ዓባይ ገመዱ

ኧረ ልጅ ኧረ ልጅ

ኧረ ልጅ ገመዱ

ቤትማ ምን ይላል ዘግተውት ቢሄዱ

የሚል የቃላዊ ግጥም ሀገርኛ ብሂል አለ። የሥነ ቃሉ መልዕክት፤ ልጅ ከተወለደ ባልና ሚስት አይፋቱም፣ እናትም አባትም የመኖር ጉጉት ይኖራቸዋል፤ ከራሳቸው በላይ ለልጃቸው ስለሚያስቡ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ…. ለማለት ነው፡፡ በልጅ ገመድ ተሳስረዋል ለማለት ነው፡፡

ይህ የቃላዊ ግጥም ሀገርኛ ብሂል ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያስታውሰኛል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን ልጅ ሆኗል፤ መላው ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስር ገመድ ሆኗል፡፡ የጋራ ልብ እና የጋራ ሳምባ ሆኗል። ለምሳሌ፤ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና በተለያየ ጎራ ያሉ ምሑራን ሲናገሩ የጋራ ጉዳይ የሚጠቅሱት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው። ‹‹የጋራ ጉዳዮቻችን›› ሲሉ ምሳሌ የሚያስቀምጡት የህዳሴውን ግድብ ነው። የእገሌ የሚባል ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ የሚባል የጋራ ጉዳይ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ያለውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን በሕይወት የሌሉትን ሁሉ አንድ ያደረገ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ (በተለይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልማድ) መንግሥት በተተካካ ቁጥር ያለፈውን ሥርዓት መውቀስ የተለመደ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግን ይህን ልማድ ሁሉ የሻረ፣ ያለፈውን ትውልድ ሁሉ ያስተሳሰረ ገመድ ነው፡፡ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ከአቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ መለስ ዜናዊን ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር ያስተሳሰረ ገመድ ነው፡፡ ያን ትውልድ ከዚህ ትውልድ ጋር በቅብብሎሽ ያስተሳሰረ ነው፡፡ ያሰቡትም፣ ያስጀመሩትም፣ ያስፈጸሙትም በአንድ ገመድ እንዲተሳሰሩ አድርጓል፡፡

የዓባይ ግድብ አንድ የጋራ ጉዳይ ሆኖ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ጓዳ ጎድጓዳ ነካክቷል። ተማሪው ለደብተር ከሚሰጠው ላይ አዋጥቷል፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከካፍቴሪያ ምግቡ ላይ ቀንሶ አዋጥቷል፡፡ ይህ በማንም ሰው ልብ ውስጥ የሚረሳ አይሆንም። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገነባው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ እዚህ ላይ በ2004 ዓ.ም አካባቢ በብዙ መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ገጾች አጀንዳ ሆኖ የነበረ የአንዲት እናት ነገር ይጠቀሳል፡፡

በደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል ውስጥ ነው፤ ሕዝቡ አቅሙ የቻለውን ሁሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እያዋጣ ነው፡፡ አንዲት ድሃ ሴትዮ ይህን ነገር ያያሉ፡፡ ድሃ ናቸው በሚል ማንም አልጠየቃቸውም፡፡ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሲያዋጡ አስተዋሉ፡፡ ጉዳዩም ለዓባይ ግድብ መሆኑን ሰሙ። እኚህ ሴትዮ በቀጥታ ወደ አስተባባሪዎች ነበር የሄዱት፡፡ በቤታቸው ውስጥ ያለው ንብረት አንዲት ዶሮ ነበረች፡፡ ያቺን ዶሮ ይዘው የበኩሌን ካላዋጣሁ አሉ፡፡ ‹‹ግዴለዎትም!›› ቢባሉም ‹‹በዓባይ ግድብ ላይ እጄ መኖር አለበት›› አሉ፡፡ የሴትዮዋ ዶሮ ተወሰደች፤ ተወስዳ ዶሮዋ በጨረታ ተሸጠች፡፡ በጨረታው የተገኘው ገቢ ከአካባቢው ከተሰበሰበው ይበልጥ እንደነበር ክስተቱን የተከታተለ በወቅቱ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ይሠራ የነበረ ጋዜጠኛ ሲያወራ ሰምቻለሁ፡፡

እዚህ ላይ ብዙ ነገር እንረዳለን፡፡ ሴትዮዋ በዓባይ ጉዳይ ላይ የቤታቸውን የመጨረሻ ገንዘብ የሆነችውን ዶሮ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ዐሻራ ላይ እጄ ይኑር ብሎ ማሰብ ትልቅ ብልህነት፣ አርቆ አስተዋይነትና ፍልስፍና ነው፡፡ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ሥነ ልቦና ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያዊ አቅሙ በቻለ ሁሉ ይታገላል እንጂ እኔ አልችልም ብሎ አይቀመጥም። እኚህ ባለ አንድ ዶሮ ሴትዮ ከኢንቨስተሮች እኩል የተሳትፎ ድርሻ አላቸው፡፡ ዓባይን ከዓድዋ ድል ጋር የምናመሳስለውም ለዚህ ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ሁሉም በመደፈር ስሜት በነቂስ እንወጣው ሁሉ፤ እኚህ ሴትዮም ‹‹ባለ ሀብት ይሳተፍ›› ብለው ዝም አላሉም፡፡ ዓባይ የኢትዮጵያውያን ገመድ ነው ስንል ማሳያዎቻችን እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡

የዓባይ ግድብ እነሆ 13 ዓመታት ሆኑት፡፡ በእነዚህ 13 ዓመታት ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ሁነቶች ተከናውነዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በኦሮሚያና አማራ ክልል ውስጥ መረር ያሉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ነበሩ፡፡ ከ2010 ዓ.ም የለውጡ መንግሥት ከመጣ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ጨምሮ ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ፡፡ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የግብፅ መንግሥት አቅሙ በፈቀደ መጠን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጭ ነበር፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጫናዎች ሲደረጉ ነበር፡፡

እነዚህ ሁሉ የውጭና የውስጥ ጣጣዎች ሲደረጉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግን እየተገነባ ነበር። ምንም እንኳን የነበረው የውስጥ የፖለቲካ ሁኔታ ያሳደረው ጫና አልነበረም ባይባልም የመላው ኢትዮጵያ የጋራ ጉዳይ የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግን እነሆ በቅብብሎሽ ቀጥሏል፡፡ ያለፈውን ትውልድ ከአሁኑ ትውልድ ጋር፤ የአሁኑን ትውልድ ከሚቀጥለው ትውልድ ጋር ሊያስተሳስር እነሆ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

የዘንድሮውን የዓባይን ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ቀን መታሰቢያ ለየት የሚያደርገው የመጨረሻው ምዕራፍ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የህዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ቀን የሚከበረው ለማስታወስ ብቻ እንጂ ግድቡ እዚህ ላይ ደርሷል፣ ይህን ያህል በመቶ ተጠናቋል በሚሉ አኃዛዊ መረጃዎች አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ የምናስታውሰው፤ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ እና ከመጠናቀቁ በፊት ኢትዮጵያ የነበራት የኤሌክትሪክ አቅርቦት ይህን ያህል ብቻ ነበር በሚል ታሪክን ለማስታወስ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በዚህ ሥራቸው ሊኮሩ ይገባል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ የጋራ ኩራት፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ሀብት ነው።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ የይቻላል መንፈስን የሚያሳይ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ትርፍ የሚያስገኝ ነው፡፡ በራስ አቅም የመሥራትን፣ ጀምሮ የመጨረስን፣ ተደራድሮ የማሸነፍን አቅም የሚያሳይ ነው፡፡ እንደነኢንጂነር ስለሺ በቀለ ያሉ ጀግኖችን ልክ እንደነአክሊሉ ሀብተወልድ በዓለም አቀፍ የድርድር መድረክ ላይ በታሪክ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መሥራትና መፈጸም እንደምትችል ያስመሰከረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን በጋራ ጉዳዩ ላይ አንድ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡

በአጠቃላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ የታሪክ ገመድ ነውና የአብሮነትና የአሸናፊነት ተምሳሌት ሆኖ ትውልድን ያስተሳስራል!

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You