“ከሕዝባችን ጋር ተባብረን በመስራታችን የተረጋጋ የፖለቲካ አካባቢ ተፈጥሯል” – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር፤

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 11ኛ ክልል ሆኖ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት አልፎታል። ለክልሉ መመስረት ዋና መነሻ የሆነው ደግሞ በሕዝቦች ሲነሱ የነበሩ የፍርሃዊ ተጠቃሚነት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፤ የመልማት ፍላጎት፤ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እና ተጠቃሚነትን የመሳሰሉ ጥቄዎችን ለመመለስ ነው።

እኛም በዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን፣ የክልሉን መመስረት ተከትሎ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ከመመለስ አኳያ በተለይም የክልሉ አመራሮች የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት እና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ ያከናወኗቸውን ተግባራት፤ የነበሩ ችግሮችና የቀጣይ የቤት ስራዎቻቸው ላይ በማተኮር፤ ከክልሉ ርዕስ መስተዳደር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶክተር) ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል። መልካም ምንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተመሰረተ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል፤ አዲስ ክልል እንደመሆኑ መጠን ለሕዝቡ ምን መልካም አጋጣሚዎች ተፈጠሩለት? ምን ችግሮች ገጠሙት?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- ክልሉ በይፋ ተመስርቶ ስራ ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ እያስቆጠረ ይገኛል። በእነዚህ ዓመታት በክልሉ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ በርካታ ለውጦች ታይተዋል። የክልሉ መመስረት ዋና ምክንያት ሕዝቡ ያነሳቸው የነበሩትን በርካታ የፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ነው። በተለይም የመደራጀትና ራስን የማስተዳደር፤ የሀብት ክፍፍል፤ የስልጣን ክፍፍል፤ የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ነው።

በመሆኑም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በጊዜው እና በወቅቱ የሚፈታ የአስተዳደር መዋቅር የለም በሚሉ የሕዝብ ጥያቄዎች መነሻነት የተፈጠረ ክልል ነው። አሁን ላይ እነዚህን ጥያቄዎች የክልሉ አመራር ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህም በዋናነት ከፖለቲካና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች አኳያ መጀመሪያ ክልል ሆኖ ሲደራጅ እንደ አመራር የፈታነው አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተለይም በታችኛው የእርከን የመዋቅር ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ነው።

ከእነዚህ መካከል በርካታ ወረዳዎችን ከልዩ ወረዳነት ወደ ዞን የማምጣት፤ የከተማ አስተዳደርን የቀበሌ ወሰን አደረጃጀቶችን መከለስ፤ የገጠር ቀበሌዎችን በተለይም በጣም ሰፊና ለአስተዳደር ምቹ ያልሆኑትን ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ የሚሉት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። ይህንን ያደረግነው በጥናት ላይ ተመሰረተን ነው። በዚህም የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ ተችሏል።

ከዚህ ባለፈ በክልሉ ባሉት ዞኖች፣ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ የተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢ በመፍጠር ረገድ አመርቂ ስራዎች ተከናውነዋል። ለውጡ በመጣ ማግስት አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች በርከት ያሉ የጸጥታ ስጋት እና የሰላም መደፍረስ ነበረባቸው። በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አጠቃላይ የማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች የተገቱበት ጊዜ ነበር፡፡

ለአብነትም፣ በሸካ ዞን የኪ ወረዳና አካባቢው፣ ቴፒ ከተማ፣ በቤንች ሸኮ ዞንና አካባቢው፣ በቤንች ማጅ፤ በምዕራብ ኦሞ ዞን እና አካባቢው ሰፊ የፀጥታ ስጋት የነበረበት ነው። በዚህም የሕዝቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተገታበት፤ የተለያዩ ሕገ ወጥ ቡድኖች ተፈጥረው አካባቢውን የተቆጣጠሩበት ሁኔታ ነበር። እነዚህን ችግሮች በመለየት ሰላማዊ የፖለቲካና የማኅበራዊ እንቅስቃሴን የሚገድቡ ነገሮችን ከማጽዳት፤ ከማረምና ከማስተካከል አኳያ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

አዲስ ዘመን፡- ከተሰሩት ስራዎች በተጨባጭ ማሳያ ቢጠቅሱልን?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ የሰላምና ፀጥታ መዋቅሩን በማደራጀት በአቅምና በሎጂስቲክ በመደገፍ ወደ ማኅበረሰቡ በማውረድ ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል። በዚህም ማኅበረሰቡ ለሰላሙም፣ ለልማቱም ተባባሪ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

ይህን ለማድረግ ስራ ስንጀምር፣ “አመራሩ በሰዓቱና በወቅቱ ችግሩ እንዲፈታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየን? አመራሩ ማኅበረሰቡን ከጠየቀ እና ከአወያዩ በኋላ ችግሩን በመፍታት ረገድ ውጤት አይታይም። ጥቆማ እንሰጣለን፤ ምስክረትነት እንሰጣለን እናንተ መፍትሔ አትሰጡም። በዚህም እነዚህ ሕገ ወጥ ቡድኖች መልሰው እኛን ያጠቁናል። አሁንም ይህ የሚደገም ከሆነ ከእናንተ ጋር ብንተባበርም ውጤት አናመጣም፤” የሚሉ ጥያቄዎች ከማኅበረሰቡ ቀርበው ነበር።

ነገር ግን ከሕዝቡ ጋር በግልጽ እውነቱን ይዘን በመወያየት እና ፈጥነን ወደ ውሳኔና እርምጃ በመግባት በውይይት የሚመለሱትን ሕገ ወጥ ቡድኖችን በውይይት፤ በምክክር የሚመለሱትን በመመካከር፤ ጫካ ገብተው ሽፍታ ሆነው የቀሩትን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመመካከር የጋራ ሕዝባዊ ውይትና ምክክር ተደርጎ መጠነኛ የወንጀል ድርጊት ውስጥ የገቡትን ከሕዝቡ ጋር በማስታረቅ ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።

በንብረት፣ በሕይወት እና በሌሎች የሰብዓዊ ጥሰት ሰፊ ጉዳት ያደረሱ፤ በተባባሪነት የተሳተፉትን አካላት ደግሞ ወደ ሕግ የማቅረብ ስራ ተሰርቷል። ነገር ግን ከዚህ ውጭ አሻፈረኝ ብለው በጫካ መሽገው ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር ግጭት ለመግባት የሞከሩትን እርምጃ የመውሰድና የማስተካከል ስራ ተሰርቷል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የከልሉ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- አሁን ላይ በተሰራው ስራ በክልሉ ፍጹም ሰላም እንዲሰፍን ተደርጓል። ይሄን ለማረጋገጥም ወደ ሕብረሰቡ ወርዶ መረጃ መውሰድ ይቻላል። አጠቃላይ በክልሉ ሰላምን ከማስፈን አንጻር እንደ ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰዱ ስራዎችንም አከናውነናል።

ከዚህ አንጻር በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተሳትፈው በሕግ ቁጥጥር ስር የነበሩ፣ ሕይወት ያጠፉት፣ በከባድ የሰብአዊ ጥሰት የተያዙትን፣ የሰው ንብረት ያወደሙ እና ተባባሪዎቻውን በመለየት እንደ ተሳትፏቸውና እንደ በደላቸው መጠን ለበደሏቸው የሕብረተሰብ ከፍሎች ካሳ መከፈል አለባቸው በሚል የካሳ ስርዓት በመዘርጋት እንደ በደሉ መጠን ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የሕብረተሰባችን ክፍሎች በካሳ ስርዓቱ ከ75 ሺ ብር እስከ 150 ሺ ብር ድረስ እንዲካሱ ተደርጓል። በዚህ አሰራር ከእስር የተፈቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዜጎች ዛሬ ላይ ሰፈራቸውና አካባቢያቸውን እንዲሁም ከተሞቻቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።

ከዚህ ባሻገር በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ አካባቢ ከኑሮው ዘየ ጋር ተያይዞ በግጦሽ እና በከብት ስርቆት ጋር አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶች አሉ። ጋብቻ ለመፈጸም በርከት ያለ ከብት ስለሚያስፈልግ ከብቱን ማግኘት አንዱ ከአንዱ ጋር የመቀማት ሂደት ውስጥ ወደ ግጭት የመግባት ጉዳዮች አሉ። እነዚህን በምክክርና በንግግር እየፈታልን ነው። ከዚህ ውጭ በክልሉ የሚታይ የከፋ የጸጥታ ስጋት አሁን ላይ የለም። በዚህ በኩል ሲታይ ከሕዝባችን ጋር አብረን መስራት በመቻላችን የተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢን መፍጠር አስችሎናል።

አዲስ ዘመን፡- በኢኮኖሚው ዘርፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር ምን እየተሰራ ነው?

ኢንጂነር ነጋሽ(ዶ/ር)፡- በኢኮኖሚው ዘርፍ ክልሉ በተነጻጻሪነት ከሌሎች አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ያለው ነው። ምቹ የሆነ የመሬት፣ የውሃ፤ የደን ውጤቶችና የአየር ጸባይ ባለቤት ነው። ምን አልባት በአማካይ በዓመት ውስጥ ዘጠኝ ወራት ያህል ዝናብ አለው። ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ያለው ክልል ነው። የሚታረስ ለም መሬት በስፋት ያለው ነው። ስለዚህ ይህን የተፈጥሮ ጸጋ እንዴት አድርገን ለሕዝቡ ልማት ማዋል አለብን? የሚል ቁጭት ስለነበረን በግብርና እና በተፈጥሮ ሀብት ዘርፉን ሰፊ ስራዎችን ሰርተናል።

ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል ጾም የሚያድሩ መሬቶች እንዲታረሱ፤ በበጋ እንዲያመርቱ የማድረግ፤ እርጥበት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ፤ በቡና ምርት አካባቢው የታወቀ ነውና ይሄን ምርትን እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚለውን ለአርሶ አደሩ ተከታታይ የሆነ የአቅም ግንባታ ስራዎች የመስራት፤ የማስፋፋትና ከአረንጓዴ ልማት አሻራ ጋር በማያያዝ፤ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት በተለይም በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላሞች ላይ እና አካባቢው በሚታወቅባቸው የበግ ዝርያዎች (የቦንጋ በግ) ላይ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ይህም በአንድ በኩል የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አሳድጓል። በሌላ በኩል የሀገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አንጻር የራሱን አስተዋጾ እያበረከተ ነው። ከዚህ ባሻገር ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል ምንጭ እየሆነ እና እየተነቃቃ የመጣበት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል። አሁን ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዓመት ከ55 እስከ 65 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ ነው። ይህም ማደግ አለበት። ይህን የተመለከቱ የክልሉ ደጋማ አካባቢዎች ቡናን ለማብቀል እየተለማመዱ ነው።

በክልሉ እንደ ኮረሪማ፤ ዝንጅበል፤ እርድና መሰል ቅመማ ቅሞች በስፋት ይመረታሉ። በጫካ ማር ክልሉ በስፋት የሚታወቅ ነው። በዚህም በርካታ የማኅበረሰባችን ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከዚህ በፊት ለአርሶ አደሩ ትልቅ ማነቆ የነበረው ምርጥ ዘር የግብዓት ችግር ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በቀጣይም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በማሰብ ክልሉ ምርጥ ዘርን ከተለያዩ አካለት ጋር ተቀናጅቶ የማምረት ስራ ጀምሯል። በዚህም የተሻለ ምርት መሰብሰብ ተጀምሯል። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ምርጥ ዘርን ክልሉ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ክልሎች ለማቅረብ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው።

በሌላ በኩልም በክልሉ ውስጥ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አሉ። በውሃ፤ በመንገድ፤ በጤናና ትምህርት ተቋማት፤ የተለያዩ የቢሮ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው። የመንግስት ተቋማት መድረስ ያልቻሉባቸው ቦታዎች ላይ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ክፍተት መሙላት አለብን ብለን በክልሉ የኮንስትራክሽን ቢሮ በማቋቋም ወደ ስራ ተገብቷል። በዚህም በጥናት በዲዛይንና በግንባታ ዘርፍ በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማት ክፍተት ያለባቸውን አካባቢዎች ተረክበው እንዲሰሩ ለማድረግ እየሰራን ነው።

በተመሳሳይ፣ የገቢና የሀብት አሰባሰብ ትልቁ የክልሉ የትኩረት መስክ ነው። እንደ ክልል ተመስርተን ስራ ስንጀምር አምስት ቢሊዮን ብር እዳ በመያዝ ነው። ዕዳው በግልጽ የተለየ ዕዳ ሲሆን፤ ከነባሩ ክልል በክፍፍል የደረሰን ነው። በግልጽ ያልተለየ የጡረታና መሰል ውዝፍ ዕዳ ቢኖርም የተለየውን አምስት ቢሊዮን ብር ዕዳ ይዘን ስራ ጀምረናል። ዕዳው ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝና ለሌሎች መንግስታዊ ወጪዎች ተብሎ የተመደበ ነው። ይህን ዕዳ ለመመለስ መስራትና ሌላ ሀብት መፍጠር አለብን ብለን ራሳችን የውስጥ የገቢ አቅም የማሳደግ ስራ ሰርተናል።

ክልል ሆኖ ስራ በጀመረ የመጀመሪያው ዓመት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር፤ ሁለተኛው ዓመት ላይ አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ገቢ መሰብሰብ ተችሏል። በተያዘው ሶስተኛው ዓመት ላይ ስድስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ አሁን ላይ የእቅዱን 48 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ከዚህ በላይ ማሳደግ አለብን ብለን እየሰራን ነው። በተፈጠረው ሀብትም ዕዳችን መመለስ አለብን ብለን ከአምስት ቢሊዮን ብር ዕዳ በሁለት ዓመት ውስጥ ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ዕዳ መመለስ ችለናል። ቀሪውን እዳ እስከሚቀጥለው ግማሽ በጀት ዓመት ድረስ ለመመለስ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ይህ ሲሆን የሚሰበሰበውን ገቢ የማሳደግ ስራ ተከናውኗል። የገጠር መሬት መጠቀሚያ ግብር አዋጅ በምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ አንድ ለውጥ የሚያመጣ ነው። የኢንቨስትመንት መሬት ግብር ተሻሽሏል። የደረጃ ‹ሀ› ግብር ከፋዮች ተመን በጣም ዝቅተኛ የነበረው ተለይቶ እንዲሻሻል ተደርጓል። ግብር በመሰብሰብ ለተለያየ ግላዊ ጥቅም ይውል የነበረውን ስርዓት በማስያዝ በሕግና በስርዓት እንዲመራ የማድረግ ስራ ሰርተናል።

ከሀብት ምዝበራ ጋር ተያይዞ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ላይ ውስን የሕዝብና የመንግስት ሀብትን ለግል ጥቅምና ለተለያየ ዓላማ የማዋል አዝማሚያ በሰፊው ይስተዋል ነበር። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ኦዲት በማስደረግ የኦዲት ግኝትን የማስመለስ፣ ተጠያቂነትን የማስፈን፣ በሙስናና ብልሹ አሰራር ውስጥ የገቡትን ወደ ሕግ የማቅረብና የመጠየቅ ስራዎች ተሰርተሰዋል። እነኝህ ስራዎችም በዋነኝነት በስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ቢሮ አማካኝነት የተከናወኑ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ያለውን የመሰረተ ልማት ችግር ለይቶ ከመስራት አኳያ ምን ጅምሮች አሉ?

ኢነጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- ክልሉ ሰፊ የመሰረተ ልማት ችግር ያለበት ክልል ነው። የመንገድ፤ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት እና ሰፋፊ ግንባታዎች ተጀምረው እስከ ዘጠኝ ዓመታት በላይ ሳይጠናቀቁ ባሉበት ቆመው የሚገኙበት ክልል ነበር። ይህን ችግር ለመቅረፍ በክልሉ በጀት አቅም መጠናቀቅ የሚችሉትን እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሆስፒታሎች፤ ጤና ጣቢያ ተቋማትን፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ መንገድ፣ ድልድዮችን እና መሰል መሰረተ ልማቶችን ልየታ በማድረግ እና ስራዎቻቸውን በማጠናቀቅ አሁን ላይ የማስመረቅ ስራዎችን ሰርተናል። ይህም በሁሉም አካባቢዎች ሚዛናዊና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የተከናወነ ነው።

ለእነዚህ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ትልቁን የሀብት  ምንጭ አድርገን የተጠቀም ነው የማኅበረሰብን ተሳትፎ ነው። ለምሳሌ፣ ባለፉት ጊዚያት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በስድስት ወራት ብቻ 840 ሚሊዮን ብር ከሕዝብ ቃል የተገባ ሲሆን፤ 264 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። በመንገድ ዘርፍ በሁለት ዓመት ውስጥ 220 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ማሽኖችን በመከራየት በርካታ የገጠር መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ክልል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በፕሮጀክቶች ላይ የገጠሙ ችግሮች የሉም?

ኢነጂነር ነጋሽ (ዶክተር)፡- የገጠሙ ችግሮች አሉ። በተለይም ትላልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ፣ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሰሩባቸው ቦታዎች ላይ ሰፊ ሀብት የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ፈተናዎች ነበሩ። በዚህም ሕዝቡ ኃላፊነት ወስዶ መንግስትን መጠበቅ የለብንም በሚል ስሜት ሀብት የማሰባሰብ ስራ በመስራት ከተሞችን ለማልማት፤ በከተሞች አካባቢ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል። ለዚህ ደግሞ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው የአስተዳደር እርከን ተናቦ የመስራትና ፍትሃዊ የልማትና መሰረተ ልማት ተደራሽነት የሰፈነበት አካባቢን መፍጠር አለብን ብለን በልኩ እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ዕምቅ ሀብት ያለው ሆኖ እያለ ሕዝቡ ከሀብቱ ፍታዊ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ። እርስዎ ይህን እንዴት ይመከቱታል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡– ሀብት መኖርና ሀብቱን በስርዓት መጠቀም ሁለቱ ተመጋግበው መሄድ አለባቸው። ሀብቱን በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም። የክልሉ ሀብት የሚባለው መሬት፤ ውሃ፤ መልካም የሆነው አየር ጸባዩ ነው። የመንግስት ዋና ተልዕኮ ሀብቱን በአግባቡ በመረዳት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል አሰራሮችን መዘረጋትና አቅጣጫ ማሳየት ነው። ከዚያ ውጭ ግን የክልሉን ሕዝብ ሀብት የሚቀራመት አካል የለም።

የፌደራል መንግስትም ይሁን ሌሎች ክልሎች የክልሉን ሕዝብ ሀብት የወሰደ የለም፤ የሚወስድም አይኖርም። ሀብቱ በእጃችን ነው፤ የምንጠቀመውም እኛው ነን። ሕዝቡ አልተጠቀመም የተባለው ሌላ አካል እየወሰደ ነው ከሚል መነሻት ከሆነ ስህተት ነው። ግን ያለውን ሀብት አሟጠን አልተጠቀምንበትም ከሆነ ጥያቄ ልክ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት የክልሉ ሕዝብ ለልማት መዋጮ ሲጠየቅ የሚዋጣው አስር ብር ነበር። አሁን ግን ከ30 ሺህ በላይ ጥሬ ገንዘብ የሚሰጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ሕዝቡ የክልሉን ሀብት ከመጠቀሙ የመነጨ ስለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው።

ምን አልባት ለእኛ ትልቁ ፈተና የመሰረተ ልማት ነው። አርሶ አደሩ ምርት ያመርታል። ግን ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ የሚያወጣበት የመንገድ የመሰረተ ልማት ችግር አለ። በዚህ ላይ ከሆነ በጣም የሚያስማማ ነው። እኛም የምናውቀው ነው። የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር አርሶ አደሩ አምርቶ ለገበያ ከማድረሱ በፊት ያመረተው ምርት በስብሶ የሚደፋበት አጋጣሚ አለ። እግር ጥሏችሁ ወደ ቴፒ፣ በከፋም፣ በሸካ ብትሄዱ ጥቅል ጎመን እና መሰል የግብርና ምርቶች መንገድ ላይ ተጥለው ልታገኙ ትችላላችሁ። ይህ አርሶ አደሩ ወደ ገበያ አምጥቶ የሚሸጥበት መንገድ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነው።

ድንችን በአይሱዙ ጭኖ ለመሸጥ በኩንታል በኩንታል አስሮ አስሮ ያስቀመጠ አርሶ አደር በመንገድ ችግር አይሱዚው ሳይመጣ ይቀርና ድንቹ እዚያው ማሳው ውስጥ በስብሶ ይቀራል። ሽንኩርትም እንደዚሁ። እነኝህን ችግሮች ለመፍታት በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ነው።

የእኛ ክልል ሕዝብ አሁን ላይ መንግስትን ምግብ አይጠይቅም። ውሀ እና መብራትም አይጠይቅም። ቁጥር አንድ የሚጠይቀው ጥያቄ የመንገድ መሰረተ ልማትን ነው። የክልል አመራሮች በየሄዱበት የሚጠየቁት የመንገድ ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ ፍትሀዊ ነው። እንደመንግስትም ስናየው ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የመንገድ ስራዎች ሲሰሩ እና ሲመረቁ ነበር። እዚህ አካባቢ ግን የመንገድ ስራዎች ትኩረት አልተሰጣቸውም ነበር። በመሆኑም አሁን ላይ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የመንገድ እጥረት አለ።

ሆኖም፣ በክልላችን ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶ የተጀመሩ በርከት ያሉ መንገዶች አሉ። እነዚያ መንገዶች ግንባታ ሲጠናቀቅ የክልሉ ትልልቅ ችግሮች አብረው ይፈታሉ። ነገር ግን የአስፋልት ግንባታ በባህሪው ሰፊ ሀብት የሚጠይቀው ነው። በመሆኑም መንግስት ላይም ጫና ይፈጥራል።

በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ ከፌደራል መንግስት ጋር ከአራት ጊዜ በላይ ምክክር እና ውይይቶችን አድርጓል። አንዳንዶችን መፍትሔ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

አብዛኛዎቹ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች 40 እና 50 በመቶ ስራቸው የተጠናቀቀ ስለሆነ ከመንገድ ጋር ያሉ ችግሮች በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ባሉት ጊዜያት ይፈታሉ ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን ፡- ከቡና ንግድ ጋር ተያይዞ ችግር እንዳለ ይነገራል ? ይህ እንዴት ይመለከቱታል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- ቡና ጋር ያለው ትክክል ነው። በቡና ንግድ ዘርፍ ትልልቅ ሸፍጦችም አሉ። ንግድ ስርዓቱ ውስጥ ቀላል የማይባል ሸፍጥ አለ። አርሶ አደሩ ያመርታል፤ በዩኔን ተደራጅቷል። ለዩኒየኑ ምርት ያቀርባል፤ ዩኒየኑ ደግሞ ትስስር ፈጥሮ ውጭ የሚልከውም ወደ ውጭ ይልካል፤ ሀገር ውስጥ ለሚያስረክበውም ያስረክባል።

በግብይት ስርዓቱ ውስጥ አርሶ አደሩ ወደ ውጭ የሚልክበት አግባብ ነበረው። በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ የሚፈጠሩ ቀላል የማይባሉ ችግሮች አሉ። እነኝህ ችግሮች በተደራጀ መልኩ የሚከናወኑ ስላልሆኑ ገበያው ውስጥ የሚፈጠሩት አልፎ አልፎ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህን ማነቆዎችን ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በመሆን እየፈታን እንገኛለን።

አሁን በእኛ ክልል ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ የቡና ማሳ አለ። ይህ ቀላል አይደለም። የአራንጓዴ አሻራ ስራ ከጀመርን ወዲህ ይህ የቡና ማሳ እየሰፋ ነው። በዓመት ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ቡና እየተከልን ነው። እስከ 80 ሚሊዮን የቡና ችግኝ በየዓመቱ እንተክላለን። አሁን ላይ ሰው ጥቅሙን ስለተገነዘበ ቡናን በስፋት እየተከለ ነው። ስለዚህ ይህ የሀገር ችግር እንዳይገጥመው አንደ ክልል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ ለሰራተኞች ደምወዝ የመክፈል ችግር ገጥሟችሁ እንደነበር ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ደምወዝ የመክፈል አቅም ከመገንባት አንጻር አሁን ላይ ክልሉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- እኛ ካለን ዓመታዊ ሀብት እና በጀታችን ውስጥ ትልቁ ወጭ ለሰብኣዊ መብት ወጭ የሚደረግ ነው። ሰብዓዊ መብት የምንለው ደግሞ ደምወዝ እና ጡረታ ነው። ለእነዚህ በጀት ሳንመድብ ለሌላ ተግባር በጀት አንመድብም። የትኛውም የልማት ስራ ቢሆን ይዘገያል እንጂ ደምወዝ እንከፍላለን፤ የጡረታ መዋጮ እንሸፍናለን። ክልሉ እንደተመሰረተ መጀመሪያ ዓመት እና የሁለተኛው ዓመት ግማሽ አካባቢ በክልሉ ላይ ውዝፍ እዳዎች ስለነበሩ ደምወዝ እና የጡረታ ከፍያ ለመክፈል ጫና ፈጥሮብን ነበር። ደምወዝ ለመክፈልም ተቸግረን ነበር። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በብድር እና በተለያዩ ሁኔታዎች ከፌደራል መንግስቱ ያገኘናቸውን ገንዘቦች ተጠቅመናል። አሁን ግን እነዚህ ችግሮች ተፈተዋል።

አንዳንድ መዋቅሮቻችን ላይ የደምወዝ በጀት ብለህ ቆርጥህ ልከህ በአስተዳደራዊ ብልሽት ምክንያቶች ለደሞዝ የተላከውን ገንዘብ ለሌላ ዓላማ የማዋል ነገር አለ። እኛ ግን ገንዘቡን የላክነው ደምወዝ እንዲከፈል ለማድረግ ነበር። እናም ለተባለው ዓላማ መዋል ሲገባው ላልተፈለገ ዓላማ ሲያውሉ የተገኙ አመራሮች አጋጥመውናል። በዚህም ሳቢያ ደምወዝ ያልተከፈላቸው ሰራተኞች አግኝተናል። ይህን ችግር በፈጠሩ አመራሮች ላይ እርምጃ ወስደናል። የማስተካካያ ስራዎችንም ሰርተናል። እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ካልሆኑ በስተቀር እንደ ክልል ፕሮጀክቶችንም አቁመን ቢሆን ደምወዝ እንከፍላለን።

አዲስ ዘመን ፡- ቦንጋ በኢትዮጵያ የንግድ ታሪክ ግንባር ቀደም ከተማ ናት። አሁን ደግሞ የክልል መንግስት መቀመጫ ሆናለች። ከዚህ አንጻር ቦንጋ ከሌሎች የክልሉ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ትችል ዘንድ ምን እየሰራችሁ ነው?

ኢንጂነር ነጋሽ(ዶ/ር)፡- ትክከል ነው፤ ቦንጋ ታሪካዊ ከተማ ናት። ነገር ግን ቦንጋ ብቻ አይደለም ሁሉም የክልላችን ከተሞች ማደግ አለባቸው። መቀየር እና መለወጥ አለባቸው። አሁን ትልቁ ጥያቄ የነበረው የከተሜነት መስፋፋትን የሚመጥን የመሰረተ ልማት መኖር አለበት ነው። እውነት ነው ቦንጋም ረጅም እድሜ ያስቆጠረች ናት። ግን የእድሜዋን ያህል አላደገችም። ስለዚህ ቦንጋም፣ ተርጫም፣ ሚዛንም፣ አመያ እና ሌሎችንም ከተሞች እናሳድጋለን ካሉ ከተማው ራሱን የሚያሳድግበት ስትራቴጂክ ፕላን መፍጠር አለበት፡፡

እኛ እንደክልል አመራር ትልቁ ስራችን መሆን ያለበት ምቹ የሆነ ፖሊሲ መቅረጽ ላይ ነው። የእኛ ስራ ከተሜነትን፣ የከተማ መስፋፋትን እና የከተማ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን መቅረጽ ነው። የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ነው። ከተሞችን ለልማት ምቹ የማድረግ ስራ መስራት ነው። የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የመሰረተ ልማት ጥናትና ዲዛይን መንደፍ፣ ከፌደራል መንግስት የሚገኘውን ሃብት በአግባቡ ማስተዳደርም ትልቁ የእኛ ተልእኮ ነው።

ነገር ግን እኛ የከተማ መሬት አናስተዳድርም። የቦንጋ ከተማ መሬት የማን ነው? የቦንጋ ሕዝብ እና የቦንጋ ከተማ ነው። የሚዛን፣ የቴፒ፣ የተርጫም ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ከተማ አስተዳደሮች የከተማ ገቢ ማስገኘት የሚያስችል መሬት አላቸው። የገቢ ማስገኛ ማዘጋጃዊ ርዕሶች በርካታ ናቸው። ከንግድ ትርፍ የሚገኘው ሀብት ቀላል አይደለም። ከእነዚህ ሃብት ያመነጫሉ። ስለዚህ እያንዳንዱ ከተማ ከራሱ የሚያመነጨውን ሃብት ለከተማው ልማት ማዋል አለበት። ካልተሰበሰበ ደግሞ ችግሩ የከተማው ነው። ሰብስቦም ለልማት ካላዋለ አሁንም ችግሩ ከተማውን የማስተዳደሩ አካላት ኃላፊነት ነው፡፡

የእኛ ትኩረት በከተማዋ አቅም ያማይሸፈኑ የመሰረተ ልማት ክፍተቶች በሚኖሩበት ሰዓት፣ በገጠሩ አቅም የማይሸፈኑ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ባሉበት ወቅት ድጋፍ ማድረግ ነው። ስለዚህ ከተሞች በዚያ ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው። ከመንግስት ምንም መጠበቅ የለባቸውም። ምክንያቱም ከበቂ በላይ ሀብት መፍጠር የሚችሉበት እድል አለ። እየፈጠሩ እንደሆነ እያያን ነው። ያ ግን በአግባቡ ለስራ ይውላል ወይስ አይውልም? የሚለውን ክልሉ በቀጥታ ጣልቃ የሚገባበት አግባብ የለውም። ምክንያቱም ከተሞች የራሳቸው ከተማ አስተዳደር፤ ምክር ቤት፤ የራሳቸውን በጀት የሚወስን እና ያንን በጀት ደግሞ የሚያስተዳድር ተቋም አላቸው። ስለዚህ የእኛ ስራ ክትትል እና ድጋፍ የማድረግ ነው።

ከዚ ውጭ ለሁሉም ከተሞቻችን ተመሳሳይ ፓኬጆች ይወርዳሉ፤ የክትትል እና ድጋፍ ስራም ይሰራል። ስለሆነም ቦንጋ ታሪካዊት እና የክልሉ መንግስት መቀመጫ ብትሆንም በራሷ አቅም ማደግ እና መለወጥ አለባት የሚል እምነት አለኝ። ይህ አሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የምንሰራበት ነው።

አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሃብት ተጠቅሞ ወደ ኢኮኖሚ ከመቀየር አንጻር ምን እየተሰራ ነው?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- እውነት ነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትልቅ የቱሪዝም አቅም አለው። በዚህ ክልል ውስጥ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ትልልቅ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ። የ12ኛው እና የ14 ኛው ክፍለ ዘመን የእምነት ተቋማት እስካሁን ምንም ችግር ሳይገጥማቸው እና ሳይበላሹ ደህንነታቸው ተጠብቆ ይገኛሉ። በዚህም ማኅበረሰቡ ሊመሰገን ይገባል።

ለምሳሌ፣ የደን እና የዱር እንስሳት መጠበቂያ ፓርኮች የጨበራ ጩርጩራ እና የኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች በክልላችን ውስጥ ይገኛሉ። ወደ ሸካ እና ወደ ካፋ ጠለቅ ብለን ስንገባ በጣም ትላልቅ፣ አስደማሚ እና አስደናቂ ፏፏቴዎች አሉ። የተፈጥሮ ሀይቆችም እንዲሁ በርካታ ናቸው። የሸካ እና የካፋ ዞኖች “ባዮስፌር” በዩኔስኮ የተመዘገበ ነው። በውስጡ በርካታ ብዘሃ ሕይወት ይገኛል። ይህ ቀላል የሚባል ሃብት አይደለም። በተጨማሪም የጊቤ ሶስት እና ኮይሻን በመሰሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች የተፈጠሩ ሰው ሰራሽ ሃይቆች አሉ። የአርብቶ አደሩም ባሕል ያልተበረዘ እና ያልተነካ በመሆኑ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችል ነው።

አዲስ ዘመን፡- እነኝህን ሃብቶች ለአካባቢው ልማት ለማዋል ምን እየተሰራ ነው?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በክልላችን ብዙም ያልታዩ እና ያልተነገረላቸው እንዲሁም ያልተዘመረላቸውን ሀብቶቻችን እንዲታወቁ እና የገቢ ምንጭ መሆን እንዲችሉ ትልቅ እድል ፈጥሮልናል። ለምሳሌ፣ ሃላላ ኬላን ከአካባቢው ማኅበረሰብ በስተቀር ማንም አያውቀም ነበር። አሁን ግን በገበታ ለሃገር ለምቶ ትልቅ የቱሪዝም መነቃቀትን ፈጥሯል። የጨበራ ጩርጩራም በተመሳሳይ በገበታ ለሀገር ተጠቃሚ በመሆኑ ትልቅ የቱሪዝም ሃብት እድል ተፈጥሮለታል።

በቤንች ሼኮ ሚዛን አማን ከተማ ላይም በገበታ ለትውልድ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ተጀምሯል። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የትራንስፖርት ኮሊደሩን ያሰፋል። ቦንጋ ላይ ቀላል የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ተጀምሯል። የቱሪዝም ኮሪደሩን ለማስተሳሰር እድልም የሚፈጥር ነው።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስፋት በየከተሞቹ ደረጃቸውን የጠበቁ የእንግዳ ማረፊያ መገንባት ያስፈልጋል። በክልላችንም ደረጃቸውን የጠበቁ የእንግዳ ማረፊያ ለመገንባት በተለያዩ ከተሞች የተጀመሩ ስራዎች አሉ። ከዓመት፣ ሁለት ዓመት በኋላ ከእንግዳ ማረፊያ ጋር ተያይዞ የተሻለ ለውጥ እንደሚኖር ይጠበቃል። ይህ በግሉ ሴክተር የሚለማ ስለሆነ የግሉ ባለሀብት በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፍ ስራዎችን እየሰራን ነው። በዚህ አጋጣሚም ባለሃብቱ በክልላችን መጥቶ እንዲያለማ ጥሪ እናቀርባለን።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ የኢንቨስተሮችን ለመሳብ ምን እየሰራ ነው?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- ክልላዊ ኢኮኖሚን በማሳደግ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ የበኩላችንን እናበርክት! ብለን ስንነሳ አንዱ የተመረጠው የኢንቨስትመንት ሴክተር ነው። እንደሚታወቀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝቦች ለኢንቨስትመንት ዘርፉ በጣም ምቹ ነው። በተለይ በግብርና እና በማእድን ዘርፉ ላይ ሰፊ እድሎች አሉ፡፡

የግብርናው ዘርፍ አሁን ላይ በጣም እየተነቃቃ ነው። በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ባለሀብቶች ወደ ስራ ገብተዋል። ቀደም ብሎ ወደ ግብርናው ዘርፍ ገብተው ውጤታማ ያልሆኑትን ባለሀብቶች ሁሉ የማብቃት ስራዎችን እየሰራን ነው። ይህም ትልቅ አቅም እየፈጠረ እንደመሆኑ መስፋት እና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሁለተኛው፣ ክልሉ ምቹ የሆነው በማዕድን ዘርፉ ላይ ነው። በተለይ አሁን ላይ በዳውሮ፣ በኮንታ እና ካፋ በድንጋይ ከሰል ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል። በእነኝህ አካባቢዎች ከከሰል ድንጋይ በተጨማሪ የብረት ማእድናትን ወደ ምዕራብ ኦሞ ስንሄድ የወርቅ ምርት በስፋት አለ። ይህ ወደፊት እየሰፋ የሚሄድ ነው።

በክልላችን ከግብርና እና ከማእድን በተጨማሪ፣ በማኑፋክቸሪንግ በተለይም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው። ለአግሮ ኢንዱስትሪ ክልል ምቹ ነው። በዘይት መጭመቂያ፣ በእንስሳት ተዋጾ ማቀነባባሪያ ላይ ቢሰሩ ባለሃብቶች አትራፊ ይሆናሉ። ክልላችን በሌሎች ዘርፎች ላይ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉት። እነኝህን አማራጮች ለመጠቀም በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ክልላችን እየመጡ ነው። ኢንቨስተሮችም ወደክልላችን ሲመጡ በቢሮክራሲ እንዳይሰላቹ ለማድረግ በአጭር ቀናት ውስጥ የሚስተናገድበትን አሰራር ዘርግተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ በወርቅ ግብይት ላይ ጤናማ ያልሆኑ አካሄዶች መኖራቸው ይነገራል። በዚህ ላይ ምን እርሶ ምን ይላሉ?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- በክልላችን ከፍተኛ የሆነ የወርቅ ምርት ቢኖርም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕገ ወጥ የወርቅ ግብይት እየታየ ነው። የግብይት ስርዓቱ ጤናማ አይደለም። ምርት ይመረታል ነገር ግን የራሱን የግብይት ሰንሰለት ተከትሎ ወደ ብሄራዊ ባንክ መግባት ሲገባው ብዙ ጊዜ በሕገወጦች እጅ ሲገባ ይስተዋላል።

ለዚህ ምክንያቶች ብዙ ናቸው። ነገር ግን በእኛ ደረጃ የለየነው ሕገ ወጥ ቡድኑ ብሔራዊ ባንክ ከሚገዛው ዋጋ በግራም ከ1500 እስከ 2000 ብር ከፍ አድርጎ ከአምራቾች ይገዛል። ስለሆነም አምራቾቹ ወደ ባንክ ከሚሄዱ ይልቅ ወደ ሕገወጥ ቡድኖች ሄደው መሸጥን ይመርጣሉ። ሕገ ወጦችን ለመከላከል ክልሉ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ስራዎች እያተከናወነ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር አንጻር በክልሉ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር)፡- በኢኮኖሚው ሴክተር ውስጥ በሀገራችን ብሎም በክልላችን አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ተብሎ የተወሰደው የስራ አጥነት ቁጥርን መቀነስ እና የኑሮ ውድነትን ተጨባጭ በሆነ መልኩ መከላከል ነው። ይህ በፓርቲያችን ውስጥ በየቀኑ የምንሰራው እና የምንገመግመው ነው። ለምሳሌ፣ እንደ ክልል ትምህርታቸውን ተምረው ጨርሰው ከቤታቸው ለተቀመጡ የተለያዩ ወጣቶች እና ለአርሶ አደር ልጆች የተለያዩ የስራ እድሎች እየተፈጠሩላቸው ነው።

ከዚህ ቀጥሎ ክልሉ በተነጻራሪ የተሻለ አቅም ያለው በእርሻው ላይ ስለሆነ በአንድ ዓመት ብቻ 37 የሚደርሱ የእርሻ ትራክቶሮችን በመግዛት ለወጣቶች አከፋፍለናል። መሬት ደግሞ በዞን እና ወረዳ እንዲዘጋጅ አድርገናል። በሁሉም ዞኖች ወጣቶችን አደራጅተን ወደ ስራ አስገብተናል። በዚህም ሦስት ሺህ 500 የሚጠጉ ወጣቶችን በግብርናው አሰማርተናል። ይህም የሆነው በሁለት ዓመት ከአራት ወር ውስጥ ነው። አንዳንዶቹ በጣም ውጤታማ ናቸው፡፡

በዚህም በአትክልት እና ፍራፍሬ የተደራጀ 25 አባላት ያሉት በአንድ ቡድን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በጥሬ ገንዘብ 10 ሚሊዮን ብር ማፍራት ችሏል። ለስንዴ አምራቾች ደግሞ በተለይም በከፋ ዞን ዞኑ በራሱ ወጭ ቤት ሰርቶ ነው ወጣቶችን ወደ ስራ ያስገባው። ከቤት በተጨማሪ መንገድ ሰርተንላቸዋል። ግብዓት አቅርበንላቸዋል። ዳውሮ ላይ በጣም ውጤታማ ሆነዋል። ይህ ወደፊት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በቀደሙት ጊዜያት ወጣቱ በእርሻ ላይ ለመደራጀት ፍላጎት አልነበረውም። ትራክተር ገዝተን ከሰጠን በኋለ ግን በርካታ ወጣቶች ተነቃቅተው ወደ ስራ ገብተዋል። ወደፊትም በማዕድን ዘርፉ በተለይም በከሰል ድንጋይ እና በወርቅ ማምረቱ ላይ ወጣቶች የሚሰሩበትን እድል ለመፍጠር እየሰራን ነው። ወጣቶችን ከባለሀብቶች ጋር ለማስተሳሰር እና ለማደራጀትም እየሰራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

ኢንጅነር ነጋሽ(ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ።

በሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You