ጊዜው ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ውበታቸውን እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ በርካታ አማራጮች የቀረቡበት ነው። አሁን ላይ በተለያየ መንገድ ተዘጋጅተው ለገበያ የቀረቡ ሰው ሰራሽ መዋቢያዎች ተቀባይነት ማግኘትም ችለዋል፤ የዚህ ምክንያት ደግሞ ፋሽን ከመከተል ጋር በቀጥታ የሚያያዝ መሆኑን በዙዎቹ ይስማማሉ።
የዛሬው የፋሽን ገጻችን በጸጉር ፋሽን በተለይም ‹‹ሂውማን ሄር›› በሚባለው የጸጉር መዋቢያ ላይ ያጠነጠነ ነው። ይህ አይነቱ የጸጉር ፋሽን በተለያዩ ሀገሮች የተለመደ ሲሆን፣ በተለይ በአፍሪካውያን ዘንድ የለሰለሰ ባህሪ ያለው አርቴፊሻል ፀጉር በስፋት በፋሽንነት ይዘወተራል።
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች በቀኝ ግዛት ስር በወደቁበት ጊዜ ሴቶች ባላቸው የቆዳ ቀለም ብቻም ሳይሆን ባላቸው ተፈጥሯዊ ጸጉር ጭምር እንዲሸማቀቁበት እና እንዲያፍሩበት ይደረጉ ነበር ። በአውሮፓ በሚኖሩበት ጊዜም የተለያዩ የስራ እድሎችን ለማግኘት የሚፈልጉት አፍሪካውያን ነጮችን መስሎ ለመገኘት ይሞካክሩ እንደነበርም ይገለጻል። የአፍሪካውያን ጸጉር በባህሪው ጥቁር እና ጠንካራ ሲሆን አፍሪካውያኑ በነጮቹ ተቀባይነት ለማግኘትና ነጻ ሆኖ ለመንቀሳቀስ በሚል ከፋብሪካ የሚወጡ ቀለም መቀየርያ ኬሚካሎችን፣ የጸጉር ማለስለሻ ምርቶችን ይጠቀሙም ነበር ይባላል።
በሂደት እነዚህ ፈጠራዎች እየተቀየሩ ሰው ሰራሽ ጸጉር በገበያው ላይ ተዋወቀ። ጥቁር እንስቶችም በጸጉራቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው መገለል ለመዳን ምርቶቹን ከመጠቀም ባለፈ እ.አ.አ በ1980ዎቹ ጥቁሮች ባስነሱት አመጽ በራሳቸው ጸጉር የመኩራት እና የመዋብ መብታቸውን ማስከበር ችለው ከእነዚህ የተለያዩ ኬሚካሎች እና ሰው ሰራሽ ምርቶች ራሳቸውን ማላቀቅ የቻሉበት ሁኔታ እንዳለም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ በየጊዜው የሚተዋወቀው ሰው ሰራሽ የጸጉር ምርት በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብቶ አሁን ሰዎች ለመዋብ ይጠቀሙበታል። ከእነዚህ ሰው ሰራሽ ጸጉሮች አንዱ ‹‹ ሂውማን ሄይር ›› የሚባለው ነው። ይህም ሙሉ በሙሉ ከሰው ጸጉር የሚመረት ሲሆን፣ ከተለያዩ ግብዓቶች በፋብሪካ ሂደት ውስጥ አልፈው የሚወጡ ሴንቴቲክ ተብለው የሚታወቁ ተመሳሳይ ጸጉሮችም አሉ። አነዚህን ምርቶች ለዓለም ገበያ በስፋት የሚያቀርቡት ህንድ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ጣልያን የሚገኙበት ሲሆን በዓመት ውስጥ ቀላል የማይባል ገቢን ከዚህ ዘርፍ ብቻ ለሀገራቸው ያስገባሉ።
ወጣት እምነት አሰፋ ምርቶቹን ከተለያዩ ሀገራት በማስገባትና በመሸጥ ስራ ላይ ትገኛለች። ‹‹ ጋሜ ጸጉር›› በሚል ስያሜ የራሷን ሱቅ ከፍታ ሂውማን ሄር እና ሴንቴቲክ የሚባሉ የጸጉር አይነቶችን ትሸጣለች። በዚህ ስራዋም በርካታ ደንበኞችን አፍርታለች። ጋሜ የሚለው ስያሜ በራሱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚገኝ የጸጉር አሰራር አይነት ነው።
እምነት ከልጅነቴ ጀምሮ ስራ በጣም እወድ ነበር ትላለች። ‹‹ይሄን ስራ የጀመርኩት ከሽያጭ ሰራተኞች ላይ ተቀብዬ አትርፌ ራሴ እየዞርኩ በመሸጥ ነበር ›› የምትለው እምነት፣ ይህን ስራ የጀመረችው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት መሆኑንም ታስታውሳለች። ይህንንም በወቅቱ የማኅበራዊ ገጽን በመጠቀም ታስተዋውቅ ነበር። ያኔ የሚሸጥበት ዋጋም አይነቱም ትንሽ እንደነበር ገልጻለች። ‹‹ አሁን ጊዜው ተቀይሮ የተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች መጥተው እዛ ላይ አስተዋውቃለሁ፤ የራሴን ሱቅም ከፍቼ እያስመጣሁ ለመስራት በቅቻለሁ ›› ትላለች።
እንደ ደንበኞቿ ፍላጎት ከብራዚል፣ ከጣልያን እና ከቻይና ምርቶች ታስገባለች። የምርቶቹ ልዩነት ጥራታቸውና ረጅም ጊዜ ለመጠቀም የሚያስችሉ መሆናቸው ላይ ነው ስትል ገልጻ፣ እነዚህ የጸጉር ምርቶች ረጅም ዘንፋላ እና ጥቁር ዛላ ያለው ጸጉር ከመሆን አልፈው በአሁኑ ሰዓት በተለያየ አማራጭ፣ ቀለም፣ በገበያ ላይ ቀርበዋል ስትል ታብራራለች። እነሱም ባንግ፣ በተፈጥሮ ጸጉር ላይ የሚሰፉ፣ ኮፍያ ሆነው ማጣበቂያ የሚያስፈልጋቸው እና የማያስፈልጋቸው፣ ፍሪዝ፣ ዌቭ ዌቭ የጸጉር አሰራርን የሚመስሉ፣ ስትሬት የምንለው ደግሞ በእሳት የተሰሩ ጸጉሮች ናቸው በማለት ታብራራለች።
እሷ እንዳለችው፤ እነዚህ ጸጉሮች ለገበያ ሲቀርቡ በግራም እና በኢንች ልዩነት ይኖራቸዋል። ግራሙ የጸጉሩ ብዛት ሲሆን፣ ለአንድ ሰው የሚያስፈለግው ጸጉርም እስከ 200 ግራም ሁለት ጥንድ ጸጉር ርዝመቱ ደግሞ ከ24 ኢንች እስከ 30 ኢንች ይደርሳል።
ብዙውን ጊዜ ወደ እምነት ሱቅ የሚመጡ ደንበኞች ብዛት እንዲኖረው ስለሚፈልጉ 300 ግራም እና ዌቭ የጸጉር ስታይልን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ከረጅም ጸጉር ይልቅ አጭር ጸጉርን ምርጫቸው ያደረጉ ደግሞ በብዛት ኮፍያ የሚባለው እንዲሁ የሚጠለቀው ጸጉር በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ሲሆን ዋጋውም ከሌሎቹ ወደድ ይላል።
በአሁኑ ሰዓት እንደ ፋሽን ብዙዎች የሚመርጡት የጸጉር አይነት ፍሪዝ ሆኗል። እሱም አንድ ጊዜ ከተሰሩት በኋላ መታጠብ የሚችሉት በመሆኑ ምርጫቸው ያደርጉታል። ታዲያ እነዚህ ሰው ሰራሽ ጸጉሮች ልክ እንደ ሌሎች የኤክትሮኒክስ ምርቶች በእምነት ሱቅ ውስጥ ከአንድ ዓመት ዋስትና ጋር ይሸጣሉ።
‹‹ዋስትና ያስፈለገው ጸጉሩ ሕይወት የሌለውና የማያድግ በመሆኑ አያያዝ ይፈልጋል። ተጠቅመውት ቢበላሽባቸው እኛ ጋ ያመጡታል፤ አስተካክለን እንሰጣቸዋለን ›› የምትለው እምነት አንድ ሂውማን ሄር በጥንቃቄ ከተያዘ እስከ ሁለት ዓመት እንደሚያገለግል ተናገራለች። ከዛ በላይ መጠቀም ለሚፈልጉ ደንበኞቿ ግን ሁለት ሂውማን ሄር ቢኖራቸው ትመክራለች።
በየቀኑ ብዙ ደንበኞችን በእድሜ ክልል ያልተገደበ ፈላጊዎች ታስተናግዳለች ‹‹ አንዴ ካደረጉት ለረጅም ጊዜ ስለሚጠቀሙት መተው ይከብዳቸዋል፤ ስለዚህ ሂውማን ሄር ሱስ የሆነባቸው ደንበኞች አሉኝ›› ስትል ገልጻ፣ ‹‹በወር በሳምንት መጥተው የተለያየ አይነት ይገዙኛል›› ስትል ገልጻለች። እነዚህ ሂውማን ሄሮች በእምነት ሱቅ ውስጥ ከ18 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 45 ሺህ ብር ድረስ እንደየ ግራሙ እና ርዝመቱ ለሽያጭ ይቀርባሉ። በሌሎች ሱቆች እና ስም ባላቸው መሸጫዎች ደግሞ 60 ሺህ ብር እና ከዛም በላይ በገበያው ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ሂውማን ሄሮች ለውበት ተብለው የሚሸመቱ ሲሆኑ በየእለቱ ለመጠቀም ፍላጎት ለሌላቸው፣ ለመግዛት አቅም የሌላቸው፣ ለሰርጓ ቀን ብቻ ለምትፈልግ እንስት በኪራይ መልክ እንደሚቀርብም ሰምተናል። እምነትም ለአንድ ቀን ከአራት ሺህ 500 ብር ጀምሮ ለኪራይ እንደሚቀርብ ጠቅሳ፣ የሚከራዩ ደንበኞች ጸጉሩ የሚሸጥበትን ዋጋ አስይዘው እንደሚከራዩ ነግራናለች።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም