በሞስኮው ጥቃት ተሳታፊ ናቸው የተባሉት ላይ ክስ ተመሠረተ

ሩሲያ በሞስኮ የሙዚቃ ዝግጅት 137 ሰዎችን ገድለዋል ባለቻቸው 4 ግለሰቦች ላይ ክስ መሠረተች። ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ተጠፍንገው አንዱ ደግሞ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል። ባሳለፍነው ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. አራት ግለሰቦች በፈጸሙት ጥቃት 137 ሰዎችን መገደላቸው ይታወሳል።

ለዚህ ጥቃት እስላሚክ ስቴት ወይም አይኤስ ኃላፊነቱን ወስዶ ጥቃት አድራሾቹ ጥቃቱን ሲያደርሱ የሚያሳይ ምስል ለጥፏል። የሩሲያ ባለሥልጣናት ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ ዩክሬን በዚህ ጥቃት ተሳታፊ ሆናለች ብለዋል። ዩክሬን በጥቃቱ አለመሳተፏን ገልጻ ከሩሲያ የቀረበባትን ክስ አጣጥላለች።

በጥቃቱ በመሳተፍ በሽብር ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች ዳሌርደዘሆን ሚረዞዬቭ፣ ሳኢዳካራሚ ሙሮዳሊ ራቻባሊዞዳ፣ ሻመሰዲን ፋሪዱኒ እና ሞሐማዳሶቢር ዳይዞቭ ናቸው። አራቱም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ አካላዊ ጉዳት እንዳለባቸው ይታያል።

የሁለቱ ተከሳሾች ዓይን ጠቁሮ የሚታይ ሲሆን የሌላኛቸው ተከሳሽ ጆሮ እንዲሁም አንገቱ በፕላስቲክ ተጠቅልሎ ነበር። በተሽከርካሪ ወንበር የመጣው ተከሳሽ አንድ ዓይኑን ማጣቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በቴሌግራም ቻናል ላይ የወጣ የፍርድ ቤት መግለጫ የታጃኪስታን ዜጋ የሆነው ሚራዞዬቭ እንዲሁም ራቻባሊዞዳ ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል ይላል።

በዚህ ጥቃት ክስ የተመሠረተባቸው እነዚህ አራት ግለሰቦች ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአራት ሰዓታት በኋላ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት። አራቱ ተጠርጣሪዎች ወደ አዳራሹ በመግባት ያገኙት ሰው ላይ በዘፈቀደ በመተኮስ ባደረሱት ጥቃትም ከገደሏቸው 137 ሰዎች በተጨማሪ 140 ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

ባለሥልጣናት እንደገለጡት በጠቅላላው 11 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና አራቱ ተጠርጣሪዎች ወደ ዩክሬን ድንበር ሲያቀኑ ነው የተያዙት ብለዋል። ሩሲያ አይኤስ ለጥቃቱ ኃላፊነት ስለመውሰዱ እስካሁን ያለችው ነገር የለም። ይልቅ በዚህ ጥቃት ዩክሬን ተሳታፊ ስለመሆኗ ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ታጣቂዎቹ የተያዙት ወደ ዩክሬን ለማምለጥ ሲሞክሩ ነበር ብለዋል። ዩክሬን በጥቃቱ እጇ አለበት የተባለውን ክስ አስተባብላ “የማይመስል ነገር ነው” የሚል አስተያየት ሰጥታለች። ይህ ጥቃት ከመፈጸሙ ከሳምንታት ቀድሞ በሞስኮ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በመዲናዋ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ማሳሰቢያ አውጥታ ነበር።

ነገር ግን የሩሲያ መንግሥት ይህን ማስጠንቀቂያ በወቅቱ በሩሲያ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ “ፕሮፖጋንዳ ነው” በሚል አጣጥሎታል። ከዚህ ጥቃት በኋላ አሜሪካ ይህን ጥቃት ያደረሰው አይኤስ ስለመሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለኝም ብላለች።

አይኤስ ሩሲያን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እአአ 2015 ላይ ከግብፅ ወደ ሩሲያ በሚበር አውሮፕላን ላይ ቦምብ ጠምዶ አብዛኛዎቹ የሩሲያ ዜጎች የሆኑ 224 ሰዎችን ገድሎ ነበር። እአአ 2017 ላይ ደግሞ አይኤስ በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ባቡር ጣቢያ ላይ የቦምብ ጥቃት ፈጽሞ 15 ሰዎችን ገድሏል።

የደኅንነት ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ አይኤስ ሩሲያን ዒላማ አድርጎ ከያዘባቸው ምክንያቶች ዋነኛ በሶሪያ በነበራት ተሳትፎ ነው። ሩሲያ ከኤይኤስ ጋር ሲዋጉ የቆዩት የበሽር አላ-አሳድ አስተዳደርን ለማስቀጠል ድጋፍ አድርጋለች እንዲሁም አይኤስ ከሶሪያ እንዲወጣ ትልቅ ወታደራዊ ሚና ተጫውታለች ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2016 ዓ.ም

Recommended For You