በጎ ትውልድን በማፍራት ለጠንካራ ሀገር ግንባታ የሚተጋው ድርጅት

በስነ-ምግባርና በጠንካራ የስራ ባህል የታነፀ ትውልድ ለጠንካራ ሀገር ግንባታ አስተማማኝ መሰረት ነው። ይህን እውነት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ግለሰቦችና ተቋማት በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመገንባት ጥረቶችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። በእንዲህ ዓይነት ተግባራት ላይ ከተሰማሩ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ ‹‹ኒው ብራይት ኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት ሴንተር›› (New Bright Community Development Center) ነው።

‹‹ኒው ብራይት ኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት ሴንተር›› የተመሰረተው በ2009 ዓ.ም ነው። መስራቾቹም በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ነበሩ። ወይዘሮ ፀዳለ ክንፉ ከ‹‹ኒው ብራይት›› መስራቾች መካከል አንዷ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። መስራቾቹ ተቀጥረው የሚሰሩበት ድርጅት በታዳጊዎች ሰብዕና ቀረፃና በማኅበረሰብ ልማት ላይ ያስመዘገባቸው ስኬታማ ለውጦች ‹‹ኒው ብራይት››ን ለመመስረት እንዳነሳሳቸው ይገልፃሉ።

‹‹እንሰራበት የነበረው ድርጅት ኅብረተሰብን በማገዝና ሕፃናትን በመቅረፅ ረገድ የሚሰራው ሁሉ ያስደስተን ነበር። በወቅቱ ወጣት ስለነበርን መልካም ወጣቶችን ለመገንባትና ለማፍራት እንደሰው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ምን ማድረግ እንዳለብን እናስብ ነበር። ስራ የጀመርኩት በመምህርት ስለነበር ልጆች ላይ መስራት ትውልድ ላይ መስራት ስለመሆኑ አምን ነበር። በዚህ ሃሳብ መነሻነት በ2009 ዓ.ም ‹ኒው ብራይት› ተቋቋመ›› በማለት ስለድርጅቱ አመሰራረት ያስታውሳሉ።

እምቅ አቅሞች ያሏቸው ወገኖች አቅሞቻቸውን አውጥተው እንዳይጠቀሙ መሰናክል የሚሆኑባቸውን ተግዳሮቶች ተሻግረው አዲስ የሆነ ተስፋና ብርሃን እንዲያዩና ከራሳቸው አልፈው ማኅበረሰባቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ የሚያግዝ ተቋም የመመስረት ፍላጎታቸውን መነሻ በማድረግም ድርጅቱን ‹‹ኒው ብራይት›› ብለው ሰየሙት።

ወይዘሮ ፀዳለ እንደሚሉት፣ ‹‹ኒው ብራይት›› ራሱን የቻለ፣ ብቁ የሆነና በራሱ የሚተማመን ማኅበረሰብ ተፈጥሮ የማየት ራዕይ ያለው ሲሆን፣ ይህን ለማሳካት ደግሞ ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተመራጭ በመሆናቸው ትኩረቱን በእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አድርጎ መስራትን መርጧል። ‹‹ታዳጊዎች በሚፈለገው መልክ ለመቅረፅና ለመገንባት ምቹ ናቸው። ወጣቶች እምቅ አቅም ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ሴቶች ደግሞ በቤተሰብና በሀገር ደረጃ ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ በእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አተኩሮ መስራት ለሀገር ግንባታ ወሳኝና አዋጭ መንገድ ነው›› ይላሉ።

ድርጅቱ በሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች (በትምህርት፣ ታዳጊዎችንና ወጣቶች በማብቃት እና በማኅበረሰብ ግንባታ) ላይ አተኩሮ ይሰራል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ‹ኒው ብራይት›፣ ከኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ በፊት በነበረው የድርጅቱ ማዕከል ውስጥ ከክፍለ ከተማው ለተመረጡ ታዳጊዎችና ወጣቶች የምገባና የማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎቶችን እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ ብዙ ስልጠናዎችን ይሰጥ ነበር።

‹‹ከእኛ ጋር የሚሰሩ የመንግሥት ተቋማት (የሴቶችና ሕፃናት፣ የወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤቶች…) መርጠው በሚልኩልን መሰረት ልጆቹን እንቀበላለን። እኛም ከማኅበረሰብ አስተባባሪዎች ጋር በመተባበር የማጣራት ስራ እንሰራለን። ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ልጆችን የምንመርጥበት መስፈርት ልጆቹ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸው የሚገኝበት ደረጃ ነው›› በማለት ያስረዳሉ።

ታዳጊዎቹና ወጣቶቹ በማዕከሉ ውስጥ ከማጠናከሪያ ትምህርት በተጨማሪ የቋንቋ፣ የስዕል፣ የኮምፒውተር (Information Communications Technology) እንዲሁም የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎችን አግኝተዋል። ወደ ማዕከሉ ከመጡ በኋላ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያገኛሉ። ከመደበኛ የትምህርት ጊዜያቸው በኋላ የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙና ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ይደረጋል። ስልጠናዎቹ የሚያተኩሩት በሕይወት ክህሎት፣ በአጠናን ዘዴና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው። የቤተ- መጻሕፍት አገልግሎት ያገኛሉ። በተለይ ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች መምህራን በመቅጠር የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣቸዋል። እነዚህ ተግባራት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የራሳቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ።

‹‹ኒው ብራይት›› ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተለየ መልኩ በማዕከሉ የሚሰጠው የስዕል ጥበብ ትምህርት፣ ታዳጊዎቹና ወጣቶቹ ክህሎታቸውን እንዲያሳዩ ከማስቻሉ ባሻገር፣ የስዕል ዐውደ ርዕዮችን አዘጋጅተው የግንኙነት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ፣ ልምድ እንዲያዳብሩና ገንዘብ እንዲያገኙ አግዟቸዋል ።

በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መግባት ሲችሉ የገንዘብና የስነ ልቦና እገዛዎች (የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ምን እንደሚመስል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ምን ዓይነት እድሎችና ፈተናዎች እንዳሏቸው… የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችና የመሳሰሉት) ይደረጉላቸዋል። ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባት ላልቻሉት ደግሞ በግል ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ ነፃ የትምህርት እድል (Educational Sponsorship Program) ይሰጣቸዋል። በዚህም የትምህርት ክፍያ፣ ወርሃዊ የኪስ ገንዘብ፣ የትራንስፖርት ወጪና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ይሰጧቸዋል።

ድርጅቱ ከተመሰረተበት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ 61 ወጣቶች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው በስራ ላይ ይገኛሉ። ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በድርጅቱ ድጋፍ ይማሩ ከነበሩ ልጆች መካከል በአሁኑ ወቅት ስራ ይዘው፣ ቤተሰብ መስርተው የሚኖሩ አሉ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በተለያዩ ባንኮችና በሌሎች ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ የፋይናንስና አስተዳደር ባለሙያዎች፣ መሃንዲሶች፣ መምህራን… አሉ።

የውጭ የትምህርት እድሎችን አግኝተው በውጭ ሀገራት እየተማሩ የሚገኙ እንዳሉም ወይዘሮ ፀዳለ ይናገራሉ። ‹‹ከአካዳሚያዊ ስኬታቸው በተጨማሪ የማኅበራዊ ሕይወት ስኬታቸው ትልቅ ለውጥና ስኬት ነው፤ ሀገር የምትሰራው ከቤተሰብ ስለሆነ ቤተሰብ መመስረታቸው ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ አስተዋፅዖ አለው። በልጆቹ ማሕበራዊና ስነ ልቦናዊ ሕይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣታችን ትልቅ ስኬት ነው›› በማለት የድርጅቱ ተግባራት በታዳጊዎቹና ወጣቶቹ ሕይወት ላይ ዘርፈ ብዙ አዎንታዊ ለውጥ ስለማምጣታቸው ይናገራሉ።

‹‹ኒው ብራይት›› በየዓመቱ ከ120-150 ለሚሆኑ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ የሚገልፁት ወይዘሮ ፀዳለ፣ ‹‹መንግሥት የምገባ መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት እኛ የምገባ መርሃ ግብር ነበረን። ተማሪዎቹ ከትምህርት ቤት ወደ ማዕከሉ ሲመጡ በተቀጠረላቸው ምግብ አብሳይ አማካኝነት ምግብ በልተው ወደ ጥናትና ስልጠናቸው ይገቡ ነበር። ይህ ተግባር ልጆቹ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም ለቤተሰቦቻው ጫና በማቅለል ትልቅ ሚና ነበረው›› ሲሉ ያብራራሉ።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ያለው የድርጅቱ አሰራር በተወሰነ መልኩ ተቀይሯል። ድርጅቱ ስራዎቹን ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር እያከናወነ ይገኛል። ‹‹ስራችን ለውጥ ማምጣቱን ታሳቢ በማድረግ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበን መስራት ነበረብን። ስለሆነም ጥያቄያችንን ይዘን ለአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አቀረብን›› የሚሉት ወይዘሮ ፀዳለ፣ ጥያቄያቸው አወንታዊ ምላሽ አግኝቶ ስራቸውን እንደቀጠሉ ይገልፃሉ።

‹‹ኒው ብራይት›› ከመንግሥት መዋቅሮች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርሞ፣ በማዕከሉ ውስጥ ሲያከናውናቸው የነበሩትን የስልጠናና የአቅም ግንባታ ተግባራት (የቤተ-መጻሕፍት፣ የቋንቋና የኮምፒውተር እና የኪነጥበብ ስልጠናዎችን) በክፍለ ከተማው ውስጥ ወደሚገኙ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት፣ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ስራዎቹን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤቶች ወስዶ መተግበር ጀመረ። ይህም ብዙ ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ እንዳስቻለው ወይዘሮ ፀዳለ ይናገራሉ።

የመምህራንን አቅም ለማጎልበት መምህራን ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል። ተማሪዎችም የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎችን አግኝተዋል። የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎቹም ተማሪዎች ለትምህርታቸውና ለራሳቸው ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው፣ የተግባቦት ክህሎታቸው እንዲሻሻል እንዲሁም የጥሩ ራዕይ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያግዙ ናቸው።

‹‹ኒው ብራይት›› በትምህርት ቤቶች ውስጥ እያከናወነ የሚገኘው ሌላው ተግባር ሴት ተማሪዎች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ነው። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ትምህርት ቤቶች (ዐፄ ነአኩቶለአብ ፩ኛ ደረጃ ት/ቤት እና እንጦጦ አምባ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት) ለሚማሩ 200 ተማሪዎች በየወሩ የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ተማሪዎቹን ጨምሮ ኅብረተሰቡ ስለጉዳዩ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችንም እየሰጠ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ጊዜ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ማግኘት እንደሚኖርባቸው የሚያስገነዝብ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት እንዲቀረፅ ጥረት ለማድረግ አቅዷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሴቶች መሰረታዊ የንግድ ስራ ስልጠናዎችን ወስደው በገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ስልጠናዎችን ይሰጣል፤ ግብዓቶችን ያሟላል። ሴቶች ችግሮቻቸውን የሚጋሩባቸውን፣ መሪነትንና የቁጠባ ባሕልን የሚለማመዱባቸውን እንዲሁም አቅማቸውን የሚያጎለብቱባቸውን ራስ አገዝ የቁጠባ ቡድኖችን እንዲያደራጁ እገዛ ያደርጋል።

‹‹ሴቶች የመሪነት ሚና እንዲኖራቸው ስልጠናዎችን እንሰጣለን፤ ሴቶች ድርብርብ ኃላፊነቶችን የያዙ በመሆናቸው የሴቶችን አቅም መገንባት ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን የመገንባት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው›› በማለት 75 በመቶ የሚሆኑት የድርጅቱ ስራዎች ሴቶችን የተመለከቱ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ወይዘሮ ፀዳለ ያብራራሉ። ስራው አድካሚና ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩትም አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡበት እንደሆነም ይገልፃሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ልዩ ልዩ ኅብረተሰባዊ መዋቅሮችን በመጠቀም ማኅበረሰቡ ችግሮችን የመለየትና የመከላከል አቅሙን ለማሳደግ የሚያስችለውን ሁለንተናዊ ንቃት እንዲያዳብር የማኅበረሰብ ልማትና ግንባታ (Community Development) ስራዎችን ይሰራል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በ‹‹ኒው ብራይት›› ስራዎች ከ3000 በላይ ወገኖች ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሆነዋል። በእነዚህ ወገኖች ስር ያሉ ሌሎች ዜጎች ከግምት ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ድርጅቱ በስራዎቹ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ዜጎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እንደሆኑ መገመት አያዳግትም።

ወይዘሮ ጸዳለ እንደሚሉት፣ ‹‹ኒው ብራይት›› ባከናወናቸው ተግባራት የታዩ አዎንታዊ ለውጦችን ወደ ሌሎች የአዲስ አበባና የክልል አካባቢዎች የማስፋት የአጭር ጊዜ እቅድ አለው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ የሆነ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ታዳጊዎች ሰብዕናቸው የሚቀረፅበት፣ ራሳቸውን የሚያውቁበትና አቅማቸውን አውጥተው የሚጠቀሙበት ማዕከል መገንባት ደግሞ ከረጅም ጊዜ እቅዶቹ መካከል ይጠቀሳል።

‹‹በትምህርት ቤቶች ውስጥ የኪነ-ጥበብ ክበባትን እያቋቋምን ተማሪዎች ተሰጥዖዎቻቸውን እንዲያወጡ እያደረግን ነው። የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ረገድ በስፋት መስራት እንፈልጋለን። በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሚቀረፁባቸው እውነተኛ ስፍራዎች እንዲሆኑ ጥረት እናደርጋለን። ስራዎቻችን ለመስራት ሰላም ስለሚያስልግ ሰላምን ሁሉም ስራዎቻችን ጋር በማቀናጀት ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው። በእነዚህ እቅዶችና ተግባራት አማካኝነት ራሱን የሚያውቅና ብቁ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚቻል እናምናለን›› ይላሉ።

ወይዘሪት ትሁት በፍቃዱ በ‹‹ኒው ብራይት›› ድጋፍ ተደርጎላቸው በአሁኑ ወቅት በጥሩ የሕይወት ጎዳና ላይ ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል አንዷ ናት። ትሁት ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ድርጅቱ ባደረገላት ድጋፍ ነው። በድርጅቱ ነፃ የትምህርት እድል ድጋፍ (Educational Sponsorship Program) አማካኝነት የትምህርት ክፍያን ጨምሮ የትራንስፖርት፣ የትምህርት ቁሳቁሶች፣ የኪስ ገንዘብና ሌሎች ክፍያዎችን በመሸፈን በ2010 ዓ.ም ከሆፕ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ሳይንስና ዘላቂ ልማት ጥናት (Environmental Science and Sustainable Development) የመጀመሪያ ዲግሪዋን እንድታገኝ አስችሏታል። ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ አካውንቲንግና ፋይናንስ (Accounting and Finance) በማጥናት በአንድ የውጭ የግል ድርጅት ውስጥ የፋይናንስና አስተዳደር ባለሙያ (Finance and Administration Officer) ሆና እየሰራች ትገኛለች።

‹‹ብዙ ድጋፎችን ያደረገልኝ ‹ኒው ብራይት› አሁን ላለሁበት ሕይወት መሰረት የሆነኝን ልምድ ያገኘሁበት ድርጅት ነው። የድርጅቱን የቋንቋ፣ የኪነ-ጥበብ፣ የኮምፒውተር፣ የሕይወት ክህሎትና ሌሎች ስልጠናዎች ተጠቃሚ ሆኛለሁ። በገንዘብም ሆነ በስነ-ልቦና ዘርፍ በርካታ ድጋፎችን አግኝቻለሁ። ስልጠናዎቹ የሚቀርቡት ለእኛ በሚያስፈልገን መልኩ ነበር። ድጋፎቹና ስልጠናዎቹ ራሴን እንዳውቅና እንድጠብቅ አግዘውኛል። ያን እድል ባላገኝ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ አልደርስም ነበር›› በማለት ከድርጅቱ ያገኘችው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አሁን ለምትገኝበት ሕይወት መሰረት እንደሆናት ታስረዳለች። በ‹‹ኒው ብራይት›› ድጋፍ ለቁም ነገር ከበቁ ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመተባበርም በድርጅቱ የበጎ ፈቃድ አገልግቶችን ለመስጠት እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝም ወይዘሪት ትሁት ገልፃለች።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You