በዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና የሚሳተፈው ቡድን ዛሬ ይሸኛል

የዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ከጥቂት ቀናት በኋላ በሰርቢያ ቤልግሬድ ይካሄዳል፡፡ ዘንድሮ ለ45ኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ የዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም የሀገር ውስጥ ዝግጅቱን አጠናቆ ዛሬ ምሽት ሽኝት እንደሚደረግለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

እአአ ከ1973 አንስቶ ሳይቋረጥ እየተካሄደ አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰው ይህ ቻምፒዮና በ5 የውድድር ዓይነቶች በመጪው ቅዳሜ መጋቢት 22/2016 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ በ10ኪሎ ሜትር አዋቂ፣ በ8እና6 ኪሎ ሜትር ወጣቶች እንዲሁም ድብልቅ ሪሌ፤ ከ51 የዓለም ሃገራት የተወጣጡ 485 አትሌቶችን ያሳትፋል፡፡ በአንጋፋው አትሌት መሃመድ ከድር የብር ሜዳሊያ የጀመረው የኢትዮጵያ የሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ውጤታማ ጉዞም እንደ ቀነኒሳ በቀለ ያሉ በውድድሩ ትልቅ ታሪክ የሰሩ አትሌቶችን በማፍራት ቀጥሏል። በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ስኬታማ ከሆኑት ሃገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር በግልም ሆነ በቡድን የበላይነት ከሚጠበቁ ጠንካራ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡

የዘንድሮው የኢትዮጵያ የሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ብሄራዊ ቡድንም ዝግጅቱን አጠናቆ የውድድሩን መጀመር ብቻ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያን በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ የሚወክሉ አትሌቶች በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና የተመረጡ ሲሆን፣ ከወር በፊት በቱኒዚያ በተካሄደው የአፍሪካ ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮናም ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን አቅሙን ማሳየት ችሏል፡፡

14 ሴት እና 14 ወንድ በአጠቃላይ 28 አትሌቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ የሃገር አቋራጭ ቡድን፤ ከየካቲት 28/2016 ዓ.ም ጀምሮ ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል። በረጅም ጊዜ የቻምፒዮናው ተሳትፎ ባስቆጠረቻቸው ሜዳሊያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ ክብሯን አስጠብቃ በስኬታማነት ለመመለስ የሚያስችሉ አትሌቶችም በቡድን ስብስቡ ተካተዋል፡፡

በሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ የሆነችው ጎረቤት ሃገር ኬንያ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀዳሚ ተፎካካሪ ስትሆን፤ የኡጋንዳ አትሌቶችም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት በባትረስ በተካሄደው ቻምፒዮና በአዋቂ ወንዶች የወርቅና የነሃስ ሜዳሊያ ያጠለቁት ኡጋንዳውያን ጃኮብ ኪፕሊሞ እና ጆሹዋ ቺፕቴጊ ሜዳሊያውን በድጋሚ ወደሃገራቸው መመለስን ዓላማ ማድረጋቸውን የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያሳያል፡፡ ይሁንና የወርቅ ሜዳሊያው አምና በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ተበልጦ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ከተገደደው ወጣቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁ አረጋዊ እጅ የሚወጣ አይመስልም፡፡ አትሌቱ በውድድር ዓመቱ ተሳትፎው ምርጥ አቋም ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ የወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ፉክክሩ ከወዲሁ ተጠባቂ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በድብልቅ ሪሌ ከሚሳተፉ 12 ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ እንደተለመደው ሜዳሊያ የማግኘት እድሏ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ ከተካተቱ አትሌቶች አንዱ የሆነው ሃጎስ ገብረህይወት ደግሞ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል። በሪጋ የጎዳና ላይ ቻምፒዮና እንዲሁም ከቀናት በፊት በጋና አክራ የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለሃገሩ ማስመዝገብ የቻለው ሀቦስ ሰርቢያ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠልቃል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች በሚደረገው ውድድርም አምና አውስትራሊያ ላይ ተሳትፈው ልምድ ማግኘት የቻሉት በሴት ለምለም ንብረት፣ በወንዶች ደግሞ አቤል በቀለን የመሳሰሉ ወጣት አትሌቶችም በቤልግሬድ በድጋሚ የሚታዩ መሆናቸውን ተከትሎ በግላቸው ሜዳሊያ የማስመዝገብ ግምትም አግኝተዋል።

በዚህ ቻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ፤ በሴቶች ደግሞ ደራርቱ ቱሉ እና ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉ አትሌቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ ሃገር ሲታይ ደግሞ ኢትዮጵያ ኬንያን በመከተል 107 የወርቅ፣ 115 የብር እና 63 የነሃስ በጥቅሉ 285 ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ አምና በአውስትራሊያዋ ባትረስ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ 2 የወርቅ፣ 7 የብር እና 1 የነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን ማግኘቷ የሚታወስ ነው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You