
ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ቢኖሩም በታሪክ የሚወሳና የትውልድ አሻራ የሆነውን የዓባይ ግድብን በልጆቿ ብርቱ ጥረት ወደ ማጠናቀቂያው አድርሳለች።
ጀግኖቿ ዓድዋ ላይ እንደፈጸሙት ጀብዱ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በዓባይ ግድብ ድሉን በመድገሙ ብዙዎች ዓባይን “ዳግማዊ ዓድዋ” ሲሉ ይደመጣሉ። “የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” የተሰኘው ሰነድ እንደሚያመላክተው፤ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ 11 ሀገራት ይገኛሉ። እነዚህ ሀገራት በተፋሰሱ ውስጥ በተለያየ የኃይል መጠንና የውሃ አጠቃቀም ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ከሚገኙት ወንዞች መካከል ኢትዮጵያ በዓባይ፣ በተከዜ (አትባራ) እና ባሮ (አኮቦ) ወንዞች አማካኝነት ከፍተኛውን የውሃ አቅርቦት ታበረክታለች። በሌላ በኩል በተፋሰሱ የውሃ አቅርቦት ላይ ምንም አስተዋጽኦ የሌላት ግብጽ ውሃውን በመጠቀም ረገድ ረጅም ርቀት ሄዳለች። ግብጽ ላለፉት በርካታ ምዕተ ዓመታት ወንዙን በበላይነት ለመቆጣጠር የተለያዩ ስልቶችን ስትከተል ኖራለች።
አሁንም ቢሆን ከተፋሰሱ ጋር በተያያዘ የምታራምደው ፖሊሲ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና እያሳደረ ይገኛል። ሆኖም ኢትዮጵያን በየወቅቱ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ያላትን የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም እንቅፋት ቢፈጥሩባትም በሕዝባዊ አንድነት ግድቡ አሁን ላለበት ደረጃ በቅቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ግድቡ የኢትዮጵያ ወዳጆች የተደሰቱበትና በተቃርኖ የቆሙ ደግሞ የተከፉበት ፕሮጀክት መሆኑን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ እያደገች መሆኗና በዚህ ላይ ሌላ አቅም ከጨመረች በመዳረሻዋ ስጋት ያለባቸው ስለመኖራቸው ያነሱት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም፤ ኢትዮጵያ በዓለም ክብር እንዲሰጣት መደረጉ የመጣው ደግሞ ተከባብሮ መሥራት በመቻሉ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
የዓባይ ግድብ ከጅማሮው እስካሁን ሀገራዊ አንድነትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው በመግለጽ፤ ግድቡ ለዚህ መድረሱ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ኅብረትን፣ አንድነትና ጥንካሬ ኃይል እንደሆነ ያሳየ ፕሮጀክት ነው ይላሉ።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አቶ ሞቱማ መቃሳ እንደሚሉት፤ የዓባይ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ያሳየ፤ በዓለም ደረጃ ታላቅነቷን ያስመሰከረ፤ ብዙ ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም መስራት እንደሚችሉ ያመላከተ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ አንድ የውሃ ግድብ ኢሊያም የኢነርጂ ማመንጫ ፕሮጀክት ሳይሆን፤ ሀገርን የገነባ ፕሮጀክት ነው ይላሉ። ኢትዮጵያዊያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነሳሳ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ሕዝብን አንድ ያደረገው ትልቁና ዋናው የዓባይ ግድብ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
አቶ ሞቱም እንደሚገልጹት፤ ግድቡን ለመገንባት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር አልተገኘም። በራስ አቅም ለመገንባት የተጀመረ ነው። “መሐንዲሶቹም እኛው፤ ፋይናንስ አድራጊዎችም እኛው” በሚል የሥራ እንቅስቃሴ ነው የተጀመረው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ መልኩ ተቀብሎ ፕሮጀክቱ የአንድ ተቋም ሳይሆን የሕዝብ ፕሮጀክት መሆኑን አምኖ ካለውም ከሌለውም እያዋጣ ነው ሥራው እንዲሠራ ያደረገው።
ትልቁ ነገር የገንዝብ መዋጮ ብቻ ሳይሆን በሃሳብ አንድ ሆኖ መንቀሳቀስ ነው የሚሉት አቶ ሞቶማ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልክ እንደ ዓድዋ ድል በዚህ መልኩ ተንቀሳቅሶ ግድቡን አሁን ላለበት ደረጃ ማብቃቱን ይናገራሉ። ግድቡን ወደማጠናቀቂያው ማድረስ የተቻለው ያለውም የሌለውም የኔ ነው ብሎ በመነሳቱ ነው ይላሉ።
“በሁሉም ሥራዎች አምነን ከተነሳን ኢትዮጵያዊያን ብዙ ነገር መሥራት እንደምንችል ያሳያል። በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያዊያን መሳሪያ ኖሯቸው አይደለም። ጠላትን በጦር መሳሪያ እንችላቸዋለን ብለው አይደለም። ነገር ግን ቁርጠኛ ስለሆንን ነው ማሸነፍ የቻልነው” በማለት ይህ ቁርጠኝነት በዓባይ ግድብ ላይም መንጸባረቁን ይናገራሉ።
አሁንም በተጀመረው ሂደት ቀሪ ሥራውን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ አይሆንም በማለት ሁሉም ተባብሮ በመሥራት ግድቡን ከፍጻሜው ማድረስ እንደሚጠበቅበት ነው ያመላከቱት።
“ፕሮጀክቱን ለማስተጓጎል በየጊዜው ሲነሱ የቆዩ ጫጫታዎች አሁንም አልቆሙም፤ ሆኖም ፕሮጀክቱን አላስቆሙም ወደፊትም የሚቻል አይደለም። ይህ የሆነው ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ በመኖሩ ነው” ይላሉ አቶ ሞቱማ። ለኢትዮጵያ አሉታዊ አመለካከት ባላቸው አካላት በተለያየ መንገድ የሚሰነዘረውን ነገር ሁሉ ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ መመከት እንዳለበትም ነው የሚያስረዱት።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ የዓባይ ግድብ ከጅማሬው አንስቶ ብዙ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ቢኖሩም እንኳን ልክ እንደ ዓድዋ ድል በትልቅ ሞራል፣ በትልቅ ተነሳሽነት፣ ያለምንም የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋ ልዩነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ የገነባው መሆኑን ይገልጻሉ።
ከመሠረቱ ለየትኛውም የፖለቲካ ፍጆታ የማይውል፣ የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጥ መሆኑ ታምኖበት ስለተጀመረ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የትኛውም የፖለቲካ ልኂቃን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ማህበረሰብ አንቂዎች ልዩነት እንደሌላቸው ቀሲስ ታጋይ ይናገራሉ።
ቀሲስ ታጋይ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያን በዘላቂነት ከድህነት መውጣት የማይፈልጉ ኃይሎች ቢችሉ በራሳቸው ካልሆነም በተልዕኮ ጦርነትን ያወጁበት ፕሮጀክት ነው። እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ በግድቡ ጉዳይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተከሰዋል። ሆኖም ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ቀጥላለች። ፕሮጀክቱም ፍጻሜ አግኝቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከችግር የሚያላቅቃት ይሆናል።
“ግድቡ የአንድነት፣ የአብሮነት አሻራ የሆነና የጥላቻን ግንብ በማፍረስ በአብሮነት የምንዘልቅበት ግንብ የገነባንበት እንጂ የኃይል ማመንጫ ብቻ አይደለም” ሲሉም ይገልጹታል።
ኃይል አመንጭቶ ኢትዮጵያን ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን፤ በራሷ ኃይልና በራሷ አቅም በራሷ አንጡራ ሀብት ገንብታ ማሳየት እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከረችበት መሆኑንም ያመላክታሉ። “ድሆች ስንባል ባለጸጎች መሆናችንን ያሳየን፤ በሃይማኖት በብሔር እነርሱን ማሸነፍ እንችላለን ለሚል ኃይል አብሮነትና አንድነታችንን በላቀ ሁኔታ ገንብተን ያስመሰከርንበት ግድብ ነው” ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ “የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የዓባይን ጉዳይ እንደ ብሔራዊ ጥቅም አድርጎ በመውሰድ ሊንቀሳቀስበት ይገባል። የዓባይ ጉዳይ ከፖለቲካ አመለካከትና ከመንግሥታት ሥርዓት በላይ ነው። ስለዚህም ሕዝቡ የታሪኩና የትርክቱ አካል እንዲያደርገው፤ የትምህርት አንዱ ጉዳይ እንዲሆን፣ የውጭ ጉዳይና የልማት ስትራቴጂ ዋና አካል እንዲሆን በብርቱ መሥራት ይገባል። ውሃውንና የውሃ ቴክኖሎጂን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ጉዳያቸው እንዲያደርጉት በፖሊሲ መካተት ይኖርበታል። የሚዲያና የኪነ ጥበብ ጉዳዮችም የዓባይን ጉዳይ የዘወትር ጉዳያቸው እንዲያደርጉት የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም