የአዲስ አበባ ፖሊስና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ52 ኪሎ ግራም የቦክስ ስፖርት ተፋላሚ ነች። በቅርቡ የተካሄደውና ኢትዮጵያ በ9 ስፖርቶች ተሳትፋ 8ኛ ደረጃን ይዛ ባጠናቀቀችበት 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ሀገሯን ወክላ በሴቶች ቦክስ ስፖርት ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች። ይህን አስደናቂ ታሪክ የጻፈችው ወጣቷ ባለተስፋ ቦክሰኛ ምክትል ሳጅን ቤቴልሔም ገዛኸኝ ናት።
ቦክሰኛዋ ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ሲሆን፤ ለቤተሰቧ የመጀመሪያ ልጅ ነች። የቦክስ ስፖርትን በ2005 ዓ.ም ስትጀምር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለአራት ዓመታት በፕሮጀክት ሠልጥናለች። በፕሮጀክት የነበራትን ስኬታማ ጊዜን አጠናቃ በ2008 ዓ.ም ማገባደጃ የአሁኑን ክለቧን አዲስ አበባ ፖሊስን ለመቀላቀል በቃች።
ለውጤታማነቷ የአባቷ ሚና የማይተካ መሆኑን የምትናገረው ሻምፒዮና ቦክሰኛ፤ ከቦክስ በፊት በቴኳንዶ ስፖርት ትሳተፍ ነበር። በሁሉም የስፖርት ዘርፎች እንድትሳተፍ ፍላጎት የነበራቸው አባቷ ወደ ቦክስ እንድትገባም እንዳስመዘገቧት ታስታውሳለች። አባቷ በስፖርት ውስጥ ያሳለፉና አሁንም በዛው ውስጥ ያሉ መሆናቸው ስፖርት ላይ እንድታተኩር ፍላጎት ሊያሳድርበት ችሏል። ይህም በእሷ ብቻ ሳይወሰን ታናናሽ እህቶቿም ጭምር ትምህርታቸውን በማይጎዳ መልኩ በስፖርት ውስጥ እንዲያልፉ አድርጓቸዋል።
የቦክስ ስፖርት ሕይወቷ በውጤታማ ጅማሮ እንዲታጀብ የአሠልጣኞቿ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የምትጠቁመው ታታሪዋ ቦክሰኛ፣ በቦክስ ስፖርት የመጀመሪያዋ ሴት አሠልጣኝ መስከረም ጮሮ መሠረት እንድትይዝ ማድረጓን ታስረዳለች። ከአሠልጣኟ ጋር ያላት ግንኙነትም ክለብ ከገባች በኋላም ቀጥሎ ዛሬ የደረሰችበት ከፍታን እንድትይዝ ሊረዳት ችሏል። በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የልምምድ ጊዜያት ክፍተትን የምትሸፍነውና ተጨማሪ ልምምዶቿን የምትሠራው ከዚችው ከቀድሞ አሠልጣኟ ጋር በመሄድ ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ቦክስ ክለብ አሠልጣኞችም ለውጤታማነቷ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ‹‹አቅም እንዳለኝ ስለተመለከቱ በደንብ ተጭነው ያሠሩኝ ነበር›› በማለትም ሁኔታውን ታስረዳለች። አዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ የመጀመሪያው ሴት እና ወንድ ቦክሰኞችን የያዘ ክለብ በመሆኑ ትልቅ ምስጋና ይገባዋልም ትላለች።
በቦክስ ስፖርት ሁሌም ዝግጅት ላይ መሆን ግዴታ ቢሆንም ለውድድር ሲሆን ግን ያለው ጫና ከፍ እንደሚል ታወሳለች። ለውድድርና ከውድድር በኋላ የሚሠሩ ልምምዶች ቢኖሩም ከአክራው ውድድር በፊት 15 የዝግጅት ቀናት ብቻ ነበራቸው። የመጣው ውጤትም ብሔራዊ ቡድን ከመግባታቸው በፊት የክለብ አሠልጣኞች የሚሰጡት ሥልጠናና በግል የሚደረጉ ልምምዶች አስተዋፅዖ አለው። ብሔራዊ ቡድን የነበሩት አሠልጣኞችና የተመረጡት ስፖርተኞች ብቃት ያላቸው መሆኑና የቡድኑ የነበረው ጥሩ መንፈስ ሌላው ሊጠቀስ የሚችል ጉዳይ ነው። በውድድሩ ስፍራ የነበረውን ከፍተኛ ሙቀት በመቋቋም የተመዘገበው ውጤት የአሠልጣኞቹና የቡድኑ አባላት ያልተቋረጠ የሞራል ድጋፍም ነው። ብዙም ነገር ባልተሟላበት ሁኔታ ይሄ ውጤት መመዝገቡ፤ ከዚህም የበለጠ ከባድ ነገር ቢመጣ መወጣትና ምቹ ነገር ቢፈጠር የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም ያመላክታል ትላለች።
በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ሦስት ጨዋታዎችን ከአልጄሪያ፣ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ እና በፍጻሜው የሞሮኮ ተጋጣሚዎቿን በማሸነፍ ነው። ‹‹ሁሉም ጨዋታዎች ከባድ ቢሆኑም አልከበዱኝም›› የምትለው ቤተልሔም ከሁሉም በላይ የኮንጎዋ ቡጢኛ በጥቂቱም ቢሆን እንደተፎካከረቻትና በብልጠት አሸንፋ ወደ ፍጻሜ ማለፏን ታስታውሳለች።
በብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድልን ስታገኝ ይህ የመጀመሪያዋ ባይሆንም ውጤት ያመጣችበት የመጀመሪያ ውድድሯ ነው። ለኦሊምፒክ ማጣሪያ ሴኔጋል ላይ በተካሄደው ውድድር በ50 ኪሎ ግራም ተሳትፋ ውጤት ባይቀናትም ትልቅ ልምድ ልታገኝበት ችላለች። ያገኘችው ልምድ ውድድሩን አክብዳ እንዳትመለከተውና ለድል እድትበቃ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ማጣሪያዎቹን አልፋ በፍጻሜ ለወርቅ ስትፋለም ያለው ጫና ከባድ ቢሆንም እንደምታሸንፍ እርግጠኛ ነበረች። በውድድር ላይ የልምድ ጉዳይ ቀዳሚው ሲሆን የሠሩትን ነገር ተግባራዊ በማድረግ ውጤትን ማስመዝገብ ይቻላል። ዕድል ያለማግኘትና የልምድ ማነስ ካልሆነ በስተቀርም በርካታ አቅም ያላቸው ሴት ቦክሰኞች መኖራቸውንና በትንሽ የቡድን አባላት የተመዘገበው ውጤት የሚያበረታታ እንደሆነም ነው የምትገልጸው።
ኢትዮጵያውያን ቦክሰኞች በቴክኒክ የላቁ እንደሆኑና በዳኛ ተፅዕኖና በልምድ ማነስ በሚሠሩ የቴክኒክ ጥፋቶች እንደሚሸነፉም ታዝባለች። አሁን የተመዘገበው ውጤት ለሷ በር ከፋች በመሆኑ ይህንኑ ተጠቅማ የኦሊምፒክ ማጣሪያን በማለፍ በፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ማምጣት እቅዷ እንደሆነም በራስ መተማመን ትናግራለች።
የቦክስ ስፖርት ሴቶችም ከሠሩ ውጤታማ የሚሆኑበትና ብዙ ነገሮችን ሊያስተምር የሚችል በመሆኑ የሚሰጠው ግምት መቀየር እንደሚኖርበት ትናገራለች። ቀጣይነት ያለው ውጤት እንዲመጣ ክለቦች የሴት ቡድንን እያቋቋሙ፣ ፌዴሬሽንም አቅሙ በሚፈቅደው መጠን የሚያደርገው ድጋፍ ቢኖርም መንግሥት ለስፖርቱ የሚሰጠው ትኩረት ግን ከዚህ ከፍ ሊል ይገባልም ባይ ነች።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም