፣ ለአምራቹ እና ለአርሶ አደሩ በሚፈልጉት ልክ ገንዘብ ማቅረብ አለመቻላቸው ነው። ነጋዴዎች በወቅቱ ገንዘብ ካላገኙ በተፈለገው ልክ ቡናን መግዛት እና ለውጭ ገበያ ማቅረብ አይችሉም። ቡና በባህሪው በወቅቱ ግዥ ተፈጽሞ በወቅቱ ካልተሸጠ (ከዋለ ከአደረ) ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ወደ ውጭ ተልኮ የሚያመጣው ገቢ እምብዛም ነው።

ከሞላ ጎደል ቡና በሥርዓት የሚመራ እንደመሆኑ መጠን ሥርዓት አበጅተን እየመራነው ነው። ነገር ግን በግብይት ሰንሰለቱ ላይ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ችግሮች ዘርፉን አልፎ አልፎ ለጉዳት ሲዳርጉት ይታያሉ።

አዲስ ዘመን ፡- ክልሉ በቅመማ ቅመም እና ማር ይታወቃል። ከዚህ አንጻር ያለው የግብይት ሥርዓቱ ምን ይመስላል?

አቶ ማስረሻ፡- በክልል በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ ሀብት ነገር ግን ሌላው የግብይት ሥርዓት ያልተበጀለት ዘርፍ የቅመማ ቅመም እና የማር ግብይት ነው። በርግጥ የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር በቅመማ ቅመም እና ማር ግብይት ላይ ደንብ ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ነው። የግብይት ሂደቱ ምን መሆን አለበት የሚለው ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚጸድቅ ይሆናል።

ይሁን እንጂ የቅመማ ቅመም እና ማርን ግብይት እንደቡና መቆጣጣር አትችልም። ምክንያቱም ቅመማ ቅመም እንደ ቡና የግብይት ሰንሰለት የለውም። አሁን ላይ ሁሉም እንደፈለገ በጉሊት ሳይቀር ሲሸጥ ታገኘዋለህ። በዚህ የተነሳ በክልላችን እርድ፣ ዝንጅብል፣ ኮረሪማ በከፍተኛ ሁኔታ በርካሽ ዋጋ እየተሸጠ ነው። ከቦንጋ ከተማ ወጣ ብለን ወደ ቴፒ ብንሄድ ዝንጅብል በኪሎ እስከ 20 ብር ሲሸጥ ታገኛለህ። እርድም በተመሳሳይ መልኩ።

ከቅመማ ቅመም ምርት ጋር ተያይዞ ምንም የግብይት ሰንሰለት እና ሥርዓት ባለመኖሩ አሁን ላይ በዘፈቀደ ወደ መርካቶ እየተጫነ ነው። ከመርካቶ ደግሞ ወደ ህንድ ሀገር የሚጫንብት እድል አለ። ከህንድ ደግሞ ተፈጭቶ ይመለስና የህንድ እርድ ተብሎ ሀገራችን ላይ የሚሸጥበት ሁኔታ አለ።

ቅመማ ቅመም ለማምረት በምንችልበት አቅም ልክ አርሶ አደሮቻችን እየተጠቀሙ አይደለም። ምክንያቱም በዘርፉ የግብይት ሥርዓት የለውም። ስለሆነም በቅመማ ቅመም እና የማር ግብይት ላይ ሥርዓት ሊፈጠርለት ይገባል።

አርሶ አደሩ እርድ ፣ ኮረሪማ ፣ ጥምዝ የመሰሉ ምርቶችን ከጫካ እና ከጓሮው ሰብስቦ ለገበያ ቀርቧል። ነገር ግን ግብይቱ ሥርዓት ስለሌለው አርሶ አደሩ በትንሽ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዳል። አንዳንዴም የግብይት ሥርዓት ባለመኖሩ አርሶ አደሩ ምርቱ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ተመን ሲያወጣ ይስተዋላል።

በዚህም ኮረሪማ እስከ ሶስት መቶ ብር ድረስ የሚሸጥበት ወቅት አለ። አንዳንዴ ደግሞ ከሚጠበቀው በታች ዋጋ ወርዶ ሊሸጥ ይችላል። ምክንያቱም የግብይት ሥርዓት የለውም። የሕዝባችንን ብሎም የሀገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ በዘርፉ ላይ በጋራ ሥርዓት ማበጀት ይጠበቅብናል።

እንደሚታውቀው በተመሳሳይ ማር በክልላችን በከፍተኛ ደረጃ ይመረታል። ይሁን እንጂ በዚህም ዘርፍ ሥርዓት ስላተበጀለት ክልሉ በተገቢው ልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻልም።

አዲስ ዘመን፡- በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ማስረሻ፡- ክልሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሰፊው እያስተናገደ ያለው የግብርና ኢንቨስትመንትን ነው። ከዚህ አኳያ ኢንቨስተሮችን በምርጥ ዘር ማባዛት ጭምር እያሳተፍን ነው። በርካታ ኢንቨስተሮቻችን ምርጥ ዘርን እያባዙ ናቸው። የክልላችን ትልቁ የትኩረት መስክ ኢንቨስትመንት ነው። ምክንያቱም ኢንቨስትመንት ከሌለ ለውጥ የለም። በመሆኑም ለኢንቨስትመንት ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው።

ይሁን እንጂ በክልላችን ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የገጠመን ችግር አለ። እኛ አካባቢ የሚደረገው ኢንቨስትመንት አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍን መነሻ ያደረገ እንዲሆን እንፈልጋልን። አሁን ያለው ኢንቨስትመንት ልክ እንደ ማዕድን ማውጣት ነው። ቡናን አምርቶ ቡናን ለቅሞ ይዞ የሚሄድ ፤ ሰሊጥ አምርቶ ሰሊጥ ይዞ የሚሄድ። ይህ ለአካባቢው ህብረተሰብ እና ለክልሉ እምብዛም የሚጠቅም አይደለም። እኛ የምንፈልገው በክላልችን ቡና ተክሎ፣ አልምቶ፣ ቆልቶ እና ፈጭቶ “ከፊል ፕሮሰስ” አድርጎ የሚሰራ ባለሀብት ነው።

በርግጥ የኢንቨስትመንት ፈቃዱን ስንሰጥም እስከ አግሮ ፕሮሰሲንግ ድረስ ታሳቢ አድርገን ነው። ግን በተጨባጭ እነዚህን እየተመለከትን አይደለም። የቡና፣ የሻይ፣ የቅመማ ቅመም አምራቾችም ባመረቱት ምርት ላይ እንደ ወርቅ አውጭዎች እና ድንጋይ ከሰል ቆፋሪዎች ያገኙትን ምርት ይዘው የሚሄዱ ከሆነ ከመሬት ግብር ባሻገር ለክልሉ እና ሕዝቡ የሚያስገኙት ጥቅም አይኖርም።

በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት እንዳለብን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር የተጀመሩ ውይይቶች አሉ። በእነዚህ ሥራዎች የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ምርቶቻቸውን አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ሰሚፕሮሰ አድርገው የሚሸጡበትን አሠራር እንዲጀመር እየሠራን ነው።

ከግል ኢንቨስተሮች ባሻገር የክልሉ በኢንቨስትመንት ውስጥ እየተሳተፈ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት የክልሉን የምርጥ ዘር ድርጅት ማቋቋም ችለናል። አሁን ባለው ሁኔታ ክልሉ የራሱን ምርጥ ዘር እያመረተ ይገኛል። በመጀመሪያ ዙር የቦለቄ ምርጥ ዘር አምርቷል። አሁን የቦቆሎ ምርጥ ዘር ያመርታል።

ከዚህ በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ዘርፉም ክልላዊ የልማት ተቋማትንም አደራጅትን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ። እነዚህን በተለያየ መልኩ እየተጠቀምን እንገኛለን ።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በቦንጋ በግ ፣ ማር እና ቅመማ ቅምም አምራች እንደሆነ ነግረውናል። ክልሉ ያሉትን ሀብቶች በማስተዋወቅ ገቢን ከማሳደግ አንጻር ምን ተሰርቷል?

አቶ ማስረሻ፡- የቦንጋ በግን በተመለከተ በአእምሯዊ ንብረት “ፓተንት ራይት” ተመዝግቧል። ልዩ የቦንጋ በግ ተብሎ አምና ላይ በህብረት ሥራ ኮሚሽን በኩል “የብራንዲግ” ሥራ ተሠርቷል። ከዚህ በተጨማሪ ከጊቤ ወዲህ ያሉትን ፍየሎች “ከፋ ጎት” የሚል ስያሜ ተጥቷቸዋል።

ነገር ግን የከፋ በግ ልዩ የመሆኑን ያህል እና ለሀገር ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር የብራንዲግ ሥራዎች ይቀሩናል። ወደፊት በሰፊው መሥራት ይጠበቅብናል። ገበሬው ላይ ትልቁ ችግር ብራንዲግ ነው።

ከማር ጋር በተያያዘ የብራንዲግ ሥራ አልተሠራም። ይሁን እንጂ የቦንጋ ማር ብለው የሚሸጡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች መኖራቸውን ባደረግነው የገበያ ምልከታ አረጋግጠናል። አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ላይ ብትሄዱ የቦንጋ ማር ተብሎ ሲሸጥ ታገኛላችሁ። ውጭ ሀገር ብትሄድ የቦንጋ እና የከፋ ማር ታገኛለህ ። ነጋዴዎች ማሩን ገዝተው ራሳቸው ብራንድ ሰጥተው ሲጠቀሙበት ይታያል። ግን አካባቢውን አያውቁትም።

ይህ የሆነው እኛ ብራንዲግ ላይ ስላልሰራን በመሆኑ መሥራት ይጠበቅብናል። ግን ማሮቻችን የሚያስተዋውቁ ድርጅቶች አሉ። አፕዴት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ውጭ ስንሄድ ታሽጋ የምትሸጥ ከፋ ማር የምትል አለች። ይህ ማር ከዚህ ክልል ነው የሚሄደው። ማቀናበሪያውም እዚሁ ነው ያለው። የሸካን ማርም እንደዚሁ እስከ ውጭ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ድርጅቶች ነበሩ። የክልላችን ማር ይታወቃል። ነገር ግን ከዚህ በተሻለ እንዲታወቅ ለማድረግ ሰፊ ጊዜ ወስደን የማስታወቂያ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል።

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በክልላችን ከሚገኘው በማሳው ላይ ቡና ብቻ ሳይሆን ማርም እያመረተ ነው። ነገር ግን ከዚህ ያመረቱትን ማር ኃይሌ ማር እያሉ ይሸጣሉ። ነገር ግን ማሩ የሚሄደው ከሸካ ነው። ከሸካ እየወሰዱ የሸካ ማር ብለው ቢሸጡ ምን አለበት!?

በአጠቃላይ ብዙ የማር ዓይነቶች ቢኖሩም በቂ የብራንዲግ ሥራዎች ስላልተሰሩ ሰዎች እንደፈለጉ ስም እየወጡ ሲሸጡ ይስተዋላል። ስለሆነም አሁን ላይ በማር ላይ ሰፊ የብራንዲግ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል። የተወሰኑ ድርጅቶች ግን በራስ ተነሳሽነት ለአካባቢው ምርቶች የአካባቢውን ስም እየሰጡ እየሸጡ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

አቶ ማስረሻ፡-እኔም አመሰግናለሁ።

በሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You