የክልል የፍትሕ ተቋማት የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ በቂ ትብብር አያደርጉም

አዲስ አበባ፡- የክልል የፍትሕ ተቋማት ችግር የተገኘባቸውን የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል በቂ ትብብር እንደማያደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የይግባኝና የውሳኔ ማስፈጸም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደነቀ ሻንቆ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ተቀብሎ ምርመራ ያካሂዳል።

አቤቱታ የቀረበባቸው ተቋማት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ውትወታና ማስጠንቀቂያ ይሰጣል ያሉት አቶ ደነቀ፤ ይህ ሳይሳካ ሲቀር ግን ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ጉዳዩ የሚመለከተው ግለሰብ በሕግ ተጠያቂ የሚሆንበት፣ በሚዲያ የሚጋለጥበትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በልዩ ሪፖርት የሚቀርብበት አግባብ መኖሩን አብራርተዋል።

ተቋሙ የሚሰጣቸውን የመፍትሔ ሃሳቦች በመቀበል ረገድ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በአዲስ አበባ መሻሻሎች ቢኖሩም በክልሎች ላይ አሁንም ከፍተኛ ችግር መኖሩን አንስተዋል።

እንባ ጠባቂ ክልሎች ላይ ያሉ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚፈለጉ አስፈጻሚ አካላት ላይ ትብብር በሚጠይቅበት ወቅት የሚያገኘው ትብብር እጅግ አነስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም በአማራ ክልል የባህርዳር ከተማ አስተዳደር፣ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደርና የወራቤ ከተማ አስተዳደር ላይ ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ አቤቱታ ቀርቦ እንባ ጠባቂ ጉዳዩን መርምሮ የሚሰጠውን ማስተካከያ ከመተግበር አኳያ ሰፊ ችግር ታይቷል ብለዋል።

በዚህም ጉዳዩን ወደ ሕግ ለማቅረብ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ የከተማዎቹ ፍትሕ አካላት አስፈጻሚውን ለመጠየቅ የሚያደርጉት ትብብር እጅግ አነስተኛ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

ችግሩ በተጠቀሱት ከተማዎች ላይ የጎላ ቢሆንም በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የሚገኙ የፍትሕ አካላት ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ያላቸው ትብብር አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የፍትሕ አካላት ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር በይበልጥ በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ እንባ ጠባቂም ከፍትሕ አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ማካሄዱን አመላክተዋል።

ወደ ተቋሙ የሚመጡና እልባት የማያገኙ አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሚፈጸሙ ጥፋቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ወደ ፍርድ ቤትና በልዩ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡ መዝገቦች መኖራቸውን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለመመርመር በሚደረግ ጥረት በቂ መረጃ ያለማቅረብና ጉዳዩን መርምሮ የሚሰጠውን ማስተካከያ ተግባራዊ ያለማድረግ ችግር መኖሩን አስታውቀዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You