የሀገር አንድነትን ለማጠናከር የብዝኃ ቋንቋዎች ትምህርት አስፈላጊ ነው

አዲስ አበባ፡- ባሕሎችን እርስ በእርስ ለመቀያየርና የሀገር አንድነትን ለማጠናከር የብዝኃ ቋንቋዎች ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ በ51 ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ቋንቋ፤ የምልክት ቋንቋና ትርጉም ላይ ያተኮረ ጉባኤ “የብዝኃ ቋንቋ ትምህርት፤ ከትውልድ ትውልድ ለሚዘልቅ ትምህርት ምሰሶ ነው!” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የብዝኃ ቋንቋዎች ትምህርት ባሕሎችን እርስ በእርስ ለመቀያየርና የሀገር አንድነትን ለመገንባት ወሳኝ ነው፡፡

በኢትዮጵያ እየተነገሩ ከሚገኙ ከተመዘገቡ 76 ቋንቋዎች 51ዱ የትምህርት ቋንቋዎች ሆነው ትምህርት እየተሰጠባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ላይ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ተናግረው፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ቋንቋዎች በየክልሉ ብቻ ተወስነው እንዳይቀሩ እንደ አገር ብዝኃ ቋንቋዎች መናገር የሚችል ማኅበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ ይህንን ማድረግ እንዲቻልም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቋንቋ ፖሊሲ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡

በቋንቋ ፖሊሲው ላይም አምስት ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ የተወሰነ ሲሆን እንደ አገር ብዝኃ ቋንቋዎች ላይ ትልቅ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሪት ፈይዛ መሐመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ቋንቋዎች ማንነትን በመገንባት፣ ማኅበረሰባዊ ትስስርን በማስቀጠል እና ልማትን በማፋጠን ሚናቸው የላቀ ነው።

ሀብት የሆነው ቋንቋ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሉት ጠቁመው፤ እያንዳንዱን የቋንቋ ሀብት ማበልጸግ ሀገርን ማበልጸግ በመሆኑ ቋንቋዎች ላይ በተለይ ከለውጡ በኋላ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር ውጤታማ የትምህርት አቀባበልን ለማጎልበት፣ ስለራስ ጠንቅቆ ለማወቅ እንዲሁም ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈን ትልቅ ጥቅም እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ጉባኤው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመናገር ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ ሲሆን በብዝኃ ቋንቋዎች እና በምልክት ቋንቋ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሑራን ቀርበዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You