ባለሥልጣኑ ዳግም ላልተመዘገቡና ሪፖርት ላላቀረቡ 1 ሺህ 854 ድርጅቶች ጥሪ አደረገ

አዲስ አበባ፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዳግም ምዝገባ ላላከናወኑና የፋይናንስ እንዲሁም ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት ላላቀረቡ አንድ ሺህ 854 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመጨረሻ ዙር ጥሪ አድርጓል።

ባለሥልጣኑ ዳግም ባልተመዘገቡና ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ዓመታዊ ሪፖርት ባላቀረቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚረዳ የውይይት መድረክ ትናንት አካሂዷል፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በዕለቱ እንደገለጹት፤ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት ዳግም ምዝገባ ላላከናወኑና ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የፋይናንስ እንዲሁም ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት ላላደረጉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመጨረሻውን ዙር ጥሪ ቀርቧል፡፡

እንደ አቶ ፋሲካው እንዳመለከቱት፤ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት አንድ ሺህ 558 ድርጅቶች ዳግም ምዝገባ አላካሄዱም፡፡

በተጨማሪም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ዓመታዊ ሪፖርት ያላቀረቡ 296 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ለድርጅቶቹ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች እንዲሁም በግል ስልኮቻቸው ለበርካታ ጊዜ ጥሪ ቢደረግም ቀርበው መመዝገብና ሪፖርት ማድረግ አልቻሉም ሲሉ አስረድተዋል።

ባለፋት ዓመታት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል ያሉት አቶ ፋሲካው፤ የሪፎርሙ ዋና ዓላማ የመደራጀት መብት በማረጋገጥ በእንቅስቃሴያቸው የሕዝብንና የመንግሥትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

እንደ ተቋም የተያዘው ራዕይ ለማሳካት እንዲሁም የዳበረና ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለመፍጠር የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ይህንንም ለማረጋገጥ የድጋፍና ክትትል መመሪያና ደንብ በማውጣት እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ቀድሞ የነበረው አዋጅ አሳሪና በርካታ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች እንዲከስሙ አድርጎ እንደነበር ያነሱ ሲሆን፤ የተሻሻለው አዋጅ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ዓውድ ተፈጥሯል ብለዋል።

ዳግም ምዝገባ ያላደረጉና ዓመታዊ ሪፖርታቸው ያላቀረቡ ድርጅቶች በመጨረሻው ዙር ጥሪ ቀርበው አሳማኝ ምክንያት ካላመጡ ባለሥልጣኑ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ርምጃ እንደሚወስድም አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሚያከናውኑት ተግባራት እንዲሁም ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርታቸው በተገቢው ጊዜ የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸውም አቶ ፋሲካው ተናግረዋል፡፡

ጥሪው ድርጅቶቹ የተሰጣቸው ዕድል ተጠቅመው ዳግም ሕልውናቸው እንዲያረጋግጡ ለማስቻል መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የባለሥልጣኑ የቦርድ አባል ወይዘሮ ትነበብ ብርሃኔ በበኩላቸው፤ የውይይቱ ዋና ዓላማ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ዳግም ያልተመዘገቡ ድርጅቶችን እንዲመዘገቡ ጥሪ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕልውናቸው ያላረጋገጡ ድርጅቶች ሕልውናቸውን አረጋግጠው ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ተግባር ማከናወን እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ ለተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ ደኅንነቱን የጠበቀና ምሕዳሩን ማስፋት እንደቻለ ጠቁመው፤ ድርጅቶቹ የተጠያቂነት መርሕ መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You