ይቻላልን በተግባር

ዓይነ ሥውራንን ጨምሮ ሌሎች አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በሥራ እና በሌሎች የአካታችነት እጦት ችግር ሳቢያ ተሳትፏቸው አናሳ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በመሠረተ ልማት፣ በአካታች ትምህርት፣ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ችሎታቸውን በመጠቀም፣ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እና መደገፍ እንደሚገባ በመፍትሔነት ከሚጠቀሱት ሃሳቦች መካከል ይጠቀሳሉ። ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲያገኙና ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንዳለበትም ይነገራል።

እንዲያም ሆኖ አንዳንድ አካል ጉዳተኞች ችግሮች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ መፍትሔ ላይ ይበረታሉ። የሚያጋጥማቸውን ችግር ወደ ጎን በመተው በጽናት ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ደግሞ የተፈጠረላቸውን አጋጣሚም ይሁን ያገኙትን ዕድል በሚገባ በመጠቀም ለብዙዎቻችን አርዓያ መሆን ችለዋል፡፡ የመጡበትን አድካሚ መንገድ ከማሰብ ይልቅ ያለፉበትን ጽናት ለሌሎች ጉልበት ይሆን ዘንድ ያጋሯቸዋል፡፡

ውልደታቸው ጎንደር ልዩ ቦታው ጎርጎራ ይባላል። የወታደር ልጅ ናቸው፡፡ በአምስት ዓመታቸው በኩፍኝ በሽታ ዓይነ ሥውር ሆኑ፡፡ እኚህ ሴት ወይዘሮ ዘነበች በላቸው ይባላሉ፡፡ አባታቸው ዓይናቸው ወደ ቀድሞ ዕይታው እንዲመለስ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ በኋላ ላይ ግን አባት ልጃቸውን ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ አመጡ፡፡ አዲስ አበባ በተለምዶ ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቀድሞ ስያሜው ‹‹ቀጨኔ የሕጻናት ማሳደጊያ››ን ተቀላቀሉ፡፡ ልጅነታቸውን ያሳለፉት በማሳደጊያው ሲሆን እስከ ሰባተኛ ክፍል የተማሩትም እዛው ነው፡፡ የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በቀድሞ ስያሜው ‹‹እቴጌ መነን ትምህርት ቤት›› በአሁኑ ‹‹የካቲት 12 ትምህርት ቤት›› ተከታትለዋል፡፡

እርሳቸው በተማሩበት ወቅት ትምህርት ቤቱ ሴቶች ብቻ ይማሩበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለመምህርነት በቀጥታ ወደ ወላይታ በማቅናት የዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ትምህርት ቤቱ ተዘጋ፡፡ የተዘጋበት ምክንያት እና የነበረውን አቤቱታ አቅርበው በመንግሥት ቀጣሪነት የመምህርትነታቸውን ሙያ ቀጠሉ፡፡ በዛም ዓይነ ሥውራንን ለአስር ዓመታት ያህል አስ ተምረዋል፡፡

ከወላይታ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም የሥነ ዜጋ መምህርት በመሆን በፀሐይ ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምረዋል፡፡ ወይዘሮ ዘነበች በአጠቃላይ ለ35 ዓመታት ያህል በመምህርትነት ማገልገል የቻሉ ሲሆኑ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮም ‹‹ብራይት ወርልድ ፎር ብላይንድ ዉሜን አሶሴሽን›› በተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅትን በሥራ አስኪያጅነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ወላጆች የልጆቻቸው የወደፊት ሕይወት ያማረ እና የሠመረ እንዲሆን እገዛቸው ባይለይ መልካም እንደሆነ ይታመናል፡፡ የወይዘሮ ዘነበች ወላጆችም በዚህ ረገድ ጥሩ የሚባሉ ነበሩ፡፡ ልጃቸውን በሚገባ ስላሳደጓቸው በልጅነታቸው ይህ ነው የሚባል ነገር አልጎደለባቸውም፡፡ የከፋ ችግርም አልገጠማቸውም። እንደውም ‹‹ዓይነ ሥውር መሆኔ አይታወቀኝም›› ይላሉ ወይዘሮ ዘነበች፡፡

የልጅነት ጊዜያቸው አብቅቶ ወደ አዋቂነት ዕድሜ ከተሸጋገሩ በኃላ ግን አንዳንድ ችግሮችን ማስተዋላቸውን አልሸሸጉም፡፡ ዓይነ ስውር በመሆናቸው ዕቃ ለመግዛት ሲፈልጉ የፈለጉት ዕቃ እንደሌለ ተነግሯቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ነገር ሲያጋጥማቸው ፈጣሪያቸውን ‹‹ግን ለምን?›› ብለው ጠይቀዋል፡፡ ታዲያ ወይዘሮ ዘነበች በዚህ ነገር ብዙም አይብሰለሰሉም፡፡ የሰዎች ይህን የሚያደርጉት ባለማወቃቸው ቢሆን ነው ብለው ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ፡፡ በጉዞ ወቅት መንገድ ሲስቱ ሰዎች ዝም ማለታቸውንም ታዝበዋል፡፡

ወይዘሮ ዘነበች መምህርት በነበሩበት ወቅት የሚያስተምሩት ዓይናማ ተማሪዎችን ነበር፡፡ ተማሪዎች አብዛኛዎቹን መምህራን እንደሚያስቸግሩ የሚታወቅ ቢሆንም በእርሳቸው ክፍለ ጊዜም ክፍል ለቀው የሚወጡ አንዳንድ ተማሪዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ድርጊቱም ከአንድም ሁለት ግዜ አስከፍቷቸዋል። ይህም ያለማወቅ ወይም የግንዛቤ እጥረት መሆኑና ፈጣሪንም ሆነ ሰውን ማማረር እንደማይገባ ይገልፃሉ፡፡

ለወይዘሮ ዘነበች ከሁሉም በላይ ፈተና የሆነባቸው ነገር ቢኖር ልጅ ወልዶ ማሳደጉ ነበር፡፡ ይህንንም ቢሆን በሚገባ አልፈውታል፡፡ መምህርቷ ዛሬ የሦስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን በሚገባ አሳድገው እና አስተምረው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል፡፡ የልጅ ልጅ አይተው ስመዋል፡፡ ያጋጠማቸውን ችግሮች ሁሉ ተቋቁመው ትውልድ በመቅረጽ አሳልፈዋል። ዛሬ ደግሞ ሴት ዓይነ ሥውራን ችግሮችን በጽናት እንዲያልፉ እና የተለያዩ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅት በሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ይገኛሉ። ወይዘሮ ዘነበች ፈተናዎችን ተቋቁሞ እና ሠርቶ መቀየር እንደሚቻል ለብዙዎች ከሕይወት ልምዳቸው እንዲማሩ ማድረግ ችለዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ዘነበች ያሉ ዓይነ ሥውራንም ሆኑ ሌሎች አካል ጉዳተኞች በቤተሰባቸው መልካም አስተዳደግ፣ በራሳቸው ብርታትና ጥረት መሥራት እንደሚችሉ በተግባር ማሳየት ችለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው አካል ጉዳተኞች ፈተናዎችን ተቋቁመው ለስኬት እንዲበቁ የተለያዩ የግንዛቤ ሥራዎች መሠራት እንዳለበት ወይዘሮ ዘነበች ያመላክታሉ፡፡ በተጨማሪም እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ እና መንግሥታዊ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ ብሎም ለእነርሱ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ስኬታማ እንዲሆኑ ማገዝ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You