በኢትዮጵያ በአመሠራረታቸው ቀደምት ከሆኑና ለኢትዮጵያውያን ጉልህ አገልግሎት ከሰጡ የሕዝብ ተቋማት መካከል የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።
ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘን ለተሻለና ለከፍተኛ ሕክምና የሚመጡ ታካሚዎች መዳረሻ የነበረው ‹‹አንድ ለእናቱ›› ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀድሞ “የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል” ይባል ነበር። ሆስፒታሉ አሁን ያለውን ስያሜ ያገኘው በ 1967 ዓ.ም ሲሆን “ጥቁር አንበሳ” ማለት በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች ስያሜ ነበር። ፋሺስት ጣሊያንን በሽምቅ ውጊያ ተፋልመው ድል ላደረጉ ጀግኖች አርበኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ሆስፒታሉ ጥቁር አንበሳ ሊባል ችሏል።
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1954 ዓ.ም። ዕለተ -ሐሙስ የያኔውን የልዑል መኮንን ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ፣ የዛሬውን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል። የመሠረተ ድንጋይ በተጣለበት በዓል ላይም ክቡራን ሚኒስትሮች፣ የወቅቱ መኳንንቶች የሆስፒታል ዳይሬክተሮች፣ ሐኪሞች እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ሰዎች ተገኝተው ነበር። በዕለቱም የመታሰቢያ ሆስፒታሉ ቦርድ ፕሬዚዳንት የነበሩት ክቡር ከንቲባ ዘውዴ ገብረሕይወት ባደረጉት ንግግር ሆስፒታሉ ሊሠራበት የታቀደው ቦታ ለዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ታስቦ እንደነበር አውስተው፤ በሥፍራው የሚተካው ታላቅ ሥራ ለተወዳጁ ለልዑል መኮንን ኃይለ ሥላሴ መስፍን ሐረር መታሰቢያ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሠራው ሆስፒታል መሆኑን ገልጸው ነበር።
ከንቲባው በንግግራቸው አያይዘው እንደገለጹት በተወዳጁ መስፍን ስም ለሚቆመው ሆስፒታል ማሠሪያ በወቅቱ የተሰበሰበው የገንዘብ መዋጮ ዝርዝር፡- ከአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብና ከመንግሥት ሠራተኞች ሁለት ሚሊዮን 436 ሺህ 515 ከ 64 ሳንቲም፤ ከኤርትራ 302 ሺህ 557 ከ 25 ሳንቲም፤ ከሐረርጌ 252 ሺህ 862 ከ 53፤ ከሸዋ 238 ሺህ 909 ከ 05፤ ከሲዳሞ 208 ሺህ 632 ከ 60፤ ከከፋ 188 ሺህ 898፤ ከወለጋ 128 ሺህ 182 ከ 77፤ ከኢሉባቦር 118 ሺህ 17 ከ 22፤ ከቤጌምድርና ከሰሜን 107 ሺህ 631፤ ከትግሬ 104 ሺህ 100፤ ከወሎ 103 ሺህ 859፤ ከአሩሲ 18 ሺህ 626፤ ከጎጃም 92 ሺህ 863፤ ከገሞ ጎፋ 59 ሺህ 900፤ ከባሌ 47 ሺህ 328 ከ 50 ተዋጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ልዩ ልዩ ወዳጅ ሀገሮች የሰጡት እርዳታም ነበር።
በ1965 ዓ.ም አንድ መቶ ሃያ ሶስት ሺ ስኩየር ሜትር ከሆነው የሙሉ ጊቢው ስፋት አርባ አምስት ሺ ስኩየር ሜትርን ቦታ የያዘ ባለስምንት ፎቅ ሕንጻ ግንባታ ተከናወነ። ለሕንጻው ግንባታ እና አንዳንድ የሕክምና ግብዓቶችን ለማሟላት የፈጀው ብር ሃያ አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ አምስት ሺ ሶስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ (21,605,399) ነበር። ይህም ገንዘብ ከመንግሥት ሠራተኛ፣ ከነጋዴ፣ ከገበሬና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሰበሰበ እና ከመንግሥትም ተመድቦ በጊዜው ተቋቁሞ በነበረ ከፍተኛ ኮሚቴ በኩል የተሰበሰበ ነበር።
ዘመናዊና በቂ የሕንፃ ግንባታ ግብዓት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ባልነበረበት በዚያ ዘመን ዛሬ ለብዙዎች የፈውስ ማዕከል የሆነው ይህ ዘመን ተሻጋሪና ታሪካዊ ሆስፒታል በ12 ዓመት ተገንብቶ ተጠናቋል። የሕዝብን ፈቃደኝነትና ትብብር አግኝቶ የተገነባውን የዛሬው ጥቁር አንበሳ የያኔው የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታልን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 24 ቀን 1966 ዓ.ም፣ ቅዳሜ ከቀትር በፊት መርቀው ከፍተዋል። ሆስፒታሉ ተመርቆ ወደ ሥራ በገባበት ዘመን በግዙፍነቱ ከአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነበር።
በወቅቱ ሆስፒታሉ ተመርቆ ወደ ሥራ ሲገባ የሕክምና ሕንፃው 500 አልጋዎች እንዲይዝ የተደራጀ ሲሆን፣ በዘመናዊ መልኩ የተደራጁ የተመላላሽ ሕሙማን ሕክምና ክፍሎች፤ እንዲሁም ሰባት የኤክስሬይ፣ ዘጠኝ የኦፕራሲዮንና ሁለት የላብራቶሪ ክፍሎች ነበሩት። ከዚህ በተጨማሪ ለሕክምናና ለነርስ ትምህርት ቤት፣ ለሐኪሞችና ለአስታማሚዎች መኖሪያ የሚሆኑ አራት ዘመናዊ ሕንፃዎች የተሠሩለት ሲሆን፤ በሕክምናው ድርጅት ሕንፃ ካሉት 500 አልጋዎች 25ቱ ነፃ ሕክምና የሚሰጥባቸው ነበሩ።
የሕክምና ድርጅት ሕንፃውን ጨምሮ በጠቅላላው አምስቱን ሕንፃዎች ለመሥራትና ከአንዳንድ ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁስ የማሟያ ዋጋ ጭምር 21 ሚሊዮን 605 ሺህ 399 ብር ወጪ ነበር በጊዜው ሆስፒታሉ የተገነባው።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከንጉሣዊ ቤተሰቦችና ሹማምንቱ ባለፈ በወቅቱ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የነበሩት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የቆጵሮስ ሪፐብሊክ መንግሥት ፕሬዚዳንት እና በ1966 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የአፍሪካ ጥልቅ ምርምር ተሸላሚ የነበሩት የሴኔጋል ሪፐብሊክ መሪ ክቡር ዶክተር ሊዋፖ ልድ ሴዳር ሴንጎር ተገኝተው ነበር።
ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ከልዩ ልዩ ወዳጅ ሕዝቦችና መንግሥታት በተገኘው የገንዘብ መዋጮ የተሠራውን ይህን ሆስፒታል ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በመረቁበት ጊዜ ተቋሙ ለሀገር ብሎም ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን ፋይዳ በሚመለከት እንደተናገሩት፤ ‹‹ሆስፒታሉ ከፍተኛ የሕክምና ተግባር በመፈፀም፤ የሕክምና ባለሙያዎችን በማሠልጠንና ችሎታቸውን በማጎልመስ፤ እንደዚሁም ልዩ ልዩ ምርምርና ጥናት በማድረግ የሚያበረክተው አገልግሎት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጤና ይዞታ መሻሻል ከፍተኛ ጥቅም እንዲሰጥ ተስፋ የተጣለበት ድርጅት ነው።
ሐኪሞችን በማሠልጠንና የሕክምና ምርምር በማድረግ ወደፊት የሚፈጸመው ተግባር ጥቅሙ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሀገሮችም ጭምር አገልግሎቱን እንደሚያበረክትና ለመላው ዓለም ኅብረተሰብ ደህንነት በሚከናወነውም ዓለም አቀፍ የጤና ጥበቃ ተግባሮች ተሳታፊ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፤ ለዚህም የሕንፃው ትልቅነትና የዕቃው መደራጀት ብቻ ከታሰበው ግብ ሊያደርስ ስለማይችል የሚመለከታቸው ኃላፊዎች፤ ሆስፒታሉን ለመምራትና ለማካሄድ ኃላፊነት የተሰጣቸውን ባለሥልጣኖች ጥረትና ትጋት የሚጠይቅ ስለሆነ የሚጠበቅባቸውን ግዳጅ ፈጽመው እንዲገኙ ከፍ ያለ አደራ ተጥሎባቸዋል›› በማለት በጊዜው አሳስበው ነበር።
ንጉሠ ነገሥቱም አክለው፤ “ዘመናዊው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጥበብ የሀገራችን የወሰን ክልል ዘልቆ ብርሃኑን በመዘርጋት በአሁኑ ጊዜ፤ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በቦታ ርቀትና በሀገር ድንበር መጋረጃነት ሳይለያዩ በጉርብትና የሚኖሩ የአንድ ዓለም ቤተሰቦች ናቸው። በሽታም በሀገር ወሰን የማይገታ ስለሆነ የሰው ልጅ ጉልበቱንና ኃይሉን አስተባብሮ የጋራ ጠላቱ የሆነውን በሽታን ለማጥፋት የሚያደርገው ጥረት ከፍ ያለ ጥቅም እንደሚያስገኝ የታወቀ ነው።
የስዊስ መንግሥትና የበርን ካንቶን ለዚህ ሆስፒታል ስላደረጉት ከፍ ያለ እርዳታና ዜጎቹም በተለይም ፕሮፌሰር ሙለር በዚህ ጠቃሚ በሆነ የመተባበር ሥራ ስላደረጉት ጥረት እናመሰግናለን። ይህ ሆስፒታል አገልግሎቱን እንዲጀምር በማድረግ በኩል የስዊስ መንግሥትና ሕዝብ ያደረገው የመተባበር እርዳታና ያሳየው በጎ ፈቃድ በኢንተርናሽናል ደረጃ የሚደረግ መተባበር ከፍ ያለ ጥቅም የሚሰጥ ለመሆኑ የሰው ልጅ ያለውን ጽኑ እምነት በተጨማሪ የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም በላይ ይህ መተባበር በኢትዮጵያና በስዊስ መንግሥትና ሕዝብ መካከል ለብዙ ጊዜ ጸንቶ ለኖረው የቅርብ ወዳጅነት ዓይነተኛ ምስክር ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለልጃችን ለልዑል መኮንን ባለው የፍቅር ስሜት ተነሣሥቶ ይህ ሆስፒታል ለመታሰቢያው እንዲውል በበጎ ፈቃድ ያዋጣውን ገንዘብ እንደታሰበው ከፍጻሜ ለማድረስ ከፍ ያለ ጥረታቸውን ያስተባበሩትን ሁሉ፤ እንደዚሁም የመሥሪያም ሆነ የገንዘብ ርዳታ የሰጡትን የወዳጅ ሀገሮችና በተለይም የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክን፣ የሶቪዬት ኅብረትንና ታላቋን ብሪታኒያን፣ በኢትዮጵያ ያሉ የውጭ ሀገር ሰዎችንና ኮሚኒቲዎችን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ” ሲሉ ንጉሠ ነገሥቱ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተናግረው ነበር።
በወቅቱ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ክቡር አቶ ከተማ አበበ ባደረጉት ንግግር ደግሞ “እንደሚታወቀው ሁሉ ጤንነት በሽታን የማስወገድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የአካልና የአእምሮ ደኅንነትን ማግኘት ነው። የዕለቱንም ሆነ የከርሞውን ሰላምታ የምንለዋወጠው “ጤና ይስጥልኝ” በሚል መልካም ምኞት ስለሆነ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ለጤና የምንሰጠው ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑን ያስታውሰናል።
ጤንነቱ ያልተጠበቀ ሕዝብ፤ አእምሮው ሊጎለምስና የዕውቀትና የጥበብ ባለቤት ሊሆን አይችልም። ለኅብረተሰቡም ሆነ ለሀገሩ ልማት መላ ጉልበቱንና ኃይሉን አስተባብሮ በቂ የሥራ ፍሬ ለማበርከት እንደማይችል የታወቀ ነው። የሕዝብን ጤንነት ለመጠበቅ፤ የጤና አገልግሎት ድርጅትን ብቻ ማስፋፋት በቂ ስለማይሆን፤ ልዩ ልዩ ሥራዎችን በአንድነት መፈጸም አስፈላጊ ይሆናል›› ሲሉ አሳስበዋል።
‹‹ይህ ታላቅ ሆስፒታል የተሠራው ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት እንዲሠጥና የወደፊት የኢትዮጵያ ሐኪሞች የሚማሩበት እንዲሆን ግርማዊነትዎ በሰጡት መሪ ትእዛዝ መሠረት ሲሆን፤ በሁለቱም አቅጣጫ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ታምኖበታል›› በማለትም ተናግረው ነበር።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ንግግር ካደረጉት የውጭ ዜጎች መካከል በኢትዮጵያ የስዊዝ መንግሥት አምባሳደር የነበሩት ክቡር ሚስተር ለንገንባኽር ባደረጉት ንግግር “የዚህን ታላቅ ዕቅድ ሥራ ለመጀመር እዚህ የሚገኙት ስዊስና ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች አማርኛና ስዊስ መሆናቸው ቢታወቅም፤ ይህን ከፍተኛ ክብር የተቀዳጀውን ሥራ በሚያከናውኑበት ወቅት ግን የሚወያዩትና የሚግባቡት የማንኛውም ሥልጣኔ መገናኛ በሆነው በሰብአዊ ስሜት ቋንቋ ነበር›› ሲሉ አምባሳደሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሆስፒታሉ ተመርቆ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት በሕክምናው ዘርፍ ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ ግልጋሎት ከሚሰጡ ተቋማት ግንባር ቀደም ነው። ከሕክምናው ሥራ ጎን ለጎንም አንቱታን ያተረፉ የሕክምና ጠበብቶችንና አጀብ ያስባሉ ዶክተሮችን አፍርቷል። እያፈራም ይገኛል። በዚህም ሀገሪቱ ዛሬ ላይ በዘርፉ ለደረሰችበት የሕክምና ደረጃ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 20 ሚሊዮን በሚገመትበት ዘመን በሕዝብ የተባበረ ክንድ የተሠራው ይህ ሆስፒታል፤ ዛሬ ላይ በትንሹ በዓመት 500 ሺህ ተመላላሽ እና 20 ሺህ ተኝተው የሚታከሙ ህሙማንን እያገለገለ ይገኛል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ለሕብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት በመስጠት ፈር ቀዳጅ ነው። ለአብነትም ለካንሰር ሕመምተኞች የጨረርና የኒኩሊየር ሕክምና በመስጠት ለብዙዎች ሕይወት መቀጠል ምክንያት ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በዓመት ሕመሙ እንዳለባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቁ ከስምንት ሺህ በላይ አዳዲስ ታካሚዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በመምጣት የተቋሙን በር ያንኳኳሉ። ሆስፒታሉ እነዚህን አዳዲስ ታካሚዎች ጨምሮ ሕመሙ እንዳለባቸው አውቀው የፀረ ካንሰር መድኃኒት (ኬሞ ቴራፒ) እና የጨረር ሕክምና ለሚወስዱ በድምሩ በዓመት ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የካንሰር ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል።
በልብ ሕክምና እንዲሁ ሆስፒታሉ ለኢትዮጵያውያን አበርክቶው ከፍተኛ ነው። የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና በመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀደምት እንደመሆኑ ከሀገሪቱ ከአራቱም ማዕዘን በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ወገኖች መዳረሻ ነው።
ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 24 ቀን 1966 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት በሕክምናው ዘርፍ ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ ግልጋሎት ከሚሰጡ ተቋማት ግንባር ቀደም ነው። ተቋሙ የሆስፒታሎች ሁሉ ቁንጮ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል በመሆኑ፤ በሀገሪቱ የጤና አገልግሎት ቅብብሎሽ ሥርዓት ውስጥ የመጨረሻውና ከፍተኛው የጤና ክብካቤ መስጫ ነው።
እኛም በዚህ የባለውለታዎቻችን ዓምድ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባውንና ለዘመናት ከአራቱም ማዕዘናት ለሚመጡ የከፍተኛ ሕክምና ፈለጊዎች አለኝታ ሆኖ ያገለገለውን አንጋፋ ተቋም አመሰገንን። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም