ኢትዮጵያ ያጣችው ወጣት ኮከብ ተጫዋች

ከቀናት በፊት በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አንድ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያስደነገጠ መርዶ ተሰማ፡፡

ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የባህርዳር ከተማው ክለብ የማሀል ሜዳ ኮከብ ተጫዋች አለልኝ አዘነ ህልፈት ነበር፡፡ መጋቢት 18-2016 ዓ.ም ንጋት ላይ የተሰማው አስደንጋጭም፣ አሳዛኝም የሆነው የተጫዋቹ ድንገተኛ ህልፈት ማንም የጠበቀው አይደለም፡፡ የተስፈኛው ኮከብ ተጫዋች ህይወት ማለፍ እስከ አሁን ድረስ ምክንያቱ በምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ባይታወቅም ጉዳዩ በፖሊስ እየተጣራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተጓዘባቸው ዘመናት በሀገሪቱ ሊግና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ በርካታ ከዋክብቶችን እያስመለከተ ዛሬ በሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

የወጣቱ አለልኝ ህልፈት የስፖርት ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያዊያንን ያሳዘነ ሆኗል፡፡ ተጫዋቹ በእግር ኳስ ችሎታው ብቻ ሳይሆን ባለው ምስጉን ስነ ምግባር፣ ለጋስነቱ፣ ሰው አክባሪነቱና ታታሪነቱ የብዙዎች ምሳሌም በመሆን ይጠቀሳል፡፡ ወጣቱ ኮከብ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ብዙ ስኬታማ ተጫዋቾችን በማፍራትና በቱሪስት መስህብነቷ በምትታወቀው አርባምንጭ ከተማ ወዜ በምትባል ቀበሌ በ1990 ዓ.ም ከአባቱ አቶ አዘነ ኃይሌና ከእናቱ ወይዘሮ ዳቄ ቱሮ ተወለደ፡፡

የእግር ኳስ ቴክኒሻኑ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በወዜ ሙሉ አንደኛ ደረጃ፣ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት፤የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአርባምንጭ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የእግር ኳስ ጅማሮውን ያደረገው እዛው በተወለደበት አካባቢ በሚገኘው ገረመው በሚባል ፕሮጀክት ሲሆን በ2007 ዓ.ም የአርባምንጭ ተስፋ ቡድንን ተቀላቅሏል፡፡

በቡድኑም በነበረው ቆይታ በትጋቱ የሚታወቅና ጠንክሮ በመስራት ትልቅ ደረጃ በመድረስ ብዙዎች ከኳስ ብቃቱና ከስራ ትጋቱ በተጨማሪ በምስጉን ባህሪው እንደ አርአያ የሚመለከቱት ስፖርተኛም መሆን ችሏል፡፡ የአርባምንጭ ተስፋ ቡድን ጊዜውን በአግባቡ የተወጣው አለልኝ እራሱን ለማሳደግና በትልቅ ደረጃ ለመጫወት ያስችለው ዘንድ ለአርባምንጭ ተስፋ ቡድን ተጫውቷል፡፡ በተስፋ ቡድኑ ከተጫወተ በኋላ ከሀገሪቱ ታሪካዊ ክለቦች አንዱና የትውልድ ስፍራው ክለብ ለሆነው አርባምንጭ ከተማ ዋናውን ቡድን ተቀላቅሎ እራሱን ማሳየት ቻለ፡፡ በዚህም ክለብ ጥሩ የሚባልን እንቅስቃሴ በማስመልከት ከክለቡ ጋር ድንቅ ጊዜ ነበረው፡፡ በአዞዎቹ ቤት የነበረውን ስኬታማ ቆይታን በማጠናቀቅ ሀይቆቹን በመቀላቀል እራሱን በትልቅ ደረጃ በማስመልከት ድንቅ ጊዜን አሳልፏል፡፡

በሀይቆቹ ቤት የነበረው ድንቅ የ2 ዓመታት ጊዜ ይበልጥ እራሱን በትልቅ ደረጃ የሚያስመለክትበት እድልን ፈጥሮለታል፡፡ የአለልኝ ቀጣይ ማረፊያና በትልቅ ደረጃ እራሱን ያሳየበት የጣና ሞገዶቹ ቤት ሲሆን ሀይቆቹን በመልቀቅ ብዙ ክብሮችን ማግኘት ወደ ቻለበት ባህርዳር ከተማ አመራ። በጣና ሞገዶቹ ቤት ህይወቱ እስካለፈችበት ቀን ድረስ የሶስት ዓመታት ቆይታ የነበረው ሲሆን ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እያሳየ ባለው ድንቅ ፉክክር የእሱ አስተዋጽኦ የጎላ ነበር፡፡ ክለቡ ሲያሸንፍ የእሱ ሚና በሚያስቆጥራቸው ጎሎችና ክለቡ በተጋጣሚዎቹ ላይ በሚወስደው የመሀል ሜዳ ብልጫ ላይ የወጣቱ ኮከብ ሚና የጎላ ነው፡፡

በክለቡ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት በሚያስቆጥ ራቸው ጎሎች የሚታወቅ ሲሆን፤ ክለቡን የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ከማድረጉም በተጨማሪ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንዲሳተፍ ካደረጉ ተጫዋቾች ዋንኛው ነው፡፡ በጣና ሞገዶቹ ቤት ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው አለልኝ በክለብ ደረጃ አንድ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡ በሊጉ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴም በ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡

ተጫዋቹ በሀገሪቱ ካሉ ድንቅና የዘመኑ እግር ኳስ የሚጠይቀውን የተከላካይ አማካኝ ሚናን የተላበሰ ተጫዋች ነው ይሉታል፡፡ ከርቀት አክርሮ በመምታት የሚያስቆጥራቸው ማራኪ ጎሎቹ፣ ሜዳ ላይ ለተከላካዮች የሚሰጠው ሽፋንና ምቾት፣ ጨዋታ የማንበብ ብቃቱና አደጋን የመከላከል ችሎታውም ይደነቅለታል፡፡ በክለቡ ባሳየው ድንቅ ችሎታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወክሎ በመጫወት እራሱን ማስመልክት ችሏል። ግዙፉ አማካኝ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ተከፋይ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡

ዘንድሮ በሊጉ ለክለቡ ብዙ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት የቻለ ሲሆን፤ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ወደ ትውልድ ስፍራው ለእረፍት አምርቶ እዛው እንዳለ በተወለደ በ26 ዓመቱ በድንገት ህይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡ ተጫዋቹ በቅርቡ ትዳር መስርቶ የነበረ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ወጥቶ ለመጫወትም እየሞከረ ነበር፡፡

ሥርዓተ ቀብሩም መጋቢት 18/2016 ዓ.ም በትውልድ ስፍራው አርባምንጭ ከተማ ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡ ክለቡ ባህርዳርም ተጫዋቹ ይለብሰው የነበረውን 23 ቁጥር ማሊያ ለክብሩ ሲባል እንዳይለበስና በክብር እንዲቀመጥ ወስኗል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You