የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው። ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ ሰዓቱ ረፍዷል። እየተደናበረ ወደክፍል ሲሄድ ትምህርቱ ተጠናቆ ተማሪ ተበትኗል። ግራ ቢገባው ወደ ሰሌዳው ዞር ቢል ሁለት የሂሳብ ጥያቄዎችን ተፅፈው አየ። ‹‹የቤት ስራ መሆን አለበት›› ብሎ ማስታወሻው ላይ ፅፏቸው ወደ ማደሪያ ክፍሉ ሄደ። ማደሪያ ክፍሉ ገብቶ እንደሌላው ግዜ ጥያቄዎቹን ለመስራት መሞከር ጀመረ። ግን ከበዱት። ‹‹ዛሬ ደግሞ ምኑን ነው ያመጣብኝ!›› እያለ ጥያቄውን ለመስራት ክፉኛ ታገለ።
በጣም ከበደው። መጨረሻ ላይ ግን ለሁለቱም ጥያቄዎች መፍትሄ አገኘላቸው። በማግስቱ የቤት ስራውን ሊያስረክብ እየተቻኮለ ወደ ፕሮፌሰሩ ቢሮ ሄደ። የቢሮውን በር ከፍቶ ሲገባ ፕሮፌሰሩ አጎንብሰው መነፅራቸውን ዝቅ አድርገው እያነበቡ ነበር። ወረቀቱን ወደሳቸው ዘረጋ። እርሳቸው ግን ቀና ብለው እንኳን ሳያዩት ‹‹እርሱ ጋር አስቀምጠው!›› ብለውት አስቀምጦ ወጣ። መልሶ የሚያገኘውም አልመሰለውም።
የሆነ ቀን በጥዋት የሚኖርበት ክፍል በር ተንኳኳ። ግራ ተጋብቶ በሩን ሲከፍት ፕሮፌሰሩ ፈገግ ብለው ፊት ለፊት ቆመዋል። ‹‹እንኳን ደስ ያለህ! መመረቂያህን በሚገባ ሰርተሃል›› ብለው እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉለት። ግራ ገባው ‹‹የምን መመረቂያ ነው! የቤት ስራውን እኮ ነው የሰራሁት›› ሲላቸው ፕሮፌሰሩ በግርምትና በአድናቆት እያዩት ‹‹በጣም እኮ ነው የሚገርመው! እኔ እኮ እነዛን ሁለት ጥያቄዎች ጥቁር ሰሌዳ ላይ የፃፍኳቸው ተማሪዎች ሂሳብ ታሪክ ውስጥ መልስ ያልተገኘላቸው የስታትስቲክስ ጥያቄዎች ናቸው። ለጠቅላላ እውቀታችሁ ይሆናችኋል፤ እወቋቸው ብዬ ነበር የፃፍኳቸው። አንተ ቀለል አድርገህ እንደ የቤት ስራ ሰርተኸው መጣህ። እንኳን ደስ አለህ በድጋሚ መመረቂያህን ሰርተሃል›› አሉት።
ይህ እ.ኤ.አ በ1939 በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በርክሌይ ውስጥ የተፈጠረ እውነተኛ ታሪክ ነው። ተማሪው ጂዮርጅ ዳንዚግ ይባላል። እንደውም በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ‹‹እኔ እውነቱን አስቀድሜ ባውቅ ኖሮ ጥያቄዎቹን አልሞክራቸውም ነበር›› ብሏል። እኛም ነገሮችን የምናይበት መንገድ በጣም ወሳኝ ነው። በራሳችን ማመን ስንጀመር ለማሰብ የሚከብዱ፣ ለማመን የሚያስቸግሩ ጉዳዮችን ሁሉ እናሳካለን።
ታላቁን የፎርድ ተሽከርካሪ የፈጠረው ሄነሪ ፎርድ ‹‹አልችልም ካልክ አዎ! ልክ ነህ አትችልም፤ እችላለሁም ካልክ አዎ! ልክ ነህ ትችላለህ›› ይላል። በጣም ወሳኙ በሕይወትህ ውስጥ አመለካከትህ ነው ወዳጄ! ምንም ነገር እንድታደርግ ከፈለክ አእምሮህ ‹‹እችላለሁ›› ብሎ መጀመር አለበት።
‹‹እኔ ጎበዝ ተማሪ ብሆን እኮ ደስ ይለኛል ግን አልችልም! ሰነፍ ነኝ! ፣ ከዚህ በፊት ጥሩ ውጤት አምጥቼ አላውቅም›› እያልክ ይሆናል። ‹‹እኔ በስራዬ፣ ባለሁበት ቦታ ቢሳካልኝ፣ ብጠነክር ደስ ይለኛል። ግን አልችልም፣ ለስራ አልሆንም፣ አልተፈጠርኩም›› እያልክም ይሆናል። ‹‹እኔ ፍቅረኛ ቢኖረኝ፣ ጓደኞች ቢኖሩኝ እኮ ደስ ይለኛል። ግን አልችልም፣ አይሆንልኝም፣ ሰው አይወደኝም፣ ተግባቢ አይደለሁም፣ ተጫዋች አይደለሁም፣ አልችልም›› እያልክም ይሆናል።
‹‹ብቻ መጠንከር፣ ልበ ሙሉ መሆን፣ በራስ መተማመን እንዲኖረኝ ማድረግ አልቻልኩም። ምክንያቱም ከብዶኛል›› እያልክ ይሆናል። አንድ ጉዳይ ላይ ለራስህ የምትነግረው ነገር፣ የምትሰጠው ብያኔ ወይም ድምዳሜ አመለካከት ነው። እንደምትችል የምታምናቸው ጉዳዮች አሉ። የማታምናቸው፣ ምትጠራጠራቸው፣ አልችልም ምትላቸው ጉዳዮችም አሉ።
ታላቁ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲ ሃርቫርድ አንድ ጥናት አካሂዷል። ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ተቀጥረው እንዲሰሩ፣ ጥሩ ገቢ እንዲያገኙ የሚረዳቸው ምንድነው ተብሎ ጥናቱ ተጠና። የመጣው የጥናቱ ውጤት ግን አስቂኝ ነበር። በትልቅ ውጤት የተመረቁ አይደሉም። ወይም ከትልቅ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ አይደሉም እዛ ስኬት ላይ የደረሱት። ‹‹ማንኛውንም ስራ ብቀጠር እሰራለሁ፤ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥም ብሆን እችላለሁ›› ብለው የሚያምኑና እንዲህ አይነቱ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የትም ቦታ ብቁ መሆን ይችላሉ፤ የደረጃ እድገት ያገኛሉ ነው ጥናቱ።
አንዳንዴ በዙሪያችን ከእኛ ያነሰ እውቀት፣ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃ ኖሯቸው ከእኛ የተሻለ የሕይወት ከፍታ ላይ፣ የኑሮ ሁኔታ ላይ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ብዙ ሰዎች አሉ። ‹‹ይሄማ በአቋራጭ ነው የበለጠን›› የምንላቸው ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ ግን የእውነት የበለጡን በአመለካከታቸው ነው። ‹‹እችላለሁ›› ስለሚሉ፣ ድፍረት ስላላቸው፣ ወድቀው ተነስተው በምንም ውስጥ ገብተው ይሳካላቸዋል።
እኛ ብዙ ችሎታ አለን። ብዙ እውቀት አለን። ‹‹አልችልም የሚለው አመለካከት ወደኋላ አስቀርቶናል። ስለዚህ ‹‹አልችልም›› የሚለውን አመለካከት መስበር ያስፈልጋል። ይህን አመለካከት ደግሞ በሚከተለው መልኩ መስበር ይቻላል።
1ኛ. ውስጥህ ነው ወሳኙ!
ውጪህ የውስጥህ ነፀብራቅ ነው። ውስጥህ ያመነበትን ውጪህ ያስተጋባል። ‹‹እኔ እኮ አልችልም የምለው ወድጄ መሰለህ! ተፈጥሮዬ እኮ ነው። በቃ የሚያግዘኝ የለም። ሁኔታዎች አይመቹም›› ካልክ በቃ! ውስጥህ ስላመነበት አትችልም፤አትቀየርም። በሰው ለውጥ ትቀናለህ። ውስጥህ ካመነበት ግን የእውነት ውጪህ መቀየር ይጀምራል። ወሳኙ ደግሞ ውስጥህ ነው።
ሰውዬው ነጋዴ ነው። መንገድ ላይ ፊኛዎች ይሸጣል። አንዳንዴ ገበያ ቀዝቀዝ ሲልበት ፊኛዎቹን ይነፋና ወደሰማይ ይለቃቸዋል። ከዛ በዚያ አካባቢ የሚያልፉ ሕፃናት ወደ ሰማይ ከፍ ብለው የሚወጡትን ፊኛዎች ያዩና ‹‹አባዬ ፊኛ ይኸው ፊኛ ግዛልኝ! እማ ፊኛ ግዢልኝ!›› እያሉ ቤተሰቦቻቸውን ያስቸግራሉ። ከዛ የቀዘቀዘው ገበያ መልሶ ይደራል።
የሆነ ቀን ግን እንዲህ አድርጎ ሲሸጥ ከኋላው የሆነ እጅ ነካው። ዞር ብሎ ሲመለከት ሕፃን ልጅ ነው። ሕፃኑ ወደሰማይ ከፍ ብለው የሚወጡትን ፊኛዎች እያሳየው ‹‹ሁልግዜ ቢጫ፣ አረጓዴ፣ ቀይ፣ ሰማያዊ ፊኛዎችን ወደ ሰማይ ስትለቅ አይሃለው፤ ጥቁር ፊኛ ግን ልክ እንደሌሎቹ ፊኛዎች ከፍ ብሎ ወደሰማይ መውጣት ይችላል?›› ብሎ ጠየቀው። ነጋዴውም በሕፃኑ ልጅ ጥያቄ እየተገረመ ‹‹ፊኛዎቹን ከፍ ብለው ወደሰማይ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው በውጪ ያለው ቀለማቸው አይደለም በውስጣቸው የተሞላው አየር ነው›› ብሎ መለሰለት።
ያንተንም ሕይወት ከፍም ዝቅም የሚያደርገው ውጫዊ ሁኔታ አይደለም። አለመማርህ፣ ሰዎች አለማወቅህ፣ የስራ ልምድ ስለሌለህ ወዘተ.. እሱ አይደለም ወሳኙ። ውስጥህ ያለው አመለካከት ነው ወሳኙ። ኮሮና የሁሉንም ሰው ሕይወት አክብዶት እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ወቅት ውስጡን አሳምኖ የተቀየረ ሰው ደግሞ አለ። ለምሳሌ በዛ ወቅት የሀያ ብሩን ማስክ ሁለት መቶ ብር ተሰልፎ የገዛ አለ። ሁለት መቶ ብር አሰልፎ የሸጠም አለ። ምግብ ቤቱን ከስሮ የዘጋም አለ። ቤት ለቤት ምግብ እያደረሰ የከበረም አለ። ወሳኙ ሁኔታው አይደለም። የገጠመው ችግር አይደለም። ውስጥህ ነው ወሳኙ።
2ኛ. አዕምሮህን ማሳመን አለብህ!
አዕምሮህን ማሳመን ማለት ስሜትህ ተቀይሮ ወደ ድርጊት እንድትገባ ነው። ከሁለት መቶ ሀምሳ ዓመት በፊት ተነሳ አንድ አዳም ስሚዝ የተሰኘ ታላቅ ኢኮኖሚስት ‹‹wealth of nation›› በተባለ ትልቅ መፅሃፉ ‹‹all money is a matter of belive›› ማለትም ‹‹ኪስህ ውስጥ የሚገባው ገንዘብ የእምነትህ ውጤት ነው›› ይለናል። ሳትሰራ፤ ሳትለፋ በእምነትህ ብቻ ታሳካለህ ማለት አይደለም። ግን እንድትጠነክር፣ እንድትበረታ፣ ወጥረህ እንድትሰራ በቅድሚያ እምነት ያስፈልግሃል። ‹‹እችላለሁ›› የሚል እምነት በጣም ወሳኝ ነው። አይምሮ ያላመነበትን ነገር ማድረግ በጣም ከባድ ነው። አየህ! ምንም ነገር ለማድረግ አይምሮህ ማዘዝ አለበት። ሰውነትህ እንዲንቀሳቀስ እንኳን አይምሮህ ማዘዝ አለበት።
የትኛው ሰው ነው ‹‹እግሬን እኮ ፒያሳ ጎዳና ላይ ሲራመድ አገኘሁት›› ያለህ። የትኛው ሰው ነው ‹‹እጄን እኮ ለጥቂት ጠቅልሎ ሊጎርስ ሲል እጅ ከፈንጅ ያዝኩት›› ያለህ። ምንም ነገር ለማድረግ አንተ ማመን አለብህ። አንተ መቀበል አለብህ። በተለይ አይምሮህ ማዘዝ አለበት። አይምሮህ በጣም የሚገርም ሃብትህ ነው። ለምሳሌ በዓለማችን እጅግ ውዱ የተባለው መኪና አለ። ይህ መኪና አንድ ሺ የፈረስ ጉልበት አለው። በጣም ፍጥነት አለው፤ ጉልበት አለው። አንተ መኪና ውስጥ ገብተህ በፈረስ ብታስጎትተው ብዙ ርቀት የምትጓዝ ይመስልሃል? አትጓዝም! ፈዘህ ትቀራለህ።
ነገር ግን ፈረሱን ትተህ መኪና ውስጥ ገብተህ ቁልፉን ብታስነሳው የፈለክበት ያደርስሃል። መኪናው አይምሮህ ነው። ቁልፉ ደግሞ አመለካከትህ ነው። አየህ! አመለካከትህ ስትቀይር አይምሮህን፤ ትልቁ ሃብትህን መጠቀም ትጀምራለህ። ጎበዝ ተማሪ ለመሆን እኮ መጀመሪያ ጎበዝ መሆን እንደምትችል ማመን አለብህ። ከዛ ስታነብ፣ ስታጠና፣ ስትጥር ጎበዝ እንደሆንክ እያሰብክ ስለሆነ አይምሮህ ክፍት ይሆናል። ይገባሃል። ጥሩ ውጤት ባታመጣ እንኳን ‹‹አይ እኔ እኮ ጎበዝ ነኝ ደግሜ አጥንቼ ጥሩ ውጤት አመጣለሁ›› ትላለህ።
ውስጥህ ካላመነበት ግን፣ ሰነፍ እንደሆንክና መቼም ጎበዝ መሆን እንደምትችል ካሰብክ ጥሩ ውጤት ብታመጣ እንኳን ራስህን ትጠራጠረዋለህ። ‹‹አይ! በእድል ነው፣ አስተማሪው ሰጥቶን ነው እንጂ እኔ እንዴት ጥሩ አመጣለሁ›› ትላለህ። ራስህን ትጠራጠረዋለህ። ለምን? እንደምትችል አላማንክም። ጥሩ ውጤት ካላመጣህ ደግሞ ‹‹ድሮም እኮ ሰነፍ እንደሆንኩ አውቀዋለሁ›› ትላለህ። ማመን ያለብህ ውስጥህ ነው። አመለካከትህ ነው ወሳኙ።
3ኛ. አቅም አጥተህ አይደለም!
ዶክተር ማይለስ ሞርኖ የተሰኘው ታላቅ ደራሲና የቢዝነስና የሕይወት አማካሪ ‹‹አንበሳን የጫካ ንጉስ ያደረገው ምንድን ነው?›› ብሎ ይጠይቃል። ግዝፈቱ ነው? አይደለም። በግዝፈትማ ዝሆንን የሚያክል እንስሳ ማን አለ። ቁመቱ ነው? አይደለም። ምክንያቱም በቁመት ቀጭኔን የሚያክል እንስሳ የለምና። በፍጥነትም ቢሆን አቦ ሸማኔን የሚስተካከል እንስሳ የለም። በአስተዋይነትም ጦጣና ቀበሮ አሉ። አንበሳን ታዲያ የጫካ ንጉስ ያደረገው ምንድን ነው ?ይለናል።
አንበሳን የጫካ ንጉስ ያደረገው አመለካከቱ ነው። ምክንያቱም አንበሳ ዝሆንን ሲያየው ምሳይ መጣ ይላል። ዝሆኑ ግን አንበሳውን ሲያየው ግዙፍ ቢሆንም ሊበላኝ የሚፈልግ እንስሳ ነው ብሎ ይደነግጣል። ‹‹አመለካከት አንዱን በይ ሌላውን ተበይ አድርጎታል›› ይለናል ዶክተር ማይልስ። አንተም የገጠመህ ችግር ሊበላኝ ነው ካልክ በአመለካከትህ ምክንያት ተበይ ትሆናለህ። ችግሬን አሸንፈዋለሁ፤ በየትኛውም መስፈርት እኔ ከችግሬ አላንስም ካልክ ግን ችግርህን ታልፈዋለህ።
ቻይናውያን ‹‹ስለመንገዱ ማወቅ ከፈለክ ከመንገዱ የሚመለሱትን ጠይቃቸው›› ይላሉ። ሌሎች ሰዎች ሕይወታቸውን ከምንም ተነስተው ከቀየሩ አንተም መቀየር ትችላለህ። እነርሱ እንዴት እንዳደረጉት ብቻ ማጥናት ነው የሚጠበቅብህ። መጀመሪያ ያደረጉት ግን አመለካከታቸውን ነው የቀየሩት። ‹‹እችላለሁ›› ብለው ራሳቸውን ያሳመኑት። በአንድ ግዜ እንደነሱ እንዴት ከፍታው ላይ እንደምትወጣ ላይታይ ይችላል። ግን ቢያንስ ለራሴ አላንስም ማለት መጀመር አለብህ። ከሚታይህ ጀምር።
ያቋረጥከውን ትምህርት፣ ስራውን፣ አዲሱን ቢዝነስ አሁን ጀምረው። ከሚታይህ ጀምር። ትልቅ አስብ፤ በትንሹ ተነስ። በትንሹ ስትታመን በትልቁ ትሾማለህ። አትርሳ! አቅም አተህ አይደለም፣ ሰነፍ ሆነህ ተፈጥረህ አይደለም። ተፈጥሮ በድላህ አይደለም። እንደማትችል ስላመንክ ነው። እንደ አንበሳው በምንም ነገር ውስጥ ከነጉድለቴ፣ ከነምናምኔ ምፈልገውን ማሳካት እችላለሁ በልና ከትንሹ ጀምር።
4ኛ. ሃሳብ፣ ድርጊት፣ ውጤት
ማንኛውም የዚህ ዓለም ውጤት ምክንያት አለው። ዓለም ከምትመራበት ያልተፃፈ ሕግ መካከል አንዱ arstotalian law of causality ወይም የመንስኤና የውጤት ሕግ ነው። ምንም ነገር ያለምክንያት አይፈጠረም። ዱብዳ የሚባል ነገር የለም። ለምሳሌ አንድ ሰው እንደማይችል ያስባል። ከዛ ስሜቱ ይዳከማል። ‹‹መነሳት የለብህም! እዛው ባለህበት ቁጭ በል!›› ይላዋል ስሜቱ። ወደ ድርጊት አይገባም። ቁጭ ይላል። ያ የስንፍና ድርጊት ሲደጋገም ልማዱ ይሆናል። ያ ልማዱ ፀባዩ ይሆናል። በመጨረሻ የዛ ሰው መዳረሻ ይሆናል። ሕይወቱን የወሰነበት ምክንያትና ውጤት ነው።
እችላለሁ የሚል አመለካከት የሚጠቅምህ አየር ላይ በደስታ እንድንሳፈፍ አይደለም። ስሜትህ እንዲቀየር ነው። ስሜትህ ሲቀየር ወደ ተግባር ትገባለህ። የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለህ። አየህ አንተ እችላለሁ ብለህ የምትችለውን ሁሉ ስታደርግ በሕይወት የማይቻለው ሁሉ ተደርጎ ታየዋለህ። በጎ ሃሳብ ሲኖርህ ስሜትህን ይቀይረዋል። ትበረታለህ፤ ትጠነክራለህ። ያ ስሜትህ ደግሞ ወደ ድርጊት ያስገባሃል። መነሻችንን አንርሳው! ሃሳብ ከዛ ስሜት ከዛ ድርጊት!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም