የሚያነቡበት ብቻ ሳይሆን የሚያስቡበት

በሳምንት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጊዜ እሄዳለሁ። የምሄደው ግን መጻሕፍት የሚነበብበት የውስጠኛው ክፍል ውስጥ ሳይሆን፤ የሚታሰብበት፣ ጽሞና የሚወሰድበት፣ ንፁህ አየር የሚገኝበት፣ ጩኸት የሌለበት፣ የውጨኛው ክፍል ቦታዎች አካባቢ ነው።

የውስጠኛው ክፍል ብዙ ጊዜ ተማሪዎች ይበዙበታል። ለዚያውም የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎችን አይቼ ነው። የደንብ ልብስ የሚለብሱት ደግሞ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ናቸው።

የደንብ ልብስ የማይለብሱ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ይኖራሉ ማለት ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ ተማሪዎች ይበዙበታል። እኔ የምሄደውና የዛሬው የአስተውሎት ጉዳዬ ግን የውጨኛው ክፍል ነው። በሄድኩ ቁጥር ከሰዎች ነፃ ሆኖ አግኝቸው አላውቅም።

ዙሪያውን ባሉ ቦታዎቹ ሰዎች በቡድንም፣ በጥንድም፣ በተናጠልም ሆነው ተቀምጠው ነው የማገኘነው። ቀስ ብሎ ከጓደኛ ጋር ለመጫወት ይመቻል፣ ለብቻ ቁጭ ብሎ በጽሞና ለማሰብ ይመቻል። እዚያ የሚያስብ ሰው ምናልባትም የሚጻፍ ነገር ያወጣ ይሆናል።

ቦታው ለማንበብ ብቻ ሳይሆን ለማሰብም የሚሆን ቦታ ነው፤ አብርሆት ቤተ መጽሐፍ! በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ከቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት በዘመናዊ መልኩ የተገነባው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት የማንበብ ባኅልን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በወቅቱ ተነግሯል።

በቅርቡ ደግሞ ከአፍሪካ የቀዳሚነቱን ደረጃ እንደሚይዝ ሲነገርለት ነበር። ይህ ቤተ መጽሀፍ ግን ከማንበብ በላይ ለማሰብም እያገለገለ ነው። አዳራሹ ውስጥ ካለው ከመደበኛው ንባብ በተጨማሪ ለዓይን ማራኪ በሆነው ግቢው ውስጥ ተቀምጠው የሚመሰጡ፣ ሀሳብ የሚለዋወጡ፣ በእጃቸው የያዙትን ነገር የሚያነቡ በርካቶች ናቸው።

ቤተ መጽሀፍ ሲባል ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ንባብ ነው፤ ዳሩ ግን ቤተ መጽሀፉ ብዙ ነገር ነው። ማንበብ ብቻ አይደለም፤ ወይም የተለመዱትን የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የአካዳሚ፣ የልቦለድ…. መጽሐፎችን ብቻ የምናነብበት አይደለም።

ከመጽሀፍነት በተጨማሪ አገርን የምናውቅበት ነው። ታሪክ የሚታይበት ነው። ቤተ መጽሀፉ ሼልፍ ላይ የተደረደረ መጽሀፍ አውርዶ ለማንበብ ብቻ ሳይሆን ቤተ መጽሀፉም በራሱ የኢትዮጵያ የሥልጣኔ አስጀማሪነት ምልክት ነው። የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን የሚያውቁበት ነው። ከሌሎች ቤተ መጻህፍት ለየት የሚያደርገው አገርኛ ነገሮች የሚበዙበት መሆኑ ነው።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙት ቤተ መጽሀፎች አካዳሚያዊና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፉ ይበዙበታል። አብርሆት ግን ብዙ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የተጻፉ መጽሀፎች አሉት።

እኔ እንኳን የማውቃቸው፤ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ የተጻፉ መጽሀፎችን በዓይኔ አይቻለሁ። አብርሆት ቤተ መጽሀፍ አገርኛ መሆኑን የሚያሳየው ሌላው ባህሪው በወቅቱ የገቡ ብዙ መጽሀፎች ከሕዝብ የተሰበሰቡ ናቸው።

ወደ ቤተ መጽሀፉ የገቡ መጽሀፎች ከሕዝብ የተሰበሰቡ መሆኑ ጥቅሙ፤ አሁን ገበያ ላይ የሌሉ የቆዩ መጻህፍትን ለተነባቢ እንዲደርሱ ማድረጉ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አይነት ከ80 ዓመታት በላይ የቆዩ የሕትመት ውጤቶች ያሉት ድርጅት በርካታ አንጋፋ ሰራተኞች አሉት። እነዚህ ሰራተኞች በተለያዩ ዘመናት የገዟቸው መጻህፍት አሏቸው። የእነዚህ ሰዎች መጻህፍት ከዓመት በፊት ለአብርሆት ሲሰጡ አስታውሳለሁ። ስለዚህ አንድ የዚህ ዘመን ወጣት አብርሆት ሲገባ አሁን ገበያ ላይ የማያገኛቸውን መጽሀፎች ያገኛል ማለት ነው። ቤተ መጽሀፉ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከዓመታት በኋላ ያስተዋልኩት ነገር ግን ከንባብ ባሻገርም የሰጠውን አገልግሎት ነው። ንባብ ሲባል ለብዙዎቻችን ትዝ የሚለን በመጽሀፍ መልክ የታተመ ብቻ ነው። ወይም በጋዜጣና መጽሔት የሚነበብ ነገር ብቻ ነው።

እነዚህ ንባቦች ናቸው። ስለእነዚህ ነገሮች ብዙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል። ስንፍና ካልሆነ በስተቀር መጽሐፍ፣ ጋዜጣና መጽሔት ማንበብ ጥሩ መሆኑን ማንም ያውቃል።

አብርሆት ቤተ መጽሀፍ ግቢ ግን ከዚህም ባሻገር ነው። ሰዎች እንዲያስቡ ያደርጋል። ማሰብ ማለት የግድ የግል ሕይወትን ከጫጫታ ነፃ ሆኖ በጽሞና ማሰብ ማለት ብቻ አይደለም። እንደዚያ አይነት ቦታ ሲያዩ ስለአገራቸው ያስባሉ። ያ ቦታ እንደዚያ አምሮ ሲያዩት ‹‹ለምን ሌሎች አካባቢዎችንም እንደዚህ ማድረግ አልተቻለም?›› የሚል ጥያቄ ይፈጥርባቸዋል።

ቀላል ማሳያ እንውሰድ። አብዛኞቹ ወደ ቦታው የሚሄዱ ሰዎች ምቹ ካልሆነ አካባቢ የሚመጡ ናቸው፤ እንደዚያ አይነት ያማረ እና ፀጥ ያለ ቦታ የሚያገኙ አይደሉም። ስለዚህ ምኞታቸው በአካባቢያቸው እና በብዙ ቦታዎች እንደዚያ አይነት ነገር እንዲኖር ይመኛሉ፣ ያስባሉ፣ አቅማቸው የፈቀደውን ያህልም ሌሎችን ያነሳሳሉ። በፊልም ወይም በሌላ የተለያየ አጋጣሚ የሚያዩትን የሰለጠኑ አገራት ቦታዎች ‹‹ለካ እዚህም ማድረግ ይቻላል›› ብለው እንዲያስቡ ያደርጋል።

አብርሆት ቤተ መጽሀፍ አካባቢ ስቀመጥ አንድ የማስተውለው ነገር የሰዎችን ስነ ሥርዓት እየተለማመዱ መሄድ ነው። በእንዲህ አይነት ቦታ ላይ ስነ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ የማወቁ ብዙዎች ናቸው። ለምሳሌ፤ ሳሮችን መርገጥ፣ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ መሄድ፣ ያልተፈቀዱ ነገሮችን ማድረግ ብዙ ጊዜ የሚስተዋል ነው። ይህ የሚያሳየው ብዙዎች እንዲህ አይነት ነገሮችን ያልተለማመዱ መሆኑን ነው።

የአስተሳሰብ ሥልጣኔያችን ነገር በተደጋጋሚ የታዘብነው ነው። እጅግ ግዴለሽ ከመሆናችን የተነሳ መደረግ ያለበትንና የሌለበትን የማገናዘብ ጊዜ እንኳን አንሰጥም። ለምሳሌ፤ ወደ አብርሆት ለመግባት ለእግረኛ መረገጫ የሚሆን ከሲሚንቶ የተሰሩ ምቾ መርገጫዎች አሉ። ከእግረኛ መርገጫው ግራና ቀኝ በእግር ለመንካት የሚያሳሳ ሳር አለ።

ያንን ሳር መርገጥ ክልክል መሆኑን ለማወቅ ማስጠንቀቂያ ማንበብ ወይም የጥበቃ ትዕዛዝ መጠበቅ ያስፈልግ ነበር? ያንን ሳር መርገጥ አያሳሳም? ስለዚህ አብርሆት ቤተ መጽሀፍ እያለማመደ ያለው የንባብ ባህልን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሥልጣኔን ነው።

በእርግጥ ሥልጣኔም የሚመጣው በንባብ ነው። ዳሩ ግን ወረቀት ላይ ያለ ጽሁፍ ከማንበብ ባሻገር መሰልጠንን በተግባር ለማለማመድም እያገለገለ ነው ማለት ነው። የሰለጠኑ አገራት ቆይተው የሚመጡ ሰዎች ያዩትን ሲናገሩ እንሰማለን።

ስለዚህ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥም የሚታይ ነገር ሲገኝ በተግባር ማሳያ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ አጋጣሚ ግን ለጥበቃዎች በጣም አዝናለሁ፤ ‹‹እንዴት ይገረሙ ይሆን?›› እያልኩ አስባለሁ። ወደዚያ ቦታ የሚሄድ ሰው የተማረ እና በከፊልም ቢሆን የሰለጠነ ነው ተብሎ የሚታሰብ ነው።

እነዚህ እንደዚህ ከሆኑ ሌላው እንዴት ሊሆን ነው? እያሉ የሚገረሙ ይመስለኛል። ስናነብ፣ ማሰብንም መሰልጠንንም እንለማመድ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You