በዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለስኬት የሚያበቃ ዝግጅት ተደርጓል

45ኛው የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከነገ በስቲያ በሰርቢያ ቤልግሬድ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑት ሃገራት መካከልም የምሥራቅ አፍሪካዎቹ የውድድሩ ስኬታማ ሃገራት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዑጋንዳ ለአሸናፊነት ጠንካራ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክለው የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን እንደተለመደው በውጤታማነት ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ አስታውቋል፡፡

በሃገር አቋራጭ ውድድሮች በውጤታማነታቸው ከሚታወቁ ሃገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ለዚህም በተያዘው ወር መጀመሪያ አንስቶ ቡድኑ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ፣ በእንጦጦ ዳገታማ ስፍራ፣ ለገጣፎ እና ቃሊቲ አካባቢዎች ዝግጅቱን ሲያከናወን ቆይቷል፡፡ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ፣ በ8 እና 6 ኪሎ ሜትር ወጣቶች (ከ20 ዓመት በታች) እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ በሚደረጉት ውድድሮች፤ በእያንዳንዱ ርቀት ከተጠባባቂ ጋር 7 አትሌቶችን እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ 4 አትሌቶችን ከ2 ተጠባባቂዎች ጋር ወደ ስፍራው ለማቅናት ተዘጋጅተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ ምሽት በተደረገው የብሔራዊ ቡድኑ የሽኝት መርሐ ግብር ላይ አትሌቶች እንዲሁም አሠልጣኞቻቸው በአካል እንዲሁም በሥነልቦና ዝግጁ መሆናቸውንና በግልና በቡድን ስኬትን ለማስመዝገብ ወደስፍራው እንደሚያቀኑ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ውድድር እጅግ ተጠባቂ ከሆኑ ርቀቶች መካከል አንዱ የአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ በተለይ በዑጋንዳ እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ለአሸናፊነት የሚደረገው ትንቅንቅ አጓጊ ነው። አምና በዚህ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊና የሜዳሊያ ባለቤት የነበሩት አትሌቶች ዘንድሮም በቤልግሬድ መሮጣቸው ደግሞ አጓጊነቱን ጨምሮታል፡፡ ባለፈው ዓመት በአውስትራሊያ ባትረስ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ለአሸናፊነት ቅድመ ግምቱን ሲያገኝ፤ ዝግጅቱም ይህንኑ እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ቀሪው ጉዳይም ለሳምንታት በቆየው የዝግጅት ጊዜ በአሠልጣኞቻቸው የተሰጣቸውን መመሪያ እንዲሁም እንደ ቡድን የተደረገውን ሁለገብ ዝግጅት ተግባራዊ በማድረግ በተፎካካሪነት ውጤት ማስመዝገብ እንደሆነም አትሌቱ ጠቁሟል፡፡ ፈታኝ ተፎካካሪዎች መኖራቸው ውድድሩን እጅግ ከባድ እንደሚያደርገው የሚጠበቅ ሲሆን፤ ቡድኑ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል፡፡ ዓመቱ የኦሊምፒክ እንደመሆኑም ከዚህ ውድድር ባለፈ አቅሙን በሌሎች ርቀቶች ላይም መድገም የወጣቱ አትሌት በሪሁ እቅድ ነው ‹‹በርካታ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በርካታ ልምዶችን ማካበት ችያለሁ፤ ከዚህ በፊት የተሸነፍኩባቸው ውድድሮች ጭምር ትምህርት ሆነውኛል፡፡ በመሆኑም ያለፈውን ስህተቴን በማረም ውጤታማ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ›› ይላል፡፡

በአሠልጣኞች ቡድን አትሌቶችን ሲያዘጋጁ ከቆዩት መካከል ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ አንዱ ሲሆን፤ አትሌቶች በጥሩ ጤንነትና በቅንጅት ዝግጅታቸውን ሲያካሂዱ እንደነበረም ይጠቁማል። ውድድሩ በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እንዲሁም ጠመዝማዛ በሆነ የውድድር ስፍራ የሚደረግ በመሆኑ ዝግጅቱም ይህንን እንዲያማክል ማለዳ ከ11 ሰዓት ጀምሮ እንደ እንጦጦ ባሉ ከፍተኛ ስፍራዎች ሲደረግ ቆይቷል፡፡ እንደአጠቃላይም ቡድኑ ጠንካራ አትሌቶችን ያቀፈ መሆኑ ውጤታማ ሆኖ እንዲመለስ እንደሚያስችለውም ያመላክታል፡፡

በአዋቂ ቡድኑ የተካተቱ አትሌቶች ልምድ ያላቸው ሲሆኑ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑት የዑጋንዳ እና ኬንያ አትሌቶች ጋርም በምን መልኩ መወዳደር እንደሚገባ ከምንጊዜውም በተሻለ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በወጣቶች በኩልም በቅንጅት ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ በድብልቅ ሪሌም በቱኒዚያ በተደረገው የአፍሪካ ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ተሳትፈው አቅማቸውን ያሳዩ ወጣት አትሌቶችን ለማሳተፍ ታቅዷል፡፡ በአሕጉር አቀፉ ሻምፒዮና በወጣቶች አብዛኛዎቹን በማሳተፍ አቅማቸውን መፈተሽና ለቤልግሬድ አስተማማኝ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ምናልባትም በአዋቂ ሴቶች አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች የማራቶን አትሌቶች በመሆናቸውና በሃገር አቋራጭ ውድድሮች ልምድም ስለሌላቸው ሊፈተኑ ይችላሉ የሚለው ግን ስጋት እንደሚሆን ነው አሠልጣኙ ያስረዱት፡፡

ስመጥርና ተተኪ አትሌቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ሃገር አቋራጭ ብሔራዊ ቡድን ስኬታማ ሊያደርገው የሚችለውን ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁንና ከጉዞ ጋር በተያያዘ የቡድኑ አባላት ቪዛ ለማግኘት አስቸጋሪ ሁኔታዎች የገጠሙት ሲሆን፤ የሰርቢያ ኤምባሲ በኢትዮጵያ አለመኖር ደግሞ ችግሩ በቀላሉ እንዳይፈታ አድርጎታል፡፡ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ኬንያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩልም መፍትሔ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You